ኢኮኖሚውን ለማከም የኮንትሮባንድን እንቅስቃሴ ማዳከም ወሳኝ ነው

በኢትዮጵያ የኮንትሮባንድ ንግድ መቼና እንዴት እንደተጀመረ የሚገልጽ የተሟላ ማስረጃ ባይኖርም እንቅስቃሴው ከተጀመረ ግን በርካታ ዓመታትን ማስቆጠሩ ይታመናል። ሀገሪቱም በየጊዜው እየጎለበተ የመጣውን ኮንትሮባንድ ለመግታት የተለያዩ ሕጎችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ አድርጋለች።

የኮንትሮባንድ ወንጀልና ቅጣትም በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 በግልጽ ተቀምጧል። ይህ አዋጅም ማንኛውም ሰው እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው የጉምሩክ ሕጎችን፣ ደንቦችን ወይም መመሪያዎችን በመተላለፍ የተከለከሉ፣ ገደብ የተደረገባቸውን፣ የንግድ መጠን ያላቸውንና የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈጸመባቸውን ዕቃዎች ከሕጋዊ መተላለፊያ መስመሩ ውጪ በድብቅ ወደ ሀገር ካስገባ፣ ካስወጣ ወይም ከሞከረ ወይም በሕጋዊ መንገድ የወጡ ዕቃዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ መልሶ ካስገባ ከአምስት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እሥራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል። እንዲሁም ከብር 50ሺ በማያንስና ከብር 200ሺ በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ ያስቀምጣል።

በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኙ ዕቃዎችን ያጓጓዘ፣ ያከማቸ፣ የያዘ፣ ለሽያጭ ያቀረበ ወይም የገዛ ሰው ከሦስት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እሥራት እና ከብር 50ሺ እስከ 100ሺ እንደሚቀጣ ያስቀምጣል። ወንጀሉ የተፈፀመው ኃይል በመጠቀም ወይም በቡድን በመደራጀት ከሆነ ደግሞ የእሥራት ቅጣቱ እስከ 15 ዓመት ከፍ ይላል።

ምንም እንኳን ሀገሪቱ ተግባሩን ለመቆጣጠር መሰል ሕጎችን ተግባራዊ ብታደርግም በኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር የማስወጣትና ማስገባት እንቅስቃሴን በሚፈለገው ልክ መግታት አልተቻላትም። ይህ ድክመትም በኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት ላይ ከባድ ተፅእኖ ሲፈጥር አመታት ተቆጥረዋል።

በኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር የማስወጣትና የማስገባት እንቅስቃሴ በአንድ ሀገር ላይ ላይ ከሚያደርሰው ኪሳራ ባሻገር ጉዳቱም የእያንዳንዱን ቤት የሚያንኳኳ ነው። የኮንትሮባንድ ንግድ ተገቢው ግብር የማይከፈልበት በመሆኑ ሀገር በቀረጥም ሆነ በታክስ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ያሳጣል። በርካታ ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸውን እንደ መንገድ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችላትን ገቢ ይነጥቃል።

የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ተወዳዳሪነት ይቀንሳል። ከወጪና ገቢ ንግድ የሚገኝን ግብርና ቀረጥ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን ያሳጣል። በዜጎች መካከል ሰፊ የገቢ ልዩነትን ያስከትላል። ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓቱን ያመሰቃቅላል። በሀቀኛ ግብር ከፋዮች ላይ የግብር ጫናን ከፍ ያደርጋል።

ጥቁር ገበያን በማስፋፋት የውጪ ምንዛሪ እጥረት በመፍጠር፣ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ያዳክማል። ባለሀብቶች በሀገር ውስጥ ያመረቱትን ምርት ገበያ ይሻማል። የሸቀጦችን ዋጋ በማናር የዋጋ ግሽበትን ስለሚፈጥር በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ ያከብዳል።

ወንጀሉ በአጠቃላይ ልማት በሚፈለገው ፍጥነትና መጠን እንዳይስፋፋ በማድረግ ድህነት በመቀነስ ፈንታ እንዲባባስ ያደርጋል። በቀደመው ሥርዓትም ሀገሪቱ በወንጀሉና በወንጀለኞቹ ተተብትባ ለከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኪሳራን ስታስተናግድ ቆይታለች።

አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም የኢትዮጵያና የኮንትሮባንድ ጋብቻ ከለውጡ በፊት እና በኋላ በሚል በሁለት ከፍለው ይመለከቱታል። ከለውጡ በፊት የነበረው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴም በገቢውም ሆነ በወጪ ምርት እጅግ ከፍተኛ እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀር ዋነኛ ተዋናይ የነበሩበት መሆኑን ያስታውሳሉ።

«ቀደም ባሉት አመታት ኮንትሮባንድ እንደ ፖለቲካ ስትራቴጂ የተወሰደ፣ ተዋናዮች ከውጭ ሆነው ከሚሳተፉት ብቻ ሳይሆን ቁልፍ በሆነ የመንግሥት ተቋማት፣ የደህንነትና የመከላከያ መዋቅር የተቆጣጠሩ አካላት በግልፅ የሚሳተፉበት ነበርም›› ይላሉ። የወንጀሉ ከፍታም አጠቃላይ ሥርዓተ መንግሥቱን የመቆጣጠር ደረጃ የደረሰ እንደነበር ያስታውሳሉ።

በአሁኑ ወቅት በመንበረ ሥልጣኑ ላይ የሚገኘው መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ማግስት አንስቶ ከባድ የሀገር የኢኮኖሚ ፈተና የነበረው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ መሆኑ እርግጥ ነው። በወንጀሉ ተሳታፊና የጥቅሙ ተጋሪ የነበሩ ግለሰቦች እንጀራቸው እንደሚቋረጥ በመረዳት ብሔርን ሽፋን በማድረግ ግጭቶችን ሲያስነሱ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና ከወንጀሉ ሁለንተናዊ አደገኛነት አንፃር መንግሥት ጠንካራ አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው። በዚህም ለውጦች እየተስተዋሉ ነው ። ይህም ሆኖ ግን ችግሩ የኢኮኖሚው ጤና መታወክ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ነው። የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከአነስተኛ እስከ ከባድ የጦር መሣሪያም ሳይቀር የሚዘወርበት እንደመሆኑ ጉዳዩ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የጸጥታና የደህንነት ችግር እየሆነ ነው ።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ሙሉ በሙሉ ለመግታት በሚደረግ ትግል ፍቱን መድኃኒት ለማጣቱ በርካታ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል። ከሁሉ በላይ ሀገሪቱ ኮንትሮባንድን ለመግታት የተለያዩ ሕጎችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ ብታደርግ ያስቀመጠችው ቅጣት ግን ዝቅተኛ መሆኑ ተዋናዮቹ የልብ ልብ እንዲሰማቸው ማድረጉም ይነሳል።

ከለውጡ በኋላ በተለይ የኢኮኖሚውን ጤንነት ለማስጠበቅ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትን ለሁለት የመነጠል ሥራ እጅግ ውጤታማ ነው። ይህ መሆኑም ሀገሪቱ በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የሚደርስባትን ዘርፈ ብዙ ኪሳራ መከላከል እንድትችል ከፍተኛ አቅም ፈጥሯል።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በተለይ ከለውጡ በኋላ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዋነኛ ነቀርሳ የሆነውን ኮንትሮባንድ በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ስኬታማ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። የጉምሩክ ኮሚሽን የተለያዩ የሀገሪቷን መግቢያና መውጫን በመጠቀም የሚገቡ እና የሚወጡ ዕቃዎች ሕጋዊውን መንገድ ብቻ በመከተል እንዲንቀሳቀሱ በሙሉ አቅሙ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ኮሚሽኑ ሥራውን ውጤታማ በሆነ መልኩ እየከወነ ስለመምጣቱ ምስክር ደግሞ በየጊዜው በቁጥጥር ስር የሚውሉ የወጪ እና የገቢ ዕቃዎች በቂ ምስክርነትን የሚሠጡ ናቸው። ኮሚሽኑ በ2015 በጀት አመትም ያከናወናቸው ሥራዎችም ውጤታማ እንደነበሩ ቁጥራዊ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ መረዳት ይቻላል።

ለአብነት የሰኔ ወርን ሪፖርት ብቻ ብንመለከት፣ ኮሚሽኑ ከሰኔ 2 እስከ 8/ 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 76 ሚሊዮን የገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ የወጪ፤ በድምሩ 141 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተይዘዋል።

ከሰኔ 9 እስከ 15/ በተደረገ ክትትል 199 ሚሊዮን የገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ የወጪ፤ በድምሩ ከ275 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተይዘዋል። ከሰኔ 16 እስከ 22/ 2015 ባደረገው ክትትል 169 ሚሊዮን የገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ የወጪ፤ በድምሩ ከ238 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተይዘዋል።

ከሰኔ 23 እስከ 29 /2015 ባደረገው ክትትል 374 ሚሊዮን የገቢ እና ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች፤ በድምሩ ከ384 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተይዘዋል።

የሐምሌን ወር ከተመለከትን ደግሞ ከቀን 7 እስከ 13 / 2015 ባደረገው ክትትል 187 ሚሊዮን የገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና ከ201 ሚሊዮን ብር በላይ የወጪ፤ በድምሩ ከ389 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መያዛቸውን መረዳት እንችላለን።

በተለይ የአዲስ አበባ ኤርፖርት በርካታ ዓለም አቀፍ መንገዶችን የሚያስተናግድ ከመሆኑ የተነሳ የኮንትሮባንድ ፍሰቱ በየጊዜው እየጨመረ እና ውስብሰብ እየሆነ መምጣቱ ይታወቃል። በበጀት አመቱ የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ስር በ11 ወራት ብቻ 152 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የወጪ እና ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የገቢ፤ በድምሩ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን መረጃዎች ያሳያሉ።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የገቢና የወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል ኤሌክትሮኒክስ፣ አደንዛዥ እፆች፣ የጦር መሣሪያ፣ ማዕድናት፣ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች፣ መድኃኒቶች፣ አዝዕርትና የዝሆን ጥርስ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስዱም ለማወቅ ተችሏል።

መሰል አፈፃፀም ማስመዝገብ የተቻለው እንደሌሎች ሥራዎች ጊዜ፣ ዕውቀት፣ ጉልበት ብቻ መስዋዕት በማድረግ ሳይሆን መተኪያ የሌለውን ሕይወት በመሰዋትና አካልን በመገበር ጭምር መሆኑም ፈፅሞ ሊዘነጋ የሚገባው አይደለም።

ይሁንና ኮንትሮባንድ እጅግ በጣም በቀላሉ የሚከበርበት በመሆኑ በቀላሉ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል የሚል እምነት የለም። ቀደም ሲል በነበረው ሥርዓት መንግሥታዊ ከለላ በሚሰጠው፣ ደህንነትና መከላከያን ሳይቀር የሚያሳትፍ ባይሆንም አሁንም ቢሆን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴው ቆሟል ማለት አያስደፍርም።

በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል በተለያዩ ጊዜያት ይህን ያህል መጠን ያላቸው ኮንትሮባንድ ቁሳቁሶች በቁጥጥር ሥራ ዋለ የሚል ዜና የሚሰማውም ለዚሁ ነው። ይሁንና በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት አድናቆት የሚነፈጋቸው አይደሉም።

የሀገሪቱን ኢኮኖሚው ለማከም የኮንትሮባንድን እንቅስቃሴ ማዳከም አሁንም በልዩ ትኩረት ሊሠራ የሚገባው ነው። ከተግባሩ ውስብስብነት አንፃር ሁለተናዊ አቅምን በየጊዜው መፈተሽና በማደራጀትና እግር በእግር እየተከታተሉ ቀዳዳዎችን ሁሉ መድፈን የግድ ይላል።

ከሁሉ በላይ ወንጀሉን ከስር መሠረቱ ለማድረቅ በርካታ ተግባራትን መከወን የግድ ይላል። ለወንጀሉ መፍትሄ ለመስጠት የኮንትሮባንድ ንግዱ እንቅስቃሴን ለመግታት የወጡ የሕግ ቅጣቶች አቅም መጨመር ይገባል። በየጊዜው የኮንትሮባንድ ተዋናዮች ተያዙ ንብረታቸውም ተወረሰ ብቻ ሳይሆን ፈፃሚዎቹንም ለሕግ በማቅረብ ጉዳያቸው የት ደረሰ ? የሚለውን ተከታትለው ሕጋዊ እርምጃዎችን ለማስተማሪያነት መጠቀም ለሕዝብ ማድረስ ተገቢ ነው።

‹‹አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ቢውልም ባለቤቱ አልተገኘም›› ከማለት ይልቅ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ የወንጀሉን መሠረት እና መሪ ባለቤቱን አድኖ ለሕግ ማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ማድረግ ፈፅሞ ሊዘነጋ አይገባም። በወንጀሉ ተዋናዮች ላይ የተቀመጠውም የሕግ ቅጣት ደረጃ ብሎም በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የሚወሰንባቸውን የሕግ ቅጣት አስተማሪ በሆነ መልኩ መቃኘት ያስፈልጋል።

በተለይ የሀገር አለመረጋጋት ሰላም መደፍረስ ለተግባሩ መጎልበት ጉልህ ድርሻ ስላለው ለዚህ ቀውስ ተገቢውን አፋጣኝ መልስ መስጠት ቀዳሚ መሆን ይኖርበታል። ከዚህ ባሻገር አደጋውን የሚመጥን ቅንጅት የቁጥጥር ሥርዓቱን ጥብቅ ማድረግና አመለካከት ላይ በቋሚነትና በስፋት መሥራት ይገባል።

መንግሥት ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የያዘውን የፀና አቋም በስኬት ለማጀብ ብሎም ወንጀሉን የሀገር ህልውና አደጋነት በመረዳት የቅጣት ሕጉን በአግባቡ ተፈፃሚ ለማድረግ በተጓዳኝ በተቆጣጣሪ ተቋማት ብሎም ክልሎች መካከል የቅንጅት ሥራ መሥራት ይኖርበታል።

የኮንትሮባንድ ተዋናዮች ስልት ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ከችግሩ ስፋትና ውስብስብነት አንጻር ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *