ሥራ አጥነትን የመቀነሱ ተግባር የሁሉም ወገን ኃላፊነት ነው!

ወጣትነት ለሥራ፣ ለትግል፣ ለለውጥ፣ ለአዲስ ነገር ተነሳሽነት ጎልቶ የሚታይበት ዕድሜ እንደመሆኑ፣ የአንዲት ሀገር ዕድገትም ሆነ ውድቀት በየዘመኑ ባለው ወጣት ትውልድ እንቅስቃሴ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡

ሥራ ፍለጋ ከገጠር ወደ ትናንሽ ከተሞች የሚፈልሱ እንዲሁም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችን ማስተናገድ የሚችል የሥራ ዕድል ባለመፈጠሩ፣ ከተሞች የሥራ አጥ ወጣቶች መናኸሪያዎች ሆነዋል። የሀገሪቱን ከተሞች ያጨናነቁ፣ ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቁጥር ማየት በዚህ ዙሪያ ሌት ተቀን መሥራት እንደሚያስፈልግ ያሳያል፡፡

በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የቅርብ ጊዜ መረጃ መሠረት፤ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ዜጎች ቁጥር 71 ከመቶ ነው። ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ቁጥር ደግሞ 25 ሚሊዮን የሚጠጋ ነው። በኦፊሴላዊ ግምት ብቻ በ16.5 በመቶ የሚያድግ የሥራ አጥነት እንዳለም ይነገራል። ምንም እንኳን ኢኮኖሚው በዕድገት ጎዳና ላይ ቢሆንም፣ በየዓመቱ በእጅጉ እየጨመረ ለሚመጣው ለዚህ አምራች ኃይል አቻ የሚሆን በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ላይ ግን አሁንም ብዙ መሥራትን ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የወጣቱን ጥም ማርካት እንዳልቻለ ይተቻል። በየዓመቱም ሦስት ሚሊዮን አዲስ ሥራ ፈላጊዎች ገበያውን ይቀላቀላሉ፡፡ ከአርባ በላይ ከሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችም በየአመቱ ከ150 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይመረቃሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሀገሪቷ ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እንዳለባት የሚያሳዩ ናቸው፡፡

ለዚህም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ነው፡፡ መንግሥት የወጣቶችን ሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የራሱን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ግልፅ ነው። የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችም አሉ፡፡ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮችም ባላቸው አቅም በተመሳሳይ ሁኔታ በጀት በመመደብ ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረጉ ነው፡፡

ይህ ጥረት ግን ካለው የሥራ አጥ ቁጥር አኳያ በቂ አይደለም። ይህን ችግር ለመቅረፍም ዘርፈ ብዙና መጠነ ሰፊ የሆኑ አማራጮችን መዘርጋትና መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ይህ ደግሞ የሁሉም ወገን ኃላፊነት ነው።

መንግሥት ችግሩን ለማቃለል የሚያደርገውን ጥረት ወጣቶች በተለይም ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ምሩቃን ከመንግሥት ሥራ ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር ሊደገፉ ይገባል። ሥራ ፈጠራ በትምህርት ብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም። በቀለም ትምህርት ጎበዝ መሆን ብቻውን የራስ ሥራ ለመጀመር አይበቃም። ጥንካሬና ራዕይ፣ በራስ መተማመንና ለፈተናዎች ሁሉ ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል። ሥራ መፍጠር ለየት ያለ አተያይ ይፈልጋል። የማኅበረሰቡን ችግር ለየት ባለ መረዳት ማየት ያስፈልጋል።

የሥራ ፈጠራና ክህሎት ሚኒስቴርም ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉ ወጣቶችን በተለየ መልኩ የሚደግፍበትን አሰራር የበለጠ አስፍቶና አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ዘርፉ ኢንዱስትሪውን የመግራት እና የመምራት ድርብ ኃላፊነት እንዳለበት አውቆም በጥብቅ ዲሲፕሊን ሊመራ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የሥራ ፈጠራና ክህሎት ሚኒስቴር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያከናወናቸው ተግባራት ከአዲሱ ተልዕኮው አኳያ መሰረት የተጣለባቸው እንደሆኑ ይታመናል፡፡ እነዚህ መሰረቶች ተልዕኮዎቹን መሸከም መቻላቸውን ማረጋገጥና ጥልቀት እንዲኖራቸው መረባረብ ይገባል፡፡

በዚህም ዕቅዱ በክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንዱስትሪ ሰላም ላይ ያሉ ውዝፍ ሥራዎችን የሚያካክስ፣ የሚፈጠረውን አዳዲስ ፍላጎት የሚያስተናግድ እንዲሁም በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት አዎንታዊ ሚና መጫወት የሚያስችል አድርጎ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት፣ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት በዘርፉ አስቻይ ተቋማት በመሆናቸው አቅም ገንቢ ሆነው መውጣት ይገባቸዋል፡፡

ተጠሪ ተቋማቱ ሌላውን ለመሸከም ራሳቸውን በሁለት እግራቸው ማቆም፣ የጎንዮሽ ትስስርና ቅንጅታቸውን ማጠናከር እንዲሁም አምስቱ ሀገራዊ የትኩረት ዘርፎች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጀመረውን አበረታች የሥራ ፈጠራ መንገድ አጠናክሮ ከቀጠለ፣ ወጣቱም ከሥራ ጠባቂነት ይልቅ በይበልጥ የራሱን ሥራ ለመፍጠር ከጣረ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍ እንኳን ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ በዚህ ላይ የባለሀብቱ ሚናም ትልቅ ዋጋ ያለው እንደመሆኑ ሁሉም ወገን ኃላፊነት እንዳለበት አውቆ ሊሰራ ይገባል!

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 24/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *