እሱ የከተማን ህይወት ኖሮበት አያውቅም። ገጠር መወለዱ ደግሞ ሁሌም ስለ አዲስ አበባ እንዲያልም አድርጎታል። ይህ ስሜቱ ከልጅነት ዕድሜው ጋር አብሮት አደገ። ጥቂት ከፍ ሲል ግን ያሰበው ተሳካለት። የነበረበትን ቀዬ ለቆ ወደ መሀል አገር አመራ። የምኞቱን አላጣም። የልጅነት ህልሙ የሆነችውን ሸገር ሲያገኝ በእጅጉ ተደሰተ፤ የልቡም ደረሰለት።
ካሚል አዲስ አበባ እንደደረሰ ህይወቱን ያሟሸው ትምህርት ቤት በመግባት ሆነ። ገጠር እያለ ርቀት ተጉዞ ይማር ነበር። አሁን ደግሞ በእንግድነት ያረፈባቸው ዘመዶቹ ዕድሉን አልነፈጉትም። እንደ እኩዮቹ ደብተር ይዞ ቀለም ቆጥሮ መመለስ ጀመረ። ይህኔ ሙሉነት ተሰማው።
ዘጠነኛ ክፍል ሲደርስ ግን የቀድሞ ስሜቱ አብሮት አልነበረም። ተምሮ የመለወጥ ሃሳቡን ቀይሮ ሰርቶ ገንዘብ ለማግኘት ያሰላስል ያዘ። ይህን ምኞቱን ለማሳካት ደግሞ ወደ ዲላ መውረድ አለበት። በዚህ ስፍራ ራሱን የሚችልበት መንገድ አያጣም። ተቀጥሮ መስራት ከቻለ ነገን ቀጥሮ ማሰራት ይችላል። በሃሳቡ ከቆረጠም የሚያልመውን ያሳካል።
ካሚል ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ዲላ ሲያመራ በያዘው ዕቅድ ተማምኖ ነበር። በስፍራው ሲደርስም የመጀመሪያውን ስራ ሻይ ቤት በመቀጠር ጀመረ። ጥቂት ጊዜያት እንደቆየ ለኪሱ ገንዘብ አላጣም።
የፍላጎቱን ሞልቶ ብሩን መቁጠር ቻለ። ይህ ብቻ ግን ብዙ ለሚያልመው ሰው በቂ አልሆነለትም። ዛሬም ስለነገው የሚያስበው ቋቱ በወጉ አልሞላም። ትናንትን አልፎ የተጓዘበት መንገድ እንዳሰበው ሆኖ አልቀናም። ዳግም ከውስጡ እየሞገተ ከራሱ እየመከረ ቀናትን ቆጠረ።
ከጥቂት የዲላ ቆይታው በኋላ ግን ህይወት እንደሰለቸው ተሰማው። ይህኔ በእንግድነት ተቀብላ እንጀራ የሰጠችውን ከተማ ሊርቃት ወሰነ። ውሳኔው ደግሞ የመልስ ጉዞውን አዲስ አበባ እንዲያደርግ አስገደደው። ለእሱ አሁንም ከሸገር ሌላ ህይወት የለም። ሁሌም ኑሮውን በሚወዳት ከተማ ቢያደርግ ይመርጣል። ተመልሶ ሲመጣ ግን አዕምሮው በብዙ ጉዳዮች ተወጠረ ።
አሁን ካሚል ተማሪ አይደለም። ቋሚ ስራና መተዳደሪያም የለውም። ይህ መሆኑ በከተማ ህይወት የሚያዘልቀው አይደለም። እናም ለቀጣዩ መንገድ መላ ሊፈልግ ግድ ሆነ። በሃሳብ ውሎ ሲያድር አንድ ጉዳይ ጆሮው ገባ። ምን አልባት የሰማው ሁሉ እውነት ከሆነ ትናንት የሚያስበውን ዕቅድ ሊያሳካ ይችላል። ፈጣን ምላሽ የሚያሻው ዕቅዱ ካሚልን ደላሎች ደጃፍ ሲያመላልሰው ከረመ።
ደላሎቹ እስከዛሬ በርካቶችን ከሀገር አሻግረዋል። እሱም ወስኖ ባህር ካቋረጠ እንጀራ እንደሚወጣለት ተነግሮታል። ይህን ሲሰማ ካሚል በተባለው መንገድ ለመጓዝ አላንገራገረም። ጓዙን ሸክፎ በቀጠሮው ዕለት ከመሰሎቹ ጋር ተቀላቀለ። ለደላሎቹ ከእጁ ያለውን ከፍሎም በሶማሊያ በኩል የቦሳሶ ወደብን ድንበርን አቋርጦ ከሀገር ራቀ። አስቸጋሪውን የባህር ላይ ጉዞ አልፎም ሳውዲ አረቢያን በጉልበት ስራ ተዋወቀ።
የካሚልና የሳውዲ ቆይታ መልካም የሚባል አልሆነም። ወደ ሀገሪቱ ሲገባ ህጋዊ ያልመሆኑ በክፉ አይኖች ያስቃኘው ጀመረ። በስጋትና በመሸማቀቅ የዘለቀው ህይወትም ለከፋ እስርና ድብደባ ዳረገው። ህገወጥነቱ ሲረጋገጥ በፖሊሶች ተይዞ ወደሀገሩ ተባረረ። አሁን ካሚል ስለዛሬ የሚለው ተስፋ ተሟጧል። ሰርቶ የያዘው ሮጦ የቋጠረው ጥሪት የለውም።
ከሳውዲ መልስ ስራ ፈት መሆን ሲጀምር ዘመዶቹ ቤት ከመጠጋት ሌላ ምርጫ አልነበረውም። በመንገድ ምልልስ ያቃጣለው ጊዜ ዋጋ ሊያስከፍለው ግድ ሆነ። በስደት ዓለም ካለፈባቸው መንገዶች ብዙ ተምሯል።
በሀገሩም ሰርቶ ለመኖር ወስኗል። አዲስ አበባ አሁንም አላሳፈረችውም። ቀናትን ከተረጋጋ በኋላ ስራ ጀመረ። ቤትና ሰራተኛን እየደለለ፣ አሮጌ ዕቃዎችን እየሸጠና እየለወጠ ህይወቱን ቀጠለ። የቅርብ ዘመዶቹን አሰባስቦም ብቸኝነቱን ሊረሳ ሞከረ።
መሪማ አክመል ደግሞ ሁሌም ለቤቷ ሙላት እንደሮጠች ነው። ማልዳ ከዕንቅልፏ ስትነቃ ስለውሎዋ ታስባለች። የዕለት ገቢዋን ለማግኘት የቤቷን ጎዶሎ ለመሙላት የላቧን ወዝ ትከፍላለች። አንዲት ልጇን ለማስተማር ገንዘብ ያሻታል። ለሚኖሩበት ቤት ኪራይና ለቀለብ ወጪዎችም የእሷ ድጎማ ካልታከለ ኑሮን መግፋት አይቻልም።
የቤቱ አባወራ ለጎጆዋ መቆምና ለቤተሰቧ መኖር ኩራት ነው። ከእሱ ጋር ገና በልጅነት የመሰረቱት ትዳር በጽኑ ዕምነት አስተሳስሯቸዋል። ይህ መሆኑ የጋብቻቸውን መሰረት አጠንክሮ ዓመታትን በጽናት አሻግሯቸዋል።
መሪማ ሁሌም ቢሆን የባሏን ሰላም ውሎ መግባት ትመኛለች። ልክ እንደእሷ ሁሉ ለቤተሰቡ የሚኖረው አባወራ በስራ ደክሞ ሲመለስ በሚስቱና በልጁ መኖር ይደሰታል። ህይወትን ከዛሬ ለነገ የተሻለ ለማድረግ ደግሞ ልክ እንደባለቤቱ የእሱም ጉልበት አርፎ አያውቅም።
ወይዘሮዋ ጎጆዋን ለማቅናት ጓዳዋን ለመሙላት የማትሞክረው የለም። እስከዛሬ አቅምና ጉልበቷ የፈቀደውን ሁሉ ስትከውን ቆይታለች። አሁን ደግሞ ከምትኖርበት አካባቢ እልፍ ብላ የምትቸረችረው ከሰል እንጀራዋ ሆኗል። የአካባቢው ሰው እንደአቅምና ፍላጎቱ በላስቲክ የተዘጋጁ የከሰል ቋጠሮዎችን ከመሪማ ይገዛል። በዚሁ ሰበብ ጥሩ መግባባት ያተረፈችው ወይዘሮ የዛሬውን ስትሸጥ ለነገው ደግሞ ደንበኞችዋን ታግባባለች።
ከሰሉን ሸጣ ገንዘብ ለመያዝ ጸሀይና ብርድን አትመርጥም። ዝናብ አልያም ጎርፍ አያሰጋትም። ሁሌም ራሷ ላይ ጨርቋን ጠምጥማ ደቃቁን ከአንኳሩ እየመጠነች ትቋጥራለች። የተቋጠረው ተሽጦ ሲያልቅም ለትርፍ ከገዛቻቸው ሙሉ ማዳበሪያዎች አንዱን ዘርግፋ በእጇ ታንጓልላለች። ሁሌም ቢሆን ህይወቷ በዚህ ውሎ የተቃኘ ነው።
ለእሷ በከሰል ጥላሸት የጠቆሩት እጆቿ አሳቀዋት አያውቁም። በእነሱ ቀንን ገፍታለች። የቤተሰቦችዋን በልቶ ማደር አይታለች። ዛሬም ቢሆን ጉልበቷን ገብራ ስለነገው እያሰበች ነው። የባሏን መልካም መሆን እየተመኘች፣ የልጅዋን ቁምነገር ትመኛለች። በእሷ ጤና ማደር ተሻግራም ፈጣሪዋን ታመሰግናለች።
መሪማ መልከመልካም የምትባል ወይዘሮ ነች። ከደንበኞቿ ባለፈ ከአካባቢው ነዋሪ ጋር የተለየ ቅርበት አላት። አላፊ አግዳሚውን በሰላምታ፣ የቀረባትን ሁሉ በጨዋታ የምትግባባው ሴት በእሷ ዙሪያ ካሉ ሌሎች ጋር ስታወጋ መዋል ልማዷ ነው። በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ «የባሸዋም ትምህርት ቤት» ግንብን ደገፍ ብላ ከሰሏን ስትቸረችር በርካቶችን አውቃለች። ከእነሱ ተግባባታም ክፉ ደጉን አውርታለች።
በዚህ አካባቢ ከሚመላለሱ ሰዎች አንዱ ግን መሪማን በተለየ ጥላቻ ያስተውላታል። ሁሌም እሷ ካለችበት አቅራቢያ ሲደርስ ፊቱ ይቀያየራል። አልፏት ከሄደ በኋላም እጆቹን በንዴት እያወናጨፈ ይበሳጫል። አንዳንዴ ደግሞ የዛቻ በሚመስል ስሜት ሲያስፈራራት ታየዋለች። እንዲህ መሆኑ በአጋጣሚ ነው ስትልም ለራሷ ትይዘዋለች። ሁኔታው ሲደጋገም ግን ለሚያውቋት በርቀት አሳይታ እውነታውን ተናገረች።
መሪማ ሰውዬውን በዚህ መንገድ ሲያልፍ ከማየት በቀር በቅርበት አውርታው እንደማታውቅ እርግጠኛ ነች። የእሱ ሁኔታ ግን የሚያውቃት ያህል ሆኖባታል። ግልምጫና መኮሳተሩን ብትለምደውም አልፎ አልፎ የሚያሳያት የዛቻ ስሜት ግን ሰላም እየነሳት ነው። ሰውዬው አንዳንዴ ቆም ብሎ ያስተውላትና ትዝብት በሚመስል አስተያየት ገላምጧት ያልፋታል።
የሰውዬውን ድርጊት ደጋግማ ያስተዋለችው ወይዘሮ ነገሩ ቢብስባት ለምትቀርባቸው ሁሉ አሁንም ሁኔታውን አሳወቀች። በአካባቢው ያሉ ጓደኞቿም የእሷን ተደጋጋሚ ስጋት አስተውለው ሁኔታውን ሊታዘቡ ሞከሩ። ሰውዬው በውስጡ ንዴትና ጥላቻ ስለመኖሩ አውቀዋል። የእሱ ያልተገባ ባህርይ ቢያስገርማቸውም ተወት እንድታደርገው ከመምከር ውጭ ያሉት አልነበረም።
መሪም አሁን ከሰሏን ለመቸርቸር ከመንገድ ስትወጣ ከተለየ ስጋት ጋር ሆኗል። ቀድሞ ደንበኞችዋን በተለየ አክብሮት መመልከቷ ለገበያዋ መልካም ሲሆንላት ቆይቷል። አሁን ግን የምታየውን ሁሉ መጠራጠር ጀምራለች። የአይን ሰላምታ ከሌለው ሰው ጋር በርቀት መገለማመጡ ፍራቻ ሆኖባታል። ሰውዬው በምን ምክንያት ይህን እንደሚያደርግ ያለማወቋ ደግሞ ያልተመለሰ ጥያቄዋ ነው።
አሁን መሪምና ያልታወቀው ግለሰብ በርቀት መተያየቱን ለምደውታል። እሱ አጠገቧ ሲደርስ ሆን ብሎ በሚያሳየው ድርጊት መሪም ትሸበራለች። አስቀድማ ካየችው ግን ሳያደርስባት በፊት ትሸሸዋለች። ሰውዬው ርቆ መሄዱን ስታረጋግጥ ደግሞ ተመልሳ በስራዋ ትቀመጣለች። አይኖችዋ በስጋት እንደዋለሉ፣አካሏ በፍራቻ እንደራደም ቀኑ አልፎ ምሽቱ ይደርሳል።
ከመሪም ጋር በየቀኑ የአይን ጦርነት የያዘው ጎልማሳ ከስደት ተመልሶ በአካባቢው የሚውለው ደላላ ካሚል ነው። ካሚል ከሳውዲ መልስ ኑሮውን ከቀጠለ በኋላ የቅርብ ዘመዶቹን ሰብስቦ መኖር ጀምሯል።
በየጊዜው እሱን ፈልገው የሚመጡ ባለጉዳዮች የመብዛታቸውን ያህል በየቀኑ ወሬ የሚያመላልሱለትም ጥቂቶች አይደሉም። በአካባቢውና በሚውልበት መንደር መሃል ሁሌም አዳዲስ ወሬዎች ይሰማሉ። በየጊዜው የሰዎች ስም እየተነሳ በሃሜት ይዘለዘላል። አንዳንዶቹ እየፈጠሩ፣ሌሎችም እያጋነኑ ቀኑን በወሬ ሲራኮቱ ይውላሉ።
ካሚል እስከዛሬ የብዙዎች ማንነት በሀሜት ሲለወስ ሰምቷል። እሱም ተሳታፊ የሆነባቸው ትኩስ ወሬዎች ጥቂት አይደሉም። ይህ መሆኑ ደግሞ ለአካባቢው አዲስ ሆኖ አያውቅም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከሚራገበው ሀሜት መሀል የእራሱን ስም ማግኘቱ ከልብ እያበገነው ነው። ወሬው በእሱም ሆነ በሚያውቁት ዘንድ የተለየ ትኩረት አግኝቷል። ከምንም በላይ ደግሞ ለካሚል ይህ አይነቱ ወሬ የተለመደና ተራ የሚባል አልሆነም።
ደላላው ካሚል የስሙን መጉደፍ ከሰማ ወዲህ የሚቀርባቸውን ሰዎች ለማየት መሸማቀቅ ጀምሯል። «እሱ ዘመዶቹን ሰብስቦ መኖሩ ለመርዳት ሳይሆን ለሌላ ፍላጎቱ ነው» እየተባለ መነዛቱን ሰምቷል። ሀሜቱ ለጆሮው የደረሰው ዘግይቶ ቢሆንም እውነቱን ካወቀበት ጊዜ አንስቶ ግን ሰላምና ዕንቅልፍ አጥቷል። አንድ ቀን ግን ሲብከነከንበት ለቆየው ጉዳይ ፍንጭ ለማግኘት ነገሩን ከስሩ ማጣራት ጀመረ።
በጊዜው «ስምህን ያጎደፈውን እናውቃለን፣ ሲባልም ሰምተናል ያሉት አንዳንዶች ያወራውን ሰው ማንነት ላለመግለጽ ሊደብቁት ሞከሩ። ጥቂት ቆይተው ግን እርግጠኞች መሆናቸውን ባረጋገጠ መልኩ እጃቸውን አንዲት ሴት ላይ ቀሰሩ። ካሚል ስምህን አጥፍታለች የተባለችውን መሪምን ካወቃት ወዲህ በምክንያትም ያለምክንያትም በአጠገቧ መመላለስ ጀመረ። ባያት ቁጥር ዓይኖቹ በጥላቻ ተሞሉ። ልቡ ቂምና ጥላቻን አረገዘ።
ካሚል ይህን ጥላቻውን እንድታውቅ በአጠገቧ በተመላለሰ ቁጥር ጉዳዩ ከምታየው በላይ መሆኑን ለማሳወቅ እያስፈራራ ዛተባት። ያለምንም ትውውቅ ማስጠንቀቂያው የደረሳት መሪም በየቀኑ በሚያሳያት ያልተገባ ምልክት ውስጧ በፍርሀት ራደ። ካሚል መረበሿን ሲመለከት ንዴቱ ባሰባት። ስታየው የመደንገጧን ጉዳይ ከሀሜቱ ጋር አያይዞም እሷ ያለችው ሁሉ «እውነት ነው» ሲል ደመደመ ።
ግንቦት 1 ቀን 2005 ዓ.ም ማለዳ የግንቦት ጸሀይ ገና በማለዳው መድመቅ ጀምራለች። መሪም የዕለቱን ስራዋን ለመጀመር ከቤቷ የወጣችው አስቀድማ ነበር።ሁሌም በምትቀመጥበት ትምህርት ቤት ጥግ ከማዳበሪያው የቀነሰችውን ከሰል በወጉ ማሰር ጀምራለች። ይህን ማድረግ ከመጀመሯ አጠገቧ የደረሰውን ካሚል ያየችው በርቀት ነበር። የዛን ዕለት ግን እንደቀድሞው ትኩረት ሰጥታ አልተረበሸችም። ስታየው መሸሽም ሆነ መራቅ አላስፈለጋትም።
ካሚል እንደለመደው ጥርሱን እየነከሰ መዛት ጀምሯል። በአጠገቧ ሲመላለስ ሀሜቱ ትውስ እያለው ነው። ያለአግባብ ለጎደፈው ስሙ መነሻ እሷ መሆኗን በማወቁ ጥላቻው ጨምሯል። የዛሬው ግዴለሽነቷ ደግሞ ይበልጥ እያበገነው ነው። ነገሩን ደጋግሞ ሲያስበው ሰውነቱ በንዴት ጋለ። እጆቹም መንቀጥቀጥ ጀመሩ። ጥቂት ቆይቶ ግን ያሰበውን ለማድረግ ወሰነ። ተመልሶ ወደቤቱ ለመሄድም ርምጃውን አፈጠነ ።
የዘወትር ገላማጯ ካጠገቧ መራቁን ያየችው ወይዘሮ ተረጋታ ስራዋን ቀጥላለች። ላስቲኩን በከሰል እየሞላች፣ደቃቁን ከአንኳሩ እየለየች ማሰር ጀምራለች። ድንገት ቀና ስትል ግን ከሰውዬው ጋር ዳግም ተፋጠጡ። በጣም ደነገጠች። ከደቂቃዎች በፊት ርቆ ስለመሄዱ እርግጠኛ ነበረች።
ካሚል ወገቡን ደጋግሞ ዳሰሰ። የያዘውን አላጣውም። በጨርቅ እንደተጠቀለለ ከጎኑ ተሽጧል። ጊዜ አላጣፋም። ስለቱን ከጨርቁ ለይቶ መዞ አወጣው። መሪም የሚያደርገውን ስታይ ክው አለች። የካሚል እጆች ፈጠኑ። ቢላዋውን በቀኝ አንገቷ ላይ ደጋግሞ አሳረፈው። በዚህ ብቻ አልበቃውም። ከወጋበት ነቅሎ ክንዷ ላይ አምስት ቦታ ወጋት። አሁንም ቢላዋውን ነቀለ። አንገቷና ጆሮ ግንዷ ስር ደጋግሞ ወጋት። ስለቱን እንደገና ነቀለው። ባዘጋጀው ሰማያዊ ጨርቅ ጠቅልሎም እግሬ አውጭኝ ሲል ተፈተለከ።
አካባቢው በከፍተኛ ጩኸት ተደባለቀ። ስፍራው በማያቆም ደም ራሰ ። ትንፋሿ መኖሩን የጠረጠሩ መሪምን ወደ ሆስፒታል ሊያደርሱ ፈጠኑ። ከሚል ደም የተነከረውን ቢላዋ እንደያዘ ወደ ዊንጌት አቅጣጫ ሮጠ። ማንም እንዳልተከተለው ሲያውቅ ቢላዋውን ከአንድ ግቢ ወርውሮት ተረጋግቶ ተራመደ። ጥቂት ቆይቶ አንድ አውቶቡስ ሲመጣ ተመለከተ። በእጁ ምልክት አሳይቶና ለምኖ ተሳፈረ።
መሪምን የያዙ ጎረቤቶች ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ደጃፍ ደርሰዋል። በእጅጉ የተጎዳችው ወይዘሮ ግን ለህክምና ሳትበቃ ትንፋሿ ተቋርጧል። ሁሉም በከባድ ሃዘን ተውጠው ወደቤት ሲመለሱ መረጃ የደረሰው ፖሊስ አካባቢውን ከቦ ማስረጃዎችን ሰበሰበ። የሟችን አስከሬን ለምርመራ ልኮም ተጠርጣሪውን ማሰስ ጀመረ።
የፖሊስ ምርመራ ድርጊቱን ፈጽሞ ከአካባቢው የተሰወረው ካሚል ከስፍራው ርቋል። ፖሊስ ስለሰውየው ማንነት መረጃዎችን አጣርቶ ምስክሮችን ለይቷል። ተጠርጣሪው ሮጧል ወደተባለበት አቅጣጫ የምርመራ ቡድን ተላከ። ጉዳዩ እንደተባለው ሆኖ ተፈላጊው በቅርብ አልተገኘም። ጥቂት ቆይቶ ግን ፖሊስ አንድ የስልክ መልዕክት ተቀበለ። ተጠርጣሪው በአቅራቢያው ከሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እጁን ለህግ መስጠቱ ታወቀ።
ግለሰቡን ለማግኘት ካለበት ስፍራ የደረሰው ቡድን ቃሉን በአግባቡ ተቀብሎ ወንጀሉን የፈጸመበትን ቢላዋ መገኛ ጠየቀ። ካሚል የሆነውን ሁሉ አልሸሸገም። ድርጊቱን አምኖ ቢላውን የጣለበትን ስፍራ ጠቆመ። ፖሊስ ከቢላው ላይ ያገኘውን ደም ለፎረንሲክ ምርመራ ወሰደ። ግለሰቡን በማረፊያ አውሎም የክስ መዝገቡን አደራጀ።
በከሳሽ የሟች ባለቤት አቶ መሀመድ ሰይድና በተከሳሹ ካሚል ሁሴን መሀል ያለው የክስ ሂደት ቀጥሏል። ዓቃቤ ህግ የቀረበለትን የክስ መዝገብ መርምሮ ለዕለቱ የችሎት ውሳኔ አቅርቧል። በምክትል ሳጂን መንግስቱ ታደሰ የሚመራው ቡድን ምርመራዎቹን አጠናቋል። በፖሊስ የምርመራ መዝገብ 800/07 በበቂ ማስረጃዎች የተደራጀው መዝገብ አስፈላጊ ማስረጃዎችን በበቂ መረጃዎች አዛምዶ ለፍርድ ሂደት አዘጋጅቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 3/2011
በመል ካምስራ አፈወርቅ