ትኩረት የሚሻው ሳይማሩ የሚሠሩና ማስረጃ የሚሸጡ ተቋማትን የማደን ጉዳይ

ኢትዮጵያ ውስጥ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የመማር ህልም ያላቸውን ዜጎች ተስፋ ያስቆረጠ፤ በትክክለኛው መንገድ ተምረው የዲግሪ ባለቤት የሆኑ ዜጎችን የሥራ ዕድል ያጣበበ፤ አገልግሎት ፈላጊ ዜጎቻችንን ለእንግልትና ለጉዳት የዳረገ ከባድ ቀውስ ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል።

በኢትዮጵያ ምድር ከትናንት እስከ ዛሬ ሀሰተኛና የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃ የያዙ በርካቶች ናቸው። ሳይማሩ የሚሠሩም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ከመቼው ደርሶ ማስተርስ ያዘ፣ ከመቼው ደርሶ ዲግሪ ያዘ የሚባልላቸው በርካቶች ናቸው። በርካቶች ከመማር ይልቅ ዲፕሎም እና ዲግሪ ገዝተዋል።፡

እነዚህ በሀሰት ማስረጃ የሙያ ባለቤት የሆኑ ግለሰቦች የኪሳራ አቅምና ጥፋት መጠን በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በሀሰት ማስረጃ መምህር የሆነ ሰው በሥነ ምግባር፣ በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የታነፀ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት አይችልም።

በሀሰት ማስረጃ ዶክተር የሆነ ሰው አክሞ ማዳን አይቻለውም። በሀሰት ማስረጃ ዳኛ የሆነ ሰው በሙያው ሰዎችን እኩል አያይም። በመርህና በሕግ ተመስርቶ ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ ጥቅማ ጥቅምን መሠረት ያደረገ ውሳኔን ቀዳሚ ምርጫው ያደርጋል።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ አንድ የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛ አይደለም የሚባለው ሃሰተኛ ስለሆነ ብቻም አይደለም። ተቋማቱ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲያስተምሩም፣ መስፈርቱን ያላሟሉ ተማሪዎችን ተቀብለው ሲያስተምሩ እና በሌሎች መንገዶች ሕግን ባልተከተለ መልኩ የተገኘ የትምህርት ማስረጃ ጭምር ነው።

የኢፌዴሪ የትምህርት ሥልጠና ባለሥልጣን የትምህርት ጥራትን ከመቆጣጠር ባሻገር የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነትን የማረጋገጥ ሥራን የሚከውን ተቋም ነው። የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ፣ ከሀገር ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተገኙ የትምህርት ማስረጃዎችን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ የሚከናወን ነው።

ሂደቱ አንድ ከሀገር ውስጥ የተገኘ የትምህርት ማስረጃ የሚያቀርበው ምሩቅ የእውቅና ፈቃድ ባለው ተቋምና የትምህርት መስክ ተመዝግቦ መማሩን፤ በሀገሪቱ የመግቢያ መስፈርት የተመዘገበ እና በሥርዓተ- ትምህርቱ መሠረት የሚጠበቁበትን አሟልቶ ስለመመረቁ የሚረጋገጥበት ነው።

የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እየተበራከተ ስለመምጣቱ ከአመት አመት የሚወጡ ቁጥራዊ ማስረጃዎች በግልጽ ያሳያሉ። የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን በዘንድሮ በበጀት አመቱ ፍተሻ ከተደረገባቸው 22ሺ የትምህርት ማስረጃዎች 10 በመቶዎቹ ሐሰተኛና መስፈርቱን የማያሟሉ መሆናቸውን ማሳወቃቸውም አይዘነጋም።

የትምህርትና ሥልጠና የባለሥልጣን የተቋማት ቁጥጥርና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቸሩጌታ ገነነም፤ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ የችግሩን ግዝፈት ቁጥራዊ በሆነ መልኩ አስደግፈው ማብራሪያ ሰጥተውበታል።

‹‹ከዚህ በፊት የይረጋገጥልኝ ጥያቄ በስፋት የሚመጣው ከግለሰቦች ነበር›› ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አሁን ላይ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት በመጣ አቅጣጫ መሠረት የሁሉም ተቋማት ሠራተኞችን የትምህርት ማስረጃ ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው። በበጀት አመቱ 40 የሚሆኑ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞችን የትምህርት ማስረጃዎች የማረጋገጥ ሥራ መሠራቱንና ውጤቱም በቀጣይ ይፋ እንደሚሆንም ለማወቅ ተችሏል።

በአሁኑ ወቅትም የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣንን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሐሰተኛ ውጤት ገዝተው በሕገወጥ መንገድ ሥራ ላይ በተቀመጡ አካላት ላይ መረር ያለ አቋም መያዛቸውን ተከትሎ በሁሉም አቅጣጫ በርካቶች ሲደናበሩ ይስ ተዋል ጀምሯል።

አንዳንድ የትምህርት ተቋማትም በስማቸው የሐሰተኛ የትምህርት መረጃ እንደወጣና ቅጥር የሚያወጣ ተቋም ሁሉ ቅድሚያ ከእነርሱ ጋር ትክክለኛ መረጃ ሊለዋወጥ እንደሚገባ መጠቆም ጀምረዋል። በስልጤ ዞን በተደረገ ፍተሻ በርካቶችን ማጋለጥ ሲቻል አንዳንዶች እግሬ አውጪኝ ማለታቸውም ይታወሳል።

አሁኑ ወቅት መሰል እርምጃዎችን በመራመድ በተደረጉ ማጣራቶች ተገኙ የተባሉት የሐሰተኛ ማስረጃዎች በጥቂት ተቋማት ብቻ መሆኑ ደግሞ ጠንከር ያሉ ምርመራዎች ቢደረጉ ከዚህም የላቁ ሐሰተኛ መረጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቋሚ ነው።

ሳይማሩ የሚሠሩና ማስረጃ የሚሸጡ ተቋማትን የማደን ጉዳይ የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን ከሚሠራው እልህ አስጨራሽ ተግባራት ተለይቶ ሊታይ የሚችል አይደለም። መሳ ለመሳ መታየት ያለበት ዐብይ ጉዳይ ሊሆንም የግድ ነው።

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ባዘጋጀው የአሠራር ረቂቅ መመሪያና ስታንዳርዶች ውይይት መድረክ ባስተላለፉት መልዕክት፣‹‹ከዚህ በኋላ የተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ እንደ ከረሜላ ማደል ማቆም አለብን ›› ማለታቸው ይታወሳል።

ሚኒስትሩ ‹‹በሁሉም የፌዴራል ተቋማት የሠራተኞችን ማህደር መመርመር ጀምረናል። ምን ያህሉ እውነተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዞ ነው? ምን ያህሉ አይደለም የሚል ምርመራ እያካሄድን ነው፤ ከራሳችን ጀምረን» ማለታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

የመንግሥት መሰል ቆፍጣና አቋምና እርምጃም እጅጉን የሚበረታታ ነው። ይሁንና አሁንም ቢሆን ለሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ዘላቂ መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል። ሀገር ተረካቢ መልካም ዜጎች ለማፍራት በትምህርት ዘርፉ ትክክለኛ ደንቦችና ፖሊሲዎችን መተግበር ያስፈልጋል።

መንግሥት ደንብና ፖሊሲዎች ላይ ማሻሻያ ከማድረግ ባለፈ ለተፈጻሚነቱ በቁርጠኝነት መሥራት አለበት። እንደ ሀገር መወሰድ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ መንግሥት ግልፅ የሆነ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይኖርበታል። ሂደቱን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ማስተሳሰርም ፈፅሞ ሊዘነጋ አይገባም።

የተመረቁ ተማሪዎችን የትምህርት ማስረጃ ትክክለኝነት የሚያረጋግጥ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን ከሁለት አመት አስቀድሞ ሰምተን ነበር። አሠራሩ ተቋማት እና ግለሰቦች ሠራተኞችን ለመቅጠር በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንዳይታለሉ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው እንደመሆኑ ወደ ሥራ የሚገባበትን አግባብ ማፍጠን ያስፈልጋል።

የትምህርት ተቋማትም ከሕግና ደንብ በላይ የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ብቁ ዜጎችን የማፍራት ሞራላዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው በቁርጠኝነት መሥራት የግድ ይላቸዋል። ተቋማቱ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን የማፍራት ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት መሸከማቸውን ተገንዝበው የተቀመጡ ደንብና መመሪያዎችን አክብረው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

የተማሪዎቻቸውን ዝርዝር መረጃና የትምህርት ማስረጃ ከምዝገባ እስከ ምረቃ ድረስ ለሚመለከተው ባለድርሻ አካል የመላክ ግዴታ እንዳለባቸውም ሊዘነጉት አይገባም። ተማሪዎችም ቢሆን ወደ ትምህርት ተቋማት ከመግባታቸው አስቀድሞ ተቋማቱን ፈቃድና አስፈላጊውን መስፈርት ስለ ማሟላታቸው ማረጋገጥን መዘንጋት አይኖርባቸውም።

ከዚህም በላይ ግን በሐሰተኛ ማስረጃ መንቀሳቀስ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ራሳቸውን አሊያም ቤተሰባቸውን እንደሚያሳጣቸው ጠንቅቀው ሊረዱት ይገባል። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሰጡ ተቋማትን በሕገ-ወጥ መንገድ ዲግሪ ያገኙ ተመራቂዎች፤ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ከጠቅላይ አቃቢ ሕግ ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ፣ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር እንዲሁም ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በጋራ መሥራት ይኖርበታል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *