አዲስ አበባ፡-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ሥርዓት የሆነው ኢትስዊች በክፍያ አካታችነት ደረጃው በማሻሻል ወደ መሠረታዊ ከፍ ማለቱን ተገለጸ።
የኢትስዊች ቺፍ ፖርት ፎልዮ ኦፊሰር አቶ አቤኔዘር ወንደሰን ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ኢትስዊች አካታች የክፍያ አገልግሎት የመስጠት ሥራዎቹን የጀመረው እኤአ በ2022 ነው። እስካለፈው ዓመት ድረስም አገልግሎቱ በደረጃ ምደባ አልገባም ነበር። ባለፉት ሁለት ዓመታት ባደረገው እንቅስቃሴ የነበረበት ደረጃ በማሻሻል ወደ መሠረታዊ (Basic) ደረጃ ማደግ ችሏል።
ኩባንያው ከግለሰብ ወደ ግለሰብ (P2P) እና ከግለሰብ ወደ ተቋማት (P2B) ፈጣን የክፍያ አገልግሎት ማሳለጥና አካታችነትን ማስፋት በመቻሉ የመሠረታዊ ደረጃን እንዳገኘ አመልክተው፤ ይህንን ደረጃውን ያገኘው በአሕጉሪቱ የፈጣን አካታች ክፍያ ሥርዓትን ለማበረታታት የሚሠራው አፍሪካኔንዳ የተባለው ፋውንዴሽን ይፋ ባደረገው የ2024 ዓመታዊ ሪፖርት መሆኑን ተናግረዋል።
የፋውንዴሸኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሮበርት ኦቾላ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ አካታችና ፈጣን የክፍያ ሥርዓት የፋይናንስ አካታችነትን፣ የኢኮኖሚ ፍትሐዊነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ይረዳል።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ 400 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በፋይናንስ ሥርዓት ተደራሽ አልሆኑም ያሉት ሮበርት ኦቾላ (ዶ/ር) ፤ እንደ አፍሪካኔንዳ ሪፖርት ከሆነ በአሁኑ ወቅት በአሕጉሪቱ በ26 ሀገራት የሚንቀሳቀሱ ፈጣን የክፍያ ሥርዓቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ፈጣን የክፍያ ሥርዓቶች ሁሉም ቀጥተኛ (ላይቭ) የሆነ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ አመልክተው፤ በሌሎች 27 ሀገራት ደግሞ የክፍያ ሥርዓቶቹን በቀጣዮቹ አስራ ስምንት ወራት ውስጥ የመጀመር ሀሳብ እንዳለ ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ በመላው አፍሪካ አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኙት ተቋማት በዓመቱ 49 ቢሊዮን በላይ የሆኑ ክፍያዎችን ያሳለጡ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በገንዘብ መጠን ሲታይ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ እስከ አሁን ያልተካተቱ ዜጎችን ለማዳረስ የተቋማቱን አካታችነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ተቋማቱ በአካታችነት መመዘኛ ሲታዩ በ3 ደረጃ የሚከፈሉ ሲሆን እነሱም ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ሲያድጉ መሠረታዊ (Basic)፣ ያደጉ (Progressed) እና የበቁ (Mature) የሚል ደረጃ ይሰጣቸዋል ነው ያሉት።
እስከ አሁን በአሕጉሪቱ የበቁ የሚለው ከፍተኛ የአካታችነት ደረጃ ላይ የደረሰ አገልግሎት ሰጪ እንደሌለ የአፍሪካኔንዳ ሪፖርት አመልክቶ፤ ዘጠኝ የክፍያ ሥርዓቶች (ሲስተሞች) ያደጉ (በፕሮግረስ) ደረጃ የሚገኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክፍያ ሥርዓት ኢትስዊችን ጨምሮ 12 ሥርዓቶች (ሲስተሞች) ደግሞ መሠረታዊ (ቤዚክ) በሚባለው ደረጃ ተካተው ይገኛሉ ብሏል።
እንደ አቶ አቤኔዘር ገለጻ ኢትስዊች አገልግሎቱን ይበልጥ አካታች እና ተደራሽ ለማድረግ አሁን በርካታ ሥራዎች እየሠራ ነው። በዚህም በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ አሁን ካለበት ደረጃ ወደ ያደገ (ፕሮግረስድ) መድረስ ይችላል።
ሥርዓቱ (ሲስተሙ) ወደዚህ ደረጃ ከፍ ቢል ለሀገሪቱና ለዜጎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ አቶ አቤኔዘር አብራርተዋል። ከዚህም ጠቀሜታ አንዱና ዋነኛው የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን በማቅለል ዜጎች ባንክ በሌለበት አካባቢ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የክፍያ ሥርዓቱም ከስጋትና ውጣ ውረድ ነፃ ሆኖ በቀላሉ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት።
ለአካታችና ፈጣን የክፍያ ሥርዓት አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ዲጂታል መሠረተ ልማት ነው ያሉት አቶ አቤኔዘር፣ ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂና የዚሁ አካል የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ለዜጎች የማዳረስ ሥራ ፈጣንና አካታች የክፍያ ሥርዓትን ለማስፋፋት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የዲጂታል ፋይናንስ እና ፈጣን የክፍያ ሥርዓት ባለሙያ እንዲሁም የአፍሪካኔንዳ ፋውንዴሽን የማኅበረሰባዊ ትግበራ አምባሳደር አቶ ግሩም ፈቃዱ ሀገሪቱ ያፀደቀችው የመረጃ ግላዊነት አዋጅም የዜጎችን ወይም የዲጂታል ፋይናንስ ተጠቃሚዎችን የመረጃ ግላዊነትና የፋይናንስ ደኅንነት ለመጠበቅ ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ይህም ወደፊት ሀገሪቱ ይበልጥ ፈጣንና አካታች የፋይናንስ ሥርዓት ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት ጥሩ መሠረት እንደሚሆን አቶ ግሩም አብራርተዋል። ብቸኛው የፈጣን ክፍያ አገልግሎት ሰጪ የሆነው ኢትስዊች ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሁሉም ባንኮች ባለአክሲዮን የሆኑበትና በ2016 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በኋላ 789 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር አትርፏል። ኩባንያው ከግብር በፊት ያስመዘገበው ትርፍ በ97 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ታውቋል።
ዘካሪያስ ወልደማሪያም
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም