ለሀገር ተስፋ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር

ኢትዮጵያን አድምቆ ለመሳል የሰላ ብዕር ያስፈልጋል። ብዕሩ ደግሞ የእውቀትና የማስተዋል ብዕር ነው። ይሄ የእውቀትና የማስተዋል ብዕር ከትምህርት እና ከሥርዓት የሚገኝ የሀሳብ፣ የተግባርና የለውጥ ንቅናቄ ነው።

ቤት ለመሥራት ሲሚንቶና አሸዋ ወይም ምሰሶና ማገር እንደሚያስፈልግ ሀገር ለመሥራትም ትምህርት ቁልፍ ነገር ነው። እውቀት ሁለት ዓይነት መልክ አለው። አንዱ ሀገር የሚኩል ሲሆን አንዱ ደግሞ ሀገር የሚያስነውር ነው። ሀገር የሚኩሉ እውቀቶች በበጎ ሥርዓት ተመርተው በለውጥ እና በትጋት ከትናንት ወደዛሬ የመጡ ሲሆኑ በተቃራኒው ሀገር የሚያስነውሩ እውቀቶች በደከመ መርህ በኩረጃ የተገኙ ናቸው።

በመሠረቱ በኩረጃ የተገኘ እውቀት እንደእውቀት መጠራት የሚቻለው አይደለም። እውቀት መነሻው ከራስ በራስ ለራስና ሌላው ነው። በኩረጃ ወይም ደግሞ በደካማ የትምህርት ሥርዓት የተገኘ እውቀት የኋላ ኋላ ራስን ጎድቶ ለሀገር የሚትርፍ ዱብዕዳ ነው። የትምህርት ሚኒስቴር አሁናዊ እንቅስቃሴ ከእንዲህ ዓይነቱ የእውቀትና የሥርዓት ዝቅታ ሀገርን መታደግ ነው።

ከዚህ እውነት በመነሳት ኢትዮጵያ ተስፋን ከሰነቀችባቸው የሥርዓት ለውጦች መሀል አንዱ በትምህርቱ ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ ቀዳሚው ነው። የትምህርት ሚኒስቴር በተጠናና በተፈተሸ አካሄድ የሀገራችንን የትምህርት ሥርዓት የነበረበትን የጥራትና የመማር ማስተማር ክፍተት በመረዳት ተስፋ ሰጪ ለውጦችን በማድረግ ላይ ይገኛል።

ከእነዚህ ለውጦች ውስጥ አንዱ ሰሞነኛው የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና ‹exit exam› ይጠቀሳል። ይሄ የትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓት ለውጥ ለብዙዎቻችን ተስፋ ሰጪ የመሆኑን ያክል ስንፍናንና ኩረጃን ልምድ ላደረጉ አንዳንድ ተማሪዎች ፍርሀትንና ኩርፊያን የቀሰቀሰ እንደነበር አንዳንድ ጉርምርምታዎችን ለማድመጥ ችለናል።

በአዲሱ ሥርግት ደስ ያላቸው እነሱ የኢትዮጵያን ለውጥና እድገት የሚፈልጉ እንዲሁም ደግሞ በራስ በመተማመን ከትናንት ወደዛሬ የመጡ እንደሆኑ ይታመናል። በተቃራኒው ለምን የሚል መሠረት የሌለውን ጥያቄ የሚያነሱት ደግሞ ሀገርንም ሕዝብንም ወዴትም ከማይወስድ የኩረጃ ሥርዓት መውጣታቸው የፈጠረባቸው ስጋት መሆኑ አያጠያይቅም።

የሆነው ሆኖ በየትኛውም መስፈርት ቢታይ የትምህርት ሚኒስቴር አዲሱ የለውጥ እንቅስቃሴ በትምህርት ጥራት ማነስ ለውጥ አጥቶ የነበረውን የትምህርት ሥርዓት ወደፊት አንድ ርምጃ የሚወስድ እንደሚሆን፤ በለውጥ ማግስት የሚሰሙ አንዳንድ ድምጾች የተለመዱ መሆናቸውም ይታመናል።

ከዚህም ከዛም የምንሰማቸው ድምጾች የብርክ ድምጾች ናቸው። ፈሪዎች ካልሆኑ ጎበዞች አያወሩም። በአዲሱ የሥርዓት ለውጥ እየጮሁና እየተሸበሩ ያሉት በኩረጃ አልፈው በኩረጃ እንጀራ ለመብላት እየሮጡ ያሉ ፈሪዎች ናቸው። የጎበዝ ድምጽ ሀገርን በሚለውጥ የመርህና የሥርዓት ለውጥ ውስጥ መሳተፍ ነው።

እንዴትም ይሁን ለውጥ ያስፈልገናል። በአንድ ዓይነት የመማር ማስተማር ሥርዓት አንድ ዓይነት ሀገር ይዘን ከትናንት ዛሬ መጥተናል። ለጠየቀን ሁሉ ትምህርት ሀገር የሚለውጥ የሥልጣኔና የዘመናዊነት ፋና ወጊ ነው እንላለን። ለጠየቀን ሁሉ መማር ያስከብራል ሀገርን ያኮራል እንላለን። በትምህርት ሥርዓታችን በኩል ግን ይሄን እውነት የሚያረጋግጥ ሥርዓት አልነበረንም።

ጥራት የሚጀምረው አላዋቂዎችን ከማጥራት ነው። ለውጥ የሚመጣው በራሱ የሚተማመን ዜጋን የሚፈጥር ሥርዓትና መርህ ስንፈጥር ነው። ሥርዓቶቻችን እውቀትና ጥራትን መሠረት ካላደረጉ በራሱ የሚተማመን ትውልድ መፍጠር አይቻላቸውም። መርሆቻችን ከኩረጃ የጸዱ፣ ከምንም በፊት ለሀገርና ትውልድ የሚበጁ ሆነው ወደመሬት እስካልወረዱ ድረስ «ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ» እንደሚባለው ነው።

ተግባርና ንግግራችን መሳ ለመሳ ሄደው ሀገር መፍጠር አለብን። የገባንን የእውቀትና የትምህርት አስፈላጊነት በገባን ልክ ተግብረን ለሀገራችን ችግር መፍቻነት ልንጠቀመው ይገባል። ትምህርት የለውጥ ቁልፍ ነው እያልን በኩረጃ የምናልፍ ከሆነ ትልቁ ስህተታችን ከዚህ የሚጀምር ነው።

በቴክኖሎጂው ዘርፍ ዓለምን እየመሩ ያሉ ኃያላኖችን መለስ ብለን የትምህርት ሥርዓታቸውን ብናስተውል እጃችንን አፋችን ላይ የሚያስጭን እንዲህም አለ እንዴ የሚያስብል አግራሞትን ነው የምናስተናግደው። ዓለም የሠለጠነችው በትምህርት ነው። ኃያላኖቹ የአሁኑን የተሰሚነት ሚና ያገኙት በእውቀት ነው።

እንደ ጃፓንና ቻይናን የመሳሰሉ አስደናቂ የትውልድ መቅረጫ የትምህርት ሥርዓት ያላቸውን ሀገራት ለማየት መጣፍ አገላብጫለሁ፤ ከመደነቅና ከመገረም በቀር ያተረፍኩት አልነበረም። እጅግ የበረታ፣ ከዛሬ ርቆ ነገንና ከነገ ቀጥሎ ያለውን ትውልድ ባገናዘበ መልኩ የሚሰጥ የትምህርት ሥርዓት አላቸው።

ወደሕንድና አሜሪካ ብትሄዱ በትምህርት ሥርዓትና ግንዛቤ ከእኛ ምን ያክል ርቀው እንደቆሙ እንረዳለን። ዓለም የገባው እኛ ያልገባን ወይም ደግሞ ገብቶን ግን ደግሞ በገባን ልክ እየተገበርነው ያልሆነ የትምህርት ሥርዓታችን ነው። እኛ ለምን የመውጫ ፈተና አስፈለገ? ስንል እናጉረመርማለን ከላይ በጠራሁላችሁ ሀገራት ያሉ ተማሪዎች ግን አይደለም ለውጥ የሚያመጣ ሥርዓትን ሊኮንኑ ቀርቶ በዝቅተኛ የትምህርት ሥርዓት መንግሥትን የሚሞግቱ ናቸው።

ዜጎች የሥርዓት መልኮች ናቸው። የዛሬውን እኛንና ሀገራችንን የፈጠራት የትናንት የትምህርት ሥርዓታችን ነው። የመጣንበት የመማር ማስተማር ሥርዓት በምንፈልገው ልክ ሀገር ካልሰጠን፣ በምንፈልገው ልክ ትውልድ ካልቀረጸልን፣ በምንፈልገው ልክ እውቀትን መሠረት ያደረገ በራሱ የሚተማመን ዜጋ ካልፈጠረልን ለአዲስ ሥርዓት እንገደዳለን።

ትምህርት ሚኒስቴር ለአዲስ ሥርዓት የተገደደው በዚህ ዓይነቱ ተግዳሮት ነው። ተግዳሮቶቻችን ወደ በረከት ተቀይረው በምንፈልገው መልኩ ውጤት እስኪሰጡን ድረስ የሥርዓቱ አንድ አካል በመሆን ለጋራ ጥቅም በጋራ መቆም ነው ሊያስጨበጭብልን የሚገባው።

ሀገር እንፈልጋለን፣ በሥልጣኔ ወደፊት መሄድ የሁላችንም የጋራ ህልም ነው ግን ከእንዲህ ዓይነቱ የእረፍት ምኩራብ ለሚያደርሱን ለአዲስ ሥርዓቶች የምናጉረመርም ነን። ባለፈው የትምህርት ሥርዓት ላይ ብዙ ጥናቶች ተደርገው እጅግ የሚያሳዝን ውጤቶችን ሰምተናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ እኔም በነፃ ሀሳብ አምድ ስር የተለያዩ ጽሑፎችን አስነብቤአለሁ።

የእውቀት ጽንሰ ሀሳብ የማይገባበት ስፍራ የለም። የሀገራት ነባራዊ የሥልጣኔ ልኬት በትናንትና በዛሬ በነገም የእውቀትና የሥርዓት የመርህም አቅጣጫ የተወሰነ እና የሚወሰን ነው። በሀገራችን ውስጥ ከትናንት እስከዛሬ የታዩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም የማኅበራዊ ጥያቄዎች እውቀትንና የመማር ማስተማርን ሥርዓት ተንተርሰው የተነሱ እንደሆኑ እማኝ አያሻም።

እንደሀገር ብዙ ቀዳዳዎች አሉብን። የቀዳዳዎቻችን መነሻ የእውቀት ክፍተት እንደሆነ እናምናለን። ክፍቶቻችንን ለመጠገን ያለን አማራጭ በእውቀት የሚመራ የትምህርት ሥርዓት መገንባት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎች በመንግሥት ተቋም ውስጥ ብሔራዊ ፈተናቸውን ወስደው በሰማነው ውጤት ሥርዓታችን ምን እንደነበር ታዝበናል።

ከዚህ ባለፈ የትምህርት ሥርዓቱን ጥብቅና አስተማማኝ ለማድረግ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የመውጫ ፈተና ተዘጋጅቷል። በዚህ ፈር ቀዳጅ ጅማሪ ውስጥ የምንናፍቃት ኢትዮጵያ የድህነት ማቋን አውልቃ አዲስ እንደምትለብስ እናምናለን። ይሄ አሁን ላለችውና ወደፊትም ለምትፈጠረው ኢትዮጵያ ተስፋን የሚሰጥ የሥርዓት ለውጥ ነው።

የትምህርት ሚኒስቴር የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ይረዳኛል፣ ትውልድ እና ሀገርን ከውድቀት ይታደጋል ብሎ በሚያምነው አዲስ የትግበራ አቅጣጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ አጋርነቱን እየተወጣ ነው። በዚህም የመጀመሪያ በሆነው እና አዲስ ለውጥን ያመጣል ተብሎ በታመነለት የመውጫ ፈተና ከግልም ከመንግሥትም 180 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ፈተናው ላይ ይቀመጣሉ ተብሎ ይታሰባል።

ከሐምሌ 3 እስከ ሐምሌ 8 በተሰጠው የኦንላይን የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና ላይ ተቋማት ተማሪዎቻቸውን ዝግጁ በማድረግ ለፈተናው ቀርበዋል። ከዚህ የመውጫ ፈተና ጋር በተያያዘ ፈተናውን ማለፍ የማይችሉ ተማሪዎች ፈተናውን ደግመው የመውሰድ ዕድል የተመቻቸላቸው ሲሆን፤ በተማሪዎች ምረቃ ላይ የሚሳተፉት ግን የመውጫ ፈተናውን ያለፉ ተማሪዎች ብቻ እንደሚሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።

የትምህርት ሚኒስቴር እንዲህ ዓይነቱን አዲስ ትግበራ ሲጀምር በብዙ ጥናት ውስጥ አልፎ ነው። ሀገራችን አሁን ካለችበት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ትኩሳት እንድትወጣ እውቀትን መሠረት ያደረገ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል። ይሄ እምነት መሬት ወርዶ ውጤት እንዲያመጣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሊሆን የሚችለው ካለፈው የተሻለ፣ ጥራትን መሠረት ያደረገ የመማር ማስተማር ሥርዓትን መዘርጋት ነው።

በዚህም መሠረት ከፈተና አወጣጥና ከአስተራረም ጀምሮ ባለው ሂደት ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለውጥ አድርጓል። ተማሪዎች በመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብተው እንዲፈተኑ ከዚያ በኋላም ባለው ጊዜ የመውጫ ፈተናዎችን በማዘጋጀት ቁርጠኝነቱን ጀምሯል። ይሄ በእንዲህ እያለ የመምህራኖችን የብቃት ምዘና እና ትክክለኛነት ከማረጋገጥ አኳያ ረጅም ርቀት የሚያስኬድ ትልም ተልሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

የሚያስፈልገን የሥርዓት ለውጥ ነው። የመጣንበት እና ወዴትም ያላደረሰንን የትምህርት ሥርዓታችንን ጥራት ተኮር በሆነ አዲስ እሳቤ መቀየር አለበት። ፖለቲካችን አንድ ዓይነት ነው፣ ኢኮኖሚያችን፣ የትምህርት ሥርዓታችን እንደነበረ ነው። እኛም ትውልዱም እንደነበርን ነን።

ወደፊት የሚወስድ፣ ወደህልማችን የሚያደርስ አዲስ ሥርዓት በሁሉም ረገድ ያስፈልገናል። ህልም የሚጀምረው ከሀሳብ ነው። በልባችን ውስጥ የማደግ፣ የመለወጥ ህልም አለ። ለህልማችን የሚመጥን ሀሳብና ሥርዓት ግን የለንም። ያጣነው ምን እንደሆነ ማወቅ አለብን። ያጣነው ሥርዓት አይደለም፣ ያጣነው ህልም አይደለም። ያጣነው ለውጥ ተኮር የሆነ ሥርዓት ነው።

ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን ብለን ስንናገር ትልቅ የሚያደርገንን የኃይል ሞገድ ተላብሰን ሊሆን ይገባል። የሰው ልጅ ካለ እውቀት፣ ካለ በጎ ሥርዓት ትልቅ ሊሆን አይችልም። ብዙዎቻችን ትልቅ መሆንን ከንግግር ባለፈ፣ ከምኞት ባለፈ በተግባር ስንገልጠው አንታይም።

በተዓምር ትልቅ የሆነ ሀገር እና ሕዝብ የለም። ትልቅነት ያለው በተፈተነ ተግባር ውስጥ ነው። ወዳለፈው ጊዜ ብኩርናችን ለመመለስ እንዳለፈው ጊዜ ዓይነት የአብሮነት ሥርዓት ያሻናል። ወደምንመኘው የማደግ እና የመለወጥ እውነታ ለመጠጋት ከኩረጃ በጸዳ፣ ጥራት ተቀዳሚው በሆነ የመማር ማስተማር መርህ ውስጥ ማለፍ ይጠበቅብናል።

ትልቁ ጥያቄ በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ምንድነው? የሚለው ነው። የዚህ ጥያቄ መልስ ለሁላችንም ግልጽ ነው። በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሰላም ነው። ተነጋግሮ መግባባት ነው። አንድነት ነው። ጥራት ያለው ትምህርት ነው። እኚህ እውነታዎች ወደሕይወታችን እንዲመጡ ለእነዚህ እውነቶች የሚሆን ትውልዱ ራሱን ችሎ በኩራት የሚረማመድባት ሥርዓት ያስፈልገናል።

የለመድናቸው ብዙ ልማዶች አሉ። እነዚያ ልማዶች ድህነትንና ኋላቀርነትን ከፍ ሲልም በትምህርት ሥርዓቱ ላይ እየታየ እንዳለው ዓይነት የእውቀት ክፍተትን ከመስጠት ባለፈ ፋይዳ አልነበራቸውም። በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት አዲስ ሀገር እና አዲስ ትውልድን እንደምንገነባ እያየናቸው ካሉ ለውጦች መረዳት እንችላለን። እናም ጥራት ላላት ሀገር ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት በምንም የማይወዳደር ከኋላቀርነት መውጫ በትረ ሙሴዋ እንደሆነ በመጠቆም ላብቃ።

 በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *