በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ መካከል ከነፃነት ማግስት የጀመረ ጠንካራ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። በደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ትግል ውስጥም የኢትዮጵያውያን አበርክቶ ከፍ ያለ ስለመሆኑ ያትታሉ። ይህም በሀገሪቱ መራራ የነፃነት ትግል ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዳለው ይታመናል ።
የደቡብ አፍሪካውያንን የነፃነት ትግል ፍትሐዊነትን በዓለም አቀፍ መድረኮች አጉልቶ ከማሰማት ጀምሮ፤ ለትግሉ ስኬታማነት አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን በማድረግ ሕዝቡ ለነፃነቱ ያደረገው ተጋድሎ ፍሬ አፍርቶ፤ የአፍሪካውያን የነፃነት ትግል የመጨረሻ የድል ብስራት ደውል እንዲያሰማ የኢትዮጵያውያን አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ነው።
ከነፃነት ማግስት ጀምሮም ሀገራት የሕዝቦቻቸውን የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በስፋት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። በዚህም ያስመዘገቡትም ሆነ እያስመዘገቡት ያለው ስኬት ለቀጣይ ግንኙነታቸው ትልቅ አቅም እንደሚሆን፤ ሌሎችም ትምህርት ሊወሰድበት የሚገባ እንደሆነ ይታመናል።
በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፤ በፓን አፍሪካኒዝም መርሕ ላይ የተመሠረተና እውነተኛ ወንድማማችነትን መሠረት ያደረገ ነው፤ ይህ ደግሞ በነፃነት ትግሉ ወቅት ሆነ፤ ከነፃነት ማግስት ጀምሮ በዓለም አቀፍ አደባባይ ሳይቀር በተጨባጭ የታየ፤ ለሀገራቱ ሕዝቦች የዛሬ ስኬታማ ግንኙነት መሠረት የጣለ ነው።
የደቡብ አፍሪካ ሕዝብና መንግሥትም ከነፃነት ማግስት ጀምሮ ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያንን ከፍ ባለ ወንድማዊ ፍቅር በእንግድነት በመቀበል፤ እንደሁለተኛ ሀገራቸው የሚኖሩበትን የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥረዋል። በዚህም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን ከበሬታ በተግባር አሳይተዋል። በሀገራቱ ሕዝቦች የግንኙነት ታሪክ ውስጥም አዲስ የወዳጅነት ምዕራፍ መፍጠር ችለዋል።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥትና ሕዝብ በቅርቡ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ተቀስቅሶ ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ያስከፈለው ጦርነት በሰላም ስምምነት ተጠናቆ በሀገሪቱ የሰላም አየር እንዲነፍስ ከፍያለ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ይህ አበርክቷቸው ለአፍሪካ እና ለአፍሪካውያን ሰላምና መረጋጋት ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየ ነው።
“ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” ለሚለው አህጉራዊ መርሕ የተገዛው የደቡብ አፍሪካ የሽምግልና ተልዕኮ በርግጥም አፍሪካውያን ከችግሮቻችው በላይ መሆናቸውን በተጨባጭ ያመላከተ፤ አፍሪካውያን በችግሮቻችው ዙሪያ ተሰባስበው በሰከነ መንፈስ መነጋገር የሚያስችል ዕድል ከተፈጠረላቸው ችግሮቻቸውን ተሻግረው መራመድ የሚያስችል አቅም ባለቤት ስለመሆናቸው በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
ከዚህም ባለፈ ሀገራቱ የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ የሆነውን “አጀንዳ 2063” ስኬታማ እንዲሆን በድህነት ቅነሳ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በመሰል ተግባራት በጋራ መንቀሳቀስ የሚያስችል ሠፊ እድል አላቸው፤ ይህንን ዕድል በአግባቡ ተጠቅሞ ሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚ ለማድረግም በብዙ መልኩ የተፈተነው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
በአፍሪካ ትልቅ የገበያ መዳረሻ ለመፍጠር፤ አፍሪካን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር፤ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት፤ የአህጉሪቱን ሕዝቦች የንግድ ትስስሮች በማሳደግ በቀጣይ አፍሪካውያን የተሻሉ ነገዎች እንዲኖራቸው ለማስቻል የሚያደርጓቸውን ጥረቶች አቀናጅተው መቀጠል ይጠበቅባቸዋል።
ሀገራቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች አፍሪካውያን ድምፃቸው ከፍ ብሎ እንዲሰማ ለማድረግ የሚያደርጓቸው ጥረቶች ከፍያለ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው፤ በተለይም አፍሪካውያን በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ተገቢውን ውክልና እንዲያገኙ የጀመሩት ጥረት ለአህጉሪቱ ሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት አስተዋፅዖው ያለ ነው ።
ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን በተካሄደው 4ኛው የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ የሚኒስትሮች ስብሰባ ሀገራቱ በፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊና በፀጥታ ጉዳዮች የነበራቸው የትብብር አፈጻጸም አጥጋቢ ሆኖ መገምገሙ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ሊወሰድ የሚችልና በቀጣይም ለተሻለ የሕዝቦቻቸው ተጠቃሚነት ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ነው!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2015