ያለንበት ወቅት ሀገራት የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑበት ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት የሚፈጥሩበት ነው። በተለይም አፍሪካውያን ካለፉባቸው አስቸጋሪ ውጣ ውረዶች፣ እነዚህም ውጣ ውረዶች ካስከፈሏቸው ከፍ ያሉ ዋጋዎች አንጻር ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን ቁርጠኛ የሆኑበት ወቅት ነው።
ለዚህም የሕዝቦቻቸውን ድምጽ/ፍላጎት አጉልተው ማሰማት የሚችሉበትን ፍትሐዊ ውክልና በዓለም አቀፍ ተቋማት የማግኘት መብታቸው እንዲከበር ከመጠየቅ ጀምሮ፣ የሕዝቦቻቸውን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍን ዓለም አቀፍ ፍትሐዊነት እንዲሰፍን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እያሰሙ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
አፍሪካውያን ከሁሉም በላይ ያላቸውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ሰፊ አምራች የሰው ኃይል በማቀናጀት በዓለም አቀፍ ደረጃ መለያቸው ከሆነው ድህነትና ኋላ ቀርነት ፈጥነው መውጣት ይፈልጋሉ። እንደቀደሙት ዘመናት ነገዎቻቸው በብዙ ውስብስብ ዓለም አቀፍ የሴራ ፖለቲካ ጽልመት እንዲለብስና በእኔ አውቅልሀለሁ መንገድ ያልተገባ ዋጋ መክፈል አይፈልጉም ።
ከዚህ ይልቅ ያላቸውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ሰፊ አምራች የሰው ኃይል አቀናጅተው መልማት የሚችሉበትን የእውቀት፣ የፋይናንስ፣ እና የቴክኖሎጂ ድጋፎችን ይፈልጋሉ፣ በቅድመ ሁኔታዎች በተጨናነቁ ርዳታዎች፤ ድጋፎችና የፋይናንስ አቅርቦቶች ከሚከፍሉት ያልተገባ ዋጋ ነፃ መውጣትን አጥብቀው ይፈልጋሉ።
በራሳቸው ሁለንተናዊ መነቃቃት ላይ የተመሠረተ ልማትን በማስፈን ለመጪው ትውልድ የተሻለች አህጉር በመፍጠር፤ መጪዎቹ የአህጉሪቱ ተረካቢ ትውልድ በራሱ የሚተማመን፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች ቀና ብሎ መመላለስ የሚችል ፤ ከሁሉም በላይ ከተረጂነት/ጠባቂነት ተላቆ ለሌሎች የሚተርፍበት ዘላቂ ልማት ባለቤት መሆን ይሻል።
አፍሪካውያን ይህንን መሻታቸውን በአግባቡ ለሚረዳ፤ ተረድቶም ለመደገፍ ከሚፈልግ የትኛውም ኃይል ጋር በመከባበርና የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ባደረገ መርሕ አብረው ለመሥራት ሁሌም ዝግጁ ናቸው፤ ከዚያም በላይ ለዚህ መርሕ የተገዛ አዲስ ዓለም አቀፍ ሥርዓት እውን እንዲሆን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማሰማት፣ ለድምፃቸውም ተሰሚነት የሚፈለገውን ሁሉ ለመክፈልም ቁርጠኛ ናቸው።
የአህጉሪቱ ሕዝቦች በብዙ ተጋድሎ/መስዋዕትነት የተቀናጁትን የፖለቲካ ነፃነት ምሉዕ፤ የቀደሙትን የነፃነት አባቶች ሕልም ተጨባጭ ለማድረግ፤ ከሁሉም በላይ ሉዓላዊነትን የሚሸከም የኢኮኖሚ አቅም ባለቤት መሆን እንዳለባቸው፤ ይህንን መፍጠር የሚችሉት፤ ከማንነታቸው በሚመነጭ የመልማት መሻት እንደሆነ መገንዘብ ችለዋል።
ይህ ዛሬ ላይ አፍሪካውያን የደረሱበት እውነታ፤ ዘላቂነት ያለው አህጉራዊ ልማት ለማስፈን ከፍያለ መነቃቃት መፍጠር ያስቻለ፤ ፍትሐዊ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአህጉሪቱ ሕዝቦች ተገቢውን ሥፍራ እንዲያገኙና ድምፃቸውም በአግባቡ እንዲሰማ ማድረግ የሚያስችል ነው።
በመካሄድ ላይ ባለው የአፍሪካ ሩሲያ ፎረም ሲሳተፉም፤ ፎረሙ ይህንን መሻታቸውን እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ ትልቅ አቅም ይሆናል በሚል ህሳቤና ተስፋ ነው። አፍሪካውያን ለሚያልሟቸው ብሩህ ነገዎች በፎረሙ የሚደርስባቸው መግባባቶች እና ውሳኔዎች የብርሃን ወጋገኖች ሊሆኑ እንደሚችሉ በመታመን ጭምር ነው!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2015