እናት ከወሎ፣ አባት ከደብረብርሃን ተነስተው አዲስ አበባ ተገናኙ። ከአስር ልጆቻቸው መካከል ለወላጆቻቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት አቶ ዓለማየሁ ተሾመ አዲስ አበባ ተፀንሰው፤ በእናታቸው የትውልድ አካባቢ ወሎ ወረሂሉ ልዩ ስሙ ክሬ ማሪያም ተወለዱ። ክርስትና ተነስተው ብዙም ሳይቆዩ በሕፃንነት ዕድሜያቸው በእናት እቅፍ እንዳሉ አዲስ አበባ ወሎ ሰፈር መጡ።
ወሎ ሰፈርም በአጋጣሚ የኮሎኔል አብዲሳ ኣጋ ጎረቤት በመሆናቸው ምክንያት ኮሎኒል አብዲሳ ለራሳቸው ልጆች ቄስ አስመጥተው ፊደል ሲያስቆጥሩ፤ በዚሁ አጋጣሚ ተጠቃሚ በመሆን ፊደል የመቁጠር ዕድል አገኙ። አቡጊዳ እና ወንጌልን አልፈው ፈለገብርሃን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡ። በእዛው ወሎ ሰፈር ባለው የግል ትምህርት ቤት እስከ 5ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታተሉ።
የ6ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ነፃነት ብርሃን በሚባል ትምህርት ቤት በመከታተል፤ የስድስተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን አለፉ ። የ7ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በስብስቲ ነጋሲ ትምህርት ቤት ተከታትለው፤ ትምህርታቸውን ከዛ በላይ መግፋት ባለመቻላቸው ለማቋረጥ ተገደዱ።
አዲስ ዘመን የዕለቱ የዘመን እንግዳው አድርጎ ያቀረባቸው እኚህ የላይቭ አዲስ አገር በቀል ግብረሠናይ ድርጅት መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ተሾመን ናቸው ፣ ከትምህርታቸው መቋረጥ ጀምሮ ስላለው የልጅነት ሕይወታቸው፣ በውትድርና ስላሳለፉት ጊዜና በበጎ አድራጎት ስላከናወኑት ተግባር ከእርሳቸው ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ትምህርት አቋርጠው ነበር? ትምህርትዎን ያቋረጡበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ዓለማየሁ፡- አባቴ እና አጎቴ ሰው በመግደል ወንጀል ተጠርጥረው ያለ አግባብ ጥፋተኛ ናችሁ በሚል ክስ ተመሥርቶባቸው ፤ 15 ዓመት ተፈርዶባቸው እስር ቤት ገቡ። በዚህ የተነሳ የወላጅ አባቴ ገቢ በመቆሙ አሥር ልጅ የወለደችዋ እናቴ ግራ ገባት። ቤተሰቡ ሊበተን ጫፍ ደረሰ። በዚህ ምክንያትም ቤተሰብን የማስተዳደር ኃላፊነት ከአባቴ ትከሻ ወደ እኔ ትከሻ ተዘዋወረ። ከዚህ የተነሳም ትምህርቴን ከሰባተኛ ክፍል በማቆም ቱሪስት ድርጅት በ32 ብር ከ25 ሳንቲም ተቀጥሬ ሻይ ማቅረብ ጀመርኩ።
እናቴ በበኩሏ ግንባታ በሚካሔድበት አካባቢ ጠላ እና ዳቦ በመሸጥ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመረች፤ በተሰበሰበው ገንዘብ ቤተሰብ ከመመገብ ጎን ለጎን ጠበቃ ቀጥረን ይግባኝ ጠይቅን። አንድ ዓመት ተከራክረን፤ አባቴ እና አጎቴ ከታሰሩ አንድ ዓመት ሊሞላቸው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ሲቀራቸው የሰውና ሌሎችም ማስረጃዎች ከተሰበሰበ በኋላ እንዳልገደሉ ተረጋገጠ። ልደታ ያለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነፃ አሰናበታቸው።
አባቴ ልጆቹን ለማስተዳደር ያደረግኩትን ጥረት አውቆ፤ እንደትልቅ ጀግና ቆጠረኝ። በዛ ሂደት አንድ ዓመት ያቋረጥኩትን ትምህርቴን የ32 ብር ከ25 ሳንቲምን ደመወዝ ትቶ መቀጠል አዳጋች ሆነና በሁለተኛው ዓመትም ሳልቀጥል እንዲሁ ዓመቱን በሥራ ብቻ ጨረስኩት።
ደመወዝተኛ በመሆኔ እንደልቤ ሆንኩኝ፤ ሥራውን ለመቀጠል ስል የቀኑን ትምህርት ትቼ ዑራኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ አፄ ቴዎድሮስ ትምህርት ቤት የማታ ትምህርት ጀመርኩ። ስምንተኛ ክፍል ገብቼ በጥሩ ውጤት ወደ ዘጠነኛ ክፍል ተሸጋገርኩ።
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ወታደር ሆኑ?
አቶ ዓለማየሁ፡- በትምህርቴ ብዙም ሳልገፋ ብሔራዊ ውትድርና መጣ። ወታደር መሆን ትልቁ ምኞቴ ነበር። በነበርኩበት ሰፈር ብዙዎቹ ትልልቅ ሰዎች ክቡር ዘበኞች ናቸው። የማዕረግ ልብሳቸውን ለብሰው ሲመጡ ልቤ ይደነግጥ ነበር። ብሔራዊ ውትድርና መጣ ሲባል፤ ዘጠነኛ ክፍል ትምህርት አቋርጬ ብሔራዊ ውትድርና ሔድኩኝ። ጦላይ ሠለጠንኩ፤ የምርጫ ምድቤ ደብረዘይት አየር ኃይል ሆነ።
ደብረዘይት ሰባት ወር አገለገልኩ። ነገር ግን እንዳሰቡት አልሆንኩላቸውም፤ ወደ እናቴ ዘንድ በመሔድ እየጠፋሁ አስቸግር ነበር። ስለዚህ አሥመራ ተላኩኝ። ለሦስት ዓመታት ቅጣት በሚመስል መልኩ አሥመራ አየር ኃይል ቆየሁ። በዛ ጊዜ ጦርነት ነበር፤ ሽሽት ብሎ ነገር አላውቅም።
አሥመራ በነበርኩበት ጊዜ በሕይወቴ ሰው ማለት ምን ማለት እንደሆነ በደንብ ተገነዘብኩኝ። ወታደር መሆን ምን ማለት እንደሆነ አወቅሁ። ታላቅና ታናሽ ማለት ምን እንደሆነ ሌሎችም ሀገርን የተመለከቱ ጉዳዮችን በውል ተረዳሁ። እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ራስን በሥነምግባር ማሳደግ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር አየሁ። በዕውቀት፣ በሥራ፣ የአዛዥ እና የታዛዥነት ጉዳይን በአጠቃላይ ሁሉንም ነገር ተማርኩ።
ብዙ ሺ ወታደር ባለበት ቦታ ላይ ከፖለቲካ ፍላጎት ውጪ ማነቃቃት ላይ ታዋቂ ሆንኩኝ። ጦርነቱ በረደ። ከዛ ግን ብዙ አልቆየሁም። ተመልሼ ትምህርቴን ቀጠልኩ፤ ዳግም የእናት ሀገር ጥሪ ሲባል፤ እንደገና ለጦርነት መሔድ ፈለግኩ። ሆኖም አባቴ ከለከለኝ። የኦስትሪያ ኤምባሲ ዋና ሴክሪተሪ በ240 ብር ደመወዝ በጥበቃ ተቀጥሬ ትምህርቴን ጎን ለጎን ማካሔድ ጀመርኩ። በተጨማሪ መንጃ ፍቃድ አወጣሁ፤ ሕይወት ቀጠለ፤ አሁን የአራት ልጆች አባት እና የሁለት የልጅ ልጆች አያት ለመሆን በቅቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ትምህርቱ እስከ ምን ዘለቀ?
አቶ ዓለማየሁ፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአመራርነት (Executive Leadership) የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝቻለሁ። በትምህርት የተለያዩ ሀገራትም ሄጃለሁ። ኦስትራዊቷ ዘንድ እየሠራሁ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ዘለቅኩ። በእርግጥ ቀደም ሲል ሥራው እና ሌሎች ነገሮች ተደራርበው ዩኒቨርስቲ የሚያስገባ በቂ ውጤት አላመጣሁም ነበር። ነገር ግን መንጃ ፍቃድ ያለኝ በመሆኑ ባለኝ ውጤት በዲፕሎማ መርሐ ግብር ተግባረዕድ አውቶ መካኒክ ተማርኩኝ። ጎል ኢትዮጵያ የሚል ዓለም አቀፍ ተቋም በተመሳሳይ መልኩ በጥበቃ ሥራ ተቀጥሬ ለጥቂት ወራት ሠራሁ።
ምንም እንኳ በጥበቃነት ብቀጠርም መንጃ ፍቃድ አለኝ፣ በአውቶመካኒክ በዲፕሎማ ተመርቄያለሁ እንዲሁም ከሰዎች ጋር እግባባ ስለነበር፤ ያለምንም ውድድር ወደ ተመረቅኩበት ሙያ ከመኪና ጋር ወደ ተያያዙ ሥራዎች ተዘዋወርኩ። በመሐል ሳሽከረክር የመኪና አደጋ አጋጠመኝ። በዚህ በጣም ተበሳጭቼ ለአምስት ቀን ከሥራ ቀርቼ ነበር። ሆኖም የሥራ ኃላፊዎቹ አደጋው አጋጣሚ መሆኑን ገልፀው፤ ከዛ ሥራ ላይ አንስተው ቂርቆስ አካባቢ የጎዳና ልጆችን የሚያግዝ አንድ ትልቅ ፕሮጀክት ላይ እንድሠራ አመቻቹልኝ።
በተሻለ ደመወዝ የጎዳና ልጆችን ለማሠልጠን ተቀጠርኩኝ። ይህም የበጎ አድራጎት ሥራን ለመጀመር እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ ረድቶኛል ። ሰው ቢቸግረው እና ግራ ቢገባው እንጂ ማንም ቢሆን ፈልጎ ድህነትን እና ማጣትን አይመርጥም፤ በዛ አጋጣሚ የጎዳና ልጆች የሚያድሩበት እና የሚገቡበትን ጉድጓድ ሳይ ሰው እንደዚህ እንዴት ሊኖር ይችላል? ብዬ የራሴን ሕይወት አሰብኩ።
እኔም በተመቻቸ ሕይወት ውስጥ አላለፍኩም። በቤተሰብ አስተዳደር እና በልጅ አስተዳደግ ችግር ምክንያት ብዙ ልጆች ወደ ጎዳና እንደሚወጡ አረጋገጥኩ። በቆይታዬ ሳሠለጥናቸው የነበሩ ልጆች ሰው ሆነው ቤተሰብ መሥርተው ሲያስተዳድሩ እያየሁ ነው። ሁሉም ሰው ሲፈጠር የተሰጠው ስጦታ አለ። ከዛ ስጦታ ጋር የመገናኘት ችግር አለ።
ጎል ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኜ በዛ ፕሮጀክት ለስድስት ዓመታት ከአሠልጣኝነት እስከ ሥልጠና ክፍል ኃላፊነት ቆየሁ። እየሠራሁ ትምህርቴን ጎን ለጎን ቀጠልኩ፤ አየርላንድ ሄድኩ። ከአስተዳደር ሙያ ጋር ተያይዞ ተማርኩ፤ ኒዮርክም በተመሳሳይ መልኩ ሔጄ ትምህርቴን ተከታትያለሁ፤ ወደ ጀርመንም አቅንቼ የኮሙኒኬሽን ትምህርት ተምሬያለሁ። በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲም ተምሬያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የበጎ አድራጎት ሥራው እንዴት ቀጠለ?
አቶ ዓለማየሁ፡- በጣም በሚገርመው ኮንሰርን የሚባል በጎዳና ልጆች ላይ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ድርጅት በድጋሚ ከጎዳና ልጆች ጋር እንድሠራ ቀጠረኝ። ድርጅቱ አዲስ አበባ ላይ አራት ቅርንጫፍ ያለው ሲሆን፤ የጎዳና ልጆች እና የመንግሥት ድጋፍ ሰጪ ፕሮግራም ማናጀር በመሆን ለስድስት ዓመት አካባቢ ስሠራ ቆየሁ። ውሎዬም አዳሬም ከጎዳና ልጆች ጋር ነበር። ብዙዎች እንደሚያስቡት የጎዳና ልጆች ጩቤ ይዘው የሚወጉ አይደሉም። እንደውም የጎዳና ልጆች ከሌላው ሰው በተሻለ መጠን በጎነት አላቸው።
እነዚህን ሰዎች በተሻለ መንገድ ለመርዳት ምን መሥራት አለብኝ ብዬ በማሰብ እኤአ በ2005 በአሜሪካም በሀገር ውስጥም ያሉ የሚያግዙኝ ሃሳቤን የሚረዱኝን፤ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ባለቤትን ጨምሮ ሌሎችም አግዘውኝ ራሳቸው ዶክተር ነጋሶም ሳይቀሩ በሃሳብ ደግፈውኝ ላይቭ አዲስን እ.አ.አ ግንቦት 2005 ላይ መሠረትኩኝ።
በተለይ በቤተሰብ መደገፍ ያልቻሉ፣ ትምህርታቸውን መጨረስ ያልቻሉ፣ ቤት ውስጥ ሆነው የሚቆዝሙና ማኅበረሰቡ ለማይቀበለው ሥራ የተጋለጡ ሴቶችን በማገዝ ቢያንስ ነገን ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች እንዲሆኑ አብረውኝ ካሉ ሰዎች ጋር እየሠራሁ ነው። ይህ ደመወዝ የምበላበት መደበኛ ሥራዬ ነው። 18ኛ ዓመታችንን እያከበርን ነው።
እኔ ያለፍኩት የሕይወት ውጣ ውረድ በልጅነቴ የአባቴ መታሰር፣ ውትድርና መግባቴ እና ሌሎችም ችግሮች ቢያጋጥሙኝም፤ ፈተናዎችን እንደዓለም ፍፃሜ አልቆጠርኳቸውም። አማራጮችን በማየት ከራስ አልፎ ሌሎችንም ማገዝ እንደሚቻል ጭምር በማሰብ ለብዙ ሰዎች መድረስ ችያለሁ። ከዚህ የተነሳ በሀገር ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍም ደረጃ እውቅና ማግኘት ችያለሁ ።
አዲስ ዘመን፡- ከድርጅት ሥራ ባሻገር በበዓል ሰሞን የሚሠሩት የርዳታ ሥራ አለ። የሚሠሩት ምን ምንድን ነው? የሚያከናውኑትስ በምን መልክ ነው?
አቶ ዓለማየሁ፡- በእኔ እናት ዕድሜ ያሉ ችግረኛ እናቶች ልጆቻቸው ቢኖሩ ኖሮ ነጠላ ይገዙላቸው እና ያስታምሟቸውም ነበር፤ ይሁንና እናት ወይም አያት ከመሆን አልፈው ቅድመ አያት መሆን የሚችሉ ሰዎች ያለማንም አጋዥ አልጋ ላይ ውለዋል። እነዚህን ሰዎች ማገዝ መርዳት እፈልጋለሁ። ሁሉንም መርዳት አይቻልም። እኔ ቤተሰብ የማስተዳድር ደመወዝተኛ ነኝ፤ ከቤተሰብ ጋር ተካፍሎ መብላት ብርቅ አይደለም። ቆንጥጠው መክረው ያሳደጉኝ ጎረቤቶች ቢያንስ ለበዓል በልተው ጠጥተው ተደስተው እንዲውሉ እፈልጋለሁ። ስለዚህ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ያሉ ወዳጆቼን በማስተባበር እስከ 102 ሺህ ብር ድረስ አሰባስባለሁ።
ለዘመን መለወጫ እንቁጣጣሽ፣ ለገና እና ለመውሊድ ወይም ለአረፋ በዓል ገንዘብ በማሰባሰብ ለተከታታይ 25 ዓመታት በፖስታ እያደረግኩ ለተቸገሩት ወገኖች በየቤታቸው እየሔድኩ እሰጣለሁ። በዚህ መልኩ በየበዓሉ የሚሰጣቸው ሰዎች ስም ዝርዝር አለ። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሲሞቱ፤ በእነርሱ ምትክ ሌሎች ሰዎች ይተካሉ።
አካባቢ ካሉ ልጆች ጋር በመነጋገር የባሰበት ያልተመዘገበ ይመዘገባል። ከዛም ለእያንዳንዱ ሰው አንድ ሺህ ብር ይሠጣል። ዋናው ጉዳይ አንድ ሺህ ብር መሰጠት እና አለመሰጠቱ አይደለም። ቀዳሚው ጉዳይ ሰዎቹ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ሲባሉ የሚሰማቸው ደስታ ነው። ‹‹ለካ እኛን የሚያስታውስ ሰው አለ። ›› ብለው ይደሰታሉ።
የምሰጠው ለርዳታው ካዋጡ ሰዎች ጋር በመሆን፤ በየቤቱ በመዞር ነው። ፌስቡክ በመጠቀም ርዳታ ከማሰባሰብ ውጪ ስጦታ ሲከናወን የፎቶም ሆነ የቪዲዮ ቀረፃ የለም ። የስጦታውን ጉዳይ በጎአድራጊዎቹ ስለሚያውቁ አንዱ አምስት ሺህ ሌላው አስር ሺህ እያለ ሁሉም የቻለውን ያዋጣል። ገንዘቡ ሲሞላ ሞልቷል በቃ፤ ለሰዎች ደርሷል ለማለት እና ለማመስገን በጽሑፍ መልዕክት አስተላልፋለሁ። ከዛ ውጪ የአንድም ተረጂ ሰው ፎቶ ለጥፌ ለጓደኞቼ አጋርቼ አላውቅም።
ሌላው ወሎ ሰፈር ፈርሷል። ሰዎች በለቅሶ ሳይቀር ሲገናኙ ተቃቅፈው ይሳሳማሉ፤ ይላቀሳሉ። ስለዚህ ማኅበረሰቡን ለማገናኘት ሞክሬያለሁ። ብዙ ሰው ያለው ቡልቡላ ነው። ከቡልቡላ ብቻ ሳይሆን ከሃያት እና ከካዛንቺስ ከሌላውም ሰፈር ወደ አንድ ሺህ ሰዎች ተሰብስበው ዳመራ በመሥራት እንዲገናኙ ማድረግ ችያለሁ።
ይህንን ያደረግኩት ብቻዬን ሳይሆን ሰዎችም አግዘውኝ ነበር። በዛው ተያይዞ አስር እናቶች እና 60 ሕፃናቶች ሙሉ የዓመት ወጪያቸው እንዲሸፈን እናደርግ ነበር። ለእናቶቹም ለበዓል በሬ በመግዛት ቅርጫ ቤታቸው በማድረስ፤ በተከታታይ ለሰባት ዓመት ከውጪ ሀገር ሳይቀር ሰውን ወደ አንድ የማምጣት የማሰባሰብ ሥራ ሠርተናል።
ብዙ ቤተሰቦች በበዓል እንዲታገዙ ማድረግ ችለናል። እናቶች ዳቦ ይዘው መጥተዋል። አሁን ያ አድጎ ትልቅ ማኅበር ተቋቁሟል። አሁን እኔ ንቁ ተሳታፊ አይደለሁም። ነገር ግን ሞተው ማልቅስ ሳይሆን ኖረው ሰዎችን ማገዝ የሚል ዕሳቤ በማምጣት በቅድሚያ እኔ መለስተኛ ድግስ በቤቴ አዘጋጅቼ ባስጀምረውም፤ አሁን አድጓል። ሰው ከራሱ በላይ አንድ ርምጃ ማሰብ አለበት። ሲሞት የሆነች አሻራ ትቶ መሔድ ይገባዋል። ሰዎችን ለማገዝ ብቻዬን አይደለሁም። ከነጭ እስከ ጥቁር ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ ከቤተሰብ ከጓደኛ ጀምሮ ብዙ ሰዎች አበረታተውኛል።
አዲስ ዘመን፡- ለትምህርትም ሆነ ለሥራ በተለያዩ አጋጣሚዎች አደጉ የሚባሉ ሀገሮች ሔደው ነበር። እንዴት በዛው ወደ ሌላ መስመር አላመሩም?
አቶ ዓለማየሁ፡- ከአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ወደ ኬንያ፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ማሊ፣ ዚምባብዌ እና ማላዊ ሄጃለሁ። ከአፍሪካ ስወጣ አሜሪካ፣ ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የተለያዩ ኮርሶችን ወስጃለሁ። ሜሪላንድ እና ዋሽንግተን ዲሲንም የማየት ዕድል አግኝቻለሁ። አንድም ቀን ከሀገሬ ወጥቼ ለመኖር አስቤ አላውቅም።
ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ቤልጂየም እና ሌሎች ሀገሮች ሔጃለሁ። የመቅረት ዕድል ነበረኝ። ነገር ግን ለገንዘብ ስል ስደተኛ ሆኜ ዝቅ ማለት አልፈልግም። ይሄ የግል እምነቴ ነው። እዚህ ‹‹አቶ›› የተባልኩ የተከበርኩ ሰው ነኝ። እዚህም ሆነ እዚያ ሰው የመሥራት ፍላጎት፣ አቅም እና ጉልበት እስካለው ድረስ መሥራት እና ገንዘብ ማግኘት ይችላል ብዬ አምናለሁ።
በእውነት ኢትዮጵያ ውስጥ ሠርቶ መለወጥ ይቻላል። ችግሩ ነገሮችን የምንረዳበት፣ የምናስብበት እና የሚደርሱን መረጃዎች የተዛቡ መሆናቸው ነው። በየሀገሩ ዞሬያለሁ፤ ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር ግን አላየሁም። ይህን ያልኩት አድልቼ አይደለም። ንፋሱ፣ ውሃው እና አየሩ ጥሩ ነው። ሰው ከነችግሩም ቢሆን ጥሩ ነው። በር ዘግቶ ከሰው ጋር ሳይገናኙ መኖር ለእኔ ከባድ ነው።
እንደሰው የእኔ የመጨረሻ ግቤ ምንድን ነው? ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ለሰው የሆነ በጎ ነገር አድርጎ ማለፍ እንጂ መጥፎ ነገር ተደርጎብኝ ማለፍ አልፈልግም። አንድ ሰው ዓላማ ካለው ምን እንደሚያደርግ ካወቀ ከሀገሩ የተሻለ ምቹ ቦታ የትም አያገኝም። በሀገሩ ያለው ዕድል ይሻለዋል ብዬ አምናለሁ። ወጣቶች በፍጹም አይሰደዱ እያልኩ አይደለም። ሰዎች ተሰደው ሃብት ሊያፈሩ፣ ገቢ ሊያገኙ እና ሊማሩ ይችላሉ። የእውቀት ሽግግርም ይፈጠራል። ስለዚህ ሰው ምክንያት እና ዓላማ ኖሮት፤ የት እንደሚሔድ እና እስከ መች እንደሚቆይ አውቆ አስቦ ተደራጅቶ መሔድ ይችላል። ነገር ግን በሕገወጥ መንገድ ስደተኛ ሆኖ እዛ መቅረትን አልደግፍም።
ሰዎች ነን፤ ሕይወት አጭር ናት። ይህንን ሕይወት በመባከን ማሳለፍ አይገባም። ወታደር ሆኜ ከሞት ተርፌያለሁ። የተተኮሰ ጥይት ጫማዬን ሰንጥቆ አልፏል፤ ተኩሻለሁ። ብዙ ነገር አሳልፌያለሁ። ስለዚህ በዚህ ምድር ላይ የትም ቦታ ቢሆን መኖር እንደሚቻል አምናለሁ። አዲሱ ትውልድ ለቴክኖሎጂ ቅርብ ነው። ብዙ ዕድልም አለው። ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ አላት። ሰባ በመቶ የሆነውን ወጣት በአግባቡ ብንጠቀምበት ሀገራችንን ብዙ ደረጃ ላይ ማድረስ እንችላለን።
ይህን ያህል ወጣት ባለበት ሀገር መራብ የለብንም። ግብርናው ላይ ወጣቱ እንዲሠማራ ዘርፉን ሳቢ ማድረግ አለብን። በቴክኖሎጂ መታገዝ አለበት። ከተለመደው በሬ ከመግፋት የተሻለ መሆን አለበት። ግብርና ላይ በዘመነ መልኩ ከተሠራ ወጣቶች ሠርተው የማያተርፉበት እና ሀገር የማታድግበት ምክንያት አይኖርም። እኛ ያልነው ብቻ ካልሆነ ከማለት ወጥተን ተባብረን እና ተስማምተን ከሠራን ስደት አያስፈልግም።
አዲስ ዘመን፡- በውትድርናው ዘርፍ የሀገር ዳር ድንበርን በማስጠበቅ ሂደት የቅርብ ጓደኛ ሕይወት ሲያልፍ የሚታይበት፤ አንዳንዴም በሕይወት ላይ ተስፋ መቁረጥ የሚስተዋልበት ነው። ያም ሆኖ ብዙዎች ሕይወታቸው እስኪያልፍ ውትድርናን የሙጥኝ ይላሉ። በሌላ በኩል እጅግ ጥቂት ሰዎች ውትድርናን ትተው ወደ ሌላ ሥራ ይሠማራሉ። እርስዎ እንዴት ከውትድርና ወጡ?
አቶ ዓለማየሁ፡- የአንድ ሀገር ወታደር መሆን መባረክ ነው። ሁሉም ሙያዎች የየራሳቸው ቦታ እና ክብር አላቸው። ክብራቸው በሚሰጡት ክፍያ ልክ ነው። በውትድርና ሀገርን ማገልገል የሚያስከፍለው ዋጋ ላብ ብቻ አይደለም። የሚያስከፍለው ዋጋ ሕይወትን እስከማጣት ድረስ ነው። ማሽን ላይ መሥራት ግፋ ቢል እጅ ያስቆርጣል። ውትድርና ግን ሀገር እና ሕዝብ እየጠበቁ ራስን መግደል ነው። ከዛ ውጪ ያለው በሙሉ ቀላል ነው። ረሃብና ጥማትም ሆነ ምንም ነገር፤ ለመሞት ራስን ከማዘጋጀት በላይ አይከብዱም። በሕይወት ዘመን ከባዱ ነገር ራስን ለሞት አሳልፎ መስጠት ነው። ስለዚህ ለወታደር ትልቅ ክብር እና ምስጋና ይገባል።
ወታደር የሆነ ሰው ሹፌር መሆን ይችላል፤ አገር ማስተዳደርን ጨምሮ በየትኛውም የሥራ እና የኃላፊነት ዘርፍ ላይ ማገልገል ይችላል። ብዙ ሰው ውትድርናን ከመግደል እና ከመሞት ጋር ብቻ ያስተሳስረዋል። ነገር ግን ውትድርና ይህ ብቻ አይደለም። በተለያየ ሙያ ከምርጥ ሥነምግባር ጋር የተገራ ዘርፍ ነው። ሙዚቀኛ፣ ጋዜጠኛ፣ ኢንጂነር፣ ዶክተር እና የተለያዩ ሙያዎች ወታደር ቤት አሉ። ነገር ግን ውትድርናን የምናስረዳበት መንገድ ከመግደል እና ከመሞት ጋር የተገናኘ ነው።
በእርግጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ውትድርና ከዚሁ ጋር የተሳሰረ መሆኑ አያስገርምም፤ ምክንያቱም ሕይወታችን ከጦርነት ጋር የተገናኘ ነው። ዘፈኖቻችን ‹ያዘው፤ በለው› ያሚሉ ናቸው። በተመሳሳይ መልኩ ውትድርናም በዚሁ መልክ ይታሰባል። ነገር ግን እዛ የሚገኘው ዕውቀት፣ ማኅበራዊ ትስስሩ፣ ከሰዎች ጋር ያለው መግባባት በየትኛውም ኮሌጅ ለመማር የሚቻል አይደለም። በትምህርት ከላይ ከላይ የሚገኝ እውቀት የትም ይኖራል፤ ነገር ግን ጥልቅ እና ከራስ ጋር የሚዋሓድ እውቀት የሚገኘው በውትድርና ቤት ነው። የውትድርና ቤት ተግባብቶ ከሰው ጋር መኖር፤ አንዱ ሌላውን ጌታዬ እና ወንድሜ እያለ የሚኖርበት ነው። ስለዚህ ወታደር ቤት የኖረ ሰው ወደ ተራው ሕዝብ ሲቀላቀል ምንም የሚከብድ ነገር አይኖረውም።
እኔ ውትድርና ሥር መቆየቴ አግዞኛል እንጂ የጎዳኝ ነገር የለም። እንደውም የሕይወቴ መሠረት የተገኘው ከወታደርና ቤት ነው። ውትድርና ቀርቶ ሰላም ባለበት በጥበቃነት መቀጠር በጣም ተራ ነገር ነው። ዓይን ሳይከደን ለስድስት ሰዓት ያለዕረፍት መሳሪያ ይዞ ከመቆም ተላቆ እየበሉ እየጠጡ አልጋ ላይ እያረፉ መጠበቅ እጅግ ተራ ነገር ነው። እዚህ ወተት እየጠጡ የፈለጉትን እየበሉ መሥራት ሲሆን፤ እዛ ኮቾሮ እየበሉ መኖር ነው። የትኛውም የሥራ ዘርፍ ከውትድርና ጋር ሲነፃፀር ለእኔ ተራ ነው።
ውትድርና ከመሞት እና ከመግደል ውጪ ባለው ሁኔታ እያንዳንዱ ሰው በዛ ሕይወት ቢያልፍ መልካም ነው። ሁለት እና ሦስት ዓመት ግዳጅ ቢኖር እና ሥልጠና ቢሠጥ በተለይ ወጣቱን በአግባቡ መጠቀም ይቻል ነበር። ወታደር ቤት መኖር በእድሜ ልክ የማይገኝ ዕውቀት ያስገኛል። በውትድርና ወንድም ወንድሙን የሚገድልበት ሳይሆን፤ ኢትዮጵያን ከሌላ ጠላት ከመጠበቅ አንፃር ሲታይ ስሜቱ ቀላል አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የሚመሩት መንግሥታዊ ያልሆነ የበጎ አድራት ድርጅት ሀገር በቀል ነው። በኢትዮጵያ ያሉት ብዙ የርዳታ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ናቸው። ገቢያቸው እና መነሻቸው ሌላኛው ዓለም ነው። ይህ እርስዎ የሚመሩት ላይቭ አዲስ ለምን እና እንዴት አገር በቀል ሆነ?
አቶ ዓለማየሁ፡– እኔ የማምነው በትክክል ችግር የሚቀረፈው ”የሀገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ” በሚለው አባባል ነው። ብዙ ከመንግሥት ጋርም የሚሠሩ የተባበሩት መንግሥታት ኮፍያ ያላቸው ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አሉ። ዓለም አቀፍ ተብለው የውጪ ድርጅት የሆኑ የማኅበረሰብ ልማት ላይ የሚሠሩ አሉ። እነርሱ በአብዛኛው የሚሠሩት ሥራ ስለሆነባቸው ነው።
ሀገር በቀሎቹ ባሕሉን ወጉን መሠረት አድርገን በአግባቡ ሕዝቡን ተረድተን እንሠራለን። ንግግሩ ቋንቋው የጎኑም የፊት ለፊቱም ይገባናል። ሀገር በቀሎቹ ስንሠራ የምናስበው ለራሳችን እናት፣ እህት ወይም ወንድም እንደምንሠራ ነው። እኔ ከአንዲት እናት ጋር ቁጭ ብዬ ሳወራ እና አንድ ፈረንጅ ከአንዲት እናት ጋር ቁጭ ብሎ ሲያወራ የመረዳት ሁኔታውም ሆነ ስሜቱ ተመሳሳይ አይደለም። ገንዘብ ስላለ ለገንዘብ መሥራት እና በስሜት መሥራት ይለያያል።
ሀገር በቀል ሆኖ መሥራት ብዙ ችግሮች አሉበት፣ የበጀት፣ የባለሙያ … ወዘተ ችግር አለ። ነገር ግን እናቴ እኔን እና ዘጠኝ ወንድም እና እህቶቼን ያሳደገችው ጠላ እና ዳቦ እየሸጠች ነው። ድህነትን የእናቶችን ችግር ኖሬበት አውቀዋለሁ። ስለዚህ የተቸገሩ እናቶችን ሳይ የሚሰማኝ እናቴን እንደማገለግል ነው። ወጣት ሴቶችን ሳገለግል የሚሰማኝ እህቴን እንደማገለግል ነው። ቅርንጫፉን አስፍቶ ሌሎችን ማገዝ ጥሩ ነው።
ነገር ግን ቅዱስ መፅሐፍም እንደሚለው ፅድቅ የሚጀምረው ከቤት ነው። እኔ ለ13 ዓመታት በዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ባልሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሠርቻለሁ። የማናጀር ደረጃ ላይ ደርሼ ከፍተኛ ተከፋይም ሆኜ ነበር። ነገር ግን ዋናው ነገር እሱ አይደለም። ፕሮጀክት ተጽፎ በጀት ከውጪ ተለምኖ እየመጣ የሀገሩ ጉዳይ በሌላ ሰው እየታዘዘ መሥራት እና በራስ ፕሮጀክት በመቅረጽ ከሰዎች ጋር መሥራት ትልቅ ነገር ነው።
አንዳንዴ ገንዘብ የማይፈልጉ ሥራዎች አሉ። ሁላችንም ስንፈጠር የተሰጠን እውቀት አለ። መንገድ ማሳየት ላይ በመሥራት ራሱ ብዙ ልጆችን ወደ ተሻለ ቦታ ማድረስ ይቻላል። በሀገር በቀል ድርጅት ተረድተው ትልልቅ ለውጥ ያመጡ፤ ቤተሰብ መሥርተው ልጆች አፍርተው ቤት የገዙ ሰዎችን ማየት ትልቅ ደስታን የሚፈጥር ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ዘንድ ሠርተዋል። አሁን ደግሞ ሀገር በቀል በሆነው ላይ ብዙ ጊዜዎትን አሳልፈዋል። ልዩነታቸው እና በዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ መታቀፉ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ምንድን ነው?
አቶ ዓለማየሁ፡- እውነት ለመናገር እነርሱም እንደሚሉት፤ ” There is no free lunch ” ማንም ካለምክንያት ለማንም ምንም አያደርግም። አንዳንድ ጊዜ ድርጅት ለድርጅት ያደርጋል ይባላል። ሰው ለሰውም በጎ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በእርግጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አራት ሺህ አካባቢ የእርዳታ ድርጅት በጣም ትንሽ ነው። ደቡብ አፍሪካ 62 ሺህ አካባቢ የበጎ አድራጎት ድርጅት አለ። አሜሪካ ከአንድ ሚሊየን በላይ የእርዳታ ድርጅት አለ። የእነርሱ እና የእኛ አሠራር ይለያያል። እኛ ስለልጅ ምግብ ስለእናት ጤና በአብዛኛው ከጤና ፣ ከምግብ እና ከትምህርት ጋር የተገናኙ ሥራዎችን እንሠራለን።
በእርግጥ የርዳታ ድርጅቶች አንዳንዴ የሌሎች ሀገሮች ፍላጎት ማስፈፀሚዎች ይሆናሉ። ነገር ግን በኢትዮጵያ ያለፈውም ሆነ የአሁኑ መንግሥት የሀገሪቱን ሕግ እና ባሕል ያልጠበቀ የትኛውም ዓለም አቀፍ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ የመሥራት መብት የለውም። በነገራችን ላይ እኛም ሕግ ጥሰን የመሥራት ፍላጎት የለንም። ምክንያቱም እኔ ያደግኩበት ባሕል፣ ወግ፣ እምነት እና አመለካከት እንዲሁም አስተሳሰብ አለ። ግፊቶች እና ጫናዎች አሉ። ነገር ግን አንቀበላቸውም።
ለምሳሌ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን እንድናበረታታ፣ ፆታ መቀየር እና ሌሎችም ከሀገሪቱ ባሕል እና ሕግ ውጪ እንድንሠራ የሚጠይቁበት ሁኔታ አለ። በእነዚህ ላይ መደገፍ እንደሚፈልጉ ይገልፃሉ። ነገር ግን እኛ የእውነት ሰዎች ነን። እነርሱ እንደፈለጋቸው ከሰብዓዊ መብት ጋር ሊያያይዙት እና ከሃይማኖት ጋር ማስተሳሰር ይፈልጋሉ። ነገር ግን የሀገራችን ሕግም አይፈቅድላቸውም።
እኔም እንደሰው በሠራሁባቸው ዘመናት አጋጥመውኛል። ነገር ግን ወደ ፊት የባሕል ወረራው ተፅዕኖ ቀላል ስለማይሆን አስቀድመን መንቃት እና ማወቅ አለብን። መንግሥት መሥራት ያለበትን መሥራት አለበት። መገናኛ ብዙኃንም በቻሉት አቅም ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው። ገንዘብ ያለው በውጪው ዓለም ነው። ሃብቱ እነርሱ ዘንድ ስላለ ፍላጎታቸውን መጫን ይፈልጋሉ። የእዚህ ምልክት አሁንም እየታየ ነው። ትንንሽ ነገሮች ይመጣሉ፤ በእኛ በኩል በፍፁም ፍቃደኛ አንሆንም። ሃብታቸውን ይዘው እዛው መቅረት ይችላሉ።
በጣም የሚያስደስተው ነገር፤ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት ባለሥልጣን አሠራሩ እና አደረጃጀቱ ተለውጦ በዚህ ላይ ይሠራል። እርሱን የሚያግዝ ደግሞ የኢትዮጵያ ሲቪል ሶሳይቲ ካውንስል አለ። ይህ ካውንስልም ተጨምሮ ሀገራዊ ስሜት ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው።
ርዳታውን አንፈልግም አንልም። ምክንያቱም እኛ ገንዘብ የለንም። ነገር ግን ርዳታው ከእጅ መጠምዘዝ ውጪ መሆን አለበት። መንግሥት ቢያበረታታ እና የሀገር ውስጥ ሃብትን ማንቀሳቀስ ቢቻል መንግሥት ዕድል ቢሰጥ ለምሳሌ በእኛ ድርጅት 100 ሺህ ብር አካባቢ ለቢሮ ኪራይ እንከፍላለን። የምንከፍለው ለእኛው አገር ሰው ነው፤ እንክፈል። ነገር ግን ይህ ገንዘብ በቀጥታ አገልግሎት ለምንሰጥበት ለበጎ አድራጎት ሥራ ቢውል መልካም ነበር። መንግሥት ቢደግፍ የተሻለ ይሆናል።
አንዳንድ ጊዜ የመንግሥት ተቋማት ያልተጠቀሙበትን ይህን ያህል በጀት ተመላሽ አደረጉ ወይም በጀት ተቃጠለ ሲባል እንሰማለን። ነገር ግን ይህ በጀት ወደ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ቢዘዋወር መንግሥት በማይደርስባቸው ቦታዎች እየደረሱ ሊሠሩ ይችላሉ። በዚህ እና በሌሎችም መሰል መንገዶች መጠቀም ከተቻለ እና ከመንግሥት ጋር መደጋገፉ ካለ የውጪውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠር ይቻላል።
በደንብ ካልተጠነቀቅን አንዳንድ ያደጉ ርዳታ ለመስጠት አቅሙ ያላቸው ሀገራት ባገኙት ትንሽ ቀዳዳ ሁሉ ፖለቲካችን ውስጥ ጣልቃ ለመግባት እና የባሕል ወረራ ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። ሀገር ማለት እናት ናት። ስለዚህ እናታችንን እንጠብቃት። እንዲህ አይነት ተግባር አይኖርም ማለት አይቻልም። አስበው በዓላማ የሚገቡ አሉ። በተቃራኒው ሳያስቡ የሚገቡ ያጋጥማሉ። ነገር ግን ጎልቶ የሚታይ ሕግን መጣስ እና ባሕልን የሚበርዝ ሃሳብን ማስተጋባት አልታየም። በግሌ ግን ወደ ፊት በእዚህ ላይ ስጋት አለኝ።
ነቅተን ቀድመን ካልተጠነቀቅን የሕፃናት እና የሰዎች መብት በሚል ሰበብ የሚታዩ እንቅስቃሴዎች ወደ እኛ ሀገርም ይመጣሉ። እንዳይመጡ መንግሥት የሚሠራው ሥራ እንዳለ ሆኖ እኛም ይህ ነገር ወደ እኛ አገር እንዳይመጣ ለጥሩ ነገር በተለይ ማኅበረሰቡን ለሚጠቅም ነገር መታገል ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ሀገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ውጤታማ እንዲሆኑ ከሕዝቡ ምን ይጠበቃል?
አቶ ዓለማየሁ፡- ወደዛ ወደዚህ መወርወሩ አያዋጣም። ሁሉም ማድረግ በሚችለው አቅም ይረዳዳ። መንግሥት ይህን አላደረገም፤ ወይም እናቴ ይህንን አላደረገችልኝም እየተባባሉ መካሰስ ውጤት የለውም። ጊዜያችንን የፈጀነው በዚህ መንገድ ነው። ዋናው ጉዳይ ሁሉም በአቅሙ ማድረግ የሚችለውን ያድርግ ።
ሁሉም እጁም አፉም ንጹሕ ሆኖ ይሥራ፤ ሥራችን ይመስክር። የወረዳው ኃላፊ በአግባቡ በቅርብ ከሠራ ተጠረቃቅሞ የሀገር እና የመንግሥት ሥራ ይሆናል። የሀገር ሥራ የመንግሥት ሥራ የሚባለው በአንድ ሰው የሚሠራ ሥራ ሳይሆን ተጠረቃቅሞ የሚሠራ ሥራ ነው። ማኅበረሰብ ስንል ለይተን አንድ አካል አንድ ግለሰብ ብለን ለማንለየው አካል ይህን ሥራ ይሥራ እንደማለት ነው። ማኅበረሰብ የተባለ ነገር ግን ተለይቶ የማይታወቅ ነው። ዋናው እያንዳንዱ ሰው ግዴታውን መወጣቱ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።
አቶ አለማየሁ፡- እኔም አክብራችሁ እንግዳ እንድሆን ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2015