መልካምነት- ለወገን አለሁ የማለት ሩጫ

ዓለማችን ከክፉ ይልቅ መልካምን ለማድረግ የምንችልና የማንችል መሆናችንን የመፈተኛ መድረክ ናት። መልካም የማድረግ ፍላጎትም ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ የሚመነጭ፣ ለአንዳንዶችም የሕይወታቸው የተሻለ ምርጫ ነው። ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ‹‹ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም›› ማለታቸውም ለዚህም ይመስላል።

ሰዎች አንዳቸው ለአንዳቸው መልካም በመሆን ያላቸውን ቢያካፍሉና መስጠትን የኑሯቸው መርህ ቢያደረጉ ተስፋ ለሌላቸው ተስፋን፤ ደስታ ለሌላቸው ደስታን ይፈጥራሉ። ንፍገት፤ ክፋት፤ ተንኮል፤ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ አድመኝነት፣ ምቀኝነትና ወንጀል በግልፅ አደባባይ ይሸነፋሉ። ፍቅር ያሸንፋል። የሕይወት ጣዕም ይጨምራል።

«ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው» እንደተባለው፣ ለመረዳትና ለመተዛዘን ዘመድ ወዳጅ አሊያም የምናውቀው ሰው ብቻ መሆን የለበትም። መልካም ለማድረግና ለመርዳትም ሞልቶ የተትረፈረፈው ባለሀብት መሆን የግድ አይልም። በብዙ መንገድ ሰዎችን ማገዝ የሚቻል ሲሆን አንደኛው ትንሽ የሚለው በጎ እሳቤና ተግባርም ለሌላኛው ግዙፍ እንደሚሆን መረዳት ግድ ይላል።

ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ መፋቀር እንዲሁም አንዳቸው ለአንዳቸው መተጋገዝና መደጋገፍን እሴት ያደረጉ ሕዝቦች ናቸው። ይህ የመደጋገፍ እሴት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ይበልጥ ጎልቶ መታየት ጀምራል። በተለይ የዕለት ምግባቸውን ማግኘት ለሚቸገሩና ለአቅመ ደካሞች ማዕድ የመጋራት ተግባር ከግለሰብ እስከ ተቋማት እየተለመደ መጥቷል።

በአሁን ወቅትም ይህን በርካታ ኢትዮጵያውያን አቅማቸው በፈቀደ አግባብ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውና እውቀታቸውን ፈሰስ በማድረግ በመልካምነት እሳቤ ደግነትን ሲያጋሩና ሳይኖራቸው ያላቸውን ሲሰጡ ብሎም መስጠትን ሲፈቅዱ እየተመለከትን እንገኛለን።

ከዚህ የህብረተሰብ መልካም ተግባር ባሻገርም የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞቻቸውን አስተባብረውና ከአጋር ድርጅቶች አሰባስበው የአቅማቸውን ለተቸገሩ ወገኖቻቸው ማዕድ ማጋራትንና እጅጉን ያረጁ ብሎም ለመኖር አዳጋች የሆኑ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች የማደስ እና አፍርሶ መስራትን ጨምሮ በተለያዩ በጎ ተግባራት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ከሁሉም በላይ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ ኢትዮጵያውያን ድንበር ሳያጥራቸው ለወገናቸው ድጋፍ ለማድረግ የሚያደርጉት ርብርብ ከአድናቆትም ባለፈ የሲቃ ስሜትን የሚያጭር ነው። ይህ የመልካምነት መገለጫ ለወገን አለሁ የማለት ሩጫ ባለፉት ዓመታትና ዘንድሮ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክልሎች በተከሰቱ ድርቅ ላይ ይበልጥ ተስተውሏል።

በአሁን ወቅትም በርካታ የበጎነት ተምሳሌቶች በራሳቸው ተነሳሽነትና መልካም ፍቃደኝነት ሃይማኖት ብሔር፣ ዕድሜ፣ ጾታና ማህበራዊ ደረጃ እንዲሁም መልካ ምድራዊ ወሰን ሳይገድባቸው የበጎነትን መንገድ በመከተል በጎ ምኞትን ተላብሰው በሀገራዊ ስሜት፣ ባህል እና ወግ ከወገን ጎን በመቆም ላይ ናቸው።

ይሁንና መሰል መልካም ዜጎች የመበራከታቸው ያህል በአሁን ወቅት በየቤቱና ጎዳናው በተለይ ደሃና አቅመ ደካማ ሰዎች ችግራችሁ ችግሬ ብሎ የሚደርስላቸው ተመልካች ዓይንና ሰሚ ጆሮ ከሁሉም በላይ መልካም ሰው ብሎም ተቋማት የሚያሻቸው መሆኑ እርግጥ ነው።

በተለይም በሕይወት ስንክሳር በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ከሰው በታች የመሆን ስሜት የተጋፈጡና ይህን ስሜት ፍራቻ ከሰው መራቅን ምርጫ ያደረጉ ወንድም እህቶቻችን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

ቀላል የሚባሉ በጋራ የመልካምነት መንገድ በመራመድ ሊቃለሉ ብሎም ሊቀየሩ የሚችሉ ችግሮች ሳይቀር በርካቶችን ሲፈትኑና ከመንገዳቸው ሲያሰናክሉም ይስተዋላል። አንዳንድ ተማሪዎች ወላጅ አልባ በመሆናቸው ከጎናቸው አይዞህ/ሽ ብሎ የሚያበረታታ ወገን ዘመድ በማጣታቸው ሌላው ቀርቶ ዩኒፎርም የሚገዛላቸው በማጣታቸው ምክንያት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ሲገደዱ መመልከትም ለዚህ በቂ ምስክር ሆኖ መቅረብ የሚችል ነው።

በእርግጥ መሰል ሸክሞችን ለማቅለል ትውልድ ካሰበው እንዲደርስ ለማድረግ በርካቶች እንደ ግለሰብም ሆነ ተቋም በመልካምነት እሳቤ ደግነትን ሲያጋሩና ሳይኖራቸው ያላቸውን ሲሰጡ ብሎም መስጠትን ሲፈቅዱ እየተመለከትን እንገኛለን። የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በተለይ በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሀገራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን መነሻ በማድረግም የመልካምነት ተግባርን በመከወን ላይ ናቸው።

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከልም ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው። ዩኒቨርሲቲው የተሰጡትን ሀገራዊ ተግባርና ኃላፊነቶች በመወጣት ሂደት በተለይ በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የማህበረሰብ ችግሮችን የሚያቀሉ ብሎም የሚያስወግዱ የተለያዩ ሰዋዊ የበጎ አድራጎትና መልካም ተግባራትን ሲሰራ ቆይቷል። እየሰራም ይገኛል።

በዚህ የበጎ ምግባር ተሳትፎ ውስጥ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ምንጊዜም ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ አቅም አጣን ሳይሉ ተባባሪነታቸው እያስመለከቱ ናቸው። ለአብነት በዚህ አመት ቦረና ከተከሰተው ድርቅ ጋር በተያያዘ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ሠራተኞችና መምህራን በራሳቸው ፈቃድ የድጋፉ ተካፋይ መሆን አለብን በሚል እንደ አቅማቸው ከ50 እስከ 100 በመቶ ደሞዛቸውን ለድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻቸውን ‹‹ይድረስልን›› ብለዋል። ተማሪዎችም የምንበላው ሥጋ ይቅርብን ብለው ሽሮን ምርጫቸው በማድረግ ለሥጋ የሚውለውን በጀት ‹‹ለወገን ድጋፍ ይሁንልን›› በማለት ወገናዊነታቸውን አስመስክረዋል።

በዚህ ሁኔታ ከተሰበሰበው ጋር የዩኒቨርሲቲው ዐሻራ ተጨምሮበት ከአራት ሚሊየን ስድስት መቶ ሺ ብር በላይ የሆነ የዓይነት ድጋፍ ለወገን እንዲደርስ ተደርጓል። መሰል የአጋርነት አይዟችሁ ባይነት ተግባር ለዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያው አይደለም። ባሳለፈነው አመትም በዚህ መንገድ የዱቄትና የእንስሳት መኖ ሣር ድጋፍን አድርጓል።

በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘው ‹‹በእኛ ለእኛ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች የበጎ አድራጎት ክበብም በጎነትን መርህ በማድረግ ተስፋ ለሌላቸው ተስፋን፤ ደስታ ለሌላቸው ደስታን ለመፍጠር በመልካምነት መገለጫ ለወገን አለሁ የማለት ሩጫቸው በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

መምህር መርጋ ደሳለኝ አሁን ላይ የበጎ አድራጎት ክበቡ ሰብሳቢ ነው። መምህር መርጋ፣ ክበቡን ስያሜ በሚመለከት ሲያስረዳም፣‹‹ድጋፍ የምናደርግ እኛ፤ ድጋፍ የሚደረግለትም የማህበረሰባችን ክፍል የሆነ ሰው ስለሆነ ልክ ለእኛ (ለራሳችን) እንደምናደርግ እናስብ ዘንድ ነው በእኛ ለእኛ የሚል ስያሜን የሰጠነው›› ይላል።

መምህሩ እንደሚገልጸው፣ የክበቡ ራዕይ፣ ከራሱ አልፎ ለሀገሩና ለተቸገሩ ወገኖች የሚያስብ ትውልድን ማፍራት ነው። ግቡም በፍቼ ከተማና አካባቢዋ ለሚገኙ ወላጅ አልባና አቅመ- ደካማ ቤተሰብ ላላቸው ተማሪዎች የደብተር፤ የእስክብሪቶና የዩኒፎርም ድጋፍ ማድረግ፤ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ ችግር ያለባቸውን በመለየት የመማር ማስተማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረግና የምክር አገልግሎት መስጠት ነው።

ከዚህ ባሻገር በፍቼ ከተማና አካባቢው ለሚገኙ አቅመ-ደካማ አረጋዊያንና መበለቶች የቁሳቁስና የአልባሳት ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ የወዳደቁ ቤቶቻቸውን መጠገን፤ ከከተማው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር በከተማው የጽዳት ዘመቻ ማካሄድ በህብረተሰቡ ጥሩ ተነሳሽነትን መፍጠርና ለትውልድ የሚያስብ ማህበረሰብን መፍጠር ነው።

የክበቡ አባላት ፍቃደኛ የሆኑ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ናቸው። አሁን ክበቡ 255 በጎ ፍቃደኛ አባላት አሉት። የክበቡ ገቢ ምንጭ ፍቃደኛ የሆኑ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ማለትም መምህራንና ከአስተዳደር ሠራተኛ በየወሩ ከደሞዛቸው ተቆራጭ የሚሆነው 20 ብር ነው።

በዚህ የመልካምነት መገለጫ ለወገን አለሁ የማለት ሩጫ ተሳታፊ የሆኑ የዩኒቨርሲቲው በጎ ፈቃደኛ አባላት መካካል ከፍተኛ አመራር ስለሆነ፣ ስላልሆነ የሚል የበጎነት ድጋፍ መጠን ልዩነትም የለም። ሁሉም የሚያዋጣው እኩል ነው።

ተምሳሌታቸው ሚሊዮኖች እናት፣ የእናትነት፣ የደግነት፣ የፍቅር፣ የቆራጥነት እና የጥንካሬ ምሳሌ ‹‹ኢትዮጵያዊቷ ማዘር ትሬዛ›› እያልን በበጎ ምግባራቸው የምናከብራቸው ዶክተር አበበች ጎበና (እዳዬ)ን ናቸው።

መምህር መርጋም ‹‹ሰው ለሰው ወይም ወገን ለወገን ፍቱን መድኃኒት ስለሆነ እኛ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ለተቸገሩ ማህበረሰባችንና ተማሪዎቻችን በገንዘባችን አስፈላጊውን እርዳታ ማድረጋችን ተገቢ ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ ግዴታችንም ጭምር ነው›› ይላል። ይህን በጎ ሥራ፤ ለወገን አሳቢ ዜጋን ለመፍጠርና ለነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለውም ያሰምርበታል።

ክበቡ በ2011 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ በጎ ሥራውን የጀመረ ሲሆን በወቅቱ ከ60 በላይ በጎ ፈቃደኛ መምህራንን በማቀፍ በ 17 ሺ500 ብር በመሰብሰብ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ 94 ወላጅ-አልባና አቅሙ-ደካማ ተማሪዎች ዩኒፎርም ድጋፍ አድርጓል።

በቀጣዩ አመት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ጋር በተያያዘ ብዙም እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻለም። ይሁንና በ2013 ዓ.ም ምንም እንኳን በጎ አድራጎቱ ክበብ ምንም ገቢ ባይኖረውም ከተወሰኑ መምህራን ጋር በመተባበር ‹‹የመስጠት ቀን›› በሚል ስያሜ ፕሮግራም በማዘጋጀት ሰው በልቡ ያሳበውን እንዲሰጥ በማስተባበር በርካታ አልባሳትንና የተወሰነም ገንዘብ ለመሰብሰብ ችሏል።

በወቅቱ ከ240 በላይ የተለያዩ አልባሳትና 18 ሺ ብር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን የተሰበሰበውን አልባሳትም በሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙና ጠያቂና ደጋፊ ለሌላቸው 116 የሕግ ታራሚ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል። እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶች ማለትም ሳሙና፤ ማስክ፤ ሳኒታይዘርና የሴቶች የፀጉር ቅባት ድጋፍ ተደርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ በፍቼ አጠቃላይ ሆስፒታል ተኝተው ለሚታከሙ ሕሙማንና የመድኃኒት መግዣ ለሌላቸው ለተወሰኑ ሰዎች የተለያዩ መድኃኒቶችን በመግዛት ድጋፍ ማድረግ ችሏል።

በ2014 ዓ.ም በፍቼ ከተማ ለሚገኙ ወላጅ-አልባ እና አቅመ-ደካማ ተማሪዎች የተለያዩ የደንብ ልብሶችን በማሰፋት በመጀመሪያ ዙር ለ85 ተማሪዎች፣ በሁለተኛ ዙር ደግሞ ለ200 ተማሪዎች ድጋፍ አድርጓል። የሁለተኛ ዙር ወጪ ሙሉ በሙሉ የተሸፈነው በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ነው።

በ2015 ማህበሩ በተለይም የትምህርት ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በተለይም በአካባቢው ለሚገኙ የአእምሮ ሕሙማን የተወሰነ ገንዘብን በማሰብሰብ ድጋፍ አድርጓል። ተጨማሪ በጎነትን የሚያስመሰክሩ ተግባራትን ለመከወን ዝግጁቱን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

መምህር መርጋ እንደሚያስገነዝበው፣ የእርዳታ ትንሽ የለውም። የደንብ ልብስ ባለመልበሳቸው በርካቶች ከትምህርት ገበታ ለመቅረት ይገደዳሉ። ከጓደኞቻቸው ተለይተው ድህነታቸው እንዲሰማቸው ይሆናሉ። የደንብ ልብስ ድጋፍ በማድረግ ብቻ አንድን ተማሪ ከትምህርት ገበታው እንዳይርቅ ማድረግ ይቻላል።

ይህን የመልካምነት መንገድ በመራመድ ብቻ ሚሊዮኖችን መታደግና የተማረ ሀገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠር ይቻላል። ነገ ከነገ ወዲያ ከራስ አልፈው ለሌሎች መትረፍ የሚችሉትን እውን የማድረግ አቅም ግዙፍ ነው።

ትንሽም ቢሆን የበጎነቱ ተቋዳሽ በሆኑ ሕፃናት ላይ የሚታየው ስሜት ልብን የሚያሞቅ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሕፃናት ስለሆኑ በቅጡ ላይገባቸው ይችላል። ይሁንና ልጃቸው የደንብ ልብስ ባለመኖሩ ከትምህርት ይቀርባቸው የነበሩ ወላጆች በሚያገኙት ድጋፍ ልጆቻቸው ከሌሎች ተማሪዎች እኩል ሆነው ሲመለከቱ የሚሰማቸው ስሜት በቃላት የሚገለፅ አይደለም።

አንድ ተማሪ በትንሽ ድጋፍ የፊቱ ፀዳል ሲያበራ የነገ ተስፋን ሲያልም መመልከት ልብን ያሞቃል። ይህን የሕፃናትና የወላጆች ደስታ መመልከትም ለክበቡ አባላት ትልቁ ክፍያ ነው። የሃሴት ምክንያት ነው። ለዩኒቨርሲቲውም ቢሆን በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ተሳትፎ የሚኮራበት ተግባር ነው።

የአባላቱ ቁጥር ከመምህራንና ከአስተዳደር ሠራተኞች ብዛት አንጻር ሲታይ በጣም ጥቂት ነው። ይህ እንደመሆኑም የአባላቱን ቁጥር ለመጨመር ብዙ ይጠበቅበታል። መምህር መርጋ እንደሚገልጸውም፣ በዚህ ረገድ በቀጣይ ፍቃደኛ የሆኑ ማንኛውንም ሰው የማካተት እቅድ ተይዟል።

የገቢ አቅም ለማሳደግም የተለያዩ የገቢ ማመንጫ ዘዴዎች የመጠቀምና በተለይም ‹‹ለወገኖች ቀን›› በሚል አመታዊ የመስጠት ቀን ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ ተጀምሯል። አቅሙን እያጎለበተ መምጣት መቻሉም የመልካምነት መንገድ ለወገን አለሁ የማለት ሩጫውን በማፍጠን በርካቶችን ለመድረስ ትልቅ አቅም የሚፈጥርለት ይሆናል።

እንደ ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በእኛ ለእኛ የበጎ አድራጎቱ ክበብ ሁሉም በየተቋሙ መሰል የበጎነት ተግባርን ቢፈፅም የበርካቶች ሞራልና ደስታ ምንጭ እንደሚሆን አያጠያይቅም። በተለይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሀገርንም ሆነ የሕዝብን ችግር በማቃለል ብሎም በማጥፋት ሂደት በመሰል ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በሌሎች ማህበራዊ ኃላፊነት ተግባራት ይበልጥ ተሳታፊ መሆን ይኖርባቸዋል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *