“የሥራ እድልን የሚፈጥር፣ የኑሮ ውጣ ውረድን የሚቀንስ ሃሳብ ሁሌም ከግለሰቦች ይፈልቃል” የሚል አመለካከት አለ። ስኬታማ ግለሰቦች ከራሳቸው፣ ከቤተሰባቸው አልፈው ለሀገርና ለትውልድ የሚቆይ ወረት፣ እውቀትና ጥበብ ያኖራሉ። በእርግጥም እያንዳንዱ ሰው አንዳች የተለየ ተሰጥኦና ልዩ ችሎታ እንዳለው ይታመናል። ይሁንና ብዙዎች በተፈጥሮ የተሰጣቸውን ጸጋ ሳይረዱት ቀርተው አልያም መንገድ አጥተው ሲባክኑ ይስተዋላል። አንዳንዶች ደግሞ ገና በጠዋቱ መክሊታቸውን የሚያሳይ የንግድ፣ የሥራ ፈጠራና የግል ክህሎት የሚያወጡበት መንገድ ያጋጥማቸውና ለነብሳቸው ጥሪ ምላሽ በመስጠት ‹‹መክሊቴን አገኘሁ›› ሲሉም ይደመጣል። በዛሬው የስኬት እንግዳ የምናስተዋውቃችሁ ግለሰብም ከእነዚህ ስኬታማ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። ለበርካታ አዳዲስ ሃሳቦች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ ለንግድና ለሥራ ፈጠራ ምክንያት የሆኑ ናቸው።
ኢንጂነር ቅደም ተስፋዬ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ ብስራተ ገብርኤል በሚባል አካባቢ ነው። የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ እና ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሎንደን ደግሞ በኤሌክትሮ ሜካኒካል ሲስተም አግኝተዋል። በትምህርታቸው የቀሰሙትን ክህሎት መሰረት አድርገው በግል የሥራ ፈጠራ ላይ ተሰማርተው “የኬ አይ ቲ ሶላር” ፣ “የአይ ሲ ኢ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን እቃዎች አስመጪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር”፣ “የቅደም ኢንተርፕራይዝ” ፣ “የኧርዝ ሊንክ ኢንጂነሪንግና ማንፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ የግሪን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ፣ የቢ ኤንድ ኬ፣ የጂኤስ አር (green smart renewable energy and technology) እና የግሪን ቴክ አፍሪካ (በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ መኪና አስመጪና አምራች ካምፓኒ ከፍተኛ የሼር) መስራችና ባለቤት ናቸው።
ኢንጂነር ቅደም ከላይ ከጠቀስናቸው የሥራ ፈጠራዎችና ድርጅቶች ባሻገር የኤሌክትሪክ መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ፣ የኃይል አቅርቦት ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው። አንዳንዶች “የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መኪኖች አባት” የሚል ስያሜንም ሰጥተዋቸዋል። በተለይ ከኤሌክትሪክ መኪኖቹ ጋር ተያይዞ በቀረጥና በልዩ ልዩ የሕግ አስተዳደሮች ዙሪያ ከመንግሥት ጎን በቅርበት እየሰሩ ይገኛሉ። የኤሌክትሪክ መኪኖች የአስር ዓመት ፖሊሲ እንዲወጣም የግል አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ዘርፉን በማህበር ለማደራጀት በሚሰሩ ሥራዎች ቀዳሚ ተሳታፊ ናቸው።
የሕይወት መሰረት
ዊሊያም ወርድስዎርዝ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1802 “My Heart Leaps Up” በሚል ርእስ ላይ ባሰፈረው አጭር ግጥም የአንድ ሰው ማንነት በልጅነቱ በገነባው ስብእና ላይ ይመሰረታል “The child is the father of the man” የሚል ስንኝ አስፍሮ ይገኛል። ይህ ስንኝ የሰው ልጅ የሕይወት መስመር ከአስተዳደጉ፣ ከአካባቢያዊ ልምዱና በልጅነቱ ካዳበራቸው እውቀቶች፣ ልምዶች እና የሕይወት ተሞክሮዎች የሚቀዳ እንደሆነ የሚመሰክር ነው። የኢንጂነር ቅደም ተስፋዬ የዛሬ ስኬት የዚህን ግጥም ስንኝ ሀሳብ የሚያጠናክር ይመስላል።
ተወልደው ባደጉበት ብስራተ ገብርኤል አካባቢ በቤተሰቦቻቸው በእውቀትና በመልካም ሥነ ምግባር ተኮትኩተው አድገዋል። በትምህርት አቀባበላቸው ፈጣን፣ ትጉህና የደረጃ ተማሪ ነበሩ። በመንግስት ሥራ የሚተዳደሩት ቤተሰቦቻቸው ለሕይወት ቁልፍ መርህ የሆነውን “ነፃነት” አጎናፅፈዋቸዋል። እንዳሻቸው ከጎረቤት፣ ከዘመድ አዝማድ፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጋር ተጫውተው የልጅነት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በካቴድራልና በከፍተኛ 23 ትምህርት ቤት በሚከታተሉበት ወቅት በቀለም ትምህርት ያስመዘግቡ ከነበሩት ስኬት ጎን ለጎን በልዩ የተሰጦና የፈጠራ ሥራ ውስጥ መሰማራት ያስደስታቸው ነበር። በሽቦ መኪና (ባስ ታክሲ፣ ትራክተር፣ አውቶሞቢል እና ጎማዎችን ይሰሩ ነበር)፣ የሥነ ፅሁፍ (ቲያትር ድርሰት) እና ሌሎች ክህሎቶችን ይሞካክሩ ነበር። ከቤተሰቦቻቸው ክትትልና ድጋፍ ጋር በቀለም ትምህርታቸው ስኬታማ እንዲሆኑና ለዛሬው ማንነታቸው ምሰሶ እንዲሆኑ አጋዥ ነበር። በተለይ ለንግድ፣ ለሥራ ፈጠራ፣ የራስን ድርጅት መስርቶ ለብዙዎች መንገድ መፍጠር የሚሉት ቁልፍ መርሆች ጥንስሳቸው ከኢንጂነር የልጅነት ዘመን የሚቀዱ ናቸው።
ኢንጂነር ቅደም በመጀመሪያ ደረጃና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው የተሳካ አፈፃፀም አሳይተው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 1986 ጀምሮ ለአራት ዓመት ያህል በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፍ እውቀትና ክህሎታቸውን አዳብረዋል። ዲግሪ መያዛቸውና ትምህርታቸውን በስኬት ማጠናቀቃቸው ግን ወደ ተቀጣሪነት እንዲያመሩ አላደረጋቸውም። ይልቁኑ ወደ ግል የሥራ ፈጠራ ማዘንበልን ነበር ምርጫቸው የሆነው። “በሥራ ሕይወት ስኬትን ማስመዝገብ የጀመርኩበት ጊዜ ነው” በማለት የያኔውን ውሳኔያቸው የዛሬ መሰረታቸው እንደሆነ ዛሬ ድረስ ያስታውሱታል።
የንግድና ሥራ ፈጠራና የስኬት መንገድ
ኢንጂነር ቅደም በከፍተኛ ውጤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1990 ዓ.ም ተመርቀው እንደወጡ ለራሳቸው “ተቀጥሮ መሥራት” የሚለው ሃሳብ ትክክል እንዳልሆነ ነግረውታል። ቀድሞውንም ቢሆን በራስ አቅም እና እውቀት አዲስ ነገር መፍጠር የሚያስደስታቸው ሰው ወዲያው ከትምህርት መልስ ያመሩት ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤት ነበር። በዚያ ቦታ ላይም በፀሐይ ብርሃን የታገዘ የውሃ ማሞቂያ አምርተው ለገበያ ማቅረብ ጀመሩ። በትምህርት ቆይታቸው ወደ ሃይል (energy) ዘርፍ ያዘነብሉ ነበርና በዚህ ሥራ ወዲያው ነበር ስኬታማ መሆን የጀመሩት። የሜካኒካል ሶላር የውሃ ማሞቂያውን እየሰሩ ለግለሰቦች፣ ለድርጅቶች ሆቴሎችና የተለያዩ አካላት በመላው ኢትዮጵያ ማቅረብ ጀመሩ። በዚህ ሙያቸውም ከራሳቸው አልፈው ለ22 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ እድል ፈጠሩ። የእርሳቸው ስኬት መንገድ ጠራጊው የኢነርጂ ልማት የሶላር ሜካኒካል ማሞቂያ ነበር።
የቀለም ትምህርት እንዳጠናቀቁ ጊዜ ሳያባክኑ በግል ሥራ ላይ የተሰማሩት ኢንጂነር ቅደም በሶላር ማሞቂያው ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተው፣ በርካታ ሠራተኞች ቀጥረው፣ በቴክኖሎጂ አዲስ የነበረውን የኃይል አቅርቦት በማስተዋወቅ ቀዳሚው ሰው ሆኑ። ለቀጣይ ስኬታቸው በር ከፋች የሆነው ይህ ሙያም የበኩር ሥራቸው ሆነ።
በሶላር ኢነርጂ ምርት ላይ ፈጣን እድገት ያሳዩት ኢንጂነር ቅደም ቀጣይ ሥራቸው አድርገው የመረጡት የኮንስትራክሽን እቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስመጣት ለልማት ሥራዎች ማቅረብ ሆነ። ይሄኛው ጉዟቸው የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (chamber of commerce) በአንድ አጋጣሚ ያመጣውን እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ነበር። በጊዜው የኮንስትራክሽን አምራች የቻይና ካምፓኒ ከእርሳቸው ጋር ባደረገው ድርድር ለኢትዮጵያ ብቸኛው የካምፓኒው ምርቶችን አቅራቢ እንዲሆኑ አስቻላቸው። ይህ በአጋጣሚ የተፈጠረ እድል በዘርፉ ትልቅ ስኬትን እንዲያስመዘግቡና ሌላ የስኬት በር እንዲከፈትላቸው ያደረገ ነበር። ይህንን ተከትሎ በሀገር ውስጥ ትልቅ ፍላጎት ያላቸውን የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች በተጨማሪ ከጣሊያን፣ ስፔን፣ ፈረንሳይና ጀርመን ከመሳሰሉ ሀገራት ያቀርቡ ጀመር። በዚህ ዘርፍ ብቻ በቋሚነት ለ58 ሰዎች ቋሚ ከ100 እስከ 200 ለሚደርሱ ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ እድል ፈጥረዋል።
ኢንጂነር ቅደም ዓይናቸውን ከገለጡበት የአቅርቦት ዘርፍ (ከኮንስትራክሽን) በተጨማሪ በውሃ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ለሀገር ውስጥ ፍላጎት ማቅረብ ጀመሩ። የመንግስት የውሃ ቢሮዎች የሚያወጧቸውን ጨረታዎች ከትላልቅና ዓለም አቀፍ የውጭ ካምፓኒዎች ጋር በመጫረት ሰብረው መግባት ቻሉ። ብቸኛው ኢትዮጵያዊ የውሃ ዘርፍ መለዋወጫ መሳሪያዎች አቅራቢም ሆኑ። የእርሳቸው በድፍረት ከትላልቅ ካምፓኒዎች ጋር ተጫርቶ አሸናፊ መሆን ለሌሎችም ባለሃብቶችም በር ከፋች ነበር። የእርሳቸውን ስኬት ልዩ የሚያደርገው ግን የሶላር፣ የኮንስትራክሽንና፣ የውሃ ዘርፉ ምርትና አቅርቦት በእኩል ደረጃ ጎን ለጎን ማስኬድ መቻላቸው ነበር። በእነዚህ ዘርፎች ላይ ስኬት እንዲያስመዘግቡ ደግሞ ከዩኒቨርሲቲ በቂ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሲስተም ምሩቅ መሆናቸው ጠቅሟቸዋል። ይህ እውቀት በተፈጥሮ ከታደላቸው የገበያ (marketing) ክህሎት ጋር ተደምሮ በንግዱ ዓለም የሚፈልጉት ደረጃ ላይ ያስቀምጣቸው ጀመር።
ኢንጂነር ቅደም የኢነርጂ ዘርፉ ላይ በሶላር ውሃ ማሞቂያ ብቻ አልተገደቡም። የዓለም ባንክ ገጠራማ በሆኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመብራት አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ በነበረው ፕሮጀክት ላይ ተሳትፈው በፀሐይ ብርሃን የሚሰራ የመብራትና ኃይል አቅርቦት ተሳታፊ ነበሩ። በዚህም ውጤታማ ሥራን አስመዝግበዋል። ይህ ውጤታማነታቸው ቀጥሎ አሁንም ድረስ በሀገረ ጅቡቲ በሶላር የኤሌክትሪክ አቅርቦት ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው።
ግሪን ቴክ አፍሪካ ሌላኛው መንገድ
ኢንጂነር ቅደም ፈጣን፣ አርቆ የሚያይ የንግድ ክህሎት ያላቸው ናቸው። ለአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችም ካላቸው እውቀት አኳያ ቀድመው ወደ ገበያ ይገባሉ። የኤሌክትሪክ መኪኖችን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለማስገባት ምርምር እና ጥናቶች ሲካሄዱ እርሳቸው የዚያ ቀዳሚ ተሳታፊ ነበሩ። ከተማሩት እና ካገኙት ልምድ አንፃር በኤሌክትሪክ መኪኖች ወደሚዘወር አዲስ ገበያ ለመግባት ጊዜ አልፈጀባቸውም። ስልጠናዎችን ቦታው ድረስ ሄደው በመውሰድ ኢትዮጵያ ውስጥ “የኤሌክትሪክ” መኪኖች እውን የሚሆኑበትን መንገድ መፈለግ ጀመሩ። ይህ የሆነው በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ከተቸረው የኤለን መስክ ቴስላ (የኤሌክትሪክ መኪና) ምርት እኩል ነበር።
ይህ ውጥናቸው ግሪን ቴክ አፍሪካን ወለደ። ኢንጂነር ቅደም ደግሞ የዚህ ውጥን አባት ሆኑ። ለዓላማው መሳካት ደግሞ አብረዋቸው በሼር ባለቤትነት አጋሮች አሏቸው። አሁን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት የሚመሩት ካምፓኒ ለኢትዮጵያና ለምስራቅ አፍሪካ አየር ንብረት የሚስማማ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በቻይና አገር ከአጋሮቹ ጋር በትብብር አምርቶ ያስመጣል። በሰንዳፋና በድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ መኪኖች የሚያመርቱ ፋብሪካ ለመገንባት በሂደት ላይ ይገኛሉ። በኬንያ በቻይና ሀገርም በባለቤትነት የሚመሯቸው የግሪን ቴክ ቅርንጫፎች አሉ። ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖችን ለማስተዋወቅ አንድ ወር የትራንስፖርት አገልግሎት በነፃ ሰጥተዋል።
የኢንጂነር ቅደም ጥንስስ “ግሪን ቴክ አፍሪካ” በሀገር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እአአ በ2022 የመጀመሪያዎቹን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖችን ያስገባ ሲሆን የእርሱ እህት ኩባንያ የሆነውን “ጎ ግሪን ዲጂታል የራይድ አፕሊኬሽን ትራንስፖርት” ደግሞ የታክሲ አገልግሎት በኤሌክትሪክ መኪኖች መስጠት ጀምሯል። ቴክኖሎጂው ለበርካታ ሥራ እድል መፈጠር ምክንያት እንደሚሆን ከወዲሁ ተስፋ ተጥሎበታል። ከሁሉም በላይ ለነዳጅ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ ገቢን የሚጨምር የትራንስፖርት ዘርፍ በሀገር ውስጥ ለመዘርጋት እሳቤውን ጀምረውታል። በተጨማሪ ባለሶስት እግር በኤሌክትሪክ የሚሰራ ባጃጅ በሀገር ውስጥ በቅርቡ ለማስገባት ቅድመ ሁኔታዎችን አጠናቀዋል።
ግሪን ቴክ አፍሪካ በ2032 አብዛኛውን የአፍሪካ ሀገራት ለመሸፈን እቅድ ይዞ እየሰራ ነው። በምስራቅ አፍሪካ ከታንዛኒያ ውጭ በሁሉም ሀገራት ይገኛል። ከዚህ ራዕይ ጎን ለጎን ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን ማፍራት ዋንኛ ግቡ ነው። ከዚህ ቀደም በኤሌክትሪክ መኪኖች ዘርፍ ጥገና ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን በነፃ በማስተማር አስመርቀዋል። አሁንም 26 ሰዎች የዚህ ሙያ ባለቤት እንዲሆኑና በሁለት እግራቸው ቆመው የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ እየሰሩ ይገኛሉ። የቱሪዝም ታክሲ ለመጀመር ከተደራጁ ማህበራት ጋርም የኢንጅነር ቅደም ግሪን ቴክ አብሮ ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሷል። ከኢትዮጵያ አየር ንብረት ጋር የሚስማሙ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በማምረት ቱሪስቶች ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ ትራንስፖርት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው።
እንደ መውጫ
ኢንጂነር ቅደም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያሉ አላስፈላጊ ቢሮክራሲዎችን መስበር ከተቻለ ሥራ ፈጣሪዎች ወደ ስኬት በቀላሉ እንዲመጡ በር ይከፍታል የሚል እምነት አላቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት በትኩረት እንዲሰራ ይመክራሉ። ከዚህ ጎን ለጎን ወጣቱ ትውልድ ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ሃሳቦች ላይ አተኩሮ መሥራት እንደሚገባው ያምናሉ። “በንግድ ዓለም ችግር ፈቺ ሃሳቦችና ፈጠራዎች ናቸው ስኬታማ የሚያደርጉት” የሚል አቋም አላቸው። ከዚህ መነሻ ወጣቶች የአካባቢን አለፍ ሲልም የሀገርን ቁልፍ ችግሮች ለይተው መፍትሄ የሚሰጡ የፈጠራና የንግድ ሀሳቦች ላይ እንዲሰማሩ ይፈልጋሉ። ይህን ካደረጉ የተሟላ ስኬት ላይ መድረስ ቀላል እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2015