ነገረ-”የክብር ዶክትሬት ፤”

የዩኒቨርሲቲዎቻችን የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ራዕያችንና ሕልማችንን የሚገልጽ፤ ጎሳንና ሃይማኖትን የተሻገሩ፤ ከቀዬና አካባቢያዊነት አጥር የዘለሉ። ከሰውነት ባሻገር ዓለማቀፋዊነትን ያነገቡ ሊሆን ይገባል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተዘወተረ የመጣው የዩኒቨርሲቲዎቻችን የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ግን እንደ ሮማውያኑ ጣኦት ጄነስ/Janus/ባለ ሁለት ተቃራኒ ፊት ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወይም አአዩ የሚሸልማቸው በብዛት ክርክርንና ውዝግብን የሚጋብዙ ቢሆንም የሀገር ባለውለታዎችንና የትውልድ አርዓያዎችን መርጦ ሲሸልም። አንዳንዴም ዓለማቀፋዊና አህጉራዊ መሆን ሲዳዳው ይታያል ።

የባህር ዳር፣ የጎንደር፣ የጅማ፣ የሐረማያ፣ የሀዋሳና የመጀመሪያ ትውልድ የሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ የሀገር ባለውለታዎችንና የትውልድ ምሳሌዎችን ከአካባቢያዊነት ጋር ሲያጣቅሱ ይስተዋላል። ሀገራዊ ጀግኖቻችን ሲሻሙና ሲናጠቁ ያጋጥማል። የተቀሩት ደግሞ ጎሳንና ወንዜ’ያዊነትን ሲያስቀድሙ ትዝብት ላይ ወድቀዋል። በአጠቃላይ የክብር ዶክትሬት ሽልማቱ የጋራ ሀገራዊ ጀግና፣ ምልክት፣ ለሀገራዊ መግባባትና ለብሔራዊ እርቅ መዋል ሲገባው ዝብርቅርቅ ያለና ወጥነት የጎደለው ነው። አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ወቅታዊና ሀገራዊ የፖለቲካ ነጸብራቁን ተከትለው ከፍ ሲልም ለፖለቲካዊ ብሽሽቅ የሚጠቀሙበት በሚመስል አግባብ የክብር ዶክትሬት ይሸልማሉ። ለዚህ ነው የአንዱ ዩኒቨርሲቲ ተሸላሚ ለሌላው የውዝግብ መነሻ የሚሆነው ።

ይሄን ሥነ ሥርዓት በአግባቡ ብንጠቀምበት ትውልድን ለማነጽና ለማቀራረብ፣ የጋራ ጀግና፣ ምልክት፣ ሕልምና ራዕይ ለማንበር በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ሀገራዊ መቀባበልና ዕርቅን ለማውረድ ወረት ይሆን ነበር። አሁን እየታዘብን ያለው አንዳንድ ሽልማት ግን ከብሔራዊ መግባባትና የጋራ ምልክት ከማቆም ይልቅ ለትችትና ለንትርክ የሚጋብዝ ነው ። አንዳንዶቹ ሽልማቶች በቲፎዞ ግፊትና እገሌ ይሸለም በሚሉ ወትዋቾችና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጫና የተሰጡ መሆኑ ይነገራል ። አንዳንድ ግለሰቦች ደግሞ የክብር ዶክትሬት ካላሸለማችሁኝ እያሉ ደጅ እስከመጥናት ደርሰዋል። ለዚህ ነው የዩኒቨርሲቲዎቻችን የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ አካዳሚያዊ ነፃነታቸውን ባከበረ ሁኔታ ሥርዓትና መዋቅር ተበጅቶለት ወጥ አሠራር ሊኖረው ይገባል የሚባለው። ዓለማቀፉ አሠራሩም ከዚህ የተለየ አይደለም ።

መቼም በዓለማችን ገናና ስም ካላቸውና ዝናን ካተረፉ ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ሀርቫርድና የል እንደ የዩናይትድ ኪንግደሙ ኦክስፎርድ የተወደሰ የለም ። በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለዓለማችን ብሎም ለሰው ዘር በመላ አርዓያነት ያለው “ልዩ ተግባር” እደግመዋለሁ “ልዩ ተግባር” ያበረከቱ ያለ ቆዳ ቀለም፣ ያለ ርዕዮተ ዓለም፣ ያለ መደብና ሃይማኖት ልዩነት የክብር ዶክትሬት ይሰጣሉ። ሁሉም ዕጩዎችን የሚመርጡበት የየራሳቸው አሠራር አላቸው ።

የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት መስጠት የጀመረው ከ17ኛው መክዘ አንስቶ ሲሆን ተሸላሚውን መርጦ የሚያቀርበው የዩኒቨርሲቲው የበላይ አካል ወይም የሀርቫርድ ኮርፖሬሽን እንደሆነ ድርሳናት ያትታሉ። የሀገር መሪዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ጸሐፊዎች፣ ከያኒያን፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ከሀርቫርድ የክብር ዶክትሬት ተሸላሚዎች ዋናዎቹ ናቸው ። የአሜሪካው የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን ፣ የጥቁሮች መብት ተሟጋች ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ፣ የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ታጋይና የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ፣ ፓኪስታናዊት የሴቶች የመማር መብት ወትዋች ማላላ የሱፍ እና የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከር በርግ ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ከተሸለሙ ታላላቅ ሰዎች ይገኙበታል ።

ኦክስፎርድ ራሱን የቻለው የክብር ዲግሪ ኮሚቴ በበርካታ ሒደቶች ማለትም የዕጩዎች መረጣን፣ ታሳቢነትን፣ በዕጩዎች ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት ውይይትን፣ የማጽደቅ ሒደትን አልፎ በመጨረሻ ኮሚቴው ተሸላሚውን መርጦ ሲያቀርብለት የዩኒቨርሲቲው ምክትል መራሄ ወይም ኃላፊ ሽልማቱን ያበረክታል። በሀገራችን ያለውን አሠራር አንጋፋውን የአአዩ በአብነት ወስደን የምንመለከተው ቢሆንም፤ አሰጣጡን በተመለከተ የሚሰነዘሩ ትችቶችን በቅድሚያ እንመልከት ።

በሀገራችን ያሉ ዩኒቨርስቲዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ ለሁለትና ሦስት ሰዎች የክብር ዶክትሬት መስጠትን እንደ ልማድ መያዛቸው ከክብር ዶክትሬት መሠረታዊ ዓላማዎች ጋር የሚፃረርና ክብሩን የሚያራክስ ነው ሲሉ የዩኒቨርሲቲ ምሑራን ለ”አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ገልጸዋል። የክብር ዶክትሬት የሚሰጥባቸው መስፈርቶች በመርፌ ቀዳዳ ግመል እንደ ማሾለክ ያህል ናቸው ያሉት ምሑራኑ፤ በአሁን ወቅት አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር ፉክክር በሚመስል መልኩ ዶክትሬቱን የሚሰጡበት አካሄድ በአስቸኳይ ሊታረም እንደሚገባው፤ በተለይ የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ምሑሩ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፤ ከሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ለተለያዩ ግለሰቦች የክብር ዶክትሬት የሚሰጥበት ሁኔታ፤ ከማዕረጉ መሠረታዊ ዓላማ ጋር የተቃረነ መሆኑን ዓለማቀፍ ልምዶችን በማጣቀስ አስረድተዋል ።

በአሁን ወቅት በትምህርት በቅተዋል ተብለው ዶክትሬት ዲግሪ የሚሰጣቸው ምሑራን ምን ያህል ችግር ፈቺ ምርምር ሠርተዋል የሚለው ራሱ ጥያቄ ውስጥ እንደገባ የጠቆሙት ዶ/ር በድሉ፤ የክብር ዶክትሬት የሚሰጠው አንድ ግለሰብ ተምረው ዶክተር ከሆኑት ባልተናነሰ ሁኔታ ማኅበረሰባዊ አስተዋፅዖ ሲያበረክትና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሲሆን ብቻ ነው። “ማዕረጉ በመደበኛ ትምህርት ከሚገኘው ዶክትሬት ይበልጣል” ያሉት ምሑሩ፤ በዋናነት ከራሱ ማኅበረሰብ ባለፈ ለዓለም ኅብረተሰብ ያበረከተው አስተዋፅዖና በዓለማቀፍ ደረጃ ያለው ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከግምት ገብቶ ነው የክብር ዶክትሬቱ የሚሰጠው ። “ማንም ሰው ከተማረ ዶክትሬቱን ያገኘዋል፤ ማንም ሰው ግን “የክብር ዶክትሬትን” ሊያገኝ አይችልም ያሉት ዶ/ር በድሉ ፤ በኛ ሀገር ግን ክብሩን እንዲያጣ ተደርጎ እየተቀለደበት ነው ይላሉ።

የክብር ዶክትሬት የሚሰጥባቸውን ዋነኛ መስፈርቶች የጠቆሙት ዶ/ሩ፤ ግለሰቡ ከትውልድ ሀገሩ አልፎ እንደ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ አበበ ቢቂላ እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት ምሥረታና ከሊግ ኦፍ ኔሽን ምስረታ ጋር ተያይዞ ስማቸው የሚነሳው አፄ ኃይለ ሥላሴ አይነት ዓለማቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሲሆኑና ለዓለም ያበረከቱት አስተዋፅዖ ለሌላው አርዓያ ይሆናል ሲባል ብቻ የሚበረከት መሆኑን አስረድተዋል። በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው አካሄድ ግን ወደ አካባቢ ተወላጅነትና ጎሳ እየወረደ መምጣቱን በመጥቀስ፤ ምን አስተዋፅዖ እንዳበረከቱ በጉልህ ያልተገመገሙ ግለሰቦች ጭምር እየተሰጣቸው መሆኑ የክብር ዶክትሬቱን ከዓላማና መርሕ ውጪ አድርጎታል ብለዋል። አብዛኞቹ የክብር ዶክትሬቱ የተሰጣቸው ግለሰቦች ይገባቸዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ ።

የዶ/ር በድሉን ሃሳብ የሚጋሩት የሕግ ምሑሩ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ በበኩላቸው፤ ጉዳዩ በእጅጉ አሳሳቢ ሆኗል ይላሉ። በሁለት መንገድ የክብር ዶክትሬት እንደሚሰጥ የጠቆሙት ፕ/ር ጥላሁን፤ በሥነ ጽሑፍና በኪነ ጥበብ ዓለማቀፍ ተፅዕኖ የፈጠሩና በሀገር አቀፍና በዓለማቀፍ ደረጃ በተሠማሩበት ሙያ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉ ሰዎች ናቸው ለማዕረጉ የሚመረጡት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሴኔት ፀሐፊ ሆነው ማገልገላቸውን የሚያስታውሱት ፕ/ር ጥላሁን፤ በደርግ ዘመን የክብር ዶክትሬት መሰጠት ቆሞ እንደነበርና ዳግም ካስጀመሩት አንዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በሥነ ጽሑፍ ለደራሲ ከበደ ሚካኤልና ኋላም ለደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ መሰጠቱን ያስታውሳሉ ።

የክብር ዶክትሬት የሚሰጠውን ግለሰብ ለመምረጥ ዩኒቨርሲቲዎች ብዙ እንደሚደክሙና ምናልባትም ለበርካት ዓመታት መስፈርቱን የሚያሟላ ግለሰብ ላይገኝ እንደሚችል የተናገሩት ፕ/ሩ፤ አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲዎች ጉዳዩን የፉክክርና የባለሥልጣናት እጅ መንሻ እያደረጉት ይመስላል ብለዋል። በአካባቢ ተወላጅነት መሆኑ ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል ያሉት ምሑሩ፤ ከሰሞኑ እየተሰጡ ያሉ የክብር ዶክትሬቶች ፖለቲካ ፖለቲካ የሚሸቱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከፖለቲካ ነፃ የሆነ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ መስፈርት ሊኖር ይገባል ብለዋል። በንጉሡ ዘመን እንደ ሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ሴዳል ሴንጎር ላሉት የነፃነት ታጋዮች የክብር ዶክትሬቱ መሰጠቱን ያስታወሱት ምሑሩ፤ በወቅቱ ክብሩ ተጠብቆ እንዲቆይ እንደ ብርቅ ነበር የሚታየው፤ የአሁኑ አካሄድ ግን ልጓም ያጣ ሆኗል። በአስቸኳይ ሊስተካከልና ሊታረም ይገባል ።

ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡት የፍልስፍና ምሑሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ ዩኒቨርሲቲ ማለት “ዩኒቨርሳል” ከሚለው ቃል እንደመሰየሙ ዓለማቀፍ ባሕሪ እንጂ አካባቢያዊ ባሕሪ እንደሌለው አውስተው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክብር ዶክትሬት ወደ ዘርና ጎሳ እየወረደ መምጣቱ ክብሩን አሳጥቶታል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲ ለግለሰቡ ሲሰጥ ዩኒቨርሲቲውንም የሚያስከብር ይሆናል ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎቻችን አካባቢያዊ በመሆናቸው ከዚሁ የአካባቢያዊ ስሜት በመነጨ ለየአካባቢያቸው ተወላጆች ለመስጠት መሽቀዳደማቸው አሳፋሪ ነው ብለዋል። ከክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ዓላማና መርሕ ጋርም ፈፅሞ የሚሄድም አለመሆኑን ተናግረዋል። የአአዩ አሠራር ከዚህ ትችት የራቀ ይሆን፤

የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሚሰጠውም አንድ ግለሰብ “እኔ የክብር ዶክትሬት ይገባኛል” ብሎ ሲያመለክት ወይም ሌላ አካል ጥቆማ ሲያቀርብ፤ የግለሰቡ አስተዋፅዖ ተገምግሞ መሆኑን የገለፀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ በተቋሙ ይገባቸዋል የሚባሉ ግለሰቦች ሊመለመሉና ማዕረጉ በሴኔት ውሳኔ ሊሰጣቸው ይችላል ።

የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ወጥ ባይሆንም የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ መመሪያ ይኖራቸዋል ተብሎ ቢታመንም የአንጋፋውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መመሪያን ለዚህ መጣጥፍ መርጨዋለሁ። በአንድ ወቅት ይሄን የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ውዝግብ አስመልክቶ በ”ቁምነገር” መጽሔት ጥያቄ የቀረበለት የአአዩ የሚከ ተለውን ምላሽ በጽሑፉ ሰጥቷል። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም ተሞክሮው ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ሊጠቅም ይችላል፤ ከዚህ ባሻገር ወጥ የሆነ አሠራር ለማስፈን በመነሻነት ያገለግል ይሆናል ብሎ ስላመነ እንደሚከተለው አቅርቦታል ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጡ የክብር ዶክትሬት ዲግሪዎች ለሀገራቸውና ለመላው ዓለም በእውቀታቸውና በሙያቸው የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ግለሰቦች እውቅና ለመስጠት የሚደረጉ ናቸው። የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ሲሰጥ ፦

1ኛ/ በተልዕኮዎቹ ውስጥ ለተካተቱ የእውቀትና ሙያዊ የሥራ ውጤቶች መርሆዎች መጠበቅ ያለውን ፅኑ አቋም ያረጋግጣል ፤

2ኛ/ ለእውቀትና ለኪነጥበብ እድገትና መበልፀግ የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ግለሰቦች ክብርና እውቅናን ይሰጣል፤ እንዲሁም

3ኛ/ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያላቸው ግንኙነትና ኅብረት ለዩኒቨርሲቲው ክብርና እውቅናን ለሚያመጡ ግለሰቦች እውቅናን ይሰጣል ።

የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የከፍተኛ ትምህርት አንዱ ዋነኛ የሥራ ፍሬ የሚገለጥበት ማረጋገጫ ነው። የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በአካዳሚኩ ዘርፍ የተለመዱትን መስፈርቶች ማለትም የትምህርት ኮርሶችን መውሰድንና ፈተና ማለፍን የመሳሰሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላትን አይጠይቅም። የክብር ዲግሪው የዶክትሬት ዲግሪ አለያም ማስትሬት ዲግሪ ሊሆን ይችላል። የክብር ዲግሪው ዶክትሬት ይሁን ወይስ ማስተርስ የሚለውን ሴኔቱ ይወስናል ።

የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ዕጩዎች ከሌሎች ሰዎች የሚለያቸው የተለየ ባሕርይና የሥራ አፈፃፀም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያላቸው፤ የክብር ዲግሪውን በመቀበላቸው ለዩኒቨርሲቲው ክብርና ሞገስን የሚያመጡ ናቸው።

ለዩኒቨርሲቲው ዓላማዎች መሳካት የተሰጡ፤ ለአካባቢያቸው፤ ለሀገራቸውና ለመላው ዓለም በተለያዩ መስኮች ለምሳሌ በሕዝባዊ ማኅበራት፤ በእውቀት ዘርፍ ሥራዎች፤ በስፖርት፣ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ወይም በኪነ-ጥበብ የላቀ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ግለሰቦች ከሚከተሉት መስፈርቶች ውስጥ አንዱን ወይም ከዚያ በላይ ካሟሉ ለክብር ዶክትሬት ዲግሪው ይታጫሉ ።

የስም አጠራርንም በተመለከተ በግለሰቦቹ ፍቃድ ላይ የተመሠረተ ሲሆን በማዕረጉ መጠራት የሚፈልጉ ተሸላሚዎች “የክብር ዶክተር” የሚለውን በማስቀደም መጠራት የሚችሉ ሲሆን በአካዳሚው ዘርፍ በጥናትና ምርምር ውስጥ አልፈው የሦስተኛ ዲግሪ እንዳገኙት ሰዎች ዶ/ር እከሌ ተብለው መጠራት አይችሉም። ለምሳሌ የክብር ዶክተር ጥላሁንን ገሠሠ / Honorable Dr. Tilahun Gessess/ማለት ይቻላል እንጂ “ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ” ብሎ መጥራት አይቻልም። ይሁንና ለመጠሪያነት ይውላል ወይስ አይውልም የሚለው ዛሬ ድረስ ጎራ ለይቶ እንዳከራከረ ነው ።

ሻሎም !

አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *