ለበጀት አጠቃቀም ውጤታማነት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል!

በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች አሉት። ሰላምና ደህንነት ከምንም በላይ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ቢሆንም የኑሮ ውድነቱን እንቆቅልሽ መፍታት ጊዜ የማይሰጥና አንገብጋቢ ነው። ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነቱ ጣራ በመንካቱ ሕዝቡ በብርቱ እየተፈተነ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርትም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከሚታይባቸው አስር የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን አስቀምጧል። ይህም የብር የመግዛት አቅም ምንኛ እየተዳከመ ስለመምጣቱ ጠቋሚ ነው።

በርግጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው የፋይናንስ ችግር አንጻር፣ አብዛኞቹ የዓለም ሀገራት እየተፈተኑ ቢሆንም፤ ችግሩ በድሃ ሀገራት እያስከተለ ያለው ቀውስ ከፍ ያለ ነው። ችግሩን ለመቋቋም የሚያደርጉትም ጥረት በብዙ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ስለመሆኑ የእለት ተእለት የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ነው።

በኛም ሀገር ከኮረናና ከጦርነት ማግስት የተፈጠረው ይህ ችግር ሀገራዊ ፈተና ከሆነ አመታት መቆጠር ጀምረዋል። ችግሩን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶችም ካለው ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ እውነታ አንጻር የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ ሊሆን አልቻለም።

የኑሮ ውድነቱ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የነካ ቢሆንም ወላፈኑ በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙትን በእጅጉ ገርፏቸዋል። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መሰረታዊ የሚባሉ ፍላጎታቸውን በተለይ የእለት ጉርሳቸውንና የመኖሪያ ቤት ኪራይ ወጪያቸውን ለመሸፈን ዳገት ሆኖባቸዋል።

ሌሎች ምግብ ነክ ያልሆኑና መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋም እጅጉን በመናሩ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ገዝቶ ለመጠቀም እጅ አጥሮታል። ወትሮም ቢሆን ለዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል የቆሙት ሸማች ሱቆችም መሠረታዊ የሚባሉ የፍጆታ እቃዎችን እንደልብ እያቀረቡ ባለመሆኑ ደሃው ተቸግሯል።

በአዲስ አበባ ከተማ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ለመጠቀም በሚል የተቋቋመው ሸገር ዳቦ ለጊዜውም ቢሆን ትልቅ እፎይታ ሰጥቶ ነበር። የሸገር ዳቦ አቅርቦት ካለው የመግዛት ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር እምብዛም በቂ ያልነበረ ቢሆንም ቢያንስ ደሃው ዳቦ ሲገዛ ቆይቷል።

የኋላ ኋላ በዱቄት ግብዓት እጥረት ሥራውን አቁሞ የደሃው ህብረተሰብ የዳቦ ፍላጎት ፈተና ውስጥ ገብቷል። አሁን ደግሞ ፋብሪካው የነበረብኝን የዱቄት ግብዓት እጥረት ቀርፌ ዳግም ወደ ሥራዬ ተመልሻለሁ ብሏል። እንዲያም ሆኖ የፋብሪካው የዳቦ አቅርቦት አስተማማኝ ሊሆን አልቻለም።

ምንም እንኳን የኑሮ ውድነቱ ወላፈን መላው የሀገሪቱን ሕዝብ የለበለበ ቢሆንም በተለየ መልኩ ግን በገጠር ቀበሌና ወረዳ ከተሞች፣ በክልል አነስተኛና ትላልቅ ከተሞች በዋናነት ደግሞ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሰዎችን ክፉኛ ገርፏል። ወላጆችም ልጆቻቸውን በቅጡ ለማሳደግ ተቸግረዋል። የትምህርት ቤት ክፍያም የትየለሌ ደርሷል።

የጤፍማ ነገር አይነሳ። እለት በእለት ዋጋው እየናረ የሄደው ጤፍ ዛሬ ላይ በኩንታል እስከ 10 ሺ ብር እየተሸጠ ነው። ነገ ደግሞ አስራ አምስትና ሃያ ሺ ብር መግባቱ አይቀሬ ነው። የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋማ አይነገር። በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያሉ አትክልትና ፍራፍሬ ለጤና ጠቃሚ ነውና አዘውትረው ይጠቀሙ ሲሉ መልእክት የሚያስተላልፉ የጤና ባለሙያዎች በዋጋ ንረቱ ምክንያት እንኳን እኛ ቀርቶ እነርሱም ገዝተው መጠቀም የሚችሉ አይመስልም።

ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ቀይስር፣ ቃሪያ፣ ጎመንና ሌሎችም ዋጋቸው የተረጋጋ አይደለም። ነዳጅም ጨምሯል። በርግጥ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ዓለም አቀፍ ወቅታዊ የነዳጅ ዋጋን ተከትሎ የሚጨምር በመሆኑ አይደንቅም። የሌሎች ምርቶች ዋጋ መናር ግን የህብረተሰቡን ኑሮ በእጅጉ እየፈተነው ይገኛል።

መንግሥት በዘንድሮው በጀት ዓመት ከአምናው የተሻለ በጀት መድቧል። በጀቱ በተለይ የኑሮ ውድነቱን ለማሻሻል ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ይታመናል። ለዚህ ደግሞ ውጤታማ የሃብት አጠቃቀም ወሳኝ ነው። በጀቱ የሀገሪቱ ትልቁ የገንዘብ ሃብት ነውና ለሚፈለገው አላማ ብቻ ስለመዋሉ ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በጀቱን አስፈላጊ ለሆኑና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ለሚያስችሉ የተመረጡ ተግባራት ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግም ተገቢ ነው። ቢያንስ ቢያንስ ህብረተሰቡ እንደ ኪሱ በልቶ እንዲያድር መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ማለትም ስኳር፣ ዱቄት፣ ዘይትና የመሳሰሉትን በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያቀርብ ይገባል። ሸማች ሱቆችም እነዚህንና መሰል ምርቶችን እንደልብ አግኝተው እንዲያከፋፍሉ መንግሥት በበቂ ሁኔታ ምርቶቹን ሊያቀርብላቸው ይገባል።

ህብረተሰቡን በከፍተኛ ደረጃ እየፈተነው የመጣውን የቤት ኪራይ ውድነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አከራዮች በተከራዮች ላይ የቤት ኪራይ ዋጋ ለሶስት ወራት እንዳይጨምሩ ማድረግ ጥሩ ርምጃ ነው። ነገር ግን እንዲህም ሆኖ በተከራዮች ላይ ዋጋ የሚጨምሩ አንዳንድ አከራዮች በመኖራቸው አስተዳደሩ ተከታትሎ አስፈላጊውን ሕጋዊ ርምጃ ሊወስድ ይገባል። በዘላቂነት ደግሞ የአከራዮችን ቤት በማየት ግምታዊ የኪራይ ዋጋ ተመን በማውጣት የተከራዩ ሰቆቃ እንዲያበቃ ማድረግ ይኖርበታል።

በሌላ በኩል ከነሽንኩርት፣ ድንች፣ ቃሪያ፣ ቲማቲምና ጎመን የየእለት ዋጋ ጭማሪ በስተጀርባ የሕገ ወጥ ደላሎች ረጅም እጅ አለበት መንግሥት በዚህ ረገድ የማያወላዳ አቋም በመውሰድ የነዚህን ጨካኝ እጆች መቁረጥ ይኖርበታል። ምርት ሳያጥር ምርት እንደጠፋ አድርገው አርቲፊሻል የዋጋ ንረት የሚፈጥሩ የሕገ ወጥ ደላላ ሰንሰለቶችን መበጠስ ይኖርበታል።

የነዳጅ ዋጋም ቢሆን በቀጣይ ተለዋዋጭና አስተማማኝ ባለመሆኑ መንግሥት በታዳሽ ኃይል ዙሪያ የጀመራቸውን አንዳንድ ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ህብረተሰቡም በታዳሽ ኃይል አማካኝነት የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችንና ሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችን የመጠቀም ልምምድ ውስጥ መግባት አለበት።

በርግጥ የኑሮ ውድነቱ ዓለም አቀፋዊ ነው። የሩሲያና የዩክሬን ጦርነትም በተቀሩት የዓለም ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል። ወላፈኑ ኢትዮጵያንም ነክቷል። በእኛም ሀገር በሰሜኑ ክፍል የተደረገው ጦርነት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መውረድ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። በዚህና መሰል ጦሶች ምክንያት ባሻቀበው ኑሮ ህብረተሰቡ በብርቱ እየተፈተነ ነውና በዚህ በጀት ዓመት መንግሥት ለዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ ይሰራል ብለን እንጠብቃለን።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 26/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *