ራሱን እንደነሐሴ የጠዋት ዝናብ በማያባራ ጭንቀት ውስጥ ከቶ እየባዘነ ያለው ተሰማ መንግስቴ ፊቱ ገርጥቷል። በሥራው ለምን ደስተኛ እንዳልሆነ እያሰላሰለ ሳያስበው ጓደኞቹ ከሚጨዋወቱበት ማምሻ ግሮሰሪ ደረሰ፡፡ ዘውዴ መታፈሪያ እና ገብረየስ ገብረማሪያም እንደልማዳቸው ፊታቸው በፈገግታ ተሞልቶ ይሳሳቃሉ፡፡
እነ ዘውዴ ተሰማን እንዳዩት ምን እንደሆነ ለመጠየቅ አላመነቱም፡፡ እርሱ ግን ምላሽ ለመስጠት ተቸገረ፡፡ ለማስረዳት ግራ ገባው፤ ለተወሰነ ደቂቃ በዝምታ ቆየ። ቀጠለና ‹‹በየሔድኩበት እያጋጠመኝ ያለው ኃላፊነትን መሸሽ እና ግዴታን አለመወጣት ያበሳጨኛል። እኔው ከምመራው ቡድን ጀምሮ በየሔድኩበት የማገኘው አገልጋይ ባለሙያም ሆነ የሥራ ኃላፊ በግልፅ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በትጋት ከመስራት ይልቅ በተቃራኒው ዳተኝነት እና ቸልተኝነታቸውን እያየሁ ውስጥ ውስጤን መብገን ከጀመርኩ ቀናቶች ብቻ ሳይሆኑ ወራቶች አልፈው ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ለምን ግዴለሽነት እንዲህ በረታ ? የሚለው ሃሳብ ማስጨነቅ ከጀመረኝ ሰነባበተ፡፡ አሁን ደግሞ እኔም በሥራዬ በፍፁም ደስተኛ መሆን አልቻልኩም፡፡›› ብሎ በረዥሙ ተነፈሰ፡፡
ዘውዴ ተሰማን እያየ ፤ ‹‹አዲስ ሆንክ እንዴ ? ኃላፊነትን መወጣት ብርቅ ከሆነ ቆየ፡፡ አንዳንዱ በግዴለሽነት አንዳንዱ ደግሞ ሌላውን ስለማያምን ከሥራ ኃላፊ ጀምሮ እስከ ባለሞያ ግዴታን የመወጣት እና ውሳኔዎችን የማስተላለፍ ጉዳይ ፈተና ከሆነ ከራረመ፡፡ ከወረዳ እስከ ክልል እና የፌዴራል መንግስት ተቋማት ድረስ አለመወሰን እና ግዴታን አለመወጣት እንደመብት መቆጠር ከጀመረ ሰነበተ፡፡ ኃላፊነት እያለበት በግዴለሽነት ውሳኔ ባለማስተላለፍ ለሚደርሰው ኪሳራ ማንም ተጠያቂ አይሆንም፡፡ ይልቁኑ እንዲያውም ግዴታዬን ልወጣ ብሎ ውሳኔ ያስተላለፈ ሰው ትንሽ ስህተት ከፈፀመ መሳሳቱ ካለመወሰኑ በላይ ዋጋ ያስከፍለዋል፡፡
ዋናው ችግር እያንዳንዱ ሰው ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ተጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታ አለመኖሩ ነው። ስለዚህ ባለሞያዎች እንደመፍትሔ የያዙት ኃላፊነትን አለመወጣት፤ አመራሮች ደግሞ ውሳኔ ከማሳለፍ ይልቅ እያሳደሩ እና ወደ ሌላ እያንከባለሉ ከህዝብ የተሰበሰበውን ግብር በደሞዝ እና በአበል መልክ እየተቀበሉ መቀለብን ዋነኛ የሕይወታቸው ገፅታ አድርገውታል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ መደበኛ ሆኖ መቀጠሉን መካድ አይቻልም፡፡ ›› ብሎ ዘውዴ ገብረየስም ሃሳቡን እንዲሰጥ መፈለጉን በሚያሳብቅ መልኩ ሃሳቡን እንደጨረሰ ለማሳየት የገብረየስን ዓይን ማየት ጀመረ፡፡
ገብረየስ በበኩሉ ‹‹ ትክክል ብለሃል፤ በዚህ ዘመን ኃላፊነትን መወጣት ‹ ለፍቅር ብቀርባት ለጠብ አረገዘች› እንደሚባለው ዓይነት ዋጋን ያስከፍላል፡፡ መሬት አስተዳደር እየሰራሁ በነበርኩበት ወቅት ከውሳኔ ጋር በተያያዘ ችግር አጋጥሞኝ ነበር፡፡ አንድ ባለሞያ የመሬት ልኬት እንዲሠራ ታዘዘ፡፡ ባለሞያው የለመዳት ምልጃ አለች፡፡ ሰዎቹ ደግሞ የምልጃ ገንዘብ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑለትም፡፡ ስለዚህ ጉቦውን አላገኘምና ሥራውን አልሠራም፡፡
ሰዎቹ ቢሮዬ ድረስ አቤቱታ ይዘው ቀረቡ፡፡ ጠርቼ ለምን ሔዶ ግዴታውን እንዳልተወጣ ጠየቅኩት። የቆየው ሥራ ስለበዛበት መሆኑን ገልጾ፤ በዛ ቀን ሔዶ ለመለካት አቅዶ እንደነበር ተናገረ፡፡ አሁኑኑ ሂድና ለካ አልኩት፡፡ ነገር ግን ትዕዛዜን አልፈፀመም፡፡ ልለካ ሄጃለሁ ብሎ የሔደው ወደ ራሱ ቤት ነበር፡፡
በማግስቱ ‹ልኬቱ ይሔ ነው› ብሎ አቀረበ፤ በልኬቱ መሠረት ሰዎቹ የሊዝ ክፍያ እንዲፈፅሙ አስተላለፍኩ። ሰዎቹ ባለሞያው እንዳልተላከላቸው ሳይናገሩ የተላለፈውን ውሳኔ ተቀብለው ሊከፍሉ ወደ ሒሳብ ክፍል ሲያመሩ ገንዘቡ በዛባቸው፡፡ መልሰው ለእኔው አለቃ እኔን ከሰሱ፡፡ ክሳቸው እኔ በልኬቱ መሠረት ይክፈሉ ብዬ ማስተላለፌን በመቃወም፤ ‹የተጋነነ ክፍያ እንድንፈፅም ያደረገው እርሱ ነው፡፡› የሚል ነበር፡፡
የይከፈል ውሳኔ ከማስተላለፌ በፊት ይዞታቸውን ሳጣራ ደረጃ አንድ ነው፡፡ ባለሞያው ለክቻለሁ ብሎ የገለፀው መሬት ስፋት መጠን ደግሞ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ክፍያውን ይፈፅሙ ብዬ ውሳኔ አስተላለፍኩ፡፡ ነገር ግን ባለሞያው የመሬቱን ስፋት የገለፀው በጂ አይ ኤስ ፕላን ላይ በተመሠረተ ግምት ሲሆን፤ ግምቱ መሬት ላይ ካለው ጋር ትልቅ ልዩነት ነበረው፡፡ በእርግጥም ክፍያው የተጋነነ ሆኖባቸዋል፡፡ ከብዙ ማጣራት በኋላ ሠራተኛው ሄዶ እንዳልለካ ተረጋገጠ፡፡ ነገር ግን ቀድሞም ቢሆን ከአለቃዬ ጋር የነበረኝ ግንኙነት የሻከረ ስለሆነ፤ የእነርሱ ክስ ተጨምሮ እኔን ብዙ ዋጋ አስከፈለኝ፡፡
ተገልጋዮቹን አለቃዬ ይምራበት ብዬ ወደ እርሱ መላክ እችል ነበር፡፡ ምክንያቱም ወደ እርሱ መምራት መብቴ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ እርሱ ብልካቸው ገንዘብ እንደሚጠይቃቸው እና ብዙ እንደሚያንገላታቸው ገምቼ ቶሎ እንዲፈፀምላቸው ብመራላቸውም የሆነው ተቃራኒ ነው፡፡ ስለዚህ ውሳኔ አስተላልፎ ችግር ውስጥ ከመግባት አለመወሰን የተሻለ መሆኑን አይቻለሁ፡፡›› ሲል ዘውዴ የተናገረውን ገብረየስ የራሱን አጋጣሚ አካቶ ዘመኑን በሚያሳይ መልኩ አብራራው፡፡
ዘውዴ ከገብረየስ ቀጠል አድርጎ ለተሰማ፤ ‹‹ አንተ እኮ የፖለቲካም የአስተዳደርም ሰው መሆን አትችልም። አንተ የምትመጥነው ለቀዳሽነት ብቻ ነው፡፡›› ብሎ እየተንከተከተ ሳቀ፡፡ ‹‹ለዛውም የመሬት አስተዳደር ላይ ሥራ ለመሥራት ከአንተ አስተሳሰብ የራቀ እና የረቀቀ አካሄድን ይጠይቃል፡፡ በደንብ ስለገንዘብ ጥቅም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ስል መሬት አስተዳደር ላይ የሚሠሩ ሰዎች በሙሉ ሌባ ናቸው ማለቴ አይደለም፡፡ ነገር ግን ደግሞ ብዙ ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ ማጭበርበርን፣ ጉቦ እና ምልጃን የለመዱ ሰዎች አሉ። የእነርሱ መኖር የአንተንም ቀና ውሳኔ አደጋ ውስጥ ይጨምረዋል፡፡ ስለዚህ በመጨረሻ እንደገብረየስ ትነጠላለህ፡፡›› አለው፡፡
ገብረየስ ግን በበኩሉ፤ ‹‹ እኔ ከሙስናው በላይ ይልቁኑ በዋናነት የማስበው ሰዎች ግዴለሽ እንዳይሆኑ ግዴታቸውን እንዲወጡ እንደውም ጭራሽ ሙሰኛ እንዳይሆኑ ዋነኛው መፍትሔው የቡድን፣ የተቋም፣ የአገር መድረሻ በግልፅ ታምኖበት መቀመጥ አለበት፡፡ ይህ ግልፅ መዳረሻ አለመኖር እና ሁሉም በሚፈልገው አቅጣጫ ኳስ እየዠለጠ መሮጡ ትልቅ ኪሳራ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
መዳረሻን አስቀምጦ መንቀሳቀስ ሲባል፤ በትክክል መዳረሻ ላይ ተማምኖ መሆን አለበት፡፡ ብዙ ተቋማት እና ተራ ቡድኖች ሳይቀሩ ትልልቅ መዳረሻዎችን ያስቀምጣሉ። ነገር ግን ተዋናዮቹ ባለሞያዎቹም ሆኑ የሥራ ኃላፊዎች መዳረሻቸውን መቀበል እና እንደርስበታለን ብለው ማመን ካልቻሉ ውጤቱ መዳረሻ ካለማወቅ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አሁንም ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ያለው ይኸው ግልፅ ግብን ለይተን በዛም ላይ ተማምነን ባለመንቀሳቀሳችን ነው፡፡ ሁሉም በዚህ ሳቢያ በማያስፈልግ አቅጣጫ ኳስ ሲጠልዝ፣ የሚፈጥረው ክፍተት እየተጠራቀመ አገራዊ መዳረሻ ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ጠባሳ ማየት ተስኖናል፡፡›› በማለት የሚያሰጋውን እና መፍትሔ ነው ብሎ የሚያምንበትን ተናገረ፡፡
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ በእርግጥም እናንተ እንደተናገራችሁት በአንድ ቡድን ውስጥ ግብን ለማሳካት ኃላፊነትን መወጣት እና ኃላፊነትን አለመወጣት ሁለቱም የሚያስገኙት ጥቅምም ሆነ የሚያስከትሉት ጉዳት ከሌለ ቢያንስ ሰዎች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ለመሞከር አይበረታቱም፡፡ እየሆነ ያለው ይኸው ይመስለኛል፡፡ ይህ አመለካከት ከአንዱ ወደ ሌላው እየተጋባ የቡድን፣ የተቋም እና የአገር ሥራ እየተበላሸ ለስኬት ማሰብ የማይጨበጥ ህልም ብቻ እየሆነብን ነው፡፡ ይሔ ደግሞ አደጋ ውስጥ ይከተናል፡፡
ነገር ግን በቀላሉ ሥራ ሠራሁም አልሠራሁም ለውጡ አልታይህ እያለኝ መሆኑ እያስጨነቀኝ ነው። ይህ በጣም አደገኛ እና በቀላሉ መታየት የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በእኔም ሆነ በሌሎች የሥራ ባልደረቦቼ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ከባድ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሰዎች እንደኔ አይነት ስሜት እየተሰማቸው ከቀጠለ ሥራቸውን በብቃት ማከናወንም ሆነ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ያዳግታቸዋል፡፡ ይህ ከእኔ እና ከአሁኑ ትውልድ አልፎ ኃላፊነትን አለመወጣት እና የራስን ተፈላጊ ሚና አለመጫወት ስር እየሰደደ ወደ ትውልዱ ከተላለፈ አገር ላይ ስጋት መደቀኑ አይቀርም፡፡
ይህ ሁኔታ እያሳሰበኝ ያለው በእያንዳንዱ የቡድኔ አባል ውስጥ እያስተዋልኩት በመሆኑ ነው፡፡ የእኔ ተግባር እነርሱም ኃላፊነት እንዳያድርባቸው ከማድረግ በተጨማሪ ኃላፊነቱን የሚወጣው ሰው ሥራም ይበላሻል የሚል ስጋት ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ በቡድን ውስጥ ኃላፊነትን ለመውሰድ ፈቃደኛ ካለመሆን አልፎ አንዱ ሌላውን መውቀስ ከጀመረ ሁኔታው ብቻ ሳይሆን ፍጻሜውም አደገኛ ይሆናል የሚል ስጋት አለኝ፡፡›› ብሎ ሥጋቱን ሲገልፅ ገብረየስ የጋራ ግብ በሚል የተናገረውን ችላ ማለቱን አሳየ፡፡
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ የዕውቀት እና የመብሰል ምልክት እያንዳንዳቸው በሕይወት ውስጥ ለሚከናወኑ ነገሮች ማለትም ዕድገትም ሆነ ውድቀት ኃላፊነትን መውሰድ ያለብህ ራስህ መሆንህን መረዳት ነው። ዳተኛ ወይም ግዴለሽ ሆነህ ኃላፊነትህን በአግባቡ ካልተወጣህ ስኬት ይርቅሃል፡፡ በአንተ በራስህ ምርጫ የሚያስፈልግህን በሙሉ ታጣለህ፡፡ በተከታታይ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ትገባለህ፡፡ ይህ ማለት ግን መቼም ኃላፊነትህን አልተወጣህምና ዓለም አበቃላት ማለት አይደለም፡፡
በአንዳንድ አጋጣሚዎች ኃላፊነትን አለመወጣት ያጋጥማል፡፡ ነገር ግን ይህ ሲደጋገም ጉዳዩን ማየት ያለብህ ከራስ አንፃር ነው፡፡ አሁን እያደረግክ ያለኸው ይህንኑ ነው፡፡ ራስህን እያየህ ነው፡፡ ይህ ተገቢ እና ትክክለኛ አካሔድ ነው፡፡ በእርግጥ ዋናው ጉዳይ ‹ይህ እንዴት ይፈጠራል?› የሚለውን መለየት መቻል ነው፡፡ አንደኛው እና ዋነኛው ቀላል ስንፍና ነው፡፡ ቀለል ያለ ስንፍና በቀላሉ መስተካከል ይችላል፡፡ ውድቀትን በመፍራት ኃላፊነትን አለመወጣትም ሌላው አንደኛው ምክንያት ነው፡፡ ይህ ስንፍና እና ኃላፊነትን ለመወጣት የመፍራት ችግር የሥራ ከባቢን ይረብሻል፡፡ የሥራ ስኬታማነትን ይቀንሳል፡፡ ይሔ ደግሞ የአንድ ግለሰብን ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ የቡድንን ስኬታማነት ያወርዳል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ አይነት ተመሳሳይ ችግሮች ካሉብህ በውል መለየት አለብህ፡፡ እኔ የምለው ግን ብዙዎች ኃላፊነታቸውን የማይወጡት ለምን እንደሚሰሩ የመጨረሻ ግባቸው ምን እንደሆነ ስለማያውቁ ነው፡፡ አንተም ይህንን ጉዳይ ልብ ብትለው ይሻላል›› አለው፡፡
ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ በማንኛውም ምክንያት ኃላፊነትን አለመወጣት እና በስራ ላይ ፍላጎት ማጣት እንዲሁም ሊያጋጥም የሚችለውን ፈተና ለመጋፈጥ ዝግጁ አለመሆን ጤነኝነት አይደለም፡፡ ሥራን መሸሽ እና አለመነቃቃት እንዲሁም ድክመትን አለመቀበል፤ ትልቅ የሥራ እንቅፋት መሆኑ አይካድም፡፡ የእዚህ ችግር ምንጭ ግን ግለሰቡ ራሱ ነው ብሎ መደምደም ይከብዳል፡፡ ሠራተኞች በቡድን መሪ ላይ ዕምነት ቢያጡ ጥፋቱ ወይም ክፍተቱ የቡድን መሪው ብቻ ነው ለማለት ያዳግታል፡፡ ነገር ግን ይህንን ችግር ለመፍታት በዋናነት የቡድን መሪው ከፍተኛ ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡
መፍትሄውም በቅድሚያ ችግሩን በአግባቡ መረዳት ነው፡፡ ቡድን ውስጥ ችግር ካለ በግልፅ ተነጋግሮ ችግር መፍታት ነው፡፡ አንዳንዴ በተለይ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና በአንዳንድ ቦታዎች ይህ ይስተዋላል። ሌላው መፍትሔ የቡድኑ አባላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እና ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ምቹ አካባቢን መፍጠር ነው፡፡
የመጀመሪያው ነገር መነጋገር ሲባል፤ በቡድንም ሆነ በተናጠል መሆን ይችላል፡፡ በሰዎች ህይወት ውስጥ መጥፎ ነገሮች እና አጋጣሚዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ ሥራቸው ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ይኖራል፤ ለዚህ መፍትሔው ተነጋግሮ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ሥራቸው ላይ ችግር እየፈጠሩ ካሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ካልተወጡ መነጋገር ሲኖር ባህሪያቸው መለወጥ እንዳለበት ይረዳሉ፤ በመነጋገር ምን አይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት እና እርምጃ መውሰድ እንደሚቻል ይረዳሉ፡፡
ከመግባባት ውጪ ግልፅ እና ትክክለኛ ያልሆነ እርምጃ መውሰድ ሰዎች ተጠቂ እንደሆኑ እንዲያስቡ የሚያስገድድ ከሆነ ደግሞ አደጋ አለው፡፡ ሥራ እንዲሠሩ አስፈላጊውን መሳሪያ ማስቀመጥ ይገባል፡፡ ይህ ስልጠናዎችን ጨምሮ በቅርበት ማነጋገር እና መምራትን ያካትታል፡፡ የቡድንህ አባላት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እና ቡድኑ እንዲሻሻል የተለያዩ መንገዶችን መቀየስ ያስፈልጋል፡፡
የመግባባት ችሎታ ወሳኝነት አለው፤ አንድ ሰው ተነጋግሮ መግባባት መቻል አለበት፡፡ የቡድንህ አባላት መስራት ያለባቸውን እና ኃላፊነታቸውን በግልፅ ማወቅ አለባቸው፡፡ ጥልቅ እና በደንብ የተተነተነ የሥራ መዝርዝር መኖር አለበት፡፡ አንዱ በተገቢው መልኩ ኃላፊነቱን አለመወጣቱ ትልቁ የተቋሙ ስኬት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ አለመረዳት ይኖራል፡፡
ቡድን ስኬታማ ካልሆነ ማጥናት እና ውስን ኃላፊነቶችን መቀያየር ይገባል፡፡ አንዳንዴ ሰዎች ራሳቸውን መቆጣጠር እንደማይችሉ እና በራሳቸው ላይ ለውጥ ማምጣት ከባድ እንደሆነ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ መላው ሥራ የሚሠሩ ሰዎችን መሸለም፤ ሽልማቱ ፍትሃዊ እና ቀጣይነት ያለው ማድረግ ያስፈልጋል፤ በተለይ መሪ ስትሆን ዓላማን ኃላፊነትን እና ግብን አረጋግጠህ መስራት ይገባሃል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ሠራተኞችም ሆኑ የሥራ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ በብዙ ጥረት ሠሩም አልሰሩ ለውጥ እንደሌለው ሊሰማቸው ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚያነቃቃቸውን ነገር ማግኘት አለባቸው። ሰዎች ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ በላይ በላዩ ሥራን ከመስጠት ይልቅ ሰርተው መጨረሳቸውን እያረጋገጡ፤ ኃላፊነታቸውን ካልተወጡም ለምን ኃላፊነታቸውን እንዳልተወጡ እየጠየቁ ሥራ መሥጠት ለውጥ ያመጣል፡፡ በራስህ በኩልም ድካም እና መሰላቸት ካለ ትልልቅ ስራዎችን ደግሞ ከፋፍሎ ማሰራት የተሻለ ነው፡፡ ዋናው እኔን የሚሰማማኝ ግን ገብረየስ ያነሳው መዳረሻን የማወቅ ጉዳይ ኃላፊነትን በብቃት ለመወጣት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ በአገር ደረጃ መታሰብ አለበት፡፡ ›› ብሎ ዘውዴ ረዥም ንግግሩን ቋጨ፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም