አቶ ክርስቲያን ታደለ, የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ- መንግሥት አንቀጽ 55(19) እና 59(2) ፤ በተሻሻለው በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 እንዲሁም የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጀት፣ ተግባርና ኃላፊነት ውሣኔ ቁጥር 3/2014 አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1-8 መሰረት ለመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተሰጡት ተግባራት በምክር ቤቱ ጸድቆ ከፌዴራል መንግሥት የተመደበ በጀት የአገሪቱን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎች፣ የአሠራር ሥርዓቶች፣ ፕሮግራሞች፣ ዕቅዶች ተከትሎ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን መከታተልና መቆጣጠር ነው።
ከዚህ በመነሳት ቋሚ ካሚቴው ከተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት አኳያ በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸው አንኳር ተግባራት እና የተገኙ ውጤቶችን በሚመለከት በዛሬው ወቅታዊ ጉዳያችን፤ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ከሆኑት ከአቶ ክርስቲያን ታደለ ጋር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቃለ ምልልስ አድርጎ ተከታዩን አጠናቅሯል፡፡
አዲስ ዘመን:- በዋናነት የቋሚ ኮሚቴው መደበኛ ሥራ ምንድነው?
አቶ ክርስቲያን:- ምክር ቤቱ ሕግ ያወጣል፤መፈጸሙንም ይቆጣጠራል። በዋናነት በሕገ መንግሥቱ ላይ እንደተቀመጠው የቁጥጥር ሥራዎችን የሚሠራው በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል ነው። ፓርላማው ይህንን ሥራ ለመሥራት 13 ቋሚ ኮሚቴዎችን አደራጅቷል። በሀገሪቱ ወደ 171 ገደማ የሚጠጉ የፌዴራል የመንግሥት ተቋማት አሉ። እነዚህ ተቋማት እንደየሥራ ባሕሪያቸው አንድ ላይ ሰብሰብ ተደርገው በ13 ቋሚ ኮሚቴዎች ሥር ቁጥጥርና ክትትል እንዲደረግባቸው ተደርጓል።
ከነዚህ 13 ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ አንዱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው። ቋሚ ኮሚቴው በዋናነት የሚቆጣጠረው ዋና ኦዲተርን ሲሆን፤ ተጠሪነቱም ለቋሚ ኮሚቴው ነው። መሥሪያቤቱ የኦዲት ግኝት ያለባቸውን ተቋማት ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል። ለምክር ቤቱም የኦዲት ሪፖርት ያቀርባል። ቋሚ ኮሚቴው ደግሞ የኦዲት ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ ተቋማትን እንዲቆጣጠርና እንዲከታተል በሕግ ተደንግጓል። ተቋማት በሌሎቹ ቋሚ ኮሚቴዎች ጭምር መደበኛ ሥራዎቻቸው ላይ ቁጥጥርና ክትትል ይደረግባቸዋል። ከኢዲት አንጻር ግን ተቋማት በተደራቢነት ለዚህ ቋሚ ኮሚቴ ተጠሪነት አለባቸው።
የኦዲት ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ ኦዲት ለማድረግ፣ አስተያየት ለመስጠት አስቸጋሪና የከፋ ችግር አለባቸው ተብለው የተለዩ የኦዲት ግኝት ያለባቸውን ተቋማት ፓርላማ ላይ በይፋ የውይይት መድረክ ይገመግማል። እንዲሁም በከተማና በገጠር የመስክ ምልከታ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋል።
ተቋማት ከታየባቸው የኦዲት ግኝት እና በተደጋጋሚ ካሰዩት ሕገወጥ ባሕሪ ባሻገር ከሚያንቀሳቅሱት የሰውና የሀብት መጠን፣ ለሕዝብና ለሀገር ካላቸው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዲሁም ለመልካም አስተዳደር፣ ለልማት፣ ለጸጥታና ፍትህ፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ … ወ.ዘ.ተ ከሚሰጡት ጠቀሜታ አንጻር የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶ በቅደም ተከተል ቋሚ ኮሚቴው ተቋማቱን ይመረምራል፣ ይቆጣጠራል፣ ይከታተላል።
በጥቅሉ የቋሚ ኮሚቴው መደበኛ ሥራ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን የኦዲት ሪፖርት መሰረት በማድረግ ተቋማት ምክር ቤቱ ባጸደቀላቸው በጀት እና ሀገሪቱ ባጸደቀችው የአምስትና የ10 ዓመት የልማት መርሀ ግብር መሰረት ሥራቸውን አዋጭነት ባለው፣ ውጤታማ በሆነ፣ የሕዝብ ተጠቃሚነትን በሚያሳድግ፣ ሁሉን አቀፍ ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ባረጋገጠ እንዲሁም የፋይናንስ ሕግጋትን በጠበቀ መንገድ ሥራቸውን እያከናወኑ ስለመሆናቸው የመከታተል፣ የመቆጣጠር፣ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርጉ ደግሞ አቅጣጫዎችን የማስቀመጥ ኃላፊነት በሕግ ተሰጥቶታል።
የኦዲት ግኝት ያለባቸውን ተቋማት ፓርላማ ላይ በይፋ የውይይት መድረክ ሲገመግም የኦዲት ባለድርሻ አካላት (ፍትሕ፣ ፕላንና ልማት እና ገንዘብ ሚኒስቴሮች፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ባለስልጣን፣ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ ዋና ኦዲተር እንዲሁም ተቋማቱን በቀጥታ የሚቆጣጠሩ ቋሚ ኮሚቴዎች) ጭምር እንዲገኙ ይደረጋል። ምክንያቱም የኦዲት ባለድርሻ አካላት ተቋማቱ ያለባቸውን ክፍተት ተረድተው በአንድም በሌላ መንገድ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ተገቢውን ሚና እንዲወጡ እንዲሁም የኩላቸውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያስፍኑ ነው።
በአጠቃላይ የቋሚ ኮሚቴው ዋነኛ ተልዕኮ ተቋማት ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ ተቋማት እንዲሆኑና የተቋማት አመራሮችም ለሀገር ጠቃሚ፣ ብቃት ያላቸው፣ የተመሰከረላቸው ብቁ አመራሮች እንዲሆኑ ማገዝ ነው።
አዲስ ዘመን:- ቋሚ ኮሚቴው በምክርቤቱ ከተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት አኳያ በ2015 በጀት ዓመት ምን ምን አንኳር ተግባራትን አከናውኗል?
አቶ ክርስቲያን:- ዋና ኦዲተር ለምክር ቤቱ ሪፖርት ካቀረበ በኋላ ሁሉንም ተቋማት ለመፈተሽ የጊዜም፣ የሰው ኃይልም ውስንነት አለ። ስለዚህ የኦዲት ግኝት የተገኘባቸውን የመንግሥት ባለበጀት አስፈፃሚ ተቋማትን በቅድሚያ ለማየት ዕቅድ ተይዞ ነበር። ከዚህ ውስጥ በበጀት ዓመቱ 37 ተቋማትን ፓርላማ ላይ በይፋ የውይይት መድረክ ገምግሟል። እንዲሁም በከተማና በገጠር በመስክ ምልከታ ቁጥጥርና ክትትል አድርጓል።
ከነዚህ ውስጥ የ19 ተቋማትን የክዋኔ እና ዘጠኝ ተቋማትን የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት ሪፖርት በይፋ የውይይት መድረክ ተገምግሟል። ቀሪዎቹ በከተማና በገጠር በመስክ ምልከታ ቁጥጥርና ክትትል የተደረገባቸው ነው። በተደረገው ግምገማ በተቋማት ላይ ከታዩ አንኳር ክፍተቶች ውስጥ የፕሮጀክት አዋጭነት ጥናትና የአካባቢ ተጽኖ ግምገማም ሳይደረግ በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች አሉ።
ለአብነት የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የእናቶችና ህፃናት ማዕከል የግንባታ የፕሮጀክት አዋጭነት ጥናት ሳይሠራላት ወደ ግንባታ ተገብቷል። መሰል በርካታ ተቋማትም አሉ።
እንዲሁም ከፋይናንስ አንጻር የመንግሥት የግዥና የወጪ መመሪያዎችን የማይጠብቁ፤ ከፍተኛ የሆነ የጥሬ ገንዘብ ጉድለትና ውዝፍ ተሰብሳቢ ገንዘብ የተገኘባቸው ተቋማት አሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ለዋቢነት ቅጣት የተጣለባቸው ወላይታ ሶዶ፣ ጂንካ፣ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲዎች በተጨማሪ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የአዳሚ ቱሉ ፀረ ተባይ ፋብሪካ በተመሳሳይ የከፋ ችግር ያለባቸው ናቸው።
ከዚህ አንጻር በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች ከበጀት አጠቃቀም አኳያ እንዲያስተካክሉ እንዲሁም የፕሮጀክት አዋጭነት ሣይሠራላቸው ወደ ሥራ የገቡ ፕሮጀክቶች ታርመው የኦዲት ማሻሻያ መርሃ ግብር እንዲያቀርቡ እና በየጊዜው ክትትል እንዲደረግባቸው ለዋና ኦዲተር ደብዳቤ ተጽፏል።
ከዚህ ባሻገር ዜጎች ለተለያየ ሥራ ወይም አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተለያዩ ተቋማት ሲያመሩ የሚያዩቸውን የአሠራር ብልሹነቶች፣ በተለይ ከፋይናንስ አስተዳደር፣ ሕግን ካለመከተል፣ ለሙስናና ብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ ክፍተቶችን ሲያዩ ጥቆማ ይሠጣሉ። “ልዩ ኦዲት ይደረግልን” በሚል የተለያዩ ጥቆማዎች ከሕብረተሰቡ ይመጣሉ። በተደራጀ መንገድና የዓሠራር ሥርዓቱን ጠብቆ ጥቆማው እስከቀረበ ድረስ ቋሚ ኮሚቴው ጥቆማውን ተቀብሎ ዋና ኦዲተር ክትትል እንዲያደርግበት አቅጣጫ ይሰጣል።
እንዲሁም የህዝብ እንደራሲዎች ወደ ተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ወይም ወደ ተመረጡበት አካባቢ ለተለያዩ ጉዳይ ይንቀሳቀሳሉ። በሄዱበት አካባቢ ወይም ተቋም ለሙስናና ብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ ተግባራትን ተመልክተው “ኦዲት ይደረግልን” የሚል ጥያቄ ለቋሚ ኮሚቴው ካቀረቡ ኦዲት ይደረጋል።
በዚህ አግባብ ለአብነት የወሎ ቴሪሸሪ ሆስፒታል አጠቃላይ የግንባታ ሂደትና የገንዘብ አሰባሰብ ሁኔታ በአካባቢው እንደራሲ “ይጣራልን” የሚል ጥያቄ ቀርቦ ከሆስፒታሉ ጋር በተያያዘ የማጣራት ሥራ በልዩ ኦዲት እንዲሠራ ቋሚ ኮሚቴው ትዕዛዝ ሰጥቷል። በተመሳሳይ በተለይ ከበጀት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ሕብረተሰቡ በተደራጀ መንገድ ጥቆማ በማቅረቡ የማጣራት ሥራ እንዲሠራ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
አዲስ ዘመን:- ምን ያህል ተቋማት በተሰጣቸው ማሳሰቢያ መሰረት ጉድለታቸውን አስተካክለዋል? ባላስተካከሉት ላይስ የሚወሰደው እርምጃ ምንድነው?
አቶ ክርስቲያን:- ቋሚ ኮሚቴው በየወቅቱ በሚያደርገው የኦዲት ማሻሻያ የድርጊት መርሃ ግብር ሪፖርት መሰረት ተቋማት የተገኘባቸውን ግኝት ለማሻሻል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ታዝበናል። ለአብነት ያለአግባብ የከፈሉትን ውሎ አበል ከሠራተኞቻቸው ደሞወዝ ላይ በየወሩ እየቆረጡ እየመለሱ ያሉ ተቋማት አሉ። ሌላው ኦዲት ግኝት የሆነ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ጠፋ ማለት አይቻልም። ምክንያቱም የገቢና ወጪ ደረሰኝ ያልቀረበባቸው ሰነዶች ሲቀርቡ ከኦዲት ግኝት ይወጣል። ስለዚህ አስረጂ ደጋፊ ሰነዶችን በማቅረብ ከኦዲት ግኝት የወጡ አሉ።
ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ፈተናዎችና ምዘና አገልግሎት ሕግ ሳይወጣለት ለተለያዩ ሠርተፍኬቶች በራሱ ተምኖ ገንዘብ ከህብረተሰቡ ይሰበስባል። በተመሳሳይ ለፈታኝ መምህራን የውሎ አበል ተመን በሕግ ሳይተመንለት በራሱ ተምኖ ሲከፍል ነበር። ተቋሙ በሕግ ሳይተመንለት ገንዘብ መሰብሰብም ሆነ ውሎ አበል እንዳይከፍል ማሳሰቢያ ተሰጥቶታል። በተሰጠው ማሳሰቢያ መሰረት ገንዘብ የሚሰበስብበትና ውሎ አበል የሚከፍልበት ሕግና ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ገንዘብ ሚኒስቴር አጸድቆ በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ ገብቷል። በዚህ መሰረት ለዘመናት ሲንከባለል የነበረ ችግር ተፈትቷል።
በተጨማሪም አንዳንድ ንብረቶች ለረዥም ጊዜ ባለቤት አልባ ሆነው የሚቀመጡ አሉ። ለዋቢነት ሊብሬ ያልወጣላቸው ተሽከርካሪዎች ነበሩ። ሊብሬ እንዲወጣላቸው ተደርጓል። ካርታ ያልተሠራላቸው ተቋማት ነበሩ። ካርታ እንዲሠራላቸው ተደርጓል። እንዲሁም አንድ ሰው የገቢና ወጪ የንብረት አስተዳደር ሥራን ደርቦ የሚሠራበት ተቋም ነበር። ይህ ስህተት እንደሆነ በተሰጣቸው ምክረ ሃሳብ መሰረት ተጨማሪ የሰው ኃይል መድበው ሥራው በተለያየ ባለሙያ እንዲሠራ አድርገዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግንባታዎችን ያከናውናሉ። ሆኖም መሰብሰብ የነበረባቸውን ተቆራጭ ገቢ (with holding tax) አይቆርጡም። ተቆራጭ ገቢ እንዲሰበስቡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። የተሰጣቸውን ማሳሰቢያ ምን ያህል ተግባራዊ አድርገዋል የሚለው በቀጣይ የሚታይ ነው። እንዲሁም በሕግ ሂደታቸው እየታዩ ያሉ ጉዳዮች አሉ።
በጥቅሉ ተቋማት በተሰጣቸው አስተያያት መሠረት የአሠራር፣ የሕግ ፣ የአደረጃጀት ማስተካከያዎችን አድርገዋል። ነገር ግን አብዛኞቹ ተቋማት በታለመለት ጊዜና ባቀዱት ዕቅድ መሠረት ጉድለታቸውን እያስተካከሉ አይደለም። ስለዚህ በተሰጣቸው ጊዜ ገደብ የማያስተካክሉ ከሆነ ቀጣይ የወንጀልና የፍታብሔር ተጠያቂነት ይከተላቸዋል።
አዲስ ዘመን:- በበጀት ዓመቱ የተመደ በላቸውን በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ያላዋሉና ከተመደበላቸው በጀት በላይ ተጠቅመው የተገኙ ተቋማት ምን ያህል ናቸው? ተቋማቱስ እነማን እነማን ናቸው? ምን ያህል ገንዘብ ከበጀት በላይ ተጠቅመዋል?
አቶ ክርስቲያን:- በተመደበላቸው በጀት ጣሪያ መሠረት ሥራቸውን ያከናወኑ መሥሪያቤቶች ጥቂት ናቸው። በአብዛኛው ከተመደበላቸው በጀት በላይ መጠቀም እና የተመደበላቸውን በጀት አሟጠው ያለመጠቀም እንደ ሀገር አሳሳቢ ችግር ተስተውሏል። በዚህም በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2014/15 በጀት ዓመት ተቋማት 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ከበጀት በላይ ተጠቅመዋል። ተቋማት ከዚህ ቀደም ከበጀት በላይ የተጠቀሙት ገንዘብ ቢሊዮን ብር ገብቶ አያውቀም።
ሆኖም ከበጀት በላይ መጠቀሙ የብሩ መጠን መብዛትና ማነስ ላይ አይደለም ቁም ነገሩ። ዋናው ቁልፍ ጉዳይ በጀትን የማጽደቅ ስልጣን ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ ነው። ከበጀት በጀት አዙሮ መጠቀምና መሰል ሥራዎችን መሥራት በየደረጃው የተቋማት ኃላፊዎች የራሳቸው ሥልጣን አላቸው። በተመሳሳይ ገንዘብ ሚኒስቴር የራሱ ስልጣን አለው። ይሁን እንጂ ያልጸደቀን በጀት መጠቀም ነውርም፤ ወንጀልም ነው። ምክንያቱም በጀትን የማጽደቅ ሙሉ ስልጣን ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ ነው። ስለዚህ ተቋማት በሕግ የተቋቋሙ ናቸው። ሕግ መከተልና ማክበር አለባቸው። ያልጸደቀን በጀት መጠቀም በሕግ ያስጠይቃል።
ነገር ግን ከበጀት በላይ መጠቀም፣ በጀትን ካለመጠቀም አንጻር ሲታይ ውስንነቱ ዝቅተኛ ነው። ምክንያቱም ምክር ቤቱ ሀገሪቱ ለወጠነቻቸው ታዳጊ ፕሮጀክቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው ተብሎ ከተያዘ በጀት ውስጥ 35 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ አልዋለም። ከበጀት በላይ ከመጠቀም ይልቅ የተበጀተን በጀት አለመጠቀም በጣም አሳሳቢ ነው።
35 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ ቢውል ኖሮ፤ ለዜጎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። የዜጎችን የመልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ይመልስ ነበር። ይህን ያህል በጀት አለመጠቀም የፍትሃዊነት ጉዳይ የሚያስነሳ ነው። በጀቱ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ዜጎች በፍትሃዊነት መንገድ የመልማት ጥያቄያቸው እንዲውል እንዲያድር እየተደረገ ነው። ተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ገንዘብ፣ ተጨማሪ ልማትን ማምጣት የሚችል ገንዘብ ጥቅም ላይ አልዋለም።
ሌላው አስፈጻሚው አካል ለምንድ ነው የማይጠቀመውን ገንዘብ ምክር ቤቱ እንዲያጸድቅ ያደረገው? የሚለውን ጥያቄ ያጭራል። ይህም አስፈጻሚው አካል የበጀት አስተቃቀድ ችግር እንደነበረበት የሚያሳይ ነው። በጀት የሚበጀተው ለህዝብ ልማት ነው። በመሆኑም አስፈጻሚው አካል የዜጎችን የመልማት ጥያቄ በወጉ እየመለሰ አይደለም የሚል ትርጓሜ የሚሰጥ ነው። ስለዚህ በጀትን በአግባቡ መጠቀም ላይ ትኩረት መደረግ አለበት።
ሌላው የውዝፍ ተሰብሳቢ የገንዘብ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው። በተለያየ አርዕስት ሲንከባለል የመጣ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የ2014/15 ኦዲት በጀት ዓመት ተሰብሳቢ ውዝፍ ገንዘብ አለ። ተቋማት በተለያየ መንገድ በሕግ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት መሰብሰብ የነበረባቸው ነገር ግን መሰብሰብ ያልቻሉት ገንዘብ ነው። ከዚህ ውስጥ ገንዘብ ሚኒስቴር ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ፣ ጤና ሚኒስቴር ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ያልመለሱት ውዝፍ ተሰብሳቢ ገንዘብ እዳ አለባቸው። በተመሳሳይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የቀድሞው ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በጣም በርካታ ያልመለሱት ውዝፍ ተሰብሳቢ ገንዘብ ያለባቸው ተቋማት ናቸው።
የተሰብሳቢ ውዝፍ የገንዘብ ተመላሽ ምጣኔ እንደ ሀገር ሲታይ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው። ለአብነት በ2013/14 የኦዲት በጀት ዓመት እንዲመለስ የሚጠበቀው ተሰብሳቢ ውዝፍ የገንዘብ ስድስት ቢሊዮን ብር ነበር። ከዚህ ውስጥ መሰብሰብ የተቻለው 44 ሚሊዮኑን ብር ብቻ ነው። አፈጻጸሙ 0 ነጥብ 65 በመቶ ነው። ይህ ማለት ትርጉሙ በጣም ብዙ ነው።
አንደኛ ምክር ቤቱ አስፈጻሚ የሆነውን አካል በወጉ እየተቆጣጠረ አይደለም ማለት ነው። ምክንያቱም ከኦዲት አንጻር አፈጻጸሙ ሲታይ 0 ነጥብ 65 በመቶ እንደማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከሕግ ውጭ የወጣ ገንዘብ በአግባቡ ተመልሶ ለታለመለት ዓላማ አልዋለም ማለት ነው። ከፋይናንስ አንጻር ሕግን የመጠበቅና የማስጠበቅ አቅማችን 0 ነጥብ 65 በመቶ ማለት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ እንደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፍትህ ሚኒስቴር … ወዘተ ከፊል የመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት ያላቸው ተቋማት በወጉ ስልጣናቸውን አልተወጡም እንደማለት ነው። ገንዘቡን ቀጥታ በመመለስ ወይም ደግሞ የወጪና ገቢ ደጋፊ ማስረጃ ሰነዶችን በማቅረብ ገንዘቡ ከኦዲት ግኝት መውጣት ነበረበት። ሁኔታው በጣም አስደንጋጭ ነው።
ችግሩ ከወዲሁ ካልታረመ በቀጣይ ተጠያቂነትን ለማስፈን አስቸጋሪ ነው። ውሎ አድሮም የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ይሆናል። ምክንያቱም ተቋማት የመንግሥትን ሕግጋት አክብረው መሥራት ካልቻሉ እና አመራሮች እንደፈለጋቸው በየራሳቸው መሻትና ምኞት ተቋማትን የሚመሩ ከሆነ ሕግ አክባሪነት እየሳሳ ይሄዳል። ሕገ ወጥነት ባህል እየሆነ ይሄዳል።
የፋይናንስ አስተዳደር እጅግ በጣም ውስብስብ ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ ነው። የመንግሥት ሉዓላዊ ስልጣን ከሚታይባቸው መስኮች ግንባር ቀደሙ የፋይናንስ አስተዳደር ነው። አንድ መንግሥት የፋይናንስ አስተዳደሩ እጅግ ጥብቅና ተገቢው ቁጥጥር የሚደረግበት ካልሆነ ህልውናው አደጋ ላይ ይወድቃል። ስለዚህ እንደ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የቤት ሥራዎችን ወስደው በሥራቸው የተደራጁ ተቋማትን ከኦዲት አንጻር ያለባቸውን ድክመቶች የማረም፣ የመቆጣጠር ኃላፊነታቸውን በወጉ መወጣት ይኖርባቸዋል።
ምክር ቤቱም ኃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል። በተለየ ሁኔታ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተቋቋሙ ተቋማት አሉ። አስተዳደራዊ ተጠሪነታቸውም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው። ስለዚህ ከፋይናንስ አኳያ ምክር ቤቱ ጥብቅ የቁጥጥር ሥራ መሥራት አለበት። የገንዘብ ሚኒስቴር በየጊዜው የፋይናንስ ሕግጋትን ባለማክበር በሚል የተቋማት ኃላፊዎችን 10 ሺ ብር በመቅጣት ብቻ ለውጥ አይመጣም።
ከሕግ ውጭ የመንግሥትን እና የሕዝብን ሥራ በማያመች መንገድ የሚመሩ ተቋማትና የተቋማት ኃላፊዎች በርካታ ናቸው። በዚህም በቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብና የሀገር ገንዘብ እየባከነ ነውእንደመንግሥት ከሕግ ውጭ በሚሠሩ ላይ ጠበቅ ያለ የሕግ ማስከበር ሥራዎች መሥራት ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ እንደ ሀገር አደጋ ውስጥ እንገባለን። ምክንያቱም ከበጀት በላይ ያለ አግባብ ጥቅም ላይ የዋለው 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር፣ ጥቅም ላይ ያልዋለው 35 ቢሊዮን ብር እና መሰብሰብ የነበረበት ውዝፍ ተሰብሳቢ 15 ቢሊዮን ብር በድምሩ 41 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በአግባቡ ጥቅም ላይ ቢውል ኖሮ ስንት ፋብሪካዎችን ይገነባ ነበር።
ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ይችል ነበር። ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ መነቃቃት ምን ያህል ሚና ይጫዎት ነበር የሚለው ሲታሰብ ገንዘቡ በጣም ብዙ ነው።
የሀገሪቱ በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ፣ በጀት በሕግዊ አሠራር ካልተመራ የጥቂቶች መጫዎቻ፤ የጭቆና በትር መሆኑ አይቀሬ ነው። ይህ እንዳይሆን ሁላችንም ታሪክ፣ ሕግ፣ ትውልድ የሰጠነን አደራ እና ስልጣን በአግባቡ መወጣት ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን:- የበጀት ጉድለት ባስከተሉ ተቋማት ላይ የተወሰደ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ ካለ ?
አቶ ክርስቲያን:- ዋነኛው የኦዲት ባለድርሻ አካል ገንዘብ ሚኒስቴር ነው። ሚኒስቴሩ በአዋጅ የተሰጠው አንዱ ስልጣን የገንዘብ ቅጣት መጣል ነው (ዋና ኃላፊውን በ10 ሺ እና የፋይናስ ኃላፊውን በ9 ሺ ብር እንዲቀጣ በአዋጅ ተደንግጓል) ። በዚህም በበጀት ዓመቱ የአራት ተቋማት የበላይ ኃላፊዎችንና የፋይናንስ ኃላፊዎችን በሕጉ መሰረት የገንዘብ ቅጣት አስተላልፏል። እንዲሁም በ14 መሥሪያቤቶች ላይ የገንዘብ ቅጣት፣ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲሁም ከባድ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ሌላው በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ጥፋት የሚፈጽሙ የተቋማት ኃላፊዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ካለባቸው ችግር አንጻር “ፋይናንስ ለማስተዳደር ብቁ አይደሉም፤ “ይነሱ” የሚል ምክረ ሃሰብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይዞ የመቅረብ ኃላፊነት ለሚኒስቴሩ ተሰጥቶታል።
ነገር ግን ተደጋጋሚ ጥፋት የሚያጠፉ ኃላፊዎችን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቦ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ከማድረግ አኳያ ውስንንት አለበት። እንዲሁም ተቋማት የወጡ የፋይናንስ ሕግጋትን ካላከበሩ በጀት የመያዝ ሥልጣን አለው። በተመሳሳይ ይህንን ስልጣኑን በሚገባ እየተጠቀመበት አይደለም።
በተጨማሪ በየተቋማቱ የውስጥ ኦዲተሮች አሉ። እነዚህ የውስጥ ኦዲተሮች ተጠሪነታቸው ለገንዘብ ሚኒስቴር ነው። በየሦስት ወሩ ሪፖርት ያቀርባሉ። የውስጥ ኦዲተሮችን ሪፖርትና ምክረ ሃሳቦችን ወስዶ በቂ እርምጃ እየወሰደ አይደለም።
ፍትሕ ሚኒስቴር ሌላኛው የኦዲት ባለድርሻ አካል ነው። ሚኒስቴሩ የፋይናንስ ሕግጋትን ሳይከተሉ ተቋማትን እየመሩ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ወይም ባለሙያዎች ላይ የወንጀልና የፍትሃብሔር ተጠያቂነት ሊያስከትሉ የሚችሉ ክሶችን የመመስረት ስልጣን አለው። የፌዴራል የሕግጋቶች ተፈጻሚነታቸውን የሚከታተልበት እራሱን የቻለ የሥራ ክፍል አለው። ስለዚህ ሚኒስቴሩ በራሱ ተነሳሽነት ወይም ደግሞ በገንዘብ ሚኒስቴር አልያም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቋሚነትና ጠያቂነት ክሱን ሊመሰርት ይችላል።
በኦዲት ግኝቱ መሰረት ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ የወንጀልና የፍትሃብሔር ክስ መመስረት እንዲችል፤ በ2013/14 የኦዲት በጀት ዓመት ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጣቸው 39 እና የኦዲት አስተያየት መስጠት ባልተቻለባቸው 8 በድምሩ 47 መሥሪያ ቤቶች በኦዲት ግኝት ላይ የወሰዱትን የእርምት እርምጃ እንዲያሳውቁ ቋሚ ኮሚቴው በደብዳቤ ጠይቆ የክትትልና የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩት ከኦዲት ግኝት ጋር ተያይዞ ነው። አንደኛው የምክር ቤት አባል ጭምር ነበሩ። ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የኦዲት ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ ነው። ከሕግ ተጠያቂነት አኳያ በጎ ጅምሮች ቢኖሩም ከችግሩ ስፋት አንጻር በቂ አይደለም።
ሌሎች አገሮች የዋና ኦዲተር ሪፖርትን ትልቅ የቁጥጥር መሳሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። በየዓመቱ አስፈጻሚው፣ ሕግ አውጭውና የዳኝነት ሶስቱ የመንግሥት አካላት የሚገናኙበት ትልቅ መድረክ ተደርጎ ይወሰዳል። እርቀን ሳንሄድ እዚሁ አፍንጫችን ስር ጎረቤታችን ኬኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣… ወዘተ ከኦዲት አንጻር እጅግ የሰለጠነ ተሞክሮና ባህል አላቸው።
በተለይ ዩጋንዳ ላይ ዓመታዊ የዋና ኦዲተር ሪፖርት ሲቀርብ ፕሬዚዳንቱ ቁጭ ብለው ያዳምጣሉ፡፡ በሪፖርቱ መሠረት በተጨባጭ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ማንኛውንም ባለሥልጣን በነገታው ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን ያነሳሉ። በሕግም ተጠያቂ ይሆናል። በኛ አገር ግን የዋና ኦዲተር ሪፖርትን እንደ ቁጥጥር፣ ሥራን እንደማሻሻያ እና ተቋማትን እንደማዘመኛ መሳሪያ አድርጎ ከመጠቀም አኳያ የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት ክፍተት አለ። የኦዲት ግኝቱን መሰረት አድርጎ ተጠያቂነትን ከማስፈን አኳያ መተዛዘል አለ።
እንዲሁም በተደጋጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሚኒስትሮች የዋና ኦዲተር ሪፖርት በሚደመጥበት ጊዜ እንዲገኙ በደብዳቤ ጭምር ጠይቀናል። ሆኖም ግን አይገኙም። የሌሎች አገር ተሞክሮዎችን ወስዶ መሥራት ይገባል። መንግሥት ኃላፊነት የወሰደው የህዝቡን ሀብት፣ ንብረት በመንግሥታዊ አሠራሮችና አመራሮች የህዝብን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን በተከተለና በሰለጠነ መንገድ ለማስተዳደር ነው። ነገር ግን መንግሥት ያወጣቸውን ሕጎች የራሱ የመንግሥት አካላት ሲጥሱ ይስተዋላል።
አንዳንድ የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የመንግሥትን ገንዘብና ሀብት ከሕግ ውጭ የማውጣት፣ ያለጨረታ ግዥ የመፈጸም፣ ሕግጋትንና አሠራሮችን ተከትሎ ለመሄድ ፍላጎት ማጣት፣ ፕሮጀክቶች ያለአዋጭነት ጥናት እና ከሀገሪቱ የልማት እቅድ ጋር ሳይጣጣሙ ሲካሄዱ ይታያል።
ተቋማት ከሀገሪቱ የፋይናንስ ሕግጋትና መመሪያዎች ውጭ ገንዘብ የሚሰበስቡ ከሆነ፤ ፓርላማው ሳያጸድቀው ተቋማት በየራሳቸው በጀት እየሰፈሩ የሚጠቀሙ ከሆነ፣ ምክርቤቱ ያጸደቀው በጀት ጥቅም ላይ ውሎ የዜጎችን ችግር ማቃለል፣ ተጨማሪ ልማት ማምጣትና የሥራ እድል መፍጠር ካልቻለ ብሔራዊ ደህንነት ሥጋት ይፈጥራል።
ከዚህ በላይ ደግሞ የብሔራዊ ደህንነት ሥጋት ሊኖር አይችልም። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የህዝብ ተወካዮችና የሚኒስትሮች ምክር ቤቶች፣ ገንዘብና ፍትሕ ሚኒስቴር መሥሪያቤቶች ተገቢውን የሆነ ቁጥጥርና ተጠያቂነት የማስፈን ሥራዎች መሥራት አለባቸው። ተቋማቱም ለሌሎች ተቋማት ጭምር አርዓያ መሆን አለባቸው።
በተለይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለይም ሰብሳቢው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥታ የሚሾሟቸው ሚኒስትሮች እና የተቋማት ኃላፊዎች አሉ። እነዚህ የሥራ ኃላፊዎች ሥራቸውን በአግባቡ ስለመወጣታቸው ተገቢ የሆነ ክትትል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር ሊደረግባቸው ይገባል። በሌላ በኩል ተፎካካሪ ፓርቲዎች የኦዲት ግኝቱን የመታገያ ሜዳ ሊያደርጉት ይገባል።
አዲስ ዘመን:- ቋሚ ኮሚቴው በበጀት ዓመቱ በሠራቸው ሥራዎች ምን ምን ተጨባጭ ውጤቶች ተገኙ?
አቶ ክርስቲያን:- አንደኛው እና ትልቁ ሞጋች ማህበረሰብ መፍጠር ነው። በፓርላማው የይፋ ግምገማ መድረክ ሲከናወን ከመደበኛው የመገናኛ ብዙኋን ባሻገር በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በቀጥታ ይተላለፋል። “ለካ ምክር ቤቱ መቆጣጠር ይችላል” የሚለውን ግንዛቤ በማህበረሰቡ ማስረጽ ተችሏል። በዚህም ማህበረሰቡ በየተቋማቱ የሚያስተውላቸውን ብልሹ አሠራሮችን በተደራጀ መንገድ ጥቆማዎችን እያደረሰ ነው። የቀረቡ ጥቆማዎች ተደራጅተው ለሚመለከተው አካል ተመርተዋል። በተዘዋዋሪ ደግሞ ተገምጋሚ ተቋም ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተቋማት ስለኦዲት እና በምክር ቤቱ ስለሚደረግ የውጭ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ግንዛቤ እንዲኖራቸው እድል ፈጥሯል።
ከዚህ ባሻገር አስፈጻሚው አካል ከመንግሥት አካላት አንዱ እንጂ ብቻውን እራሱን የቻለ ፈላጭ ቆራጭ እንዳልሆነ ማህበረሰቡ እንዲረዳ ጥረት ተደርጓል። ሕግ አውጭው አሰፈጻሚውን የመቆጣጠር ሕገ መንግሥታዊ ስልጣን ያለው መሆኑን ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ በጎ ጅምሮች ቢኖሩም፤ በተሟላ መንገድ ግንዛቤ ተፈጥሯል ለማለት ግን አያስደፍርም። ምክንያቱም አሁንም ቢሆን በግለሰባዊ ኃላፊነት ደረጃ አስፈጻሚው አካል የገዘፈ ስለሆነ ምክር ቤቱ የሰጣቸውን አቅጣጫዎች ላለመቀበል መንገራገጮች አሉ።
ሌላው በይፋዊ መድረክ የተገመገሙ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ተቋማት ሕግ አውጭው ነገ ከነገ ወዲያ እነሱም ጋር እንደሚመጣ ታሳቢ በማድረግ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አንድ የትምህርት እድል ፈጥሯል።
በኦዲት የአንድን ተቋም ሁሉንም አሠራር መፈተሽ አይቻልም። ናሙና ተወስዶ ነው ተቋሙ ኦዲት የሚደረገው። ስለዚህ ተቋማት ኦዲትን እንደመስታወት ተጠቅመው አጠቃላይ ተቋማዊ ችግሮቻቸውን ለማየት እና አሠራራቸውን ለማዘምን እንዲጠቀሙበት አንድ እድል ፈጥሯል። ትልቁ የተሰበረው አስተሳሰብ ተቋማት ኦዲት ችግር ነቃሽ ብቻ አለመሆኑን እንዲረዱት፤ ለኦዲት በጎ የሆነ ምልከታ እንዲኖራቸው፣ ሥራቸውን ለማሻሻል እንደ አንድ መሳሪያ የሚጠቀሙበት፣ ከፍለው ጭምር ኦዲት በማሠራት ተቋማቸውን ለማሻሻልና ለማዘመን ለሚያከናውኑት ሥራዎች እንደግብዓት የሚጠቀሙበት እንደሆነ የተገነዘቡበት ነው።
በተጨማሪም በተቋማት መካከል በተለይ የኦዲት ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር እንዲዳብር ጥረት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን:- ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ በጀት ዓመት በልዩ ትኩረት ሊያከናውናቸው ያቀዳቸው ሥራዎች ይኖሩ ይሆን?
አቶ ክርስቲያን:- አሉ! በዋናነት በተለመደው መንግድ ከኦዲት ግኝት አንጻር ከፍተኛ የኦዲት ግኝት የተገኘባቸው እና አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸው ተቋማትን በሙሉ እናያለን። ለአብነት የጸጥታ፣ የዲሞክራሲ እና የማህበራዊ ልማት ተቋማት አሉ። እነዚህን በልዩ ሁኔታ አይተን ተገቢውን ግምገማ እናደርጋለን፤ ተጠያቂነትም እናሰፍናለን።
ሁለተኛ ከተጠያቂነት አንጻር ተጨባጭ የሆነ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችሉ ሥራዎችን እንሠራለን። ከሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎችም ጋር በመተባበር የፍትሐብሔርና የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ጉዳዮች ካሉ በአግባቡ ተጠንቶ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እንሠራለን።
ሦስተኛው ከዚህ በፊት ከአለው የሰው ኃይል ውስነነትና የጊዜ ጥበት አኳያ ሁሉንም የፌዴራል ተቋማት (171 ገደማ ተቋማት) ሳይሆን የከፋ የኦዲት ግኝት ያለባቸውን የተወሰኑ ተቋማትን ብቻ ነበር የምናየው። በቀጣይ ዓመት እንሠራዋለን ብለን የያዝነው እቅድ ሁሉንም ተቋማት በኦዲት ሪፖርቱ መሰረት እንፈትሻለን። በዚህም አንድም ሳንቲም ብትሆን በኦዲት ግኝት የመጣች ጉድለት ተመላሽ እንድትደረግ ለሁሉም ተቋማት የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ አቅጣጫዎች እናስቀምጣለን። በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ተመላሽ መደረግ ያለባቸው ገንዘቦች ተመላሽ እንዲደረጉ፤ የፋይናንስ ደጋፊ ሰነዶች ያልቀረበባቸው ደግሞ እንዲቀርቡ፤ መጠየቅ ያለባቸውን በወንጀልና በፍትሐብሔር ጭምር ተጠያቂ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን በጥብቅ ቋሚ ኮሚቴው ይሠራል።
አዲስ ዘመን:- ውድ ጊዜዎን ሰውተው ይህን ሰፋ ያለ ቃለምልልስ ስለሰጡን እናመሰግናለን።
አቶ ክርስቲያን:- እኔም አመሰግናለሁ ።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም