የሩሲያና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ታሪካዊም ተምሳሌታዊም ነው!

በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለው የትብብር ግንኙነት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ስለመሆኑ የታሪክ መዛግብት ያትታሉ። በእነዚህ ከአንድ ምዕተ ዓመት በተሻገሩ ረጅም ዓመታት የሀገራቱ ሕዝቦች ሰፊ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት መሥርተዋል። ይህ የቆየ ጠንካራ ግንኙነታቸው ለዛሬ ትብብራቸው ጠንካራ መሠረት እና አቅም እንደሆነ ይታመናል።

በተለይም የሩሲያ ሕዝብና መንግሥት ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንደ ሀገር ስጋት ውስጥ በሚከቱ የፈተና ወቅቶች በገጠማቸው ጊዜ፤ ለችግራቸው መሻገሪያ አቅም የሚሆኑባቸው ወዳጅ ፈልገው በሚጣሩበት ወቅት ጥሪያቸውን ሰምተው ፈጥነው በመድረስ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው። ይህን ውለታቸውም በትውልዶች መካከል ሁሌም የሚዘከር የወዳጅነት፣ የክፉ ቀን ባለውለታነት ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

የታሪክ መዛግብት እንደሚጠቁሙት፤ ሩሲያውያን ለኢትዮጵያውያን ያላቸው አጋርነትና ድጋፍ የትብብራቸውን ዘመን ያህል ከረጅም ጊዜ አንስቶ የሚቆጠር ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያውያን የፋሺስቶችን የወረራ ጉዞ በመግታት ስለነፃነት ተጋድሎ ባካሄዱት በዓድዋው ጦርነት ወቅት ሩሲያውያን ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ወታደራዊ ርዳታን ጨምሮ፣ የሕክምና ድጋፍ አድርገዋል ።

በተመሳሳይ በውጪ ኃይሎች አይዞህ ባይነትና ያላሰለሰ ጥረት በእብሪት ድንበር ጥሶ የሀገርን ዳር ድንበር የተዳፈረውን የዚያድ ባሬ ወራሪ ጦር ተከላክሎ፤ በአሸናፊነት ለመወጣት በተደረገው ተጋድሎ የሩሲያ ወታደራዊ ድጋፍ ከፍ ያለ ሀገራዊ አቅም እንደነበር ይታወሳል።

በቅርቡም የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ሀገር እንደ ሀገር የሕልውና አደጋ ውስጥ በወደቀችበትም ወቅት፤ አጋጣሚውን በመጠቀም የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ ሲደረጉ የነበሩ ሴራዎችን በማክሸፍ፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት በኩል ሲደረጉ የነበሩ የተደጋገሙ የማዕቀብ ሙከራ ጫናዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ሩሲያ ከኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም አጋርነቱን በተጨባጭ አሳይቷል።

ይሄ ደግሞ ሩሲያ እና ሩስያውያን ለኢትዮጵያ ያላቸውን የማይዋዥቅ አጋርነት ከመግለጹም በላይ፣ ይሄንን አቋማቸውን (ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ያላቸውን ጠንካራ አቋም) በዓለም አቀፍ መድረክ በግልጽ ሁሉም እንዲገነዘበው አድርጓል።

በዚህ መልኩ ከሚገለጽ የዲፕሎማሲ እና የጦር አጋርነት ባሻገር፣ በትምህርት እና ሌሎችም መስኮች ለኢትዮጵያ ከፍ ያለ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እያደረገም ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል በደርግ ዘመነ መንግሥትም የሩሲያ መንግሥት እና ሕዝብ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ብዛት ላላቸው ኢትዮጵያውያን የትምህርት ዕድል በመስጠት፤ ሀገሪቱ የነበረባትን የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ትርጉም ባለው መንገድ መቅረፍ የሚያስችል ድጋፍ አድርገዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ምሑራንና ባለሙያዎችን በማፍራትም ባለውለታ መሆን ችለዋል።

ይህ የሩሲያ መንግሥትና ሕዝብ ከፍያለ ቁርጠኝነት የሚንጸባረቅበት ወዳጅነት፤ በሁለቱ ሀገራትና ሕዝቦች በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ላይ ለተመሠረተው ቀጣይ ግንኙነት ጠንካራ የመሠረት ድንጋይ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ።

በተለይም ከጋራ ተጠቃሚነት ይልቅ፤ ራስ ወዳድነትና የአንድ ወገን ተጠቃሚነት ዓለም አቀፍ መርሕ መስሎ በሚገለጥበት በዚህ ወቅት፣ አሁነኛውን የዓለም የተዛባ አካሄድ ከመቀየር አኳያ እንደ አንድ ትልቅ ተሞክሮ ሊወሰድ የሚችል ነው ።

ይህ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደገው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመረችው ሀገራዊ ጥረት ትልቅ አቅም ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ከዚያም በላይ ሀገሪቱ የብሪክስ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ የሚኖረው አስተዋፅዖም ከፍ ያለ እንደሚሆን ይታመናል።

በሁለተኛው የሩሲያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ቅዱስ ሴንት ፒተርስበርግ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በነበራቸው ቆይታ ‹‹ሩሲያ ወንድም ሀገር ነው ፤የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማሳደግና ለመወያየት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ማለታቸውም ከዚህ ተጨባጭ እውነታ በመነሳት ነው!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *