“ለልማት ተነሺዎች የተከፈለው ካሳ ከዘጠኝ ዓመት በፊት የከተማዋ ዓመታዊ በጀቷ ነበር” ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ

የዛሬው የዘመን እንግዳችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ናቸው። ከከንቲባዋ ጋር ባደረግነው ቆይታ በአዲስ አበባ ከለውጡ ወዲህ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ እየተካሄደ ያለው ኮሪዶር ልማትና ከአገልግሎት አሳጣጥ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ተዳስሳዋል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባን ለስሟ እንድትመጥን ለማድረግ ከለውጡ ወዲህ በተጀመሩ የልማት ሥራዎች ምን አይነት ውጤቶች ተገኝተዋል?

ከንቲባ አዳነች፡- አዲስ አበባ በሁሉም መልክ እየተቀየረች ነው። ከሁሉ በላይ ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ከተማ ትሆን ዘንድ የተሠሩ ሥራዎች ጎልተው ይታያሉ። አረንጓዴ ልማት ልባሱን ስናየው 2010 ዓ.ም አካባቢ ስምንት በመቶ ነበር። አሁን ከ 20 በመቶ በላይ ደርሷል። ሠላሳ በመቶ ለማድረግ እየጣርን ነው ያለነው። ይሄ ማለት በሰው ጤና፣ በአጠቃላይ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል ከተሜነትም የሚለካበት አንዱ መስፈርት ነው፡፡

በሌላ በኩል የሚቀመጡት የሰው ተኮር ሥራዎቻችን ናቸው፤ ለሰው ልዩ ትኩረት ሰጥተን፤ ነዋሪዎቻችንን በማክበር አኗኗራቸውን ዝቅ ብሎ በማየት ደስታ እና ሀዘናቸውን በመካፈል ችግሮቻቸውን ለማቃለል በበርካታ ሥራዎች አጅበን የሠራንበት ነው። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች ሠርተን ለሕዝብ ማቅረብ ችለናል። በጥቅሉ በመቶ ሺዎች እንበል እንጂ በግል ዘርፍ የተሠራውን ስንጨምር ወደ 270 ሺ የሚደርሱ ቤቶች ተሠርተው ለነዋሪዎች መድረስ ችለዋል። ከዚህ ውስጥ ወደ 39 ሺ የሚሆኑት በየቦታው ቤቶች የወደቁባቸውና የተጎዱ ወገኖቻችን ናቸው።

የመጠጥ ውሃ ሽፋን ከነበረበት 60 በመቶ ከፍ ብሏል፤ የመንገድ ሽፋን እንዲሁም ደረጃውና ጥራቱ ቀድሞ ካለው በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሏል። ‘መንገድ ለመኪና ብቻ ሳይሆን ለሰው እና ለሞተር አልባ ትራንስፖርትም ብለን በዘመናዊ መንገድ መገንባት የጀመርንበትና ትልልቅ መንገዶችን የሠራንበት ወቅት ነው። ለምሳሌ የአቃቂ ቱሉዲምቱ የቃሊቲ ቂሊንጦ ከዚያ ደግሞ ወደ ቦሌ ካርጎ የሚመጣውን መንገድ በፍጥነት የሄድንበት ነው። መንገዱ ሲጠናቀቅ ከሌሎች በእርሱ ደረጃ ካሉ መንገዶች ጋር የተገናኘ አልነበረም። ስለዚህ የከተማ አስተዳደሩ ዋነኛ ሥራ አድርጎ የወሰደው እንደ አዲስ የገነባቸውን መሰረተ ልማቶችን ማገናኘትን እንዲሁም ነባር መሰረተ ልማቶችን አድሰን አስፍተናቸው ደረጃቸው ከአዳዲሶቹ ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ማድረግን ነው። ይህ ሥራ የትራፊክ ፍሰቱ የተሳለጠ እንዲሆን በማድረግ በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፤ የትራፊክ አደጋንም ይቀንሳል።

ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ታቅደው ተሠርተዋል። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካውያንም ዘንድ ኩራት ነው ብለን የምንኮራበት የዓድዋ መታሰቢያ እንኳን የተሠራው በለውጥ ዘመን ነው። በጥቅሉ የሠራናቸው ሥራዎች ትልልቅ የሥራ ዕድሎች በመፍጠር የከተማዋን ገቢ በስምንት እጥፍ ከፍ እንዲል አድርገዋል። በአንጻሩ በወጪ ደረጃ አዲስ አባባ 50 በመቶ እንኳን ለካፒታል ፕሮጀክት ለዘላቂ ልማት የማይውልባት ከተማ ነበረች። አሁን ቁጠባን መሰረት በማድረግ እስከ 71 በመቶ የከተማዋ ገቢ የሚውለው ለዘላቂ ልማት፣ ድህነትን ለመቀነስ፣ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለካፒታል ፕሮጀክት፣ ለሰፊው የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ሥትራቴጂዎችን ለመተግበርና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ሰፋ ያለ ድጎማ ለማቅረብ ነው።

የሕዝቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል የገበያ ማዕከላትና የእሁድ ገበያ መዳረሻዎች ገንብተናል። በለውጡ ዓመታት ወደ 700 የሚደርሱ አውቶብሶችን ለሕዝቡ ማቅረብ ችለናል። እነዚህ ለውጦች በሰው ሕይወት ላይ ለውጥ ያመጡበት ሕጻናት ቦርቀው በእኩልነት መንፈስ አዕምሯቸውና አካላቸው እየተመገበ በጥሩ ሥነልቦና፤ በሀገር መውደድ ስሜት የሚያድጉባት፤ የድሃውም የሀብታሙም ልጅ እኩል ዕድል የሚያገኙባት ከተማ እንድትሆን ማድረግ ችለናል።

ኢዲስ ዘመን፡- የከተማ አስተዳደሩ ባከናወናቸው ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ነዋሪዎች ምን ያህል ተጠቃሚ ሆነዋል ?

ከንቲባ አዳነች፡- ምንም ገቢ የሌላቸው በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ምግብ ለመብላት የሚቸገሩ፣ ከቆሻሻ ገንዳ አንስተው የሚበሉ ክብራችንን ጭምር የሚያዋርድ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የነበሩ ወደ 36 ሺ የከተማችን ነዋሪዎች በቀን አንድ ጊዜ እጃቸውን ታጥበው ትኩስ ምግብ መመገብ የቻሉበትን ፕሮግራም ፈጥረናል። ፕሮግራሙ ምግብ ብቻ ሳይሆን ፍቅርና ክብር ያገኙበት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የተማሪዎች ምገባ እናካሂዳለን። ይሄም ልጆችን በትኩረት የማስተማር ትውልድ ላይ ኢንቨስት የማድረግ ሰው ተኮር ፕሮግራማችን ነው። ልጆች በቀን ሁለት ጊዜ በየትምህርት ቤቱ ይመገባሉ፤ በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ላይ በምገባ ፕሮግራም ታቅፈው ያሉ ተማሪዎች ቁጥር አንድ ሚሊየን ይጠጋል። በተጨማሪም ዩኒፎርማቸውን ጨምሮ የትምህርት ቁሳቁሶች ወላጆች ላይ ጫና ሳይፈጠር መንግሥት ያቀርብላቸዋል።

አዲስ አበባ ብዙ እርጅና የተጫጫናት ከተማ እንደነበረች እናውቃለን። አሁንም ገና በተሟላ ሁኔታ ከእርጅናዋ አልወጣችም፤ ነገር ግን ከእርጅናዋ ለመውጣት እየሮጠች ነው። ይሄ የከተማችን እርጅና በከፍተኛ ደረጃ ጫና የሚያሳድረው ነዋሪው ላይ ነው። የወዳደቁ፣ የፈረሱ ቤቶች ሆነው በላስቲክና በቁርጥራጭ ቆርቆሮ ተጠግነው፣ ነዋሪዎች ፍሳሽ ማስወገጃ፣ መጸዳጃና ማብሰያ ስፍራ ሳይኖራቸው እጅግ በጣም አስቸጋሪና ለአደጋ አጋላጭ በሆነ ስፍራ ይኖሩ የነበረበትን ሁኔታ መቀየር ችለናል። እንደጠቀስኩት 39 ሺ ቤትን ወደ ዘመናዊ የመኖሪያ አካባቢና መኖሪያ ቤት በመቀየር ነዋሪዎቻችን ንጹህ አካባቢ እንዲሆን የተቻለበት ነው። ሰው ተኮር ስንል በሕይወት ላይም የሚያመጣው ለውጥ አለ።

የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱ የተበላሸ ቦታ ላይ መኖር ለብዙ ጤና ጠንቅ የሚዳረግ መሆኑን ፒያሳ ምስክር ነው። በአብዛኛው የፒያሳ ነዋሪዎች የአስም ተጠቂዎች እንደሆኑ መረጃችን ያሳያል። በሚሊየን የሚቆጠር ሰፋፊ የሥራ ዕድልም ፈጥረንበታል። በዚህ በፈጠርነው የሥራ እድል ውስጥ የሰው ሕይወት ነው የሚቀየረው። በሴፍቲኔት ብቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ገቢ አግኝተው፤ የራሳቸውን ሕይወት መምራትና በሥራ ዕድል ተጠቅመው ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገር ችለዋል። በአጠቃላይ ያለፉት ሰባት ዓመታት አዲስ አበባ ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ መታየት የጀመሩባቸው ዓመታት ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- የከተማ አስተዳደሩ ያጋጠሙት ፈተናዎች ምንድን ናቸው ?

ከንቲባ አዳነች፡- ያለፍንበት ዘመን የለውጥ ዘመን ስለሆነ ፈተና የበዛበት ነው። አንደኛው ከተማችን የፌዴራል መንግሥት መቀመጫ፣ የዲፕሎማት ማዕከልና የብዙ የውጭ ተቋማትና ዜጎች መቀመጫ እንደመሆኗ ሰላም በማስፈን ረገድ የነበረው ጫና ቀላል አልነበረም። ሁለተኛው ነገር ደግሞ የተደራረቡና የተወዘፉ በርካታ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የነበሩባት ከተማ ናት። ሕዝቡ ለውጥ ስለመጣ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት ይጠብቅ ነበር። የነበረው የሥራ ባሕል ደግሞ ጥያቄዎቹን በፍጥነት ለመመለስ የሚያስችል አልነበረም። በተለመደ መንገድ ሰዓት ቆጥሮ ገብቶ መውጣት እንጂ ‘በዚያ ሠዓት ውስጥ ምን ያህል ሥራ ሠራሁ?’ ብሎ መለካት እና መመዘን ብዙ ያልተለመደ ባሕል ነው። ፕሮጀክቶችን በተቀመጠው የሥራ መርሃ ግብር እና ወቅት መጨረስ ፈተና እንደነበረ በሚገባ አይተነዋል።

ሌብነት ልምምድ ሆኗል። ዕድሉ ከተገኘበት ሁሉ ስርቆት ይፈፀማል። በፕሮጀክት፣ በግዢ ሥርዓትና በጉቦ ‘የመንግሥት አይደል እንዴ ምን ያስጨንቅሃል!’ እየተባለ የሚዘረፍበት እሳቤ በጣም ያገነገነበት ነው። ዛሬም ቢሆን ያልተሻገርነው ተጨባጭ ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ እነዚህን በጥቅሉ ስናያቸው ፈተናዎች ናቸው።

የሕዝቡን ጥያቄ በፍጥነት ለመመለስ የሥራ ባሕል ብቻ ሳይሆን የበጀት አቅም የሚጠይቅ ነበር። የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ፈጥነን መሥራት እንፈልጋለን ይሁንና ከለውጡ ወዲህ ስንጀምር የፌዴራል መንግሥትም ካዝና የኢኮኖሚ መናጋት የነበረበት ነው፤ ከተማችንም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ነበረች። አዲስ አበባ በእርግጥ በራሷ በጀት የምትተዳደር ከተማ ብትሆንም ብዙ መሰረቶቿ በዚያ መንገድ የተገነቡ አይደሉም።

ሌላኛው ቀላል የማይባለው ፈተና ዘመኑ ድህረ እውነት ላይ የሚገኝ ከመሆኑ አንጻር በርካታ እውነቶችን ውሸት፤ በርካታ ውሸቶችን ደግሞ እውነት አስመስሎ በማቅረብ በከፍተኛ ደረጃ ሕዝቡ የትኛው ነው ትክክል ብሎ ለመለየት በሚቸገርበት መልኩ መረጃዎች ወደ ሕዝብ የሚወርዱበት ወቅት ላይ ነን። ማኅበራዊ ሚዲያና የተለያዩ የመረጃ አውታሮች በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዴሞክራሲ ሥርዓትን የመገንባት ልምምዳችን፤ የፖለቲካ ሥርዓታችን ከነበረበት እስራት እንዲፈታና ለቀቅ ባለ ሁኔታ ሰው ዴሞክራሲያዊ መብቱን ይለማመድ ሲባል ገደብ የሌለበት አድርጎ መረዳት ይታያል። ብዙ ከባሕላችን፣ ከማኅበራዊ መስተጋብራችንና ትስስራችን ጋር አብረው ሊሄዱ የማይችሉ ልቅ የሆኑ ነገሮች ሲያጋጥሙ ነበር። የሕዝቡን አብሮነትና በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት በሚሸረሽሩ ቀላል በማይባሉ ፈተናዎች ውስጥ አልፈናል።

አዲስ ዘመን፡- ከሙስና እና ከአሠራር ብልሹነት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ የከተማ አስተዳደሩ የደረሰበትን ደረጃ እንዴት ይገልጹታል ?

ከንቲባ አዳነች፡- መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎች ጥሩ ውጤት እያመጡ ናቸው። አንዱ ቴክኖሎጂ ነው፤ ከሰው ንክኪ ነጻ ማድረግ በሌላ መልኩ ደግሞ የሚሠሩ ጥፋቶችን መድረስ፣ መለየት፣ ማረምና ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ የምንችልብት ነው። ከዚህ ቀደም ተቸግረን የነበረው ድርጊቱ እንዳለ ብዙ ሰው እየተናገረና እየታወቀ ይሁንና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ መሄድ የሚያስችል የተጨበጠ ነገር ማግኘት ባለመቻሉ ድክመቶች ያጋጥሙናል። ቴክኖሎጂ ይህንን ነገር በማገዝ በኩል ትልቅ ሚና አለው።

ሁለተኛ የሰው ኃይላችንን ለመለወጥ በምናደርገው ጥረት በከተማችን ለሠራተኞች ፈተና ሰጥተን ሥራና ሠራተኛ እንዲገናኙ አድርገናል። ፈተናው ብዙ ጉድ ነው የነገረን። ሰው የተመደበበትን የሥራ መደብ የሥራ መዘርዝር አያውቀውም። ለራሱ የማያውቀውን እንዴት ለሌላ ያገለግላል፤ የብቃት ችግር አለ ማለት ነው። ለሥራ የሚገባው ባለሙያ በተገቢው ቦታ ላይ እንዲሆን በማድረግ በኩል የሰው ኃይላችንን ለማብቃት በስልጠና እና በሥራ ላይ ግብረ-መልሶች ለውጦች እያመጣን ነው።

ሦስተኛው አዲስ የተማሩ ወጣት ልጆችን ወደ ቢሮክራሲው ማስገባት ነው። እነርሱ ላይ የሚሠራው ግንባታ ቀለል እንደሚል ታሳቢ ይደረጋል። በርካታ ሀገሮች በዚህ መንገድ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። ሌላው በየመሥሪያ ቤቱ ለሥራ የሚያስፈልገው ግብዓት ማሟላት መቻል አለበት። ሠራተኛውን መውቀስ ብቻ ሳይሆን ሠራተኛው የሚያስፈልገው የሥራ ግብዓት አለው? ሞራሉን ለመጠበቅ ጥረት እናደርጋለን? የተወሰኑ ሠራተኞች በሚሠሩት ስህተትስ ሁሉም ይወቀሳል? የሚሉት ጥያቄዎች መታየት የሚገባቸው ናቸው፡፡

እነዚህን ጨማምረን ለውጦቹን ፈጠን ለማድረግ እየሞከርን ነው። አዲስ አበባ ላይ በርካታ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራዎች ተሠርተዋል። ሠራተኛውን ለመገንባት ጥረቶች ተደርገዋል። ወደ 16 ተቋማት ጥብቅ የሪፎርም ሥራ ውስጥ ገብተዋል። በእነዚህ ተቋማቶች ላይ የሥራ ውጤት አግኝተናል። ወደ 187 የሚሆኑ አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ ተደርገዋል። የመሶብ ፕሮጀክት በፌዴራል ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ተመርቆ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጀምሯል። ቀጥሎ አዲስ አበባን ነው የምትጠብቁት፤ ዝግጅት እያደረገች ነው የምትገኘው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከተማዋ በስፋት እያካሄደች የምትገኘው የኮሪዶር ልማት ዓላማ ምንድን ነው?

ከንቲባ አዳነች፡- የከተማ መሰረተ ልማት ሥርዓት ማጣት ይስተዋላል። ከተማን ከተማ የሚያሰኙት የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓታችንን፣ የመብራት፣ የውሃ እና የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች በተስተካከለ መንገድ መዘርጋት ነው። መዋቅራዊ ፕላን የምንለው አንዱ የሚገልጸው ዋና ጉዳይም ይሄ ነው። ሌላው ዓላማ ከተማችንን አረንጓዴ ማልበስ ነው። ከተማችን ቀስ በቀስ መተንፈሻ እያጣች ነበረ። ዙሪያዋን ከበዋት ከሚገኙት ደኖች በስተቀር ውስጥ ላይ እየታፈነች ግንባታ ብቻ እየተካሄደባት ግራጫ መልክ እየተላበሰች መጥታ ነበረ።

ዓለም አቀፍ ሕግም ሳይንስም የከተማ መሬት 30 በመቶ አረንጓዴ መልበስ አለበት ነው የሚሉት። እኛ ግን 2 ነጥብ 8 ላይ ነበርን። ይሄም ቁጥር ራሱ እየተመናመነ የነበረበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ከተማ ላይ ሰዎች ተገናኝተው የሚወያዩባቸው መናፈሻዎችና ማኅበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር ተገናኝተው የሚነጋገሩባቸው ቦታዎች ያስፈልጋሉ። እንዲህ ያሉት ቦታዎች ደግሞ ሳቢ መሆን መቻል አለባቸው።

ከሁሉ በላይ ደግሞ የሕጻናት መጫወቻ ቦታዎች ያስፈልጋሉ። እውነቱን ለመናገር ከተማችን ለሕጻናት ምቹ አልነበረችም። የአዲስ አበባ ልጆች ከመኪና ጋር አባሮሽ የሚጫወቱ ናቸው። የሚጫወቱበት ኳስ መኪና ስር ሲገባባቸው ለማውጣት ሲሞክሩ አደጋ ሲደርስባቸውና ሲኮረኮሙ እናያለን። እሁድ ቀን ነው ትንሽ መንገድ ከፈት ሲል የሚጫወቱት። በኮሪደር ልማቱ አንዱ ለማስፋፋት የሞከርነው የልጆች መጫወቻና የስፖርት ማዘወተሪያ ሥፍራዎችን ነው። የኮሪዶር ልማቱ በጥቅሉ ከተማችንን ከቆሻሻ በማጽዳት ውብና ፅዱ ያደርጋታል።

አዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን አስተዋጽኦ አለው። ቱሪስቶች ፊታቸውን እንዲመልሱ በማድረግ የምትጎበኝ ከተማ ያደርጋታል። ወደ ውጪ እየተመለከትን ሁልጊዜ የሌሎችን ከማድነቅ ወጥተን ሀገርን የመውደድና በሀገር የመኩራት ስሜት በቀጣዩ ትውልድ በደምብ እየጎለበተ በተጨባጭ ሥራ እየተደገፈ እንዲሄድ ማድረግ የሚያስችል ነው። ሰፊ የስር እድል በመፍጠርም የከተማዋ ገቢ እንዲጨምር ያደርጋል። ከኮሪዶር ልማት ዓላማና ትሩፋት ጋር አያይዘን ልናነሳ የምንችላቸው ነገሮች እነዚህ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለኮሪዶር ልማት ተነሺዎች ተገቢ ካሳ አልተሰጣቸውም በሚል የሚነሳ ቅሬታ አለ። የከተማ አስተዳደሩ ምላሽ ምንድን ነው?

ከንቲባ አዳነች፡- እኛ የምንሠራው ለሰው ነው። ከተማውን የምንገነባው፣ የምናፀዳውና የምናሳምረው ለሰው ነው። ካሳን በተቻለ መጠን ፍትሃዊ እንዲሆን ነው ያደረግነው። ለኮሪዶር ልማት ስንነሳ ሰፋ ያለ እንቅስቀሴ እንደሚኖረን ታሳቢ በማድረግ የምንሰጠው ካሳ ቤት የሚሠራ መሆኑን በተመለከተ ጥናት አድርገናል። የካሳ መጠንን ቀይረን አሻሽለን ከፍ አድርገናል። እንደየ ግለሰቡ ፍላጎት በጣም በቂ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ካሳ የሚገባው ባለመብት የሆነ አንድም ሰው ካሳ ሳይሰጠው ተነስቶ ከሆነ ኃላፊነቱን እንወስዳለን። መረጃው ካለ ወደ እኛ እንዲመጣ እንጋብዛለን፡፡

ከፍ ያለ በጀት የሚጠይቁን የካሳ ክፍያዎች ሲያጋጥሙን ተወያይተን ይህን ያህል ጊዜ ልጠብቃችሁ እችላለሁ ብለው መተማመኛቸውን ወስደው እየተዋዋልን ባልነው ጊዜ እየሰጠናቸው ነው። አሁንም በሂደት ላይ ያሉ እንዳሉ አውቃለሁ። መሬቱንና ቤት የሚከራይበትን ገንዘብ አስረክበናቸዋል። እነዚህ ካሳ እንደተሰጣቸውና መብታቸው እንደተጠበቀላቸው ነው የሚቆጠሩት።

አዲስ አበባ ለኮሪዶር ልማት ተነሺዎች 20 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካሳ ከፍላለች። ከተማዋ በ2017 ዓ.ም. የከፈለችው ካሳ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ዓመታዊ በጀቷ የነበረ ነው። ስለዚህ ካሳ በሚገባ እንከፍላለን።

የአቤቱታ መስሚያ ቅሬታ ማቅረቢያ ዴስክ አቋቁመናል። የአንድ ምክትል ከንቲባ ጽህፈት ቤት ዘርፍ ይህንን ጉዳይ ብቻ እንዲመለከት አድርገናል። ረቡና ዓርብ ብትመጡ ሙሉ ቀን የሚመለከታቸው ሰዎች ትልቁ አዳራሽ ቁጭ ብለው የልማት ተነሺዎች ጉዳያቸውን ሲያሰሙ ትመለከታላችሁ። በየትኛውም ዓለም የሚሠራ ሥራ ፍፁም ሊሆን አይችልም። ሰው የሚሠራው ነገር ፍፁም አይሆንም። ስህተቶች ሲኖሩ ክፍተቶችን ስናገኝ እናስተካክላለን። በኮሪደር ልማት ሂደት ውስጥ በርከታ አመራሮቻችንን ተጠያቂ አድርገናል። እንቅልፋችንን ትተን በየጎዳናው ላይ ሌሊት የምንዞረውና ጸሐይና ዝናብ የሚፈራረቅብን ሀገራችንን ለመገንባት፣ ለማበልፀግና ዛሬን እየኖርን ነገን የተሻለ ለማድረግ ነው።

ይህንን ስናደርግ ሰው እንዲጎዳ አንፈልግም፤ ጊዜያዊ እንግልቶች ግን አሉ፤ እሱን ደግሞ ካልተቋቋሙን ባለንበት መሄድ ብቻ ሳይሆን ካለንበት መውረድም ይመጣል። ነዋሪዎቻችን አንድ የተሻለ ነገር ለማምጣት ጊዜያዊ እንግልቶችና ችግሮች ሲኖሩ ጨከን ብለው ማለፍ ይኖርባቸዋል። በርካታ ሀገራት ራሳቸውን የገነቡት በዚህ መንገድ ነው። ድንገት የተገነባ ሀገር የለም። ለምሳሌ ሕንጻቸውን ለማደስና በማስፋፊያ ሥራ ምክንያት የንግድ ሥራቸው ለጊዜው የሚቆምባቸው ሰዎች አሉ። ልማቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ጸድቶ አምሮ ሲመለስ ገቢያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ሲሻሻል አይተናል። እንደነዚህ አይነት ውጣ ውረዶችን እየታገስን በመጨረሻ ጣፋጭ ውጤት እንዳለ እያሰብን እየበረታን የምንሠራው ሥራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኮሪዶር ልማት ተነሺዎቹ የት ደረሱ ? በገቡባቸው አካባቢዎችስ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውላቸዋል?

ከንቲባ አዳነች፡- የልማት ተነሺዎቹ የት ደረሱ ለሚለው አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሲ.አር.ዲ.ኤ አካባቢ በሚገኙ በተገጣጣሚ የሕንጻ አካላት በተሠሩ ቤቶችና ገላን ጉራ፣ ልደታ ቤተክርስቲያን አካባቢ በተሠሩ ሰባት ሕንጻዎች፣ ጉለሌ እንጦጦ ጫፍ ላይ በተቀናጀ ልማት የተሠራ ብዙዎች የገቡበት በጣም የሚያምር መንደር ሆኗል። አራብሳ ለሚኩራ አካባቢ የተገነቡ 15 ሕንጻዎች እንዲሁም የካ ፈረንሳይና አየር ጤና አካባቢ በተገነቡ ሕንጻዎች ላይ ከተለያየ ቦታ ሳይሆን ማኅበራዊ መሰረታቸው ሳይናጋና ሳይበጣጠስ ዕድራቸውንና እቁባቸውን ይዘው እንዲገቡ ነው የተደረገው።

ነዋሪዎች እውነቱን ይናገራሉ። ሰው ከሆነ አካባቢ ተነስቶ ሌላ ቦታ ሲሄድ መቼም ለጊዜው እንደነበረበት ሰፈር አይሆንለትም። ነገር ግን ከጉርብትናውና ከአደረጃጀቶቹ ካልተለየ ንፁህ አካባቢና መኖሪያ ይገባዋል። ይሄ መሰረታዊ ከሚባሉት የሰው ልጅ ፍላጎቶች አንዱ ነው። ተነሺዎቹ በፊት በሚኖሩበት አካባቢ ያልነበራቸውን በርካታ መሰረተ ልማቶች ነው ያገኙት። እነዚህ ሳይቶች ላይ ስፖርት ማዘውተሪያ የሕጻናት መጫወቻ ቦታዎች አሏቸው። የልደታ፣ የለሚ ኩራ፣ የገላን ጉራና የጉለሌ ሳይቶችን ስናያቸው የእንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካ ጭምር አላቸው።

በሚሰፍሩበት አካባቢ የሚገኙ ነባሮቹ ትምህርት ቤቶች በቂ ከሆኑ እዚያ እንዲማሩ ይደረጋል። እንደ ገላን ጉራ አይነት በርከት ያሉ ተነሺዎች የሚሰፍሩበት አካባቢ ሲሆን ከሕጻናት መዋያ ኬጂ ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ለትራንስፖርት ወጪ ሳይዳረጉ እዚያው ደጃቸው ላይ በተቀናጀ መንገድ ተገንብቶላቸዋል። የአውቶቡስ ማቆሚያ ደጃቸው ላይ ተሰርቶላቸዋል። ማኅበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት በጋራ የሚገናኙባቸውና የሚወያዩበት ቦታ ሁሉ ነው የተዘጋጀላቸው። ቀድመው ከነበሩበት ከተጨናነቀ ለአፍንጫ ጭምር የማይመች አካባቢ አንፃር አየሩም ራሱ ምግብ ነው።

ሰፊ የሥራ ዕድልም ፈጥረንላቸዋል። በሔዱበት ሁሉ ፋርማሲዎች እና ሸማቾችን የመሳሰሉ አገልግሎት አቅራቢዎች በየበራቸው ነው ያሉት። በተጨማሪ ግን ትናንት ይነግዱ የነበሩ ለዛው ማኅበረሰብ የሚሸጡ ስለሆኑ እዚያው አካባቢ ሱቅ እንዲኖራቸው ተደርጓል። ተሰማርተውበት የነበረው የንግድ አይነት እየታየ መሃል ከተማ ላይ የመሥሪያ ቦታ እንዲያገኙ አድርገናል። በሁለተኛው ኮሪደር ልማት ሼድ ብቻ 1 ሺ 444 ያህል አቅርበናል። ከአንደኛው ኮሪደር ጋር በድምሩ ሁለት ሺ 300 ሼዶችን ለተነሺዎች ማቅረብ ችለናል። በሁለተኛው ኮሪደር ከአንደኛው ኮሪደር ተምረን በርከት ያሉ ሱቆችን ገንብተናል።

አዲስ ዘመን፡- ለቅርሶች ተገቢውን ጥበቃ ከማድረግ አንጻር የኮሪዶር ልማቱ እንዴት ይታያል?

ከንቲባ አዳነች፡- የኮሪዶር ልማቱ ቅርሶችን በደምብ አስተዋውቋል። የት ቦታ? ምን አይነት ቅርስ አለ? የሚለውን ጭምር ለብዙዎቻችን ያስተዋወቀ ነው። ብዙ ሰዎች በተለምዶ ስማቸው የሚነሳውን ቅርሶች ነው የሚያውቁት። ይሁንና በበርካታ ቦታዎች ላይ የቅርስን መስፈርት የሚያሟሉ አቧራ ለብሰው ቅርስነታቸው ያልተነገረላቸው በኮሪደር ልማቱ ጥገና ከተደረገላቸው በኋላ እንዲተዋወቁ ተደርጎ ለቱሪስት መስዕብ ክፍት ሆነዋል።

ለዚህ ፒያሳ ትልቅ ምስስክር ነው። የመጀመሪያው ሆቴል፣ የመጀመሪያ ሲኒማ ቤት፣ የመጀመሪያው ቲያትር ቤት፣ የመጀመሪያው ፖስታ ቤት እንዲሁም የሀገር ባለውለታ ለሆኑት አጼ ምኒሊክ፣ አቡነ ጴጥሮስ፣ አጼ ቴዎድሮስና ራስ መኮንን የተገነቡ የመታሰቢያ ሀውልቶች ይገኛሉ። በዚህ በለውጡ ዘመን ደግሞ መሀል ፒያሳ ላይ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየምን ገንብተናል።

አራት ኪሎ ያለው የድል ሀውልት እድሳት ተደርጎለት ፏፏቴ ታክሎበት ሲዋብ ነው ትውልዱ እየመጣ ላዩ ላይ የተጻፈውን ማንበብ የጀመረው። ስለዚህ የኮሪዶር ልማቱ ቅርስን ከተሸፈነበትና ከተደበቀበት በማውጣት አጉልቶ እንዲታይ እና ራሱን የቻለ ጥበቃ የሚያደርግለት የሥራ ክፍል ተፈጥሮለት እንዲጠበቅ ነው ያደረገው።

አዲስ ዘመን፡- በኮሪደር ልማቱ መሰረተ ልማት በመዘርጋት ረገድ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ምን ይመስላል?

ከንቲባ አዳነች፡- በኮሪደር ልማቱ አንዱ ልምድ የተገኘበት ጉዳይ የቅንጀት ሥራ ነው። ከዚህ በፊት መብራት ኃይል ቆፍሮ ሲጨርስ ኢትዮ ቴሌኮም ድግሞ መጥቶ ይቆፍራል። ከኢትዮ ቴሌኮም በኋላ ደግሞ መንገድ ግንባታ መጥቶ ያፈርሰዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ውሃና ፍሳሽ ሊመጣ ይችላል። እንዲህ አይነት ችግሮች አሳልፈናል። ይህ ማለት እንዲሁ ሥራዎች አልተቀናጁም በሚል ቋንቋ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፤ ሀብት ነው የሚባክነው። አንዱ የሌላውን ሥራ ሲያበላሽ አገልግሎት ስለሚቆራረጥ ማኅበረሰቡ ይጎዳል። ይህንን ችግር በቅንጅት መፍታት እንደሚቻል አምነን ኮሪደር አንድ ላይ ጀመርን። ኮሪደር ሁለት ላይ ደግሞ ከጥናትና ዕቅድ ጀምሮ በጋራ በመንቀሳቀስ በአንድ ቱቦ ውስጥ በርካታ መሰረተ ልማቶችን ማስተላለፍ የቻልንበትን ልምድ አግኝተናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኮሪደር ልማቱ የግሉ ዘርፍ ያደረገውን ተሳትፎ እንዴት ይገልጹታል?

ከንቲባ አዳነች፡- ሳይቶቹን ስንገነባ በርካታ ኮንትራክተሮች ሀገር ነው የምትለማው በሚል ማሽኖቻቸውን ከአንድ ሳምንት እስከ ሁለት ወር ያለምንም የኪራይ ክፍያ ሰጥተውናል። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ሥራዎች ደግሞ ስፖንሰር ተደርገው ተወስደው ነው የተሠሩት። ለምሳሌ ካዛንችስ የምናየው ትልቅ የእግር ኳስ ሜዳ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስና የልጆች መጫወቻ፣ ልብስ መቀየሪያ፣ መጸዳጃ ቤትና መታጠቢያ ክፍሎች የያዘ ኮምፕሌክስን ሙሉ በጀት የሸፈነው አንድ ባለሀብት ነው። በየቦታው የተሠሩትን የሕጻናት መጫወቻዎችንም እንዲሁ በጀት እየመደቡ የሠሩ ግለሰቦች አሉ። አንዳንዶቹ አንድ የሕጻናት መጫወቻን ወጪ ሙሉ ለሙሉ ወስደው ይሠራሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ እኛ መሬቱን ሥንሠራ መጫወቻዎቹን ገዝተው አምጥተው ይተክላሉ።

በወንዞች ዳርቻ ልማት በራሱ ወጪ እስከ አንድ ቢሊየን ብር የሚያወጣ ሥራን እየሠራ ያለ ባለሀብት አለ። ይሄ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ባለፈ ሀገሬ ናት የምትገነባው ብሎ ይህን ያህል በጀት መድቦ ልክ እንደ አንድ የሥራ ኃላፊ ራሱ ቆሞ እያሠራ ሳይቱ ላይ ታገኙታላችሁ። ስለዚህ የከተማችን ባለሀብቶች እንደሚችሉት የድርሻቸውን በማበርከት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ወጣቶች በጉልበታቸው፣ በሀሳባቸውና የአካባቢውን መሰረተ ልማት በመጠበቅ ጭምር የልማቱ ባለቤት መሆናቸውን አስመስክረዋል። ስለዚህ በብዙ መንገድ ነው የማኅበረሰቡ ባለድርሻነት የተረጋገጠው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ባለው ሂደት ከኮሪዶር ልማቱ ምን አይነት ተሞክሮዎች ተገኝተዋል?

ከንቲባ አዳነች፡- በኮሪዶር ልማቱ በሳምንት ለሰባት ቀናት 24 ሰዓታት በመሥራት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ታይቷል። በጋራ አመራር ሥራን ቆጥሮ ተከፋፍሎ በመምራት ውጤት ማምጣት የተመዘገበበትም ነው። ሦስተኛ በከተማችን ላይ ከመንገድ፣ ከፓርኪንግና ከተርሚናል ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን መሰረታዊ መሰረተ ልማት ሳንነካ መንገድ ዳር ተለጣጥፈው ያሉትን ብቻ በማንሳት መንገዶችን አስፍተን ደረጃቸውን የጠበቁ ማድረግ እንደሚቻል አረጋግጠናል። በተጨማሪም ከተማችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቆሻሻ ማፅዳት እንደሚቻል አሳይተናል። ከዚህ ቀደም የባሕል ለውጥ ስለሚፈልግ ረጅም ጊዜ ይፈጃል የሚባለው ትክክል አለመሆኑን ይልቁንም ቆርጠን እንደ አመራር ከዘመትን ማኅበረሰቡ እንደሚከተለን በመጀመሪያው ልማት ላይ አይተን የኮሪዶር በሁለተኛው አስፍተን የገባንበት።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

ከንቲባ አዳነች፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You