ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግና ኮምፌዴሬሽን ዋንጫ የሚሳተፉት ቅዱስ ጊዮርጊስና ባህርዳር ከነማ በመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል፡፡ በቻምፒዮንስ ሊጉ የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንዚባሩን ኬኤምኬኤምን ሲያስተናግድ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊው ባህርዳር ከተማ የታንዛኒያውን አዛም ይገጥማል፡፡
በ2023/24 የውድድር ዓመት የሚደረጉት የአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ እና የኮምፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ መርሀ ግብሮች ከትና ንት በስቲያ በግብፅ ካይሮ በተካሄደው የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ይፋ ተደርገዋል፡፡ በወጣው ድልድል መሰረትም ኢትዮጵያን የሚወክሉ ክለቦች በቅድመ ማጣሪያውና በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ተጋጣሚያቸውን አውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን የሆኑት ፈረሰኞቹ በቻምፒዮንስ ሊግ በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ የዛንዚባሩን ክለብ ይገጥማሉ፡፡ የመጀመሪያውን ጨዋታ ከሜዳ ውጪ የሚያደርጉት ፈረሰኞቹ በአንጻራዊነት ቀለል ያለ ተጋጣሚ ያገኙ ሲሆን፤ የማለፍ ቅድመ ግምትም አግኝተዋል፡፡ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታውን ከነሐሴ 12 እስከ 13 /2015 ዓ.ም እና የመልስ ጨዋታውን ደግሞ ከነሐሴ 19 እስከ 20 /2015 ዓ.ም የሚያከናውን ይሆናል፡፡ ፈረሰኞቹ ይህንን ክለብ በደርሶ መልስ ውጤት አሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ የሚችሉ ከሆነ በሁለተኛው ዙር የመድረኩ ቻምፒዮን
ከሆነው የግብፁ ሀያል ክለብ አል አህሊ ጋር ይገናኛሉ። የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ከመስከረም 4-6 እና ከመስከረም 18-20 2016 ዓ.ም ባሉት ቀናቶች የሚካሄዱ ይሆናል፡፡
የፈረሰኞቹ ተጋጣሚ ኬኤምኬኤም በሀገር ውስጥ ውድድሮች የዋንጫ አሸናፊ ሲሆን፤ በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ለአምስት ጊዜያት ተሳትፎ ማድረግ ቢችልም ይህ ነው የሚባል ውጤት የለውም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ በሀገር ውስጥ ውድድሮች ስኬታማ ሲሆን በአፍሪካ ክለቦች መድረክም የካበተ የተሳትፎ ልምድ አለው፡፡ በቻምፒዮንስ ሊግ ከአስር ጊዜ በላይ ተሳትፎ በማድረግ በአብዛኞቹ ከቅድመ ማጣሪያ ውድድሮች ሲሰናበት በታሪክ አንድ ጊዜ የምድብ ድልድል ውስጥ መግባት ችሏል፡፡ አንጋፋው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ለ2ኛ ተከታታይ ጊዜ በማንሳት ለመድረኩ ተሳትፎ የበቃ ሲሆን፤ ተጋጣሚው በበኩሉ ስምንት ጊዜ የዛንዚባር ፕሪሚየር ሊግን አሸንፏል፡፡ ፈረሸኞቹ በዘንድሮው ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ባደረጓቸው 30 ጨዋታዎች 64 ነጥቦችን በመሰብሰብ የሊጉ ቻምፒዮን ሲሆኑ 54 አራት ጎሎችን በተጋጣሚዎቻቸው መረብ አስቆጥረው 33 ግቦችን አስተናግደዋል፡፡ በአፍሪካ መድረክ ካላቸው ልምድ አኳያ የመጀመሪያውን ዙር በቀላሉ ያልፋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚሳተፉት የጣና ሞገዶች በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የታንዛኒያው ጠንካራ ክለብ አዛም ገጥሟቸዋል፡ ፡ የጣና ሞገዶቹ ይህንን ጨዋታ ካሸነፉ በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ጨዋታ ከቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ጋር የሚገናኙ ይሆናል። የመጀመሪያ ዙር ጨዋታው ከነሀሴ 12/13/2015 ዓ.ም እንዲሁም የመልስ ጨዋታው ከነሀሴ 19/20/2015 ዓ.ም ባሉት ቀናቶች ይደርጋል። ሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታዎች ከመስከረም 4/6/2016 ዓ.ም ባሉት ቀናቶች እንዲሁም የመልስ ጨዋታዎች ከመስከረም 18/20/2016 ዓ.ም ባሉት ቀናቶች እንደሚደረጉም ተገልጿል።
የጣና ሞገዶቹ በአፍሪካ መድረክ ሲሳተፉ በታሪክ የመጀመሪያቸው ሲሆን፤ ተጋጣሚያቸው አዛም በበኩሉ ብዙም የተሳትፎ ታሪክ የለውም፡፡ ባህርዳር በ2010 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን ካረጋገጠ በኋላ ዘንድሮ በሊጉ ተፎካካሪ ሆኖ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው የሚመሩት የጣና ሞገዶቹ በዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ 30 ጨዋታዎችን አድርገው 60 ነጥቦችን መሰብሰብ የቻሉ ሲሆን 51 ጎሎችን በተቃራኒ መረብ አስቆጥረው የተቆጠረባቸው የጎል ብዛት 30 ነው፡፡ አዛም በበኩሉ ከተመሰረተ ዘጠኝ ዓመታትን ብቻ ቢያስቆጥርም በሀገር ውስጥ ውድድር ስኬታማ ክለብ ሲሆን በዘንድሮ የውድድር ዓመት በታንዛኒያ ፕሪሚየር ሊግ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡
ፈረሰኞቹ እና የጣና ሞገዶቹ በአሁኑ ወቅት በእረፍት ላይ ሲሆኑ፤ ከእረፍት መልስ በቅርቡ ለአህጉራዊ ውድድሮቹ ጠንካራ ዝግጅት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ክለቦቹ በአፍሪካ መድረክ ያለባቸውን ውድድር እና የ2016 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ ታሳቢ በማድረግ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው የመቀላቀልና ኮንትራት የማደስ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም