ለሀገራዊ ምክክራችን – አጀንዳ ከቤታችን፣ ልምድን ከቀደምቶቻችን

የመግቢያ ሃሳብ

በኢትዮጵያ “የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን” በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ሕጋዊ ሰውነት ተሰጥቶት እና ኮሚሽነሮች ተሾመውለት ተቋቁሟል። በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮ እውን ለማድረግ ይችል ዘንድም ከዝግጅት ጀምሮ በየምዕራፉ የሚከውናቸውን ተግባራት በድርጊት መርሐ ግብር ታግዞ ዛሬ ላይ በሁለትና ሦስት ክልሎች የአጀንዳ እና የተሳታፊ ልየታ ሕዝባዊ ውይይቶችን እስከማድረግ ደርሷል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው ተግባሩ በሀገር ደረጃ ምክክር እንዲደረግ ማስቻል ነው። ታዲያ እንደ ሀገር የሚደረገው ምክክር ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ይሄን ነጥብ ለመመለስ ያስችል ዘንድ ታዲያ በመጀመሪያ “ምክክር” የሚለው ሃሳብ በራሱ ምንድን እንደሆነ ከተለያየ የሙያም፣ የቃላት መፍቻ መዛግብትም አንጻር ለመዳሰስ ልሞክር።

ምክክር የሚለውን ቃል ሁለት እና ከዛ በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚደረግን መወያየትን፣ መነጋገርን፣ ሃሳብ መለዋወጥን የመሳሰሉ ተግባራት የሚመለከት ነው። ይሄንኑ በተመለከተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ “ምክክር” የሚለውን፣ “መደረግ ያለበትን እና የሌለበትን ለመወሰን ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚካሄድ ውይይት፤ የሃሳብ ልውውጥ፤” ሲል ያብራራዋል።

በዚሁ አያይዞም፣ “ተመካከረ” የሚለውን፣ “ሃሳብ ለሃሳብ ተለዋወጠ” በሚል የሚፈታው ሲሆን፤ “ተማከረ” የሚለውን ደግሞ፣ “አንድን ጉዳይ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ የሌላ ሰውን ሃሳብ፣ አስተያየት ጠየቀ፤ ከሌላ ሰው ጋር ተነጋገረ፤” ሲል ያፍታታዋል። በዚህ መዝገበ ቃላት በተቀመጠው የቃል ፍቺ መሠረት፤ ምክክር ከሁለት በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚደረግ ውይይት ሲሆን፤ ለምክክሩም ምክንያት የሚሆን ሃሳብ ወይም የምክክሩ ተሳታፊዎችን ይሁንታና ምልከታ የሚሻ የጋራ ጉዳይ መኖሩን ነው።

ዓለማቀፍ የምክክር ማዕከል ሆኖ የሚንቀሳቀስ “KAICIID” የተሰኘ ተቋም በድረ ገጹ ላይ ስለ ምክክር (Dialogue)፣ “Dialogue, in general, is a process that involves mutual consultation in pursuit of common understanding through active and compassionate listening in order to discover similarities and understand dif­ferences in diverse perspectives and points of view.” ሲል አስፍሯል። ከዚህ የምንረዳው ምክክር በአንድ ጉዳይ ላይ በቅንነት ቁጭ ብሎ ድርሻ ወስዶ በመምከር በብዝኃ ሃሳብ የዳበረ የጋራ አረዳድ መፍጠር የሚቻልበት ሂደትና ዓውድ መሆኑን ነው።

በተመሳሳይ መልኩ፣ Jason Combs የተባለ ጸሐፊ “University of Dayton Blogs” የተሰኘ ማኅበራዊ ገጽ ላይ ባሰፈረው መጣጥፍ፣ ምክክርን፣ “Dialogue is a communicative process in which people with different perspectives seek understanding.” ሲል ገልጾታል። ይሄ ማለት ደግሞ ምክክር ሰዎች የተለያየ እይታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር የጋራ አረዳድ የሚፈጥሩበት ዓውድ ስለመሆኑ የሚያስረዳ ነው።

ይሁን እንጂ ምክክር ሁል ጊዜ የጋራ አረዳድ ለመያዝ ብቻ የሚደረግ አይደለም፤ ይልቁንም ሰዎች የጋራ አረዳድ የያዙባቸው ጉዳዮች ላይ የበለጠ ግንዛቤን ለመፍጠር፤ እንዲሁም ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች አፈጻጸም ላይ ጭምር እኩል አረዳድ ለመያዝ የሚያከናውኑት ስለመሆኑም ነው ጸሐፊው አያይዞ የገለጸው።

በመሆኑም ምክክር ሲነሳ፣ የሚማከሩ ሰዎች እንዲሁም የሚመከርበት ጉዳይ (የሁሉንም የጋራ ስምምነትና ይሁንታ የሚሻ የጋራ ጉዳይ) አብሮ የሚነሳ መሆኑን መረዳት ይቻላል።

እንደ አጠቃላይም ከላይ በተጠቃቀሱ ማብራሪያዎች እና ብያኔዎች መሠረት፣ ምክክር አለ ከተባለ(ለመመካከር) የግድ ከሁለት በላይ መሆንን፤ በዛው ልክ እነዚህ ሰዎች የሚመክሩበት ጉዳይ ሁሉንም የሚመለከት መሆን እንዳለበት፤ እና የሚመከርበት ጉዳይ በተመካካሪዎች ይሁንታ ላይ ተመስርቶ (በጋራ ግንዛቤ ተፈጥሮበት) ወደ ትግበራ ሊገባ እንደሚገባ የሚያስረዱ ሆነው እናገኛቸዋለን።

ሀገራዊ ምክክር ለምን?

በመግቢያው እንደ መነሻ ሃሳብ ወስጄ ለማብራራት እንደሞከርኩት፤ ምክክር ማለት፣ ምንስ መደረግ የለበትም የሚሉ ጉዳዮችን በተመለከተ ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች (ሁለት እና ከዛ በላይ) መካከል የሚደረግ ውይይትን የሚመለከት ነው። ይሄ ምክክር ደግሞ የሰዎችን አብሮ የመሰባሰብ፤ የተሰባሰቡ ሰዎችም በጋራ ቁጭ ብለው የሚመክሩበት/ሃሳብ የሚለዋወጡበት የጋራ ጉዳይ፤ ይሄንን ምክክር የሚመራ/የሚያመቻች አካል ወይም ተቋም የሚፈልግ መሆኑንም መረዳት ይቻላል።

ይሄን መሰል ምክክር ደግሞ በግለሰቦች፣ በቡድኖች፣ በማኅበረሰብ እንዲሁም በሀገርና አህጉር ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያገናኟቸውና በጋራ ሊከውኗቸው በሚገቧቸው ነጥቦች ላይ ተመሥርተው ሊያደርጉት ይችላሉ።

ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ዜጎቼ በጋራ መክረው ሊስማሙባቸው እና የጋራ አድርገው በቀጣይ ጉዟቸው የተሻለ መግባባትን ፈጥረው ሊተገብሯቸው፤ ሰላምና ልማታቸውን ማሳለጫ አድርገው ሊጠቀሙባቸው፤… የሚገቡ ጉዳዮች ስላሉ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ቁጭ ብለው ሊመክሩ እና የጋራ አቅጣጫ ሊያስቀምጡ ይገባል ብላ ዜጎቿን በጋራ ለማወያየት መንገድ ጀምራለች።

ይሄንን እንዲመራ የተሰየመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በአዋጅ ሲቋቋም፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ እና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ሥርዓት በመዘርጋት ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ከፍ ያለ ተልዕኮ ተሰጥቶት ነው።

ተቋሙም ይሄን ተልዕኮ ተቀብሎ እና ከተልዕኮው የተቀዳ “እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየት” የሚል ርዕይ አስቀምጦ ተግባራዊ እንቅስቃሴን ጀምሯል። በዚህም ሰነዶችን ከማዘጋጀትና የሀገራትን ተሞክሮ ከመቀመር ጀምሮ የተግባር መርሐ ግብር ቀርጿል፤ አማካሪዎችን ሰይሟል፤ የተሳታፊዎችን ምልመላ እና የአጀንዳ ቀረጻ ተግባራትንም ወደማከናወን ገብቷል። በዚህም ምንም እንኳን የዘገየ ቢመልስም በመዘግየት ውስጥ እየፈጠነ መሆኑን መመልከት ይቻላል።

እንደ ሀገርም በዚህ መልኩ ዜጎች በጋራ እንዲመክሩ ሲታሰብ፣ ኢትዮጵያውያን በዘመናት የአብሮነት ሂደት ውስጥ የበዙ መልካም ግንኙነቶች ያሏቸውን ያህል፤ መልካም ያልሆኑም የታሪክ አጋጣሚዎች ስላሏቸው እነዚህ መልካም ያልሆኑ የታሪክ ገጾች በነገው የአብሮነት ጉዞ ላይ መልካም ያልሆነን ጥላ እያጠሉ ሰላማቸውን እንዳይነጥቁ፣ የልማት መንገዳቸውን እንዳያቀጭጩ፤ በጥቅሉም በአብሮነታቸው ላይ መነጣጠል እንዳያንዣብብ ለማድረግ ነው።

ቀደም ሲል የጠቀስኩት “KAICIID” የተሰኘ ዓለማቀፍ ተቋም ተቋም በድረ ገጹ “Dialogue is about developing mutual respect in order to build sustainable relationships. …It builds bridges among those who are different to each other. It transforms human relationships from a state of ignorance or intolerance to a state of deeper understanding and respect for what is shared and what is not.” ሲል የጠቀሰው ሃሳብም ይሄንኑ የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ጅምር ጉዞ እሳቤ የሚያጠናክር ነው።

ከዚህ ገለጻ መረዳት እንደሚቻለውም፣ በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በቡድኖች መካከል አንድ የሚያደርጉም፤ የሚያለያዩም ጉዳዮች መኖራቸውን ሲሆን፤ ይሄን ልዩነት ለማጥበብም ሆነ አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮችን የበለጠ ተረድቶ ለማጥበቅ/ማጽናት የሚቻለው በመመካከር ነው።

ምክንያቱም፣ በጽሑፉ እንደተመለከተው፤ ምክክር ቀጣይነት ያለው አብሮነትን ለመገንባት የሚያስችል የእርስ በርስን መከባበርና መተማመን መፍጠሪያ መሣሪያ ነው። ምክክር የሰው ልጆችን አብሮነት ከአለመተማመንና ከመገፋፋት ዓውድ ወጥቶ ወደ መተማመንና በጋራ መቆም ማሸጋገሪያ ስልት ነው። ምክክር ማኅበረሰቦች በጋራ ሲኖሩ ምን አብረው መጋራት እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው አውቀው ልዩነቶቻቸው ሳያራርቋቸው በአንድነታቸው ሰንሰለት ተጋምደው እንዲዘልቁ ማድረጊያ ድር የሚሸመንበት መድረክ ነው።

ይሄ ገለጻ ደግሞ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የሚዛመድ ይመስለኛል። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ከሦስት ሺህ ዘመን በተሻገረው የአብሮነት መንገዳችን የበዙ መልካም ተግባራትን፣ የበዙም መጥፎ የታሪክ ምዕራፎችን አሳልፈናል። እነዚህ የታሪክ ገጾቻችን ደግሞ በብዝኃነታችን መስታወት ውስጥ ሲከሰቱ ለመልካምም፣ ለእኩይም ዓላማ ሊውሉ የሚችሉበት እድል የሰፋ ነው።

በዚህ ረገድ፣ የኢትዮጵያን መልካም የታሪክ ገጽ ብቻ እየገለጡ በሰዎች ልቡና መልካም የአብሮነት እሳቤን ለመትከል የሚተጉ የመኖራቸውን ያህል፤ ጥቂትም ቢሆኑ ለቂምና በቀል የሚያነሳሱ የታሪክ ምዕራፎችን ብቻ እየነቀሱ የጠብ፣ የቁርሾ፣ የመለያየት፣ የመጠፋፋትና ያለመተማማን እሳቤን በትውልዱ አዕምሮ ውስጥ ለመትከል የሚታትሩ መኖራቸውንም መመልከት ተችሏል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለቱም (መልካም መልካሙን ብቻ ይዘው የሚራመዱትም ሆኑ ክፉውን ገጽ ነቅሰው የሚሠሩት) ኃይሎች ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ኢትዮጵያውያን ሙሉ ስዕል ከማሳየት አኳያ ክፍተት ያለባቸው ናቸው። ምክንያቱም ታሪክ ምሉዕ የሚሆነው፤ ትውልዱም የቀጣይ አብሮነቱን በሙሉ መተማመን ሊያዘልቅ የሚችለው የታሪክ መንገዱን መልካምም፣ እኩይም ክስተት በልኩ ተገንዝቦ ሊማርበት ሲችል ነው።

ይሄ መሆን ካልቻለና መልካሙን ብቻ ሰምቶ ያደገ ትውልድ ችግር በገጠመው ቁጥር ካለፈ ታሪኩ የችግር መሻገሪያ የሚሆን ማጣቀሻ ስለማይኖረው በቀላሉ ለችግር እጅ ይሰጣል። በአንጻሩ፣ እኩይ እኩዩን ገጽ ብቻ እንዲያነብ ተደርጐ የተገነባ ትውልድ፣ ዘወትር ስለ ቂምና በቀል፣ ስለ መለያየትና መጠፋፋት እንጂ እንደ ሀገርና ሕዝብ በአንድ አብሮ የመኖር፣ ችግሮችን በጋራ ተጋፍጦ አሸንፎ የማለፍ፣ በጠነከረ አብሮነት ውስጥ የተጻፈ ገድልና ጅብድ፣ ኢትዮጵያውያን በማይነጣጠል የህብር ድር ስለመሸመናቸው የሚገነዘብበት ጥበብ ስለሚጎድለው ዘላቂ አብሮነትን ስለመገንባት አያስብም።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በታሪኳ፣ ኢትዮጵያውያንም በታሪካቸው ላይ ተመሥርተው ትውልድን መገንባት፤ ትውልድን ማነጽ፤ ትውልድን ለአብሮነት እንዲተጋ ማድረግ የተገባ ነው። ዛሬ ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን ከአንድነታችን ይልቅ ልዩነታችን ጎልቶ የሚገለጸው፤ ከኢትዮጵያዊነታችን ይልቅ የብሔር ማንነታችን ግዘፍ ነስቶ በየጎራችን መሽገን የምንገፋፋው፤ በመሬት እየተባላን ከወንድሞቻችን ጋር የምንጠፋፋው ይሄንን ሙሉ የታሪክ ገጻችንን አውቀን እንድናድግ ባለመደረጋችን ነው።

ከዚህም በላይ የመነጋገር፤ የመደማመጥ፤ የሚያለያዩንን ጉዳዮች በግልጽ አውጥቶ የመወያየት፤ የጋራ የሆኑ ጉዳዮቻችን ላይም ቁጭ ብለን በመምከር በሁላችንም ተመሳሳይ የጋራነት ሚዛን እንዲኖራቸው የመሥራት፤ የታሪክ ጠባሳዎቻችንን ነቅሰን አውጥተን ከመወቃቀሻነት ወደ መማሪያነት (ክፉን በክፉ ከመመለስ ይልቅ ያለፈው ክፉ ተግባር እንዳይደገም ለማድረግ) የማዋል፤ የታሪክ ጠባሳዎቻችን ከልዩነታችን የላቀው አንድነታችንን ሊሸፍኑት ከቶ እንደማይችሉ ከመግለጥ አኳያ በእጅጉ ዳተኞች በመሆናችን የተፈጠረብን ነው።

በመሆኑም ዛሬ ላይ የዚህ የዳተኝነት መንገዳችን ሊቀየር፤ የጥላቻና የጥርጣሬ እይታችን ሊታረቅ፤ የመገፋፋትና የቂም በቀል ውስጣዊ ፍላጎቶችም ካሉን በኖረው የውይይትና እርቅ እሴቶቻችን ታግዘን በይቅርታ ልንሽራቸው፤ ልዩነቶቻችን የማይነጣጥሉን፣ ይልቁንም ለአብሮነታችን ከፍ ያለ ውበትን የሚያጎናጽፉን ስለመሆኑ ልንረዳ፤ በአንድ መቆማችን አቅምና ኃይል የሚፈጥር ኅብረት እንጂ በአንድ ቋት አጉሮ የማንነት ሕልውናችንን የሚያጠፋ አለመሆኑን ልንገነዘብ በእጅጉ የተገባ ነው።

ይሄን ማድረግ የምንችለው ደግሞ ቁጭ ብለን ስንመክር ነው። ምክንያቱም፣ በመመካከር ችግሮችን መፍታት ይቻላል። በመመካከር እርቅ ይወርዳል። በመመካከር ይቅርታ ይወለዳል። በመመካከር ከችግሮች ልቆ መውጣት የሚያስችልን ልዕልና መገንባት ይቻላል። ይሄን ማድረግ ስንችል ዘላቂ አብሮነታችን በመተማመንና በመደጋገፍ ላይ ይመሠረታል። የነጋችን መንገድ በሰላም ጡብ የተገነባ ይሆናል። በጋራ ስለሰላማችን፣ በጋራ ስለብልጽግናችን መትጋት የምንችንበትን ሙሉ ቁመናን ይፈጥርልናል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ልጆቿ በጋራ ቁጭ ብለው እንዲመክሩ አስባ ወደ ተግባር ስትገባ ይሄን እውን እንዲሆን አብዝታ ስለምትሻ፤ ስለምትናፍቅም ነው። የምክክር ኮሚሽኑ የሚመራው ምክክር ዓላማም ሰላም የሆነችና ለዜጎቿ ምቹ ሀገር እውን ማድረግ ነው።

እናም የኢትዮጵያ መሻት፣ የኮሚሽኑም ዓላማ ይሰምር ዘንድ የምክክር ሂደቱን በኃላፊነትና በማስተዋል ድርሻ ወስዶ ለውጤት እንዲበቃ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል። ይሄን በማድረግ ሂደትም የሀገራትን ልምድ መዳሰስ፣ የውስጥ አቅምን መመልከት፣ ለውጤት የሚያበቁ ሂደቶችን እና ለውጤት ከመድረስ የሚያስተጓጉሉ ሁኔታዎችን በውል ተገንዝቦ መራመድንም ይጠይቃል።

ለምክክር ስኬታማነት

ቀደም ሲል ለመጠቃቀስ እንደሞከርኩት፣ ምክክር ሁለት እና ከዛ በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚደረግ ውይይት ነው። ውይይት ወይም ምክክር ደግሞ የሚመካከሩበትን ጉዳይ ይፈልጋል። ያ ጉዳይ ደግሞ ለተማካሪዎች/ተወያዮች የጋራ የሆነ ወይም ሁሉንም የሚመለከታቸው ሊሆን ያስፈልጋል።

ይሄ የሚመለከታቸው የጋራ የሆነው ጉዳያቸው ደግሞ ያልተግባቡበትና የጋራ መግባባትን የሚሻ፤ ወይም የተወሰነ መግባባት የተፈጠረበትና የበለጠ መግባባትን የሚሻ፤ ወይም ሙሉ ስምምነት የተደረሰባቸው ሆነው እንዴት በሙላት እንተግብራቸው የሚሉ ጉዳዮችና አጀንዳዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

እነዚህ በተለያየ መልኩ የሚገለጹና ለምክክር የሚመረጡ ቡድናዊ አልያም ሀገራዊ ጉዳዮች/አጀንዳዎች ታዲያ በሰከነ መንፈስ ሊመከርባቸው እና የምክክር ሂደቱ በውጤት እንዲጠናቀቅ ይጠበቃል። ይህ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ደግሞ የምክክር ሂደቱን ከሚያመቻቸው ተቋም ጀምሮ በመንግሥት፣ በፖለቲካ ኃይሎች፣ በልሂቃን፣ እንደ አጠቃላይ ለውይይቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከሚሰየሙ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ተወካዮች ከፍ ያለ ኃላፊነት ይጠበቃል።

በዚህ መልኩ የሚደረግ ምክክር ለውጤት እንዲበቃ አበርክቷቸው ከፍ ያለ ነው ተብሎ ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል የአመቻች ተቋሙ ገለልተኝነት፤ የተሳታፊዎች ልየታ እና የአጀንዳ መረጣ፤ የተሳታፊዎች የምክክር መድረኩን የመፍትሔ ማፍለቂያ ዓውድ አድርጎ በቅንነትና በአስተውሎት የመጠቀም፤ የፖለቲካና ፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት አለመኖር፤ ከመንግሥት ጫና ነጻ መሆኑ፤ ከአካባቢያዊና ዓለማቀፍ ተቋማትና አካላት ተጽዕኖ የጸዳ መሆን፤ ለቡድን ወይም ለግል ፍላጎት ሳይሆን እንደ ሀገርና ሕዝብ ለሚያሻግሩ ነገሮች ቅድሚያ ሰጥቶ ኃላፊነትን መወጣትን የመሳሰሉ ነጥቦች በተለያዩ መጣጥፎች ተጠቅሰው ይገኛሉ፤ በዘርፉ ምሑራንም ይነገራሉ።

እንደ ሀገር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያደረጉ ሀገራት ልምድ የሚያሳያውም ይሄንኑ ነው። ለዚህም ርቀን ሳንሄድ በአህጉራችን የተካሄዱ ምክክሮችን መጥቀስ እንችላለን። ምክንያቱም በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በሩዋንዳ የተካሄዱ ምክክሮች በየሀገራቱ የነበሩ ከፍ ያሉ ችግሮች መፍታት የቻሉት፤ ከችግሮቻቸው ልቀው እንዲወጡና ዛሬ ላይ የሚታዩትን ደቡብ አፍሪካም ሆነ ሩዋንዳ እውን ማድረግ የቻሉት ሀገር እና ሕዝብን ከዛሬ የተሻገረ ጉዳይ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረጋቸው ነው።

በብዙ መልኩ በእርስ በርስ እልቂት ታሪኳ የምትገለጸው ሩዋንዳ ዛሬ ላይ በሕዝቦቿ መካከል ያለውን አብሮነት ለተመለከተ፣ ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን የለውጥ ጎዳና ለተገነዘበ ምክክር ምን ያህል ታሪክ የመቀየር አቅም እንዳለው ይረዳል። የታሪክ ጠባሳዎች ለቀጣዩ መንገድ ዳገት ወይም ሰባራ ድልድይ ሆነው የሚቀመጡ አለመሆናቸውን፤ ይልቁንም ከእነርሱ ተምሮ እና እንዳይደገሙ በጋራ ቃል ተግባብቶ ችግሮቹን በይቅርታና እርቅ ቋጭቶ ስለ ነገ አብሮነትና ሀገራዊ ልዕልና በኅብር መራመድ እጅጉን ተገቢ ስለመሆኑ አምኖ ይቀበላል።

ምክንያቱም በእነዚህ ሀገራትም ሆነ ሌሎች ምክክራቸውን በስኬት ባጠናቀቁ ሀገራት የተካሄዱ ምክክሮች ከእነዚህ ጉዳዮች አንጻር የሚመዘን ነው። ገለልተኛ የምክክር አመቻች ተቋም የመሠረቱ፤ ዜጎቻቸውን ያለ ልዩነት ተሳታፊ ያደረጉ፤ የመንግሥት እና የፖለቲካ ኃይሎች ያልተገባ ጣልቃ ገብነትና ጫና ያልጎበኛቸው፤ የውጪ ኃይሎች ፍላጎትን ያልደረቡ፤ ከቡድናዊ ፍላጎት የተሻገረ የሀገርና ሕዝብን ዘላቂ አብሮነት፣ ሰላምና ልዕልና ማዕከል ያደረጉ ሀገራት የምክክር ሂደታቸው ሰምሮና ከችግሮቻቸው ልቀው ዛሬ ላይ ለሌሎች የስኬት ምሳሌ ተደርገው ለመገለጽ በቅተዋል።

ምክክርን አደናቃፊ ሁኔታዎች

እንደ ደቡብ አፍሪካ እና ሩዋንዳ ሁሉ የመን፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ እና ሌሎችም ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች እና ጉዳዮች ላይ እንደ ሀገር ምክክር አድርገዋል። እነዚህ ሀገራት ከውይይቶቻቸው ማግስት ያላቸው ገጽታ ግን እንደ ደቡብን አፍሪካ እና ሩዋንዳ አይደለም። ይልቁንም ከትናንት በተሻገረ ችግሮቻቸው ተጠምደው፤ ዛሬም የደም መሬት ሆነው ይገለጣሉ። ታዲያ በእነዚህ ሀገራት የነበረው ምክክር ለምን ከችግሮቻቸው ሊያሻግሯቸው አልቻሉም? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።

እዚህ ጋ የየሀገራቱ ልምድና አካሄድ እንደየራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ሊለያይ ይችላል። ዓውዱም፣ አመቻቹም፣ ተሳታፊውም፣ አጀንዳውም፣… እንደየሀገራቱ ነባራዊ ሁኔታ የሚገለጽም ነው። የየሀገራቱ ልምድና አካሄድ ደግሞ ለየብቻ ሊታይ የሚገባው እና ላለመውደቅ ሲባል ልምድ የሚወሰድበት ነው። ለአሁኑ ግን ምክክርን ሊያደናቅፉ እና ሊያሰናክሉ የሚችሉ ነጥቦችን ከአጠቃላይ የሀገራት ልምድ፣ እንዲሁም የባለሙያዎች ሙያዊ እይታ አኳያ ተደጋግመው የሚጠቀሱ ጉዳዮችን ጥቅል በሆነ መልኩ ለመጠቆም ልሞክር።

በዚህ ረገድ ተደጋግመው ከሚገለጹ ጉዳዮች መካከል ጣልቃ ገብነት እና ጫና አንዱ ነው። ጣልቃ ገብነት እና ጫና ከፖለቲካ ኃይሎች አልያም ከመንግሥት አካላት ሊሆን ይችላል። ዋናው ጉዳይ የመንግሥት አካላትም ሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ለማስፈጸም ሲሉ በምክክር ሂደቱ ላይ የሚያሳዩት/የሚኖራቸው ጣልቃ ገብነት እና ጫና ውጤቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ለምሳሌ፣ መንግሥት የራሱን ርዕዮተ ዓለም ለማስፈጸም ሲል ብቻ ሂደቱን ለመጠቀም ከሞከረ፤ የፖለቲካ ልሂቃን የራሳቸውን ወይም ከኋላ የሚደግፋቸውን የፖለቲካ ኃይሎችና ቡድኖች ጥቅምና ፍላጎት ማዕከል አድርገው የሚያሳድሩት ጫና፤ የውጪ ኃይሎች (መንግሥታት፣ ድርጅቶችና ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ) በድጋፍ ስም የየራሳቸውን ጥቅምና የፖለቲካ አመለካከት ለማስረጽ ሲሞክሩ፤ ወዘተ ጣልቃ ገብነትና ጫናው ሊፈጠር ይችላል።

ሌላው፣ ገለልተኛ አለመሆን፣ ለሀገርና ሕዝብ ጥቅም አለመቆም፣ ብዝኃነትን ያማከለና በብስለት የተሞላ የነቃ ተሳትፎን አለማድረግን የመሳሰሉ ጉዳዮችን የሚመለከት ነው። ገለልተኝነት ሲባል፣ የአመቻች ተቋሙ (ለምሳሌ ከኢትዮጵያ አንጻር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን) ገለልተኛ ሆኖ ከመደራጀት እና ገለልተኛ ሆኖ ሂደቱን ከመምራት አንጻር የሚገለጽ ነው። በመሆኑም የአመቻች ተቋሙ በዚህ መልኩ አለመገለጽ/ገለልተኛ ሆኖ አለመደራጀት ለምክክር ሂደት አለመሳካት የራሱ አበርክቶ አለው።

ከዚህ በተጓዳኝ የምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎች ሁኔታ(ሁሉን አቀፍ አለመሆን)፣ በተሳትፎ ሂደት የሚኖራቸው ሚና(ከራስ ፍላጎት በላቀ መልኩ የሚገለጽ ሃገርና ሕዝብን አለማስቀደም፤ እንዲሁም ሃሳብን በብስለትና በአዎንታዊ መልኩ ያለማቅረብ)፤ ተነጋግሮ ለመግባባት ራስን ካለማዘጋጀት እና ይሄንኑ ስሜት ወደሌሎች ከማጋባት አኳያ የሚገለጽ አካሄድ ለምክክሩ ውጤታማ አለመሆን የራሱ ድርሻ አለው።

ምክንያቱም ገለልተኛ ያልሆነ ተቋም የመራው ምክክር፤ ከጫናና ጣልቃ ገብነት ያልጸዳ ሂደት፤ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎን ያላረጋገጠ እና በብስለትም፣ በአዎንታዊ ሃሳብም ያልታገዘ መድረክ የሚፈለገውን አዎንታዊ ውጤት ያስገኛል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ይሆናል። በመሆኑም እነዚህና መሰል የምክክር ሂደትን አዋኪ ጉዳዮች በልካቸው ተገንዝቦ መራመድና መሥራት መክረው ውጤት አልባ ከሆኑ ሀገራት ጎራ ላለመሰለፍ ያግዛል።

የመውጫ ሃሳብ

ምክክር ሁለት እና ከዛ በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል የሚደረግን መወያየትን፣ መነጋገርን፣ ሃሳብ መለዋወጥን የመሳሰሉ ተግባራት የሚመለከት ጉዳይ ነው ካልን ዘንዳ፤ መመካከር ደግሞ ሰዎች በጋራ ሆነው ሃሳብ ተለዋውጠው የጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ የሚበጅ ተግባር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። እኛ ኢትዮጵያውያንም እንደ አገር ቁጭ ብለን ለመምከር ተቋም ያቋቋምነው፤ ኮሚሽነር ከነአማካሪዎቻቸው የሰየምነውም ይሄንን ምክክር ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ካለን የጸና መሻት ነው።

መመካከራችን የትናንቱን ቁርሾ በመሻር ለይቅርታ ራስን ለማስገዛት ሊሆን፤ መነጋገራችን ኑ በይቅርታ የተዘጋውን ፋይል ለታሪክ አኑሮ ለነገው ትውልድ የሚተርፍ አዲስ የሰላምና ፍቅር፣ የልማትና ብልጽግና ታሪክ ለማኖር የሚያስችል ኃላፊነትን በመውሰድ ሊገለጽ፤ የምምክራችን ውጤት የኢትዮጵያውያንን በህብር የደመቀ አብሮነት፣ የኢትዮጵያንም የቀጣይ ከፍታና ልዕልና እውን የማድረግ ቃል ኪዳን ማሰሪያ ሆኖ ሊታወስ የሚችል ማህተም እንዲሆን ማስቻል የተገባ ነው።

በዚህም መክረው ከወደቁት ሳይሆን መክረው ከላቁት ልምድን ልንቀስም፤ የሌሎች አጀንዳ ተሸካሚ ሳንሆን የራሳችንን ጉዳይ ይዘን በራሳችንን አቅም እና እሴት ቀምረን ልንጠቀም፤ የራሳችን አጀንዳዎችና ጉዳዮች ላይ ብቻ መክረን መክረው ችግሮቻቸውን ካሸነፉት ጎራ ተደምረን ለሌሎች አርዓያ ልንሆን የሚያስችለንን ገድል ልንፈጽም የተገባ ነው።

ይህ እንዲሆን ደግሞ በጀመርነው መንገድ አካታች እና ሁሉን አቀፍነትን ማጎልበት፤ ችግሮችን በውይይት እንጂ በኃይል መፍታት እንደማይቻል ማመን፤ በስክነት እና ኃላፊነት ስሜት በመምከር የመፍትሔ/አሻጋሪ ሃሳብ ማዋጣት፤ የፖለቲካ ተጽዕኖንና የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን ማስወገድ፤ ሕዝብ አድማጭ ብቻ ሳይሆን ተደማጭ መሆኑንም ማረጋገጥ፤ እንዲሁም ሀገር በቀል እሴቶችን መጠቀም በእጅጉ የተገባ ነው። መክረን የምንልቀውም ይሄን ስናደርግ ነው!

በየኔነው ስሻው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *