– የመሪ ርሃብ
የዓለማችን የርሃብ የስንዴ እና የበቆሎ አይመስለኝም። የትክክለኛ መሪ እንጂ።
ዓለም ሁሌም በተለየ ርሃብ ውስጥ እንድትኖር ያደረገ እና ያልተመለሰ ጥያቄ፤ ጥቂቶች የተገበሩት ፣ ብዙዎች ሞክረው ያላሳኩት ፣ በርካቶች ምን አለ እንዲህ በሆነ ብለው የሚናፍቁት፣ ከቁጥር የበዙ ሰዎች ለማየት ናፍቀው ሳያዩት ይህቺን ምድር የተሰናበቱበት ርሀብ ቢኖር በእኔ እምነት የመሪ ርሃብ ነው ብዬ አምናለሁ።
በዚህ ዓለም ላይ ብዙዎቹ ይጠይቃሉ ጥቂቶቹ ይመልሳሉ፣ ብዙዎቹ ችግር ይፈጥራሉ ጥቂቶቹ ችግር ይፈታሉ፣ ብዙዎቹ ያደንቃሉ ጥቂቶቹ ይደነቃሉ፣ ብዙዎቹ ታች ሆነው ያያሉ ጥቂቶቹ ላይ ሆነው ይታያሉ፣ ብዙዎቹ ጉልበታቸውን ያፈሳሉ ጥቂቶቹ ሀሳብ ያመነጫሉ፣ ብዙዎች ይመገባሉ ጥቂቶች ይመግባሉ፣ ብዙዎች ይቀበላሉ ጥቂቶች ይሰጣሉ፣ ብዙዎች ይማራሉ ጥቂቶች ያስተምራሉ ፣ብዙዎች ይከተላሉ ጥቂቶቹ ይመራሉ። ለዚህም ነው ከጥቂቶቹ አንዱ መሆን የሚያስፈለገው። መሪ ለመሆን ከጥቂቶቹ አንዱ መሆን ይጠይቃልና። ያኔ የዓለምን ርሀብ የምትመልስ መሪ ትሆናለህ ።
ለምሳሌ አሁን ባለንበት ዘመን የነሶሪያ ፣ ሊቢያ ፣ የመን እና የመሳሰሉት ሀገራት ላይ በነፃነት መኖር ፣ የምግብና ውሃ እጦት ፣ ጅምላ ጨራሽ አያባሬ ጦርነት፣ የሀገር መፈራረስን ርሃብ ያስከተለው የመሪ ርሃብ ነው ።
ለመሆኑ መሪነት የመሪ መንበር ላይ መቀመጥ ነውን?
መሪነት ቦታ የመያዝ ጉዳይ ሳይሆን ቦታ ይዞ ኃላፊነትን የመወጣት ጉዳይ ነው። መሪ መሆን መታደል ሳይሆን ለፀና ዓላማና ፍትህ መቆም ማለት ነው። ስለዚህ በዚህች ዓለም ላይ ውዱ ነገር መሪ ማግኘት ነው ማለት ነው። መሪ በዓለም ላይ ውድ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ የዓላማዎች መሳካትም ይሁን አለመሳካት የሚወሰነው ከመሪው ብቃት አንፃር በመሆኑ ነው ።
ስለዚህ የሚያስፈልገን መንበር የሚይዝ መሪ ወይስ የሚመራ መሪ ? የሚመራ መሪ መሆን ደግሞ ጥረትና ጥራትን ያካትታል።
መሪነት ኃላፊነትና አደራ ነው!
ኃላፊነትና ባለአደራነት የሌለው መሪነት ‘መረንነት’ ነው::
መሪነት ፍቺውም ኃላፊነትና ባለአደራነትን የሚገልፅ እንጂ ስለ ባለንብረትነት የሚገልፅ አይደለም።
መሪነት የተለያየ ትርጓሜ አለው። ሰዎች እንደየ እይታቸው የተለያዩ ትርጉም ይሰጡታል። ብዙዎች የዘርፉ ተመራማሪዎች መሪነት በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍቺ እንዳለው ይናገራሉ። ምንም ያህል ትርጉሙ ቢበዛ መሪነት ኃላፊነትና ባለአደራነት ነው። ኃላፊነትና ባለአደራነት የሌለው መሪነት ግን ‘መረንነት’ ነው::
በሌላ በኩል የተሰጣቸውን መሪነት ከግብ የማያደርሱ መሪዎች የተሰጣቸውን አደራ እና ኃላፊት በመንገድ የጣሉ ናቸው፤ እንደ ማለት ነው። የተሰጣቸውን መሪነት ከግብ ሳያደርሱ መቅረት የተሰጠ ኃላፊነትና አደራን በመንገድ ማስቀረት ነው ።
ብዙ መሪዎች ይህንን ሳይረዱ በመቅረት መሪነትን እንደ መታደል በመውሰድ ለዓለም ቀወስና ኪሳራ ምክንያት ሆነዋል። እንዲሁም ህዝባቸውን በትነዋል ከዚህም በላይ እንደ ማታ ገበያ ህዝባቸውን እና የምድሪቱን ሀብት ዘርፈዋል ቸብችበዋል።
ኃላፊነትና አደራ ስንል ግን ሀገርና ትውልድን በቅንነት፣ በታማኝነት እንዲሁም በህግ የበላይነት መርቶ ለታለመለት ዓላማና ግብ ማብቃት ነው። ይህም በትጋት በጥበብ እና ኃላፊነት በተሞላ ስልት መምራትን ይጠይቃል። መሪዎች ለመምራት ሲሾሙ የህዝባቸውን ኃላፊነትና አደራን ከታለመለት ግብ እናደርሳለን ብለው ቃል መግባታቸው አያከራክርም። ዳሩ ግን አንዳንዶች የመሪነት ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላ በተቃራኒ ሆነው ሲሰሩ ታይቷል። በመሆኑም በየደረጃው ያሉ መሪዎች በእጃችው ያለው በትር ሊመሩበት የተሰጣችው አዳራ መሆኑን እና ባለአደራ መሆናቸውን መቼም ቢሆን መዘንጋት የለባችውም። መሪነት ከህዝብ የሚቀበሉት አደራ፤ በህሊና የሚዳኙበት ኃላፊነት ነው።
መሪነት ቀላል ነው፤ አደራ መሆኑ እንጂ። ዛሬ ዛሬ አደራ ከብዙ መሪዎች ልቦና የተሰወረ ይመስላል። በመሆኑም ብዙ መሪዎች የያዙትን ኃላፊነት ልክ እንደ ርስት እና ከቤተሰብ እንደወረሱት መሬት ያዩታል። መሪነት ከአደራ የራቀ ሲሆን አሉታዊ ውጤቱ የከፋ ይሆናል። መሪነት በውጤትና በተጠቃሚ እርካታ የሚለካ ነው።
እንደሚታወቀው መልካም ዘር ተዘርቶ ክፉ ዘርን አይሰጥም ፤ መጥፎም ዘርም መልካም ፍሬን አያፈራም። የዘራኸውን ያንኑ ታጭዳለህ። አደራውን ዘንግቶ ከህዝቡ የሚሰርቅ መሪ ባለበት ሀገር ህዝቡ ሌባ እንደሚሆን ግልፅ ነው። እንዲሁም ታማኝና ጨዋ ህዝቡን ለተሻለ እድገት እና ስልጣኔ የሚመራ መሪ ባለበት ሀገር ደግሞ ህዝቡ በታማኝነት የተሰጠውን ስራ የሚሰራ፣ በተሰማራበት አገልግሎት ዘርፍ ጥራቱን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት የሚያቀርብ፣ በተቀላጠፈ የጊዜ አጠቃቀም አገልግሎቱን የሚሰጥ፣ መሆኑ አሁን ያለንበትን የዓለም ሀገራት እድገትና ውድቀት መመልከት በቂ ነው።
መሪነት አደራ ነው። ‹‹አደራ ደግሞ አይበላም።›› አደራ መብላት የሰውን ዕንባ (ላብ) እንደ መብላት ነው! ስለዚህ መሪነት በተሰጠህ አደራ ተከታዮችን በመምራት ወደ ታየው ፍፃሜና ግብ ማድረስ መሆኑን መገንዘብ ያሻል።
መሪነት ማገልገል ነው!
ከህዝብ ልብ ወጥተህ ህዝብን መምራት የማይታሰብ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011