ሀገር የሚሰሩ የሥርዓት አቅጣጫዎች

ሀገር ማለት ሰው ነው የሚል የልጅነት እውቀት አለን። በዚህ እውነት ላይ ተረማምደን ከትላንት ዛሬ ደርሰናል። ወደ ነገ መሄጃችንም በዚህ ሀገርና ሰውን ባስተሳሰረ ሥርዓት በኩል ነው። ሀገር ብለን ሰው ስንል ሀገርና ሰውን ባስተሳሰረ ሥርዓት ላይ ቆመን ነው። ፖለቲካው ልክ እንዲሆን ልክ የሆነ ሥርዓት ያስፈልገናል። መማር ማስተማሩ ግቡን እንዲመታ ውጤት ተኮር የሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ ነው።

ሥርዓት መተዳደሪያ ነው። አማኞች በቅዱስ ቃሉ እንደሚመሩ ሁሉ ሀገርም የራሷ መተዳደሪያ ደንብ አላት። በዛ ሥርዓት በኩል ነው እንደ ሀገር ፍሬ ማፍራት የምንችለው። አሁን ላሉብን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ሀገር የሚሰሩ የሥርዓት አቅጣጫዎች ያስፈልጉናል። በመማር ማስተማሩ ረገድ እንደ ክፍተት የሚነሳው እና ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ያለው ውጤት ተኮር ጥብቅ ሥርዓት ስላልገነባን ነው።

ሀገር ከድህነት አዘቅት እንድትወጣ እውቀትን መሠረት ያደረገ የመማር ማስተማር ሥርዓት እንደሚያስፈልግ የማይካድ ነው። የዓለም ወያባ መልኮች የደመቁት እውቀት በሚሉት የመፍትሔ መር እሳቤ ነው። በዚህ ረገድ አሁን አሁን ሀገራችን በበጎ የሚነሳ ስም የላትም። ያለፉት በርካታ አመታት በትምህርቱ ረገድ የከሰርንበት ነበር ብሎ መናገር ይቻላል።

ይሄን ያደረገው ደግሞ ከጥራት ይልቅ ብዛት ላይ ያተኮረው የትምህርት ሥርዓታችን ነው። ትውልዱ ከመኮራረጅ ርቆ ራሱን በቻለ መንገድ ተፈትኖ የሚያልፍበት ጥብቅ ሥርዓት አልነበረንም። በኩረጃ እና ያለፉበትን ውጤት ገንዘብ ከፍሎ በመቀበል በሀሰት እና ባልተገባ መንገድ ላይ በቀላሉ የማይታሰብ መንገድ ተጉዘናል።

መንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ገንብቶ ከመስጠት እና የዩኒቨርሲቲ ቁጥር ላይ ከማተኮር ባለፈ በትምህርት ጥራት ላይ የሰራው ሥራ እምብዛም የሚነገር አልነበረም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በየአመቱ ይሄን ያህል ተማሪዎችን አስመረቅን ከማለት ባለፈ ጥራት ተኮር የመማር ማስተማር አቅጣጫን ሲከተሉ እምብዛም አልተስተዋለም።

ይህ ችግር ዛሬ ላይ በትምህርቱ ረገድ በራሱ የማይተማመን፣ ከመፍትሔ ይልቅ ችግር ላይ፣ ከለውጥ ይልቅ ለነውጥ የበረታ አእምሮና ልብ አስታቅፎን ቁጭ ብሏል። በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ ሕይወታችን ጽንፈኛ በሆኑ የዘርና የብሔር እሳቤዎች እንድንሸነፍ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።

የእውቀት መጀመሪያ ግብረገብነት ነው። በግብረገብነት ያልተቃኘ መምህር፣ ያልተቃኘ ተማሪ በእውቀቱ ሀገር መፍጠር አይቻለውም። ሥርዓት ደግሞ ለእንደነዚህ አይነቶች ማህበራዊ ተቃርኖዎች መልስ የሚሰጥ የመፍትሔ አካል ነው። ግብረገብነት መነሻው ሥርዓት ነው። ግብረገብነትን ያላካተተ ሥርዓት ምንም ቢበረታ ሄዶ ሄዶ መቆሙ አይቀርም።

ሀገራችን የሚያስፈልጋት ግብረገብነት ያለበት እውቀት ነው። ሥርዓቶቻችን ጨዋነታችንን ሲቀሙን አይተናል። መርሆቻችን ከትላንት ወደዛሬ የመጡ ማህበራዊ እሴቶቻችንን ሲያደበዝዙብን ተመልክተናል። የትምህርት ጥራት በምንም ሳይሆን በብላሽ የመማር ማስተማር ሥርዓት የመጣ ነው። ተማሪዎቻችን ጠንካራ እና ተጠያቂነት ባለበት ሥርዓት ውስጥ ፊደል ቢቆጥሩ ኩረጃና የትምህርት ጥራት ጉዳይ በዚህ ልክ ባላሰጋን ነበር።

ግብረገብነት የሰውን ልጅ የራስ ወዳድነት ባህሪ መግራት፤ ለጥፋት የተከፈቱ በሮችን መዝጋት የሚያስችል አቅም መገንቢያ ነው። በሰብዓዊ እሴቶች ላይ ቆሞ ተነጋግሮ ለመግባባት እና ተግባብቶ አብሮ ለመኖር ቅድሚያ የሚሰጥ የተግባቦት መንፈስ ነው። እውቀትን ከሥነ ምግባር ጋር የሚያስተምሩ የትምህርት ተቋማት በትምህርቱ ዙሪያ እየተነሱ ላሉ ሀገራዊ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ ናቸው።

እውቀት ከሥነ ምግባር ጋር ሲሆን ነው ሀገር የሚቀይረው። አብዛኞቹ የሀገራችን የትምህርት ተቋማት እንዲህ ካለው ነባራዊ እውነታ ያፈነገጡ ናቸው። የዩኒቨርሲቲዎቻችን መብዛት መፍትሔ ተኮር እውቀት ካልሰጡን ዋጋቸው ምንድነው? በየአመቱ የሚመረቀው የተማሪ ቁጥር ሥራ ፈጥሮ ራሱንም ሀገሩንም ከተረጂነት ማውጣት ካልቻለ መማር ትርጉሙ ምንድነው? እኚህ እና መሰል ጥያቄዎች ሄደው ሄደው የሚቆሙት የትምህርት ሥርዓቱ ላይ ነው።

የእውቀት ማዕከል የተባሉት ዩኒቨርሲቲዎቻችንም ሆኑ የሚያስመርቁት ተማሪዎቻቸው የሥርዓት ውጤቶች ናቸው። ሥርዓቱ ካልተስተካከለ የሚስተካከል ተቋምም ሆነ ተማሪ እንደሌለ ያየነው እና የምናየው እውነታ ማስረጃ ነው። እንደ ሀገር የትምህርት ሥርዓቱን ለመቀየር እና ለማሻሻል እያደረግነው ያለነው ጥረት ይበል የሚያሰኝ፤ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው ።

ለውጥ የማህበረሰብን ዝግጁነት የሚጠይቅ ነው። ከነበረበት እና ከለመደው እሳቤ መውጣትን የሚፈልግ ነው። አምና ጀምሮ ሲሰጥ በነበረው የከፍተኛ ተቋም የመግቢያ ፈተና ላይ ብዙ ጉርምርምታዎች ነበሩ። እኚህ ጉርምርምታዎች የረጅም ጊዜ ሥርዓት የፈጠራቸው ናቸው። ተማሪዎች ከኩረጃ ነጻ በሆነ አካባቢ በመንግስት ተቋማት ውስጥ መፈተናቸው የትምህርት ጥራትን በማምጣት ለሀገር የሚበቁ ዜጎች ለማፍራት የተሻለ እድል መፍጠር የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል። ሆኖም ግን የለመድነው የመኮራረጅ ሥርዓት አዲሱን የለውጥ አቅጣጫ እንዳንቀበል ይሞግተናል።

በተለያየ ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴር በሚሰጣቸው መግለጫዎች ላይ ብዙ አሳፋሪ ነገሮች ይሰማሉ። ለትምህርት ጥራት መጓደል ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም አንዱና ዋነኛው ግን የኩረጃ ልምምድ ነው። ይሄን ለማስተካከል በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ተማሪዎች በመንግስት ተቋም ገብተው እንዲፈተኑ የሚል አቅጣጫ ተቀምጦ ከአለፈው አመት ጀምሮ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል።

ዘንድሮ የጀመረው የመውጫ ፈተና የዚህ አንዱ አካል ነው። በፈተናው የተመዘገበው ውጤት ችግሩ ምን ያህል የገነገነ ስለመሆኑ አመላክቷል። በዘርፉ ትልቅ የቤት ሥራዎች እንዳለብንም ጠቁሟል። በተለይም የግል ከፍተኛ ተቋማት በኩል የተመዘገበው ውጤት ችግሩን በትኩረት ለማጤን አስገዳጅ ነው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በመንግስት ተቋማት በኩል ለፈተናው ከተቀመጡ 77981 ተማሪዎች ውስጥ 50 እና ከዛ በላይ በማምጣት የመውጫ ፈተናውን ያለፉት 48632 ወይም 62.37 ከመቶ ናቸው። ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመውጫ ፈተና የተቀመጡት 72203 ተማሪዎች ሲሆኑ 50 እና ከዛ በላይ ያመጡት 12422 ወይም 17.2 በመቶ የሚሆኑት ናቸው።

የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ የዶክተር ሳሙኤል ክፍሌን በጉዳዩ ዙሪያ ‹የመውጫ ፈተናን ከወሰዱ አጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ 59.3 በመቶው ለመውደቃቸው አንድ ብቸኛ ምክንያት እንደሌለ ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረ ገጽ መናገራቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ተማሪዎች የወደቁበትን ምክንያት ለማወቅ ዝርዝር የውጤት ትንተና በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እንደሚሰራ የገለጹ ሲሆን በግል እና በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የታየው የማለፍ ምጣኔ ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑ ቀድሞም የነበረውን መላምት እውን ያደረገ ነው› ብለዋል።

በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው አፈጻጸም ትኩረት ይፈልጋል የሚለው የሚኒስቴር ዴኤታው ንግግር አጽንኦት የሚሰጠው እና ብዙዎቻችን የምንጋራው እውነት ነው። በዛው ልክ በጥሩ ውጤት ተማሪዎቻቸውን ያሳለፉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መኖራቸውን የጠቀሱት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ ችግሩ ሁሉንም የግል ከፍተኛ ተቋማት የሚመለከት አለመሆኑንም አስታውቀዋል።

የትምህርት ጥራትን በተመለከተ ብቻውን ተነጥሎ ጣት የሚቀሰርበት የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋም የለም። ሁሉም ተቋማት በተማሪዎቻቸው የመግቢያም ሆነ የመውጫ ፈተናዎች ላይ ዐሻራ አላቸው። ባለፈውም ሆነ አሁን ባለው የትምህርት ሥርዓት ላይ ሁላችንም ባለድርሻ ነን። ለመፍትሄውም ስንቆም በጋራ ነው። አንድ ሀሳብ ሀገራችንን አይቀይራትም። አንድ ሀሳብ የሀገራችንን የትምህርት ሥርዓት አያስተካክለውም።

መሠረታችን እውቀት ይሁን። መሠረታችንን በእውቀት ላይ ስንገነባ ነው የኩረጃ እሳቤን የምንገዳደረው። መሠረቱን እውቀት ያደረገ ትውልድ ኩረጃን እንደ ነውር ነው የሚያየው። መሠረቱን እውቀት ያደረገ ትውልድ በግብረገብ ተመርቶ መፍትሔ ተኮር ልምምዶችን ጨብጦ የራሱን ዐሻራ እንዲያሳርፍ የማንንም ምክር አይሻም።

ይሄ እንዲሆን ያለፍንባቸው የመማር ማስተማር ሥርዓቶች እውቀት መር በሆነ ሥርዓት መተካት አለባቸው። በቅርብ እንደተጀመረው የመግቢያ እና የመውጫ ፈተና አይነት ተማሪውን የሚያጸና የትግበራዊ እንቅስቃሴን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። ለችግሮቻችን የመፍትሔ አካል ሆነን ከፊት የምንቆመው በእውቀት ብቻ ነው።

የኩረጃ ልምምድ ወንዝ አያሻግርም። ትንሽ ወስዶ መንገድ የሚያስቀር ነው። ትልቁ ፈተና ደግሞ መንገድ ከቀረን በኋላ ለመንቀሳቀስ መቸገራችን ነው። ይሄ ሁሉ ከመሆኑ በፊት በራሳችን እውቀት ራሳችንን ችለን ወደፊት የምንገሰግስበትን የእውቀት በትር መጨበጥ ይኖርብናል።

ዲግሪ በብር የሚሸጥ ተቋም፣ ዲግሪ በብር የሚገዛ ተማሪ ባለባት ሀገር ላይ ድህነትንና ኋላቀርነትን ታግሎ ለመጣል የምናደርገው ትግል ስኬታማ ሊሆን አይችልም። ድህነትን ታግለን የምንጥለው በእውቀት ብቻ ነው። ከእውቀት ከጎደልን በምንም ብንሞላ ጥቅም አይኖረንም። ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ መልዕክቱ ላይ ‹ነፍስ እውቀት የሌላት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም› ይለናል። ልብ በሉ ነፍስ ገንዘብ ከሌላት፣ ጉልበት ከሌላት አላለም። እውቀት ከሌላት ነው ያለው።

እውቀት መር እሳቤ አንድ ቦታ የሚቆም አይደለም። በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ ሕይወታችን ሳይቀር ከፊት ተሰልፎ የሚገኝ ነው። የጦርነት እሳቤዎች የእውቀት መጉደል እሳቤዎች ናቸው። ድህነት መነሻው አላዋቂነት ነው። ተነጋግረን እንድንግባባ፣ ተምረን ሀገር ለመቀየር ከምንም በፊት እውቀት ያስፈልገናል። ይሄ እንዲሆን ደግሞ እውቀት የሚሰጥ ጠንካራ ሥርዓት መገንባት ይጠበቅብናል።

ኩረጃን ተለማምደን መገለጫችን እንዳደረግነው ሁሉ በጠንካራ ሥርዓት የትምህርት ጥራትንም ተለማምደን ማንነታችን ልናደርገው እንችላለን። ጠንካራ የትምህርት ሥርዓት የሌላትም ሀገር የሚታይ ተስፋ የላትም። እውቀት መር የሆነ የመማር ማስተማር ሥርዓት ሳንገነባ ይሄን ያህል ዩኒቨርሲቲ ገነባን፣ በአመት ይሄን ያህል ተማሪ አስመረቅን እያልን ለጋዜጠኛ ማብራሪያ ብንሰጥ ለሀገራችን የሚፈይድላት የለም። ዋጋችን ያለው በብዛት ውስጥ ሳይሆን በጥራት ውስጥ ነው። በጥቂት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ጥራት ያላቸው ችግር ፈቺ የመፍትሔ አካል የሆኑ ተማሪዎችን ማፍራት ይኖርብናል።

የመግቢያውም ሆነ የመውጫው ፈተና ለመንግሥት የቤት ሥራን ሰጥቶ ያለፈ ነው። በተለይ በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የታየው የውጤት ማሽቆልቆል ትምህርት ሚኒስቴር ወገቡን ታጥቆ እንዲሰራባቸው ጥቁምታ የሰጡ ናቸው። የትምህርት ጥራት በጠንካራ በሥርዓት ለውጥ የሚቀጣጠል ነው። ከዚህ ረገድ እምነት ከተጣለባቸው አቅጣጫዎች አንዱ የተማሪዎች የመፈተኛ ቦታና የአፈታተን መንገድ አንዱ ነው።

በችግሮቻችን ላይ ቁርጠኛ ካልሆንን ችግር ቤቱን ሰርቶ ለማኝና ተረጂ ነው የሚያደርገን። ሀገር የለውጥን ካባ እንድታጠልቅ የአላዋቂነት ሽርጦች መፈታት አለባቸው። አጓጉል ሥርዓቶች ቦታ ሊለቁ፤ ትውልዱ በእውቀት ሊገነባ ያስፈልጋል። በእውቀት ብቻ፣ በሥርዓት ብቻ የሚመሩ የልህቀት ማዕከላት ያስፈልጉናል።

እዚህ ውስጥ ስንዘራ ነው ዋርካ ሆነን የምንበቅለው። ዋርካ መሆን አንድም ለጥላ.. አንድም ለፍሬ ነው። ሀገራችን ጥላ አይደል ያጣችው? ሰላሳና ስልሳ መቶም የሚያፈሩ ባለእውቀት ልቦች አይደል ያጣችው? የትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓት ለውጥ ሀገርን ካንቀላፋችበት የሚያነቃ ነውና ይበል ሊባል ይገባል።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 24/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *