ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት…

(ከኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ ሙሉ ቃል)

ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ እንድታንሠራራ በበርካታ መስኮች ትኩረት ተሰጥቶ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። ከምንም በላይ ሰላምን ለማጽናት መንግሥት በአንድ እጁ የሰላም ጥሪ በማስተላለፍ ለሰላም ዝግጁ የሆኑ ታጣቂዎችን ከግማሽ መንገድ በላይ ሄዶ በመቀበል ወደ ማኅብረሰባቸው ተቀላቅለው ሰላማዊ ሕይወትን እንዲመሩ በማድረግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እስከመጨረሻው ለቀጠለው የሰላም ጥሪ ምላሽ የማይሰጡ ታጣቂዎችን በውጤታማ የሕግ ማስከበር ዘመቻዎች በማከናወን ሰላምን የማጽናት ሥራውን በከፍተኛ ውጤት እያከናወነ ይገኛል።

ከዚህም ባሻገር ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት ዋነኛው መንገድ ዘላቂ ልማት፣ ምርታማነት እና ሥራ ፈጠራን እያረጋገጡ መሄድ በመሆኑ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ፣ በርካታ ውጤቶችንም እያስመዘገበ ይገኛል። በተለይም የትኩረት መስክ ተብለው በተመረጡት የግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ኢኮኖሚ መስኮች ሰፋፊ ውጤቶች ተገኝተዋል።

  1. በግብርና ዘርፍ በ2017 ምርት ዘመን በተመለከተ

መንግሥት ኢኮኖሚያዊ እመርታ እንዲመጣ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው ተግባራት አንዱ ግብርና ነው። በዚህም የበጋና በልግ ወቅት የግብርና ሥራዎች፣ የስንዴ ምርታማነትን ማሳደግ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የግብዓት አቅርቦትና የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮች እና ሌሎችም በርካታ መርሐግብሮች በትግበራ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ በርካታ ሥራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል፦

የበጋና የበልግ የግብርና ሥራዎች አንጻር በ2017 ዓ.ም የምርት ዘመን መንግሥት የምግብ ሉዐላዊነትን ለማረጋጋጥ በትኩረት በሠራበት የበጋ መስኖ ስንዴ የተሻለ እመርታ አሳይቷል፤ በተለይ የውሃ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ስንዴን ከራስ አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል። በተያዘው በጀት ዓመት ለበጋ ስንዴ 4.2 ሚሊዮን ሄ/ር መሬት የለማ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 3.4 ሚሊዮን ሄ/ር መሬት በዘር በመሸፈን ከ 66 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል።

የበልግ አዝመራ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች 2.2 ሚሊዮን ሄ/ር መሬት በዘር መሸፈን የተቻለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 235 ሺህ ሄ/ር በክላስተር ኩታ-ገጠም/ የአስተራረስ ዘዴ የተሸፈነ መሬት ነው። ኩታ ገጠም እርሻ ለምርታማነትና ገበያ ትስስር የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ እና በልግ አምራች በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች በዚህ ዓመት የተሻለ የዝናብ ሁኔታ በመኖሩ ጥሩ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በመሆኑም በቀሪው የበልግ ወቅት የሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ልዩ ትኩረት መስጠትና መረባረብ ይጠይቃል። ባለፉት ወራት የነበረው የዝናብ መጠንና ስርጭት የበልግ የግብርና ሥራዎችን ለማከናወን፤ ተፋሰሶች በቂ ውሃ እንዲይዙ፤ ለአርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሻሻልና የእንስሳት መኖ አቅርቦትም እንዲኖር ከፍተኛ ፋይዳ ነበረው። በቀጣይም የበልግ ወቅት የመጨረሻ ወር የዝናብ ስርጭትን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። በተለይ የበልግ ወቅት የመጨረሻ ጊዜያት የዝናብ ስርጭት ሊዋዥቅና ሊለዋወጥ ስለሚችል የደረሰ ሰብልን ቀድሞ በመሰብሰብ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል። በሌላ መልኩ ይህ የአየር ጸባይ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ስለሚችል ማኅበረሰቡ አካባቢውን የማጽዳት እና የታቆሩ ውሃዎችን የማፋሰስ ተግባር ማከናወን ይጠበቅበታል።

የተፋሰስ ልማትን በተመለከተ

መንግሥት ከማኅብረሰብ አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች አንዱ የሆነው የተፋሰስ ሥራ የማኅብረሰብን ኑሮ ለማሻሻልና በግብርና ምርት ሥርዓቶች ላይ ለሚተገበሩ የሥነ ምሕዳር ሂደቶች (አግሮ ኢኮሎጂ) ውጤታማነት የሚኖረው አስተዋፅኦ የጎላ በመሆኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በመሥራት ምርትና ምርታማነትን መጨመር ተችሏል። ባለፉት ዓመታት በተሠሩ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ውጤቶቹ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ወስዶ ተግባሩን በመምራቱና ሕዝቡን በነቂስ በባለቤትነት በማሳተፉ የተገኙ ናቸው። በተቀናጀ ተፋሰስ እና የአፈር ጥበቃ ሥራ የተራቆቱ አካባቢዎች ወደ ነበሩበት ተመልሰዋል፣ ምርትና ምርታማነት ጨምሯል፣ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃዎች ጎልብተዋል፣ ተጨማሪ መሬት እንዲገኝና የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ማድረግ ተችሏል። ይህን ለማስቀጥል በዘንድሮ በጀት ዓመት እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ድረስ 5 ሚሊዮን ሄ/ር የሚሸፍን የተቀናጀ የተፋሰስ ሥራ ተከናውኗል። በዚህ የልማት ሥራ 21.4 ሚሊዮን ዜጎች በጉልበት የተሳተፉ ሲሆን ይህ በገንዘብ ሲተመን ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነው።

ከግብአት አቅርቦት አንጻር

የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና በምግብ እህል እራስን ለመቻል፣ የሀገሪቱን የግብርና ምርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ እና ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በቂ ምርት ማቅረብ እንዲቻል የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በተደራጀ ሁኔታ ማቅረብ፣ ማሰራጨትና መጠቀም ይገባል። ከዚህ አንጻር መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትንና የምርጥ ዘርን ስርጭት ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ ይገኛል።

የማዳበሪያ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ ዘንድሮ ለማዳበሪያ ግዥ ብቻ 1.3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር መድቧል። ለዘንድሮ የምርት ዘመን (2017/18) የሚገዛው የማዳበሪያ መጠን ካለፈው የምርት ዘመን የማዳበሪያ ግዥ ጋር ሲነጻጸር የ4.6 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ አለው። ለዘንድሮ የምርት ዘመን በማዳበሪያ ዋጋ ላይ የ84 ቢሊየን ብር ድጎማ ተደርጓል። ይህም በአንድ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መንግሥት ከ5ሺ ብር በላይ ድጎማ እንደሚያደርግ የሚያሳይ ነው። ለቀጣይ ምርት ዘመን እስካሁን 10.7 ሚሊዮን ተጓጉዞ ወደብ የደረሰ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 39 ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ ክልሎች በማሠራጨት ቀሪውንም በቀጣይ የማጓጓዙ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

ምርታማነትን ለማሳደግ ከማዳበሪያ በተጨማሪ የምርጥ ዘር አቅርቦት ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ ምርጥ ዘር ተሰብስቦ አራት መቶ ሺህ ኩንታል ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቷል።

  1. ማኑፋክቸሪንግ (የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን) በተመለከተ

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓላማ ለዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ሀገራዊ ሥርዓት በመዘርጋት አምራች ኢንዱስትሪው ለሀገር በቀሉ የኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬትና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ሚናውን እንዲወጣ ማስቻል ነው። ሀገራዊ ንቅናቄው ወደ ትግበራ በተሸጋገረ ማግስት ከፖሊሲና የሕግ ማሕቀፍ ማሻሻያ፣ ቅንጅታዊ አሠራርን ከማጠናከር እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶችን ከማሳደግ አንጻር አበረታች ውጤቶችን አምጥቷል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ከግምት ያስገባ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ጸድቆ ወደ ሥራ የገባ በመሆኑ በእስካሁኑ ከተኪ ምርቶች አንጻር 10.34 ቢሊዮን ዶላር መጠን ያለው ምርት ከውጭ ይገባ የነበረን ማስቀረት ተችሏል። በዚህ በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጻፀም ብቻ ከ3.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማዳን ተችሏል።

በአምራች ኢንዱስትሪው መስፋፋትና ምርታማነትን እንዲሁም ተወዳዳሪነትና የማምረት አቅም መጨመር ምክንያት ባለፉት ሦስት ዓመታት ገቢ ሸቀጥን በመተካት፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት፣ የሥራ እድል በመፍጠር እና በሌሎችም መልኮች ለኢኮኖሚው ያለው ድርሻ እያደገ ይገኛል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የብድርና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማሻሻል፣ የግብዓትና የገበያ ትስስር በመፍጠር እና ሌሎችም ጥረቶች በኮቪድ፣ በሰላም እጦትና በሌሎች ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን መልሶ በማንቃት፣ በተፈጠረው መነሳሳት፣ የተቀናጀ አሠራር እና የዘርፉን ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ መሻሻሎች በመምጣታቸው የአምራች ኢንዱስትሪው አማካይ የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 61.2 በመቶ ማድረስ ተችሏል። ይህ ከፍተኛ ስኬት ኢንዱስትሪው የተሰጠውን ትኩረትና የመጣውን ውጤት የሚያሳይ ነው።

አጠቃላይ የተግባርና የፖሊሲ ጥረቶቹን “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል ንቅናቄ በማስደገፍ በኢትዮጵያ ያለውን የአምራች ኢንዱስትሪ ዕምቅ ዐቅም በማሳየት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ዕድገት ለማስተዋወቅ፣ ለፖሊሲና አሠራር ማሻሻያነት እንደ ግብዓት የሚጠቅሙ ሀሳቦችን ለማሰባሰብ የሚያግዙ የውይይት መድረኮችን ለመፍጠርና በሀገር ውስጥ ምርትና አምራቾችን በማስተዋወቅ የሕብረተሰቡን በሀገር ምርት የመኩራት ባሕልን ለማሳደግ ተችሏል።

መድረኩ አምራች ኢንዱስትሪው ያለው እምቅ አቅም የታየበት፣ የዘርፉ ችግሮች በቅንጅት የመፍታት ጥረቶች የተቀናጁበት፣ ምርቶች የተዋወቁበትና በተመጣጣኝ ዋጋ የቀረቡበት፣ ሸማቹ በሀገር ውስጥ ምርት ያለውን አመኔታ የሚያሳድግባቸው የገበያ ትስስር አውድ ነበር። ከዓመት ወደ ዓመት በጥራት፣ በአይነት እና በመጠን በእጅጉ ያደጉ መሆናቸውን፣ ዜጎች የሀገራቸውን ምርት ለመጠቀም ፍላጎት እያሳደሩ መሆኑን፣ የዜጎች የፈጠራ እና ቴክኖሎጂን የመቅዳትና የማላመድ አቅም መሻሻሉን እና በአጠቃላይ ዘላቂ የተወዳዳሪነት አቅም እንዳለን አመላክቷል። በአጠቃላይ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚጠበቀው እመርታ እንዲመጣ በቀጣይነት የማምረት አቅማችንን ማሳደግ በአንድ በኩል፤ የሀገራችንን ምርት የመጠቀም ልማድ ደግሞ በሌላ በኩል ሊሰራበት ይገባል። ለዚህም በሀገራችን ምርቶች የመኩራት ባሕል እያደገ መምጣት ይኖርበታል።

  1. ከኮንፈረንስ ቱሪዝም አንጻር

ቱሪዝም እንደ አንድ የኢኮኖሚ ሴክተር ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ሥራ ሲገባ በዋነኝነት ሁለት ጉዳዮችን በልዩነት በመሥራት ነው። የመጀመሪያው ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማደስ እና አዳዲስ መደረሻዎችን በመገንባት ተመራጭነትን ማሳደግ ነው። በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጎንደር፣ ሶፍ ዑመር፣ ላሊበላ፣ አክሱም፣ ጂማ አባጂፋር እና ሐረር ጀጎል ቅርሶችን ለማደስ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ከዚህም ባሻገር አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስፋፋት በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ መርሀግብሮች በርካታ አዳዲስ የቱሪስት መስህቦች ተሠርተዋል።

ሁለተኛው በልዩ ትኩረት እየተሠራ ያለው የቱሪዝም ሴክተር ማስፋፋት ደግሞ በኮንፈረንስ ቱሪዝም መስክ እየተሠራ ያለው ሥራ እና እየተገኙ ያሉ ውጤቶች ናቸው። እንደሚታወቀው ሀገራችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሰለ ውጤታማና ወደ በርካታ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች የሚበር የአየር መንገድ ያላት ናት። በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ለማከናወን የሚያስችሉ በርካታ ማዕከላት በመዲናችን ይገኛሉ። በቅርቡ ተጠናቆ ወደ ሥራ የገባውን የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን ጨምሮ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም፣ የሳይንስ ሙዚየምና ሌሎችም አዲስና ነባር የስብሰባና የኤግዚቢሽን ማዕከላት ይገኛሉ። ይህንን ከሕዝባችን እንግዳ ተቀባይነትና መዲናችን እያሳየችው ካለችው ሁለንተናዊ እድገት ጋር በማቀናጀት መንግሥት የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።

በዚህም ባለፉት 10 ወራት ብቻ በአጠቃላይ 84 ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በተለያዩ ተቋማት አስተናጋጅነት ተከናውነዋል። በዚህም 30,340 የውጭ ዜጎች 171,739 ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል። ተሳታፊዎች ከኮንፈረንሱም ባሻገር ቆይታቸውን አራዝመው ሀገራችንን እንዲጎበኙ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ይህ የኮንፈረንሶች እንቅስቃሴ የሆቴልና አገልግሎት ዘርፉን በማነቃቃት፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና ሀገራችንን ለመላው ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

  1. በግንቦት ወር የሚከናወኑ ኮንፈረንሶችን በተመለከተ

በቅርቡ የተካሄደውን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያርጉ” (Invest in Ethiopia)፣ የቀጠናዊ ደህንነት ፎረም እና የሃይማኖት ጉባዔን ጨምሮ ስምንት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በመዲናችን ይከናወናሉ። ከእነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ናቸው።

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን (ETEX 2025)

ኤክስፖው ከግንቦት 8 እስከ 10 ቀን 2017 ዓ.ም የሚደረግ ሲሆን የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እና ስኬቶች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ እና ትስስሮችን ለማጎልበት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የኢትዮጵያን አቅም ለማሳየት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ነው። በኤክስፖው ላይ ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በድምሩ ከ10 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እና ከመቶ በላይ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሚታደሙ ሲሆን ኢትዮጵያ ዲጂታል ከባቢ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበለጸገ ኅብረተሰብን ለመገንባት እና የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እያደረገች ያለውን ጥረትና ያላት እምቅ አቅም ለዓለም የምታሳይበት መድረክ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ የሆኑ ተቋማት ምርታና አገልግሎቶቻቸውን ይዘው በኤግዚቢሽኑ መታደማቸው ነገ የኢትዮጵያ ግዙፍ ተቋማት ለመሆን ለሚያልሙት የሀገራችን ጅምሮች (start-ups) ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ የግብዓትና የእውቀት ትስስር በመፍጠር ለተቋሞቻችን ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።

ይህ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ በአምስት ዋና ዋና የትኩረት መስኮች የሚከናወን ነው። የመጀመሪያው የሳይበር ደህንነት (cybersecurity) ሲሆን ይህም እያደገ ያለው ዓለም አቀፍ የሳይበር ምኅዳር ትስስር ጋር ተያይዞ የሚነሱ የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይ የሚመክር ሲሆን በርካታ ሀሳቦችና ምርቶች የሚቀርቡበት ነው።

ሁለተኛው የትኩረት መስክ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት የሳበ፣ በሁላችንም ጓዳ እና በመዳፋችን ላይ የደረሰው ይህ ጉዳይ የሥራን ውጤታማነት በተለያዩ መስኮች እንዴት ሊያሻሽል እንደሚችል የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ማሳያዎች ይቀርቡበታል።

ሦስተኛው ርዕሰ ጉዳይ በስማርት ሲቲ ልማት (Smart Cities) ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው። ከተሞች በቴክኖሎጂ መመራታቸው ከአስተዳደር እስከ ሰላምና ጸጥታን ማስከበር ድረስ ስለሚኖረው ሚና የሀገራችንና የሌሎችም ተቋማት አቅምና ተሞክሮ ይታይበታል።

እንደሚታወቀው በሀገራችን መዲናችንን አዲስ አበባን ጨምሮ በአዳማ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ጅማ፣ ሐረር እና ሌሎችም ከተሞች የስማርት ሲቲ ግንባታ ጅምሮች መልካም ውጤት እያመጡ ይገኛል። በመጨረሻም በፋይናንስ ቴክኖሎጂ (Financial technology) እና በቴክኖሎጂ ትምህርት (Technology Education) ዙሪያ ውይይቶች፣ የተሞክሮ መቅሰም እና የተግባር ሥራዎች ይቀርባሉ።

የአይዲፎር አፍሪካ (ID4 Africa) ዓመታዊ ጉባኤ

ሁለተኛው ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ኮንፈረንስ የአይዲ ፎር አፍሪካ ዓመታዊ ጉባዔ ነው። ጉባኤው ከግንቦት 12 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ሲሆን በጉባኤው ከመንግሥት ውሳኔ ሰጪዎች፣ የልማት ድርጅቶች፣ ኢንዱስትሪዎች እና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበትና በአፍሪካ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት እድገትን ለማፋጠን የሚያግዝ ነው።

ከ100 በላይ ሀገራት በሚሳተፉበት ይህ ጉባኤ ሀገራችን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ያለን ከፍተኛ ቁጥር ያለው እንግዶችን ለማስተናገድ መሰረተ ልማት፣ ወደ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የተሳለጠ የአየር ጉዞ ግንኙነት መኖር እና ለሳምንት የሚቆየውን ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ ተግባራትን ለመደገፍ በቂ የኮንፈረንስ አገልግሎት መስጫ አቅምን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ከዚህም ባሻገር ግምገማው የኢትዮጵያ ፋይዳ የተገነባበት የሕግ ማሕቀፍ፣ ስትራቴጂ እና ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ ለብዙ ሀገራት አርዓያ መሆን መቻሉና “መታወቅ ለሁሉም” የሚለውን እቅድ በመተግበር ረገድ ያሳየችው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ለመመረጥ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።

በአጠቃላይ ሁለቱ ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ጉባዔዎች በተከታታይ ለአንድ ሳምንት መካሄዳቸው ሳምንቱን የቴክኖሎጂ ሳምንት” ያደርገዋል። ይህም መንግሥት ለዲጂታል ኢኮኖሚ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው። ዲጂታል ኢኮኖሚ በአንድ በኩል በራሱ ሃብትና የሥራ እድል በመፍጠር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን ቅልጥፍናና ውጤታማነት በማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።

20ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) አኅጉራዊ ኮንፈረንስ

ሌላው በዚህ ወር የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት በጋራ የሚዘጋጀው አኅጉራዊ የሰው ተኮር ኢንቨስትመንት ኮንፈረንስ ነው። ይህ ጉባዔ ከ50 በላይ ሀገራት የተወጣጡ ከ1500 በላይ ተሳታፊዎች የሚገኙበት ሲሆን ኮንፈረንሱ “የማይበገር ማኅበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ፦ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች” በሚል ከግንቦት 11 እስከ 15 ቀን 2017 ይካሄዳል።

ኮንፈረንሱ በዋናነት የሚያተኩረው ሀገራት በሚተገብሯቸው የተለያዩ የመሰረተ ልማት እና ሌሎች ፕሮግራሞች ወይም ፕሮጀክቶች እንዴት የሰው ኃይልን በስፋት መጠቀም እንደሚችሉ፣ ዘላቂና ጥራት ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል እንዲሁም በሂደቱ የሠራተኞችን ዘላቂ ተጠቃሚነት እና ደህንነት ማረጋገጥ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ነው። ይህም ካለን ሰፊ የሰው ኃይል አቅም አንጻር ጉዳዩን በከፍተኛ ሁኔታ ተገቢነት ያለው ያደርገዋል።

በተለይም በከተማና በገጠር ተግባራዊ እያደረግን የምናገኛቸው የመሰረተ ልማት፣ የቤቶች ልማት እና ሌሎች የግንባታ ሥራዎች ከአካባቢ ጋር የተስማሙ፣ በሕብረተሰብ ላይ የጎላ አሉታዊ ተጽእኖ የማያሳድሩ፣ በሥራ ቦታ የሠራተኞች ጤናና ደህንነት የተጠበቀባቸው፣ ለዜጎች ሰፊና ጥራት ያለው የሥራ እድል የሚፈጥሩ እንዲሁም ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረጉና አካታች እንዲሆኑ በፖሊሲዎቻችን፣ ሀገራዊ እቅዶቻችንና ፕሮግራሞቻችን በግልጽ አካተን የሠራናቸውን ሥራዎችና ያስመዘገብናቸውን ውጤቶች የምናቀርብ ይሆናል።

በአጠቃላይ ኮንፈረንሱ የዓለም የቴክኖሎጂ እድገት፣ ሰላምና ጸጥታ፣ የሀገራት የንግድ ፖሊሲዎች እና የአየር ንብረት ለውጥ በሠራተኞች ደህንነት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚኖራቸውን አዎንታዊ እና አሉታዊ ተጽእኖዎች በመፈተሽ ስኬቶችን ይበልጥ ለማዳበር እና ለሚስተዋሉ ችግሮች የመፍትሄ ሀሳብ ለማፍለቅ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል። ይህም ከዘላቂ የልማት ግብ ጋር የሚጣጣሙ፣ የአካባቢና ማኅበራዊ ደህንነትን ታሳቢ ያደረጉና ሰፋፊ የሥራ ዕድልን የሚፈጥሩ ኢንቨስትመንቶችን ይበልጥ ለመሳብ፣ ለማበረታታት እና ለማስፋት ዕድሎችን ይፈጥራል።

በአጠቃላይ፦

በውስን ዘርፎች ለማየት እንደተሞከረው የዚህን በጀት ዓመት በስኬት ለማጠናቀቅና ቀጣዩን የክረምትና የቀጣይ በጀት ዓመት በላቀ ዝግጁነት ለመጀመር በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል። በእነዚህ ጥረቶችም በርካታ ውጤቶች የተገኙ ቢሆንም ከኢትዮጵያ አቅምና ኢትዮጵያውያን ከሚገባን አንጻር ገና ረጅም መንገድ መሄድ ይጠበቅብናል።

ከመነሻችን አንጻር ብዙ የተጓዝን ቢሆንም ከመድረሻችን አንጻር ብዙ ስለሚቀረን በየተሠማራንበት መስክ ሰላምን በማስቀደም በትጋት፣ በፍጥነትና በፈጠራ መሥራት ይጠይቃል። ለዚህም ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንዲወጡ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት

ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ/ም

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You