ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ነው። በተለይም ባለንበት ዘመን በልማት ትናንቶቻቸውን ታሪክ፣ ነገዎቻቸውን ብሩህ ለማድረግ ደፋ ቀና የሚሉ ሀገራትና ሕዝቦች ለዕድገታቸው ስኬት የኃይል አቅርቦት ጉዳይ ለነገ የማይሉት ትልቁ የቤት ሥራቸው እንደሆነ ይታመናል።
ሀገራት የጀመሯቸው የልማት ወጥኖች ሆኑ፤ ነገ ላይ ሊደርሱባቸው ያለሟቸው የልማት ራዕዮቻቸው መሬት ወርደው በተጨባጭ ሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉት ከሁሉም በላይ በኃይል አቅርቦት ዙሪያ የሚያደርጓቸው ኢንቨስትመንቶች ውጤታማ ሲሆኑ ብቻ ነው ።
ከዚህ የተነሳም አብዛኞቹ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ሆኑ ያደጉት ሀገራት፤ የኢኮኖሚ ዕድገታቸውን / የዕድገት መሻታቸውን የሚሸከም የኃይል አቅርቦት ለማሟላት ከፍተኛ መዋለ ነዋይ በማፍሰስ የተፈጥሮ አካባቢን ጨምሮ ራሱን የሰው ልጅን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱ አማራጮችን ሳይቀር ሲጠቀሙ ይስተዋላል።
በርግጥ የኃይል አቅርቦት ጉዳይ ከኢንዱስትሪ አብዮት ዋዜማ ጀምሮ የዓለማችን ትልቁ አጀንዳ ከመሆኑ አንጻር፣ አሁን ላይ በተለይም ኋላቀር የሚባሉ ሀገሮች ለጀመሯቸው የልማት ውጥኖች ስኬት ወሳኝ አቅም ሆኖ የመገኘቱ እውነታ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
ሀገራቱ ለዕድገታቸው ሁለንተናዊ መሠረት የሆነውን የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማበልጸግ ፤ ሆነ ለኢንዱስትሪው ዋንኛ ግብአት የሆነውን የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን፤ የኃይል አቅርቦት ጉዳይ በአንድም ይሁን በሌላ ትልቁ አጀንዳቸው ነው።
ከዚህም ጎን ለጎን የሕዝቦቻቸውን ሕይወት ለመለወጥ (ለማዘመን)፤ ሕዝቦቻቸው ዘመኑን የሚዋጅ የአኗኗር ዘዬ ባለቤት በመሆን የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን በቀለለ መንገድ እንዲመሩ ለማስቻልም ይኸው የኃይል አቅርቦት ጉዳይ ወሳኝ ነው።
የኃይል አቅርቦት ልማት ከሚፈልገው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አንጻርም ለውጤታማነቱ ከሁሉም በላይ የሀገራቱን መንግሥታትና ሕዝቦች ከፍያለ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ፤ ቅድሚያ ሰጥተው ሊንቀሳቀሱበት የሚገባ የልማታቸው ስትራቴጂክ አቅም ሆኗል።
በእኛም ሀገር የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገትና / የዕድገቱን መሻት የሚሸከም የኃይል አቅርቦት ለመፍጠር ሰፋፊ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። በተለይም ሀገሪቱ ያላትን የውሀ ሀብት ለኃይል አቅርቦት ስትራቴጂክ አቅም ለማድረግ ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል። የተገኘውም ውጤት ተስፋ ሰጪ ነው።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ለማሳደግ በተደረጉ ጥረቶች፤ ብዛት ያላቸው ግድቦች ተገንብተዋል፤ አማራጭ የኃይል ማመንጫዎች ተግባራዊ ሆነዋል። በዚህም በ2015 በጀት አመት ሀገራዊ ኃይል የማመንጨት አቅምን አምስት ጊጋ ዋት ማድረስ ተችሏል። በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታትም ይህንኑ አቅም ወደ 17 ጊጋ ዋት ለማድረስ እየተሠራ ነው።
ከውሃ፣ ከንፋስ፣ ከፀሐይ እና ከከርሰ ምድር እንፋሎት ለማመንጨት የታቀደው ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል፤ እንደሀገር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመርነው ሀገራዊ ንቅናቄ ስትራቴጂክ አቅም ከመሆን ባለፈ፤ የሕዝባችንን የሕይወት ጉዞ ለማቅለል ትልቅ አቅምም እንደሚሆንም ይታመናል።
ይህ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት /የዕድገት መሻት ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሀገራዊ ጥረት፤ የተገነቡና በቀጣይም በመገንባት ላይ ያሉ ጥቃቅን ፤ መለስተኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ባላ ቸው አቅም ማም ረት የሚያስችላቸውን ዕድል የሚፈጥር ላቸው ይሆናል ።
ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ከማገዝ ባለፈ፤ የገጠሩ አካባቢን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ በማድረግ ሀገሪቱ ካላት ከፍ ያለ የቱሪዝም አቅም ተጠቃሚ የምትሆንበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል ነው።
ይህ በመንግሥትና በመላው ሕዝብ ከፍተኛ ተሳትፎና ቁርጠኝነት እየተከናወኑ ያሉ ሀገራዊ የኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም የማሳደግ ጥረቶች አሁን ባሉበት ግለት ሊቀጥሉና በጠንካራ ዲሲፕሊን ሊመሩ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2015