ማዳበሪያን በወቅቱ ለማድረስ ከሚደረገው
ርብርብ ጎን ለጎን ሕገወጥነትን ማስተካከል
ትኩረት ይሰጠው!

 የግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱን ያህል ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም፤ የዕድሜውን ያህል አቅም አጎልብቶ ሕዝቡን መመገብ የሚያስችል ቁመና መላበስ ሳይችል ቆይቷል። ከዚህም የተነሳ በሀገሪቱ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ ለረሀብ ተጋላጭ የሚሆኑ ዜጎች ቁጥር ዓለም አቀፍ አጀንዳ የመሆናቸው ጉዳይ የተለመደ ሆኖም ቆይቷል።

ይህንን ሀገራዊ እውነታ ለመለወጥ በየዘመኑ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም፤የተገኙ ውጤቶች ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት ሳይችሉ ቀርተዋል። ዛሬም ሀገሪቱ ሰፊ ለእርሻ የሚሆን መሬት፣ የውሀ ሀብት እና የሰው ኃይል ባለቤት መሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታወቀ ዜጎቿን በአግባቡ መመገብ የሚያስችል አቅም ባለቤት መሆን ሳይቻላት ቀርቷል።

በዚህም ሀገሪቱ በአደጋዎች ወቅት ቀርቶ በሰላማዊ ወቅቶችም ዜጎቿን ለመመገብ የሌሎችን የምጽዋት እጅ ለመጠበቅ ተገዳ ቆይታለች፤ ተመጽዋችነት ለሚያስከትለው ጫና ተጋላጭ ከመሆን ባለፈ በዓለም አቀፍ መድረኮች አንገቷን ቀና አድርጋ መንቀሳቀስ የምትችልበትን አቅም እየተገዳደረ ይገኛል።

ይህንን ዘመን እየተሻገረ፤ በየዘመኑ ትውልዶችን ዋጋ እያስከፈለ ያለን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት ላለፉት የለውጥ ዓመታት ሰፊ ጥረቶች ተደርገዋል። ከጥረቶቹ በዋነኛነት ከሚጠቀሱት አንዱ የግብርናውን ዘርፍ በዘመናዊ ግብአቶች የማበልጸግ ሥራ ነው።

ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት የሚያስፈልገውን ማዳበሪያ ፣ ምርጥ ዘር እና ፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን ከማስተዋወቅ አንስቶ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበሬው ፈጥኖ ከግብአቶቹ ጋር እንዲተዋወቅና በግብአቶቹ መተማመን እንዲፈጥር በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ፣ የተገኙ ውጤቶችም ዘርፉ አሁን ላለበት የተሻለ ደረጃ አብቅተውታል።

ይህንን በእውነታ ታሳቢ ያደረገ የግብርና ሀገራዊ ስትራቴጂ ቀርፆ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምሮ፤ የምርምር ተቋማት ሰፊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማድረግ፤ የግብርናው ዘርፍ ከቀደሙት ወቅቶች በተሻለ መልኩ ምርታማ የሚሆንበት ሁኔታ ተፈጥሯል፣ በዚህም አርሶ አደሩም በተሻለ መልኩ የልፋቱ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ነው።

ይህንን ባለፉት የለውጥ ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የታየውን ሀገራዊ መነቃቃት ከፍ ወዳለ እመርታ ለማሻገር በመንግሥት በኩል ብዙ ተሰርቷል። መንግሥት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በጀመረው የለውጥ ጉዞ፤ በምግብ እህል ራስን ለመቻል እያደረገ ያለው ንቅናቄ የግብርናው ዘርፍ የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል።

ግብርናው በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እና ግብአቶች በመታገዝ በአይነት ፣ በብዛትና በጥራት የተሻሉ ምርቶችን በማምረት ዜጎችን በራስ አቅም ለመመገብ መንግሥት የያዘው ቁርጠኝነት፣ ለግብርናው ዘርፍ ከፍያለ ሀብት እንዲመድብ አድርጎታል።

ከዚህ የተነሳም መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ከፍ ያለ ሀብት በማፍሰስ ትራክተሮችን ኮንባይነሮችን ምርጥ ዘሮችንና ጸረ- ተባይ ኬሚካሎችን ከፍ ባለ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ አሰራጭቷል። በዚህም በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ለዚሁ ሥራ ተደጉሟል።

መረጋጋት በተሳነው ዓለም አቀፍ ገበያ፤ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ በማድረግ ማዳበሪያ ለገበሬው በወቅቱ እንዲደርስ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል። የገበያውን ውጣ ውረድ በስኬት ለመወጣትም ባለው አቅም ሁሉ ተጉዟል።

በማዳበሪያ ግዥ ዙሪያ ያለው ዓለም አቀፍ ተግዳሮት፤ በሀገር ውስጥ የተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት መንግሥት ማዳበሪያ በወቅቱና በሚፈለገው ደረጃ ለማቅረብ ላደረገው ጥረት ዋነኛ ፈተና ሆኖ ተስተውሏል። መንግሥት ችግሩን ለመሻገር ያሳየው ቁርጠኝነት በራሱ እውቅና ሊሰጠው የሚገባው ነው።

ይህም ሆኖ ግን ብዙ ፈታናዎች አልፎ ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ማዳበሪያ በሕገወጥ መንገድ የህገወጦች መጠቀሚያ እየሆነ የመምጣቱ እውነታ፤ ማዳበሪያውን የነገ ተስፋው አድርጎ ለሚጠብቀው አርሶ አደር ብቻ ሳይሆን በመላው ሕዝብ ላይ የሚፈጸም የከፋ ወንጀል ነው።

ሕገወጥነቱ አቅም ገዝቶ የሀገሪቱ የግብርና ዘርፍ ተግዳሮት ከመሆኑ በፊት የሚመለከተው አካል፤ ከሁሉም በላይ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት ፈጥነው ሊንቀሳቀሱና ሊያርሙት ይገባል። እንዲህ አይነቱ ወንጀል አድሮ የመዋል እድል ካገኘ አጠቃላይ የሆነውን የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ የማይወጣው ቅርቃር ውስጥ ሊጨምረው የሚችል ነው ።

ከዚህም ባለፈ ህገወጥነቱ እንደ ሀገር የተጀመረውን በምግብ እህል ራስን የመቻል እንቅስቃሴ የሚፈታተን መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *