በተበላሸ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ተማሪ፣ ችግር እንጂ ሥራ ፈጣሪ ሊሆን አይችልም!

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በርካታ የመንግሥትና የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን እያስመረቁ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ተመራቂዎች በኢትዮጵያ ቀጣይ ጉዞ ውስጥ የየራሳቸውን ዐሻራ ያሳርፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ‹‹ተመራቂውን የሰው ኃይል የሚሸከም የሥራ ዕድል አለ?›› የሚለው ዐቢይ ጥያቄ ከምርቃቱ ጉዳይ ጋር ተያይዘው ከሚነሱት ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ‹‹የተማረና የሰለጠነ›› የሰው ኃይል የሥራ ገበያውን ተቀላቅሎ እንደየሙያው ተሰማርቶ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን መጥቀም እንዳለበት ይታመናል፡፡

ዘንድሮ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቀው የሰው ኃይል ሀገሪቱ በተሸከመችው ነባር የሥራ ፈላጊ ቁጥር ላይ ሲደመር፣ ጉዳዩ ከባድ የሀገር ራስ ምታት እንደሚሆን አይካድም። በእርግጥ ኢትዮጵያ ብዙ የሰው ኃይል የሚፈልግ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አቅምና በርካታ የምጣኔ ሀብት ዕድሎች አላት፡፡ ይህን እምቅ አቅም እና ሥራ ፈላጊ የሆነውን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ዜጋ የማቀናጀቱ ተግባር ዛሬም ድረስ የሚፈለገውን ያህል ውጤትና ስኬት ማስመዝገብ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ትኩረት የሚሻው ዋናው ጉዳይ ይህ ተግባር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የሀገር ሀብትንና ሥራ ፈላጊ ዜጋን የማቀናጀት ተግባር በሳል አመራር ይፈልጋል፡፡ ይህ በሳል የአመራር ሥራ ደግሞ እውቀትን፣ ሙያ አክባሪነትን፣ ሥራና ሀገር ወዳድነትን፣ ቁርጠኛነትንና ያላሰለሰ ትግልን ይጠይቃል። እነዚህን መርሆችንና ተግባራትን ያላሟላና ያላቀናጀ ጥረት ሀገሪቱ ያላትን እምቅ ሀብትና ሥራ ፈላጊውን ዜጋ ሊያስተባብርም ሆነ ስኬትን ሊያስመዘግብ አይችልም፡፡

የተመራቂዎች የሥራ ፈጣሪነት ዕድል በትምህርት ሥርዓቱ ጥራት ላይ ይወሰናል፡፡ ተመራቂዎች ሥራ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ዋነኛ ግብዓትና መደላድል መሆን የሚችለው የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱ ነው፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ጥራት (Quality) ላይ ያተኮረ ከሆነ፣ ተማሪዎች ሥራ ፈጣሪ ሆነው ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል፡፡ ይህ የጥራት ማዕቀፍ የሀገር ሀብትንና አቅምን ማወቅን ያካትታል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ የሀገር ሀብትና አቅምን መሠረት አድርጎ ሊዘጋጅ ይገባል፡፡

የአንድ ሀገር የትምህርት ሥርዓት መበላሸት የሀገሪቱ ህልውና አደጋ ውስጥ እንደገባ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሰላም የሰፈነባት፣ ማኅበራዊ መረጋጋት ያለባት፣ ምጣኔ ሀብቷ ያደገና ፖለቲካዊ የሰከነ ሀገር እውን ማድረግ የሚቻለው ጥራት ባለው የትምህርት ሥርዓት የተገነባ ትውልድ ማፍራት ሲቻል ነው፡፡ ጥራት በሌለውና በወደቀ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ትውልድ ለሀገር ህልውና ትልቅ አደጋ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹አንድን ሀገር ለማፍረስ ጦር ማዝመት ሳያስፈልግ፣ የሀገሪቱን የትምህርት ሥርዓት ማበላሸት በቂ ነው›› የሚባለውን ሃሳብ በተደጋጋሚ የምንሰማው፡፡

ሥራ ፈጣሪነትን በማያበረታታ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ተማሪ፣ ሥራ ጠባቂ ሆኖ ዕድሜውን የሚያባክን ከመሆኑም ባለፈ ጥገኛ፣ ሰነፍና የሀገር ሸክም መሆኑ አይቀርም፡፡ እንዲህ ዓይነት ባህርያት ያሉት ብዙ የሰው ኃይል ደግሞ ችግር ፈጣሪና ሀገር አፍራሽ ከመሆን ያለፈ ሚና አይኖረውም፡፡ በአጠቃላይ በተበላሸ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ተማሪ፣ ችግር እንጂ ሥራ ፈጣሪ ሊሆን አይችልም!

በራሳቸው የሚተማመኑ፣ በምክንያታዊ ትንተና የሚያምኑ፣ በሙያቸው ብቃት ያላቸው፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ አዳዲስ ግኝቶችን አፍላቂዎች፣ ጠንካራ የሥነ ምግባርና ግብረገባዊ እሴቶችን የተላበሱ፣ ለሕግ ዘብ የቆሙ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ ሆነው አጠቃላይ ሰብዕናቸው የተገነባ ዜጎችን ማፍራት የሚቻለው ጥራት ባለው የትምህርት ሥርዓት ነው።

አንዲት ሀገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የሕዝቦቿን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው በሚኖራት የሰው ኃይል እምቅ አቅም ነው፡፡ የሰው ኃይል መገንቢያው ዋነኛው መሣሪያ ደግሞ ትምህርት ነው፡፡ አስተማማኝና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ብቸኛው መንገድ ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓትን መዘርጋት ነው፡፡ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ የሚፈጠረው እነዚህን ግብዓቶች ማሟላት ሲቻል ነው፡፡

‹‹ዋናው ሽፋን/ብዛት ነው፤ የጥራቱ ጉዳይ ቀስ ብሎ ይታሰብበታል›› የተባለው አካሄድ ለኢትዮጵያ ምን እንዳተረፈላት አይተናል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ብልሽት ሀገሪቱን ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፤ እያስከፈላትም ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት ለትምህርት ዘርፍ መሻሻልና የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት አዎንታዊ አስተዋፅዖዎችን እንዳበረከተ ባይካድም፣ ዓይነተ ብዙና ውስብስብ ችግሮችም አሉበት፡፡

የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱ በንድፈ ሀሳብ እንጂ የተግባር ክህሎትና ፈጠራ ላይ ያተኮረ አይደለም። የምዘና ሥርዓቱም ለተግባራዊ እውቀት ትኩረት አልሰጠም። ሥራ ፈላጊ እንጂ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ እየተፈጠረ አይደለም። የምርምርና የቴክኖሎጂ ሥራው ጎልብቶ ኢኮኖሚውን በሚፈልገው መጠን ሲያግዝም አይስተዋልም። በዚህ ምክንያት ኅብረተሰቡ በትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱ የጥራትና የተገቢነት ጥያቄ እያነሳ ይገኛል። ከትምህርትና ሥልጠናው እውቀት፣ ክህሎትና የሥራ ፈጣሪነት አመለካከት በበቂ ሁኔታ ይዞ ከመገኘት ይልቅ ትውልዱ ዲግሪና ዲፕሎማ (ወረቀት) አምላኪ ሆኗል።

ወጣቶች፣ በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች፣ ሥራ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የትምህርት ሥርዓቱን ለዚህ እቅድና ተግባር ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱ ሥራ ፈጣሪነትን የሚያበረታታ ካልሆነ ከእነዚህ ሁሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁት/የሚመረቁት ተመራቂዎች የሀገር ተስፋ መሆናቸው አጠራጣሪ ነው፡፡

የትምህርት ጥራትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ተማሪዎችን ያማከለ ዘመናዊና አሳታፊ የመማር ማስተማር ሂደት መከተል፤ የመምህራን ጥራትና ተነሳሽነት ማጎልበት፤ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደትን መከተል፤ ተማሪዎችን ማነቃቃት፤ ጠንካራ የትምህርት ቤት አመራርን ማብቃት፤ ምቹና ጤናማ የትምህርት አካባቢ መፍጠር፤ የማስተማሪያ ግብዓቶች ማሟላት እንዲሁም የተማሪዎች ሥነ ምግባርን ማሳደግ ይገባል።

የተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚገባ የመከታተል፤ የመምህራን በጥራት የማስተማር፤ የትምህርት አመራር ስትራቴጂካዊ አመራር የመስጠት እንዲሁም የወላጆች ልጆቻቸውን በንቃት የመከታተልና የመደገፍ ተግባራት በቅንጅት ሊከናወኑ ይገባል። በትምህርትና ሥልጠና በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት ባለፉት ዓመታት የትምህርትን ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት፣ አግባብነትና ጥራትን ለማጎልበት የተሠሩ ሥራዎች ያስገኙትን ውጤት መገምገምም ይገባል፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ በሥነ ምግባር፣ በመልካም እሴትና በብቃት የታነጸ ዜጋን ለማፍራት በሚያስችል መንገድ የተቀረፀ፣ የሀገሪቱን ዕድገትና አንድነት የሚያስቀጥል እንዲሁ ሥራ ጠባቂ ከመሆን ይልቅ ለሥራ ፈጣሪነትና ለሀገር በቀል እውቀቶች ተገቢውን ትኩረት የሰጠ መሆኑን በሚገባ መፈተሽና ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

የትምህርት ሥርዓቱንም ሆነ የመማር ማስተማር ሥራ በተግባር ተኮር እውቀት በመደገፍ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት መጣር ያስፈልጋል፡፡ አዲሱ የትምህርት ሥርዓት ይህን ጥረት እውን ለማድረግ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ስለሆነም በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ሥራ ፈጣሪነትን ባህሉ ያደረገ ትውልድ እንዲፈጠር የትምህርት ሥርዓቱን ትግበራ በከፍተኛ ጥንቃቄና ትጋት መምራት ይገባል!

ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *