እንኳን ደስ አላችሁ!!!

 በየትኛውም ዘርፍ ይሁን መመረቅ ደስ ይላል። ባህላዊ-ሃይማኖታዊው (የአባቶችና እናቶች) ምርቃት መንፈስን እንደሚያለመልመው፣ ህሊናዊ እርካታን እንደሚሰጠው ሁሉ፤ ዘመናዊው ምርቃትም (ግራጁዌሽን) ሁለመናን በሃሴት ከመሙላትም ባለፈ ሁለንተናዊ ፋይዳው ቀላል አይደለም።

ሚዛናችን ወደ ሁለተኛው የሚያደላ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ወቅቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለወግ ለማእረግ ያበቋቸውን ተማሪዎቻቸውን የሚያስመርቁበት ልዩ ወቅት ነውና ስለሱ አንዳንድ ሃሳቦችን ለማንሳት ፈልጌ ነው በመግቢያዬ ሁለቱንም የምርቃት አይነቶች ያነሳሁት።

በየትኛውም መስክ ቢሆን የጀመሩትን ተግባር በድል ማጠናቀቅ ያስደስታል። አጠናቃቂ ባለቤቱን ብቻ ሳይሆን በዙሪያ ያሉ ሰዎችን (ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩም ይሁኑ ወይም ወዳጅ ዘመድ) ሁሉ ያስደስታል። በመሆኑም፣ መመረቅ (ሁለቱ “መመ-”ዎች ሲጠብቁም ይሁን ሲላሉ) ልዩ ስሜትን የሚፈጥር፤ የወደፊት አቅጣጫን የሚጠቁም ነው።

አስመራቂዎችን (ከቤተሰብ ጀምሮ፣ ዩኒቨርሲ ቲዎችንና የየተቋማቱ ማህበረሰብ አባላትን) ከልብ እንደሚያስደስት የታወቀ ነው። ባይሆን ኖሮ በምረቃው ሥነሥርዓትም ሆነ በአጠቃላይ በምረቃው እለት ተመራቂም አስመራቂም ተሞሽረው ብቻ ሳይሆን ሳቅ በሳቅ ሆነው “እንኳን ደስ አላችሁ …”ን በጋራ ሲዘምሩ ባልታዩ ነበር።

እርግጥ ነው መመረቅ በራሱ ግብ አይደለም። በመሆኑም ከመመረቅ በኋላ የሚኖረው ህይወት ሌላ አዲስ ህይወት ነው። መንገዱም፣ አቅጣጫና አካሄዱም ልዩና የራሱ የሆነ ልፋት፣ ጥረትን የሚጠይቅ ተግባር ነው። ከመመረቅ በኋላ ያለን ህይወት ከመመረቅ በፊት ካለ ህይወት የሚለዩት በርካታ ጉዳዮች አሉ።

ኃላፊነትን የመሸከም ሁኔታ ከመመረቅ በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ከመመረቅ በኋላ ያለው ይከብዳል፤ ወይም፣ ይለያል። የዚህ ደግሞ ዐቢይ ምክንያቶቹ በርካታ ሲሆኑ አንዱ ራሱ የህይወት ኡደት ነው። ይህ ኃላፊነትን የመሸከም ሁኔታ የሚጀምረው ከራስ ሲሆን፣ ራስን ከማስተዳደር የሚጀምር ይሆናል። ቀጥሎ ቤተሰብ፤ እያለ እያለ ሀገርን የመመራት ኃላፊነት ሁሉ በዚህ በዛሬዎቹ ተመራቂዎች ትከሻ ላይ የወደቀ ይሆናል ማለት ነው።

በተለያዩ ጥናቶች እንደ እንደተገለጸው፤ በአንድ ሀገር ላይ የትምህርት ተቋማት በብዛት አሉ ከተባለ በዛች ሀገር ዲሞክራሲ እግሩን እየተከለ ነው ማለት ነው ተብሎ ይተረጎማል። የተማረ የሰው ኃይል ባለበት ሀገር ዲሞክራሲ ስሩን ለመትከል ማገዶ አይፈጅም። ከተዘራ ብቅለቱም ሆነ እድገቱ ፈጣን ነው። ስርፀቱም ሆነ ተግባራዊነቱ ጊዜ አይወስድም። የእኛ ሀገር የምሩቃን ቁጥር በየአመቱ እየበዛ መሄድንም ከዚሁ አኳያ ስንመለከተው መታደል ሆኖ ነው የምናገኘው።

የሥነ ትምህርት ባለሙያዎች እንደሚሉት ደግሞ ፤ የትምህርት ፋይዳ ማንበብና መፃፍ ብቻ አይደለም። የትምህርት ፋይዳ ሥራ መያዝና ደመወዝ ማግኘት፤ አግኝቶም ራስን ማስተዳደር መጨረሻው አይደለም። የትምህርት ፋይዳው ወሰን እና ዱካ የለውም።

የተማረ ሰው በተበራከተ ቁጥር ፈጠራ እያደገ ይሄዳል። የተማረ ሰው በበዛ ቁጥር ዲሞክራሲ (ያዊነት) ምህዳሩን እያሰፋ፤ የአምባገነን(ነት) ምህዳር እየጠበበ ይሄዳል። የተማረ የሰው ኃይል በበዛ ቁጥር ሰላም እየሰፈነ፤ ጦርነት እየተወገደ፤

 መቻቻል እየነገሰ፤ መረዳትና መገንዘብ እየዳበሩ ይሄዳሉ። በጥቅሉ፣ ምክንያታዊነት የዛች፣ ምሩቃን በብዛት የሚወጣባት ሀገር ሀብትና ንብረት ይሆናል ማለት ነው።

የተማረ የሰው ኃይል በተበራከተ ቁጥር ሥርዓት አልበኝነት እየጠፋ፤ የሕግ የበላይነት እየሰፈነ፤ ሰላምና ፀጥታ እየነገሰ … ይሄዳል። አብሮነት ይደረጃል። መተሳሰብ የጋራ እሴት ይሆናል። ለመጪው ትውልድ አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች በብዛት ይፈጠራሉ።

የተማረ የሰው ኃይል በበዛ ቁጥር ሀገር እየለማ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ፣ የጥናትና ምርምር ተግባራት የእለት ተእለት ተግባራት እየሆኑ፣ የማህበራዊ አገልግሎት ተግባራት እየተሳለጡ፤ ችግር ፈጣሪነት ወደ ፈቺነት እየተሸጋገረ ይሄዳል።

በአንድ ሀገር ላይ የትምህርት ተቋማት በዙ፣ በርካታ ምሩቃን (ምሁራን) ወደ ገበያው መጡ ወዘተ ማለት ያቺ ሀገር አንድ እርምጃ ወደ ኋላ ሳይሆን ወደ ፊት ተራመደች ማለት ነው። ቢሮክራሲ ከነቅራቅንቦው ጓዙን ጠቅሎ ከሀገር ኮበለለ ማለት ነው። ሀገርና ህዝብ ከ“መልካም አስተዳደር ችግር” ተላቀቁ ማለት ነው።

የተማረ ሰው ለአንድ ሀገርና ህዝብ የአየር፣ ምግብና ውሃ ያህል አስፈላጊ ነው። ከላይ የዘንድሮ ተመራቂዎችን “እንኳን ደስ አላችሁ!!!” ስል እነዚህን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ እንጂ የምርቃት እለትዋን ብቻ አስቤ አይደለም።

በንጉሡ ዘመነ መንግሥት /በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ /ጊዜ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጭ ሀገር የሄዱ ሰዎች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በማግስቱ ወደ ሀገራቸው ይመለሱ እንደ ነበር ታሪካቸው ይነግረናል። በአካል ያጫወቱንም አሉ።

ለዚህም ምክንያታቸው ሀገሬና ወገኔ አንዳች ነገር ያደርግልናል ብለው ይጠብቁኛል የሚል ነበር። ሁኔታው የሚገርምና ለመቼውም ጊዜ ቢሆን በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል የምሩቃን (ምሁራን) ሀገራዊ ስሜትና የህዝባዊ አገልጋይነትን ያነገበ አቋም ነው።

በሥነ ትምህርትና ሥነ እውቀት ላይ ጥርሳቸውን የነቀሉ ምሁራን እንደሚሉት ሙስና፣ ቅጥ ያጣ ፖለቲካ፣ ዘረኝነት፣ አድርባይነት፣ በስልጣን መባለግ፣ አደራ በላነት፣ ለግል ጥቅም መስገብገብ፣ ወገንተኝነት፣ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” አቋም አራማጅነት ወዘተ የተማረ የሰው ኃይል ባለበት ሀገር የሚታሰቡ አይደሉም (ዛሬ የተቀየረ ነገር ካለ ባይታወቅም)።

የተማረ ሰው በበዛባት ሀገር “እኛ”ነት እንጂ “እኔ”ነት ቦታ የለውም። የሰው ልጅ “ሰው” ከመሆን ያለፈ ሌላ የሰውነት መስፈሪያም ሆነ መለኪያ የለውም። የተማረ ሰው በበዛባት ሀገር ሌብነት፣ ቀማኛነት፣ ዘራፊና ማጅራት መቺነት አይኖሩም እንኳን ባይባልም እዚህ ግባ የሚባሉ ግን አይደሉምና መማር፣ መመረቅና ማወቅ ፋይዳው ብዙ ነው።

የትምህርት ተቋማት በበዙባትና የተማረ የሰው ኃይል በብዛት ባለባት ሀገር የተገልጋይ (ህዝብ) እርካታ ሰማይ ድረስ ስለመሆኑ ቻይናና ሌሎች ሀገራትን እየጠቀሱ የሚናገሩ አሉ። ምሁራን በበዙባት ሀገር ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን የሚከተለው ህዝብ ቁጥር በርካታ ነው ይባላል።

የጤና ችግር ብሎ ነገር ቢኖርም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ባልተረጋገጠ ጉዳይ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ መድረስ ነውር እንደ ሆነ ነው የሚነገረው። እኔም፣ ከላይ የዘንድሮ ተመራቂዎችን “እንኳን ደስ አላችሁ!!!” ስል እነዚህንና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ እንጂ የምርቃት እለቷን ብቻ አስቤ አይደለምና አሁንም በድጋሚ፤ እንኳን ደስ አላችሁ!!! እላለሁ።

 ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *