«በሥነ ምግባር የታነጸና በትምህርት የጎለበተ ትውልድን መገንባት የግድ ይለናል»ዶክተር ዘላለም ሙላቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ

የትምህርት ጥራት በአንድ ጀምበር የሚመጣ አይደለም። ሰፊ ሥራን የሚፈልግ፣ የዘርፉን ተዋንያን ጨምሮ የብዙዎችን ትብብር የሚሻ ነው። ለጥራት ትኩረት የሚሰጥ የትምህርት ሥርዓት እና ፖሊሲን ከመቅረጽ ጀምሮ ተማሪዎች ከታች ተገቢውን ትምህርት እያገኙ የሚሄዱበትን አቅም ማሳደግ፤ ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነትን መፍጠር የሚጠይቅ ነው።

ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማሩ ሥራ ያላቸውን ሁለንተናዊ አቅም ማጎልበት፤ የትምህርት ግብዓቶችን መሟላት፣ የመምህራን ብቃት ማሳደግ …ወዘተ ለትምህርት ጥራት ወሳኝ እንደሆኑ ይታመናል። ጥራት ባለው የትምህርት ሥርዓትም ሀገርን በኃላፊነት መንፈስ የሚረከብ ትውልድ መፍጠር ይጠበቅብናል።

 አዲስ ዘመን፡- ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮችና ችግሮቹን ለመፍታት እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቦታል።

አዲስ ዘመን፡- ቢሮው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከመማር ማስተማር ጋር ተያይዞ ያከናወናቸው ተግባራት ምንድን ናቸው?

ዶክተር ዘላለም፡- በትምህርት ዘርፉ ያለው ትልቁ ጉዳይ የመማርና ማስተማር ሥራ ነው፤ የትምህርት ቤቶች ደረጃና ስታንዳርድ ማስጠበቅ ደግሞ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ትልቅ ሚና አለው። የትምህርት ሥራ በሶስት መንገድ ይለካል። አንደኛው በግብዓት፣ ሁለተኛው በሂደት፣ ሶስተኛ በውጤት ነው። ግብዓቱም፣ ሂደቱም ሆነ ውጤቱ የሚሰራው ሰው ላይ ነው። ከዚህ አኳያ የትምህርት ሥራ ከሌሎች ሥራ የሚለይበት ዋናው ተግባር ይህ ነው።

ሥራው ሰው ላይ መሥራትን መሠረት ያደረግና ሰው ላይ ኢንቨስት የሚያደርግ ነው። አንድን ሰው ተቀብሎ የሚፈለገው ምን አይነት ሰው እንዲሆን ነው በሚል ቀርጾ የሚያወጣ ነው። ከዚህም ዘርፉ ለተሻለ ደረጃ ሰርቶ የሚያበቃን አሰራር የሚከተል ዘርፍ ነው።

ይህን በማድረግ ሂደት ውስጥ ግብዓት ወሳኝ ነው። የትምህርት ቤቶች ስታንዳርዳቸው ሲጠበቅ፣ ደረጃቸው ሲሻሻል፣ አስፈላጊ የሚባሉ የትምህርት ቁሳቁሶች ሲሟሉ እንዲሁም አስፈላጊ የሚባሉ መሠረተ ልማቶች ሲስተካከሉ ግብዓት ሙሉ ይሆናል። ሂደቱን ቀላል፣ ምቹ፣ ሳቢ እና ማራኪ ያደርገዋል።

ግብዓት ከተሟላ ምቹ፣ ሳቢ እና ማራኪ እንዲሁም የተቀላጠፈ አገልግሎትና አሰራር ስለሚኖር ውጤቱም ያማረ ይሆናል። ውጤት ላይ ደግሞ እንደሚታየው ባለፈው ዓመት ሀገር አቀፍ ፈተና ላይ አንጻራዊ በሆነ መልኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጤት ተሽሎ ተገኝቷል። ይሁንና በወቅቱ ይፋ የተደረገው ውጤት እንደ ሀገር ያለንበትን የትምህርት ጥራትና ያለንበት ደረጃ በአግባቡ ያሳየ ነበር።

የፈተናው አወጣጥ፣ የክብደት እና ቅለቱ ሁኔታም ሆነ ተማሪዎች የተማሩበት አካባቢ ለውጤት ማነስ የራሱ ድርሻ ሊኖረው ይችላል፤ ነገር ግን በዋናነት የትምህርት ጥራት ሂደታችን ያለበትን ደረጃ በግልጽ ያሳየ ነው።

ይህ የትምህርት ጥራት ጉዳይ እንደ ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጨምሮ ብዙዎችን ሃሳብ ውስጥ የከተተ ነው፤ የትምህርት ጥራት መረጋገጥ የሁሉም ሰው ሚና ሊሆን የሚገባው ነው። ካለንበት ችግር መላቀቅ አለብን። ስለዚህም ከችግሩ ለመላቀቅ ችግሩን ማግኘት አንድ ሥራ ነው፣ ከችግሩ መላቀቅ ደግሞ ሌላኛው ትልቁ ሥራ ተደርጎ ተወስዷል።

ከችግሩ በመላቀቅ ሂደት ውስጥ የመንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የቀድሞውም የአሁኑም ተማሪዎች፣ የወላጆች፣ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ሲረባረቡ እና ሥራውን ሲሰሩ የምንናፍቀውን ውጤት ማግኘት ይቻላል። ለዚህም እንደ ሀገር ትልቅ ቁርጠኛ ሆነናል።

ይህ ቁርጠኝነት ለእኛ በተለይ የትምህርት ዘርፉን ለምንመራ አካላት በጣም ትልቅ እፎይታ የሰጠ ነው። አጋጣሚውንም እንደ ትልቅ እድል ወስደነዋል። ሁኔታውን ለእኛ እድል የሚያደርገው ምንድን የተባለ እንደሆን፣ የአዲስ አበባ የትምህርት ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተቀየረ ነው። ወደኋላ ዞር ብለን ስንመለከት ተማሪዎች ትምህርት ቤት ለመምጣት በመማሪያ ደብተር፣ እስክሪብቶ፣ በትምህርት ቤት የደንብ ልብስ እንዲሁም በምግብም እጦት ምክንያት ትምህርት ቤት የማይመጡ ሕጻናት ቁጥር ቀላል አልነበረም።

አዲስ አበባ ሁሉንም ሕጻናት ማስተናገድ የምትችል የሀብታሙም የደሃውም ከተማ ነች። ዜጎች እንደ ዜግነታቸው፣ ሕጻናት እንደ ሕጻንነታቸው የመማር፣ የማደግ፣ የመብላት፣ የመጠጣት እና ያለመታረዝ መብታቸው ተረጋግጦ መሄድ አለበት፤ይህንን ተጨባጭ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት አከናውነናል። ለምሳሌ የትምህርት ምገባ፣ ቁሳቁስ እና የት/ቤት የደንብ ልብስ ማቅረብ ጀምረናል።

የትምህርት ኢንቨስትመንት በትምህርት ሥርዓት ውስጥ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው። በተለይ የመክፈል አቅም የሌላቸውና አቅመ ደካማ የሆኑ ቤተሰቦች ላለፉት አራት ዓመታት በተከናወነው ተግባር ትልቅ እፎይታ አግኝተዋል።

በተለይ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታን ስናስተውል፤ የኑሮ ውድነቱና የገበያው መናር በነዋሪዎች ላይ ጫና የሚፈጥር ነው፤ የትምህርት ቤት የምገባ ሥርዓት ቀድሞ ባይጀመር ኖሮ ምን ሊሆን እንደሚችሉ ማሰብ በራሱ ከባድ ነው። በተለይ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች፤ ለልጆቻቸው በተደረገው መልካም ሥራ መማር መቻላቸው የድሃ ተኮር ሥራችንን እጅግ በጣም ውጤታማ ያደርገዋል።

ይህን ማድረጋችን ተማሪዎች በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ረድቷል፤ ክፍል መድገምም እንዲቀንስ አስችሏል። ከዚህ ጎን ለጎን የማለፍ ምጣኔ ከፍ ብሏል። በትምህርት የመዝለቅ ምጣኔም የተስተካከለ ሆኗል። ይህ ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው።

በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ የምናደርጋቸው ኢንቨስትመንቶች የሀብታም ወይም የደሃ ልጅ ነው በሚል የሚተገበር ሳይሆን በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ተማሪ ሆኖ በመገኘቱ የሚያገኘው አገልግሎት ነው። ስለዚህ ይህንን ኢንቨስትመንት እንደ ሂደት ወስደነው ውጤት ላይ የራሱ የሆነ ሚና እንዲኖረው ያደረግነው ሥራ ከፍተኛ ነው።

እንደ ከተማ ባለፉት ሶስት ዓመታት ትምህርት ቤቶች ላይ ግብዓት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ሰርተናል። እንደሚታወሰው በ2012 በጀት ዓመት ሁሉንም ትምህርት ቤቶቻችንን አድሰን ነበር። በወቅቱ ሲታደሱ የነበሩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች 488 ናቸው። በአሁኑ ሰዓት ግን የትምህርት ቤቶቹ ቁጥር 562 ከፍ ብሏል።

ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ ብቻ የተጨመሩትን የትምህርት ቤቶች ቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ ማየት ያስፈልጋል። በጣም ወሳኝ የሆነ ሚና የሚጫወቱ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማትን ማሟላት ነው። ከሶስት እና ከአራት ዓመት በፊት ደረጃ ሶስት የሆኑ ትምህርት ቤቶቻችን በጣም ውስን ነበሩ። በአብዛኛው ደረጃ አንድ እና ደረጃ ሁለት ላይ የነበሩ ናቸው።

አሁን ግን ይህንን አውርደነው ደረጃቸው ተስተካክሎ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶቻችን ያሉት ደረጃ ሶስት ላይ ነው። ይህ የሚያሳየው የትምህርት ቤቶቻችን ደረጃ ከፍ እያለ መሄዱን ነው። ደረጃ አንድ ላይ ከነበሩ በርካታ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አሁን የቀረን አንድ ትምህርት ቤት ብቻ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ደረጃ የምትለዩበት መስፈርት ምንድን ነው?

ዶክተር ዘላለም፡- ሁሉን ያሟላ ነው የሚባለው ደረጃ አራት ነው። ይህ በሁሉም ነገር ያማረና መያዝ የተገባውን ግብዓት የያዘ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ማከናወን የምንፈልገው ‹‹ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ›› በሚለው መርህ ትምህርት ቤቶቻችን ወደ ደረጃ አራት እንዲገቡ ማድረግ ነው። በነገራችን ላይ ይህ ‹‹ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ›› አስቀድሜ ለትምህርት አመራሩ ትልቅ እፎይታ ነው የማለቴ ምስጢር አቅም ስለሚፈጥርልን ነው። በተለይ ደግሞ ባለድርሻዎችን አነቃንቆ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡም የሚያደርግ ነው የሚል እምነት አለን።

በዚህም መሠረት ያሉንን 562 ትምህርት ቤቶችን በሙሉ መዝነን ያለባቸውን ችግር ለይተናል። ለምሳሌ የአቃቂን ክፍለ ከተማ በአብነት እንውሰድ፤ በክፍለ ከተማው ውስጥ ያሉ ትምህርት ቤቶች ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ ደረጃ እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተለይተው ተቀምጠዋል። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ምን ምን ችግር አለ? የሚለው በአግባቡ ተለይቷል።

ለአብነት፤ የአቃቂ መንግሥት ትምህርት ቤት የሚባል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አለ፤ በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ ችግሮችና የሚያስፈልገው ግብዓት ምንድን ነው? የሚለውን ብቻ ስናይ አስፈላጊዎቹ ጉዳዮች ተጨማሪ ዘጠኝ መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍት እንዲሁም ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሆን ቤተ ሙከራ ነው። በዚህ አግባብ ለ562ቱም ትምህርት ቤቶች የሚያስፈልገው ግብዓት ምንድን ነው? በሚል ሰነድ ሰንደናል።

ስለዚህ አንድ ትምህርት ቤትን ‹‹እኔ መገንባት እችላለሁ፤ የዚያን ትምህርት ቤት ችግር መቅረፍ እችላለሁ›› የሚል አካል ሲመጣ የእያንዳንዱን ትምህርት ቤት ችግር ከወዲሁ ፈትሸን የሚያስፈልጋቸውን ለይተን ስለሰነድን በቀላሉ የሚያስፈልጋቸው ይህ ይህ ነው ብለን ‹‹የምትችለው የትኛውን ነው›› በሚል ሊሰራ የሚችለውን ለይቶ እንዲወስድና እንዲሰራ የሚያስችል ጥናት አድርገናል።

ሌላው የሰራነው ሥራ ቢኖር ተቋማት ለምሳሌ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዙሪያ ያሉ ተቋማት እነማን ናቸው? ቢባል ለምሳሌ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ አለ፣ ሆቴሎች እና ሌሎች ድርጅቶች አሉ። በትምህርት ቤቱ በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው፤ ለመማር ማስተማሩ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ ተቋማትን ለይተን ለማስተሳሰር ጥረት አድርገናል።

ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ መስከረም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወስደዋል። ይህን ትምህርት ቤት አሳምረውና ብቁ አድርገው ያስረክቡናል። በተመሳሳይ ምክትል ከንቲባውም ሌላ ትምህርት ቤት የወሰዱ ሲሆን፣ ብቁ አድርገው የሚያስረክቡን ይሆናል። በዚህ መልኩ በሁሉም ክፍለ ከተማ ተመሳሳይ ሥራዎች ተጀምረዋል። ይህን መሠረት አድርገን ክትትል ማድረግ ጀምረናል።

ጉዳዩ የሚገኘው ምን ደረጃ ላይ ነው? የሚለውን ለማወቅ በ562ቱም ትምህርት ቤቶች ላይ በከተማዋ ውስጥ ያሉ ሱፐርቫይዘሮች በሙሉ ተውጣጥተው ያለፈው ረቡዕ ለሶስት ቀናት ያህል ክትትል አድርገዋል። ለክትትሉ ጥራት እንዲያመችና ተዓማኒም እንዲሆን በመታሰቡ ከአንዱ ክፍል ከተማ የመጣ ሱፐርቫይዘር ወደሌላ ክፍል ከተማ በመሄድ እንዲከታተል ተደርጓል።

ለምሳሌ ከአራዳ ክፍል ከተማ የመጣ አንድ ሱፐርቫይዘር ጉለሌ አሊያም ሌላ ክፍል ከተማ ሔዶ እንዲያይና በትክክል እና በተጨባጭ ሥራው እየተሠራ ስለመሆኑ ተከታትሎ እንዲያጣራ ተደርጓል። በየክፍለ ከተማው ትልቅ ሥራ እየተሠራ ነው። ለዚህ ሥራ መንግሥትም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶታል። በትምህርት ሚኒስቴር ፖርታል (Portal) ተዘጋጅቷል። በዚህ መሠረት አንድ ሰው የተማረበትን ትምህርት ቤት በፖርታል (Portal) ውስጥ ማግኘት ይችላል። ከዚህ በመነሳት አንድ ሰው የተማረበት ትምህርት ቤት ምን ችግር እንዳለበት በዛው አጋጣሚ ማወቅ ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንደሚሉት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለይታችኋል፤ እጅግ በጣም ከደረጃ በታች ናቸው ተብለው የተለዩ ትምህርት ቤቶች በጥቅሉ ምን ያህል ናቸው?

ዶክተር ዘላለም፡– ከደረጃ በታች ናቸው የሚባሉ ትምህርት ቤቶችን ምን ያህል እንደሆኑ መግለጽ ይቻላል፤ ነገር ግን አንዳንዴ እንደዚህ አይነት ትምህርት ቤቶችን ከደረጃ በታች ናቸው ብሎ ሲለዩ ትምህርት ቤቶች አራት ፈርጅ ያላቸው መሆኑን ነው። ሁሉ ነገር የተሟላላቸው ናቸው የሚባሉ ትምህርት ቤቶች ደረጃ አራት ላይ የሚገቡ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ደረጃ አራት ላይ መግባት የሚችሉ፤ ግን ደግሞ ያልተመዘኑ ትምህርት ቤቶች አሉ።

 ከዚህ አኳያ ከትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር ተነጋግረናል። ዛሬ ቢመዘኑ ደረጃ አራት የሚገቡ ትምህርት ቤቶች አሉ። ይሁንና የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት ያሟሉ ቢሆኑም ምዘና ስላልተደረገ ብቻ ደረጃ አራት ውስጥ መካተት አልቻሉም። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት ሰጥተን ሰርተናል።

አንድ ትምህርት ቤት ደረጃ አራት ለመግባት በምዘና ወቅት ውጤቱ ከ90 በመቶ በላይ መሆን የግድ ይለዋል። እንዲህ አይነት ምዘና ሲካሄድ አንዳንዶቹ ደረጃ ሶስት ላይ ሆነው ሲመዘኑ 89 በመቶ ውጤት አምጥተው ያቺን አንድ በመቶ ባለማሟላታቸው ብቻ እዛው ደረጃ ሶስት ላይ ይሆናሉ። በመሆኑም በቀጣይ በእነዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራ ይሆናል። በተለይም በዚህ ሶስት ወር ውስጥ ከሠራን በኋላ የደረጃ ምዘና የምናካሄድ ይሆናል። ደረጃ ሁለትም በተመሳሳይ የምንሠራበት ይሆናል።

ሁሉም ትምህርት ቤቶች ደረጃ አራት አይባሉ እንጂ ደረጃ አላቸው። ለምሳሌ ደረጃ አንድ ላይ አንድ ትምህርት ቤት አለ። ለእሱም ትኩረት ተሰጥቶት ከፍ የማድረግ ሥራ እንሠራለን። በትምህርት ቤት ደረጃ ላይ ርብርብ የተደረገ ሲሆን፣ በቀጣዩ በጀት ዓመት ይቀየራሉ የሚል እምነት አለኝ። የምዘና ውጤቱም በሂደት የሚስተካከል ይሆናል።

እውነት ለመናገር ከሌሎች ክልሎች አኳያ ሲታይ አንጻራዊ በሆነ መልኩ የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ያሉበት ደረጃ የተሻለ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። በቀጣዮቹ ጊዜያት ትምህርት ቤቶቻችንን በሙሉ ወደ ደረጃ አራት እናመጣቸዋለን ብለን በመሥራት ላይ እንገኛለን።

ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ የሠራነው ትልቅ ነገር ቢኖር በጣም ምርጥ የሆኑ ሁለት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን መሥራታችን ነው። አንዱ የእቴጌ መነን የድሮ የሴቶች ትምህርት ቤት ሲሆን፣ ለወንዶች ደግሞ ገላን ላይ ሰርተናል። ተማሪዎቹ የሚመጡት ከመንግሥት ትምህርት ቤት ነው፤ አሁን አሁን ግን ከግል ትምህርት ቤቶች መቀላቀል ጀምረናል።

አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ቤት ደረጃን ከማሻሻል ጎን ለጎን የትምህርት ጥራት ደግሞ ዋና እና አሳሳቢው ጉዳይ ነው፤ ከዚህ አኳያ ከቅድመ አንደኛ ጀምሮ ያለውን የመማር ማስተማር ሂደት በምን አግባብ ትኩረት ልትሰጡ አሰባችሁ?

ዶክተር ዘላለም፡- አዲስ አበባ ቅድመ አንደኛ ደረጃን በመጀመር ፈር ቀዳጅ ነው። ቅድመ አንደኛ ደረጃ የፖሊሲው አካል ሆኖ ክልሎችም እንዲጀምሩ ተደርጓል። እኛ በሁሉም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲኖር አድርገናል። የእነዚህ ትምህርት ቤት ቁጥር ወደ 200 ያህል የሚሆን ነው። ስለዚህ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን እንዲጠብቁና ጥራት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል። እየሠራን ያለነው ከዚህ አኳያ ነው።

እኛ ሥራ መሥራት ያለበት ከሥር መሠረቱ ነው የሚል እምነት አለን። ለምሳሌ 12ኛ ክፍል ከተፈተነው ተማሪ ይህን ያህሉ ወደቀ ሲባል ቅድመ አንደኛ ላይ ምን ሰርተናል የሚለው መጤን አለበት ባዮች ነን። ስድስተኛ ክፍል ምን ሰርተናል መባል አለበት። ለምሳሌ የ6ኛ ክፍል ሚኒስትሪ የፈተነው አዲስ አበባ ብቻ ነው። ይህ እንደ ክልል ተግባራዊ ያልተደረገ ነው። እኛ በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን ጀምረናል። ይህን የ6ኛን ክፍል ሚኒስትሪ እኛ ጀመርን ማለት ቢያንስ እዛ ደረጃ ላይ ደርሰናል ማለት ነው።

እኛ ማለፍ የማይገባውን ተማሪ አናሳልፍም። አንድ ተማሪ 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ካላመጣ ወደ ቀጣዩ ማለትም ሰባተኛ ክፍል መዘዋወር አይችልም። ስለዚህ እዚህ ላይ ይጠራል። የወደቁ ተማሪዎችም ለምን እንደ ወደቁ እና እጥረቱ ምንድን ነው ብለን ለይተን ሰርተናል። 8ኛ ክፍልም ተመሳሳይ ነው።

የትምህርት ኢንቨስትመንትን በተመለከተ በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ የምፈልገው መረጃ፤ ለተማሪዎች ምገባ፣ የደንብ ልብስና ሌላ ቁሳቁስ አቀረብን፤ ከመቅረቡ በፊት የተማሪ ቁጥር አዲስ አበባ ላይ 50 እና ከዛ በላይ አምጥቶ አያውቅም። 50 እና ከዛ በላይ የሚያመጣው ተማሪ ቁጥር 50 እና ከ50 በታች ነው።

ይህን ቁጥር ባለፉት ሶስት ዓመታት ለማሻሻል፤ በመጀመሪያው ዓመት 50 ነጥብ 03 በመቶ፣ በሁለተኛው ዓመት 57 በመቶ፤ በአሁኑ ወቅት ማለትም በሶስተኛ ዓመታችን 64 በመቶ አድርሰነዋል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው።

በቅርቡ የተጀመረው የ6ኛ ክፍል ሚኒስትሪም ሆነ ሲሰጥ የቆየው የ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተናዎች ጠንካራ እና የሚለዩ መሆን አለባቸው ወደሚለው ድምዳሜ መጥተናል። በዚህ ላይ ዘንድሮ ትኩረት ሰጥተን መሥራት ጀምረናል። ቀደም ብለን መጀመራችን በኋላ ላይ ውጤቱ ሲመጣ ትርፉን ለማየት የሚያስችል ነው።

የዘንድሮን የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ፈተና እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ ድረስ ለማውጣት ጥረት እያደረግን ነው። ከዚያ በኋላ ዝግጅታችንን እንጀምራለን። ጥራት ያለው ስታንዳርዱን የጠበቀ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ፤ ኃላፊነት የሚሰማውና ስለሀገሩ ግድ የሚለው ትውልድ ማፍራት ይጠበቅብናል።

በሥነ ምግባርም የታነጸና በትምህርትም የጎለበተ ኢትዮጵያን መረከብ የሚችል ትውልድ መገንባት የግድ ይለናል። ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መከራከርም ሆነ መወያየት የሚችል ትውልድ ያሻናል፤ ከግጭት ይልቅ መወያየትንና ችግሮችን መፍታት የሚችል ዜጋ ያስፈልገናል።

ዜጋው አስተሳሰቡ ዴሞክራሲያዊ ከመሆኑም በተጨማሪ ብዝሀነትንም መቀበል የሚችል መሆን ይጠበቅበታል። ሀገር ባለውለታው እንደሆነችም የሚያስብ ዜጋ መሆን አለበት። ሀገራችን ለሁላችንም እኩልና አስፈላጊ እንደሆነች የሚያመን መሆን ግድ የሚለው ዜጋ መሆን አለበት። እንዲህ አይነቱን ትውልድ ደግሞ ለመገንባት ከወዲሁ የየራሳችንን ድርሻ ለመወጣት መታተር ያስፈልገናል።

ይህን ማድረግ ስንችል ሀገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ፤ ብልጽግናዋም እውን መሆን ይጀምራል። ስለዚህ ሀገር የምትበለጽገው ሰው ሲበለጽግ ነው። ሀገር የምትቀየረው ኃላፊነት ያለው ትውልድ ሲኖር ነው። በዚህ ጊዜ አንድነት ይረጋገጣልና ትኩረት አድርገን እየሠራን እንገኛለን። በ2016 የትምህርት ዘመንን በዚህ ጉዳይ አተኩረን በተሻለ ሁኔታ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት እያደረግን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ትምህርት ቤት መከፈቻው በተቃረበ ቁጥር የመማሪያ መጻሕፍት ጉዳይ አሳሳቢ ይሆናል፤ ወላጆችም ለልጆቻቸው የሚሆን መማሪያ መጻሕፍት ለማግኘት ሲቸገሩ ይስተዋላል፤ ከዚህ አኳያ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ችግሩን ለመፍታት ምን የታሰበ ነገር አለ?

ዶክተር ዘላለም፡– እውነቱን ለመናገር እኛ ከመጽሐፍ ጋር በተያያዘ ከሌሎች ክልሎች በተሻለ ሁኔታ ላይ ነን። እንደሚታወቀው የመጻሕፍት ገበያው በጣም የተጨናነቀ ነበር። መጻሕፍትን አትሞ ማቅረብ ከዶላር እጥረት የተነሳ ከባድ ነው። ብዙዎቹ ግብዓቶች የሚገቡት ከውጭ ሀገርና። እሱ የፈጠረብን ጫና አለ። ይሁንና ፈተናውን አልፈን ብዙ ሙከራ አድርገናል።

በመስኩ ያጋጠሙ ፈተናዎችን አልፈን ያሳተምናቸው መጻሕፍትን ተቀብሎ ለየተማሪዎቻቸው ከማድረስ አኳያ ግን በግል ትምህርት ቤቶች አካባቢ አንዳንድ ችግሮች አሉ። መጻሕፍትን ወስዶ ለማድረስ ፍላጎት የማጣታቸው ባህሪ አጽንኦት ተሰጥቶት መገለጽ ያለበት ነው። የግል ትምህርት ቤቶች ታትሞ የመጣን መጽሐፍ ወስደው ለወላጅ ማቅረብ ላይ የፍላጎት ማነስ ስላለ ነው እንጂ ችግሩ የመጽሐፍ ማነስ ብቻ አይደለም።

ለግል ትምህርት ቤቶች የምናሳትመውን መጽሐፍ የምናስቀምጥበት መጋዘን (Store) አለ። በዚያም ውስጥ በቂ መጽሐፍ አለ። ነገር ግን ይህንን ወስዶ ከማሰራጨት አኳያ የፍላጎት ተነሳሽነት ይጎድላቸዋል። ስለዚህ አንዱ በቅድመ ዝግጅት ሥራችን ትኩረት አድርገን የምንሠራው ከትምህርት ቤት ባለቤቶች ጋር ተቀምጦ መነጋገር ነው። ለተማሪዎች መጽሐፉን በወቅቱ ማቅረብ አለባቸው።

አዲስ ዘመን፡- የግል ትምህርት ቤቶች የመማሪያ መጽሐፍ እያለ ለተማሪዎቹ ማቅረብ የማይፈልጉበት ምክንያት ምንድን ነው?

ዶክተር ዘላለም፡- መጽሐፉን ካለበት ወስደው ለየተማሪዎቹ ለመስጠት በሚያደርጉት ሂደት የትራንስፖርት ወጪ ያስወጣቸዋል። ‹‹የዚያን ያህል የትራንስፖርት ገንዘብ አውጥተን ለተማሪ መስጠት ትርፋማ አያደርገንም›› ብለው ያስባሉ። ስለማያተርፉበት መጽሐፍ ማጓጓዙን እምብዛም አይፈልጉትም። ይህ ደግሞ የሚመጣው ኃላፊነትን መወጣት ካለመፈለግ ነው።

የብዙዎቹ እይታ ገንዘብን ነው። ወጪን ማውጣት አይፈልጉም። ይህ ደግሞ በራሱ አግባብነት የሌለው አካሄድ በመሆኑ መጽሐፉን ወስደው ለየተማሪዎቻቸው እንዲሰጥ በማያደርጉ ተቋማት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ርምጃ እንወስዳለን።

ይህን ስናደርግ ሁሉንም በጅምላ አንጨፈልቅም። እሱን ማድረጉም አግባብ አይደለም። ትኩረታችን የሚሆነው መጽሐፉን ወስደው ለተማሪዎቹ በማይሰጡ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ነው። ምክንያቱም በሥነ ምግባርም ሆነ መመሪያና ሕግ የሚያከብሩ እና በታዘዙት መሠረት ወዲያው መጥተው መጽሐፉን ወስደው ለየተማሪዎቻቸው የሚያዳረሱ አሉና እነሱን የሚመለከት አይሆንም። አብዛኛዎቹ ዘንድ ግን በዚህ ጉዳይ የሚታይ ዳተኝነት አለ፤ እሱ ላይ እየሠራን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡- የመምህራን ብቁ መሆን ለትምህርት ጥራት መጠበቅ አንዱ ጉዳይ ነው፤ ከመምህራን ጋር ተያይዞ የታሰበው ጉዳይ ምንድን ነው?

ዶክተር ዘላለም፡- እንደሚታወቀው የትምህርት ጥራት የመማሪያ ቁሳቁስ ስለተሟላ ብቻ ይመጣል ተብሎ አይታሰብም። አሊያም ደግሞ ስታንዳርዱ ከፍ ስላለም ብቻ አይደለም። የመምህራን ተነሳሽነት ወሳኝ ሚና አለው። አንድ መምህር ከራሱ ጥቅም በላይ የተማሪዎች ውጤትና ስኬት ሊያሳስበው ይገባል። መምህርነት ትጋትን የሚጠይቅ ሙያ ነው።

በእርግጥ ተነሳሽነቱ የጎደላቸው መምህራን የሉም ማለት አይቻልም፤ አሉ። ያንን ተነሳሽነት በግንዛቤ ማስጨበጫ፣ በወርክሾፖች እና በተለያዩ ንቅናቄዎች ማሳደግ ያስፈልጋል። ከዚህ ጎን ለጎን የመምህራንን አቅም ግንባታ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራው ቀጣይ ተግባራችን ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው በየትምህርት ቤቱ የወላጅ ተማሪ ኅብረት አለ፤ ይህ ኮሚቴ የትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የራሱ የሆነ ድርሻ አለው ተብሎ ይታመናል፤ በዚህ ላይ ምን አይነት ውጤት ማምጣት ተችሏል? በቀጣይስ ምን ታስቧል?

ዶክተር ዘላለም፡- በነገራችን ላይ ይህ የወላጅ ተማሪ ኅብረት በጣም ትልቅ ተቋማዊ አደረጃጀት ያለው ነው። በክፍለ ከተማ ደረጃ ሥራ አስፈጻሚ የተካተተበት ነው፤ በወረዳ ሆነ በትምህርት ቤት ደረጃም አለ። ከዚህ ተቋማዊ አደረጃጀት ጋር ጎን ለጎን ሆነን እንሠራለን። በተለይ የ‹‹ትምህርት ለትውልድ›› ንቅናቄ ትልቁን ሥራ የሚሠሩ እነርሱ ናቸው። ከዚህ የተነሳ አቅም አድርገን እየሄድን ያለነው እነርሱን ነው።

በተለይም የተማሪ ሥነ ምግባር ላይ፣ ግብዓት ማሟላት ላይ፣ መማር ማስተማር ላይ፣ ትምህርት ቤቱንና አካባቢውን ምቹና ሳቢ ማድረግ ላይ፣ ሰላምና ፀጥታውን መጠበቅ ላይ፣ ደህንነትን መጠበቅ ላይ፣ የመማር ማስተማሩን ሂደት ከሚያውኩ ተግባራት ነፃ ማድረግ ላይ እየሠሩ ያሉት እነርሱ ናቸው።

እኛ ጠንካራ የሆነ ድጋፍ እንሰጣቸዋለን። እነርሱም አብረውን እየሰሩ በመሆናቸው ትልቅ አቅም ሆነውናል። በአሁኑ ወቅት የበለጠ አቅም እየፈጠርንላቸው ነው። አንዳንዶች የግል ፍላጎት ያላቸው ይመስላል፤ እነርሱን እያስተካከልን ነው። በቀጣይ ይህንኑ ሥራ አጠናክረን እንሄዳለን።

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረገው የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሳደግ ንቅናቄ ከመጀመሩ ቢሮው አስቀድሞ ትምህርት ቤቶች ያሉበት ደረጃ ለይቶ የጎደለውን ነቅሶ አውጥቷል፤ ከዚህ አኳያ የጎደለውን እንሞላለን ብለው የተንቀሳቀሱ ባለሀብቶች ይኖሩ ይሆን?

ዶክተር ዘላለም፡- በርካታ ባለሀብቶች አሉ። ከዚህም አኳያ ወደ በርካታ ትምህርት ቤቶች እየመጡ እየጠየቁም ጭምር ነው። ወጥነት ባለው መልኩ አልሆነም እንጂ ብዙ ትምህርት ቤቶች ላይ ባለሀብቶች እየገቡ የመጫወቻ ሜዳ፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ እና መሰል ነገሮችን ለመሥራት እየተረከቡ ነው። እሱ ግን በቂ ነው ብለን አናስብም።

ስንት አመራር ምን ያህል ባለሀብትን አመጣ የሚለውም የሚታይ ይሆናል። ይህን በተመለከተ ሱፐርቪዥኑ ረቡዕና ሐሙስ ያደረገውን አሰሳ ዓርብ ዕለት ሪፖርት አቅርቦልናል። የተገኘውን ሪፖርትም በቀጣይ ይፋ የምናደርገው ይሆናል። ይህ የባለሀብቱ ተሳትፎ ትልቅ አቅም የሚፈጥርልን ነውና በዚህ ላይ አተኩረን እንሰራለን።

በመጨረሻም ይህን ተከትሎ የማቀርበው ጥሪ አለ፤ ይኸውም ሀገር የጋራ ነች። ሀገር የምትኖረው ትውልድ ሲቀጥል ነው። ትውልድን ደግሞ በሚፈለገው መልኩ የሚቀርጸው ትምህርት ቤት ነው። የትምህርት ቤት ደረጃን በማሳደጉ ንቅናቄ ላይ ልጅ ስላለንና ስለምናስተምርበት ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ስንል የምናደርገው ተግባር እንደሆነ ሁሉም የሚመለከተው መሆኑን እንዲረዳ እሻለሁ።

ባለሀብቱ በሀብቱ፣ እውቀት ያለው በእውቀቱ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ በአጠቃላይ መርዳት የሚችል አካል ወደ የትምህርት ቤቶቻችን እየመጡ እንዲያግዙን አደራ ማለት እወዳለሁ።

አዲስ ዘመን፡- በ2016 የትምህርት ዘመን በዋናነት ትኩረት የምታደርጉበት ሥራ ምንድን ነው?

ዶክተር ዘላለም፡- በዋናነት የምንሠራው ሥራ ቢኖር ይህ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻልን ነው። ይህን ያህል ትምህርት ቤቶች ደረጃ አራት ሆነውልናል ብለን ልንቆጥር ይገባናል። በአሁኑ ሰዓት ደረጃ አራት ትምህርት ቤት ይህኛው ትምህርት ቤት ነው ብለን የምናሳየው የለንም። ያልመዘናቸው፤ ነገር ግን ደረጃ አራት ይገባሉ ብለን የምናስባቸው ትምህርት ቤቶች ግን አሉ። ከዚህ በኋላ ናፍቆታችን በልበ ሙሉነት ደረጃ አራት ትምህርት ቤት አለን ለማለት ነው። ዋና ትኩረታችን ይኸው ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለትብብርዎ ከልብ አመሰግናለሁ።

ዶክተር ዘላለም፡- እኔም አመሰግናለሁ።

 አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 24/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *