ከመትከል ባለፈ ቀጣዩ ቃላችን

 አስገዳጅ ሁኔታ ካላጋጠመና በጤና፣ በዕድሜ መግፋትና ከአቅም ማነስ በመጣ ክፍተት ካልሆነ በቀር/ጉዳዩ የዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን የመጪዎቹ ትውልዶች እጣ ፈንታን የሚወሰን በመሆኑ/በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞች የመትከል መርሃግብርን ያልተቀላቀለ ዜጋ አለ ብዬ አልገምትም።

በእርግጥ ችግኝ የመትከሉን ጉዳይ በአገር አቀፍ ደረጃ የጋራ አጀንዳ አድርገን ከመንቀሳቀሳችን አስቀድሞም ቢሆን እንደየአካባቢያችን የአየር ንብረት ሁኔታ እየታየ ስንተገብረው የመጣ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ቢያንስ ከተከልናቸው ጥቂት ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳገኘንበት፤ እያገኘንበት ስለመሆኑ አይካድም፡፡

ሌላው ቀርቶ በተለይ በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል ያለነው ከሰፈራችን ካለ አንድ ዋርካም በሉት ዋንዛ ጥላ ስር አረፍ ብለን የሆድ ሆዳችንን አውግተን ይሆናል/የጸሐይ ወላፈን እየገረፈን የልብ የልባችንን ልናወጋ መቼም አንችልም/፡፡ በልጅነታችን ከከባድ የጸሐይ ግለትና ከከፍተኛ ውሽንፍር ያስጣለንን ዛፍ አንዘነጋውም፡፡

አዋቂዎችም ብንሆን ከጥላው ስር ተቀምጠን የሸመገልንበት፣ እቁብ እድራችንን የተስተናገድንበት እንዲሁም አውጫጪኝ የተቀመጥንበትን ታላላቅ ዋርካዎችን ልንዘነጋ የሚቻለን አይመስለኝም፡፡ መች ይህ ብቻ አካባቢያችን የተስተካከለ የአየር ጸባይ እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገውን ደን ፋይዳ እንደሌለው አድርገን ልንቆጠር አንችልም፡፡

ይህ ሁሉ የዛፎችም ሆነ በጥቅሉ የደን ጥቅም ተቋዳሽ መሆን የቻልነው አንዲት በእጃችን መዳፍ የምትያዝ ትንሽዬ ችግኝ ከመሬት ተተክላ ታላቁን ዛፍ ስለሰጠችን ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ለነጋችን ትልቅ ፋይዳ የሚኖረውን ችግኝ መትክል መቻላችን ፋይዳው ከዚህም በላይ የትየለሌ ነው፡፡

እንደሚታወቀው 2011 ዓ.ም ሐምሌ ወር ውስጥ አገራችን ኢትዮጵያ 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ማሰቧ የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱም ችግኙን ለመትከል የታሰበው ‹‹40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ›› በሚል መሪ ሐሳብ ነው። ታዲያ በወቅቱ በአንድ ጀምበር ለመትከል ታቅዶ የነበረው 200 ሚሊዮን ይሁን እንጂ መነሳሳት ባመጣው ታላቅ ስራ ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያ የዓለም ክብረ ወሰን እንድትይዝ ማድረግ ተችሏል፡፡

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር የዚህን ያህል ቁጥር ለመትከል ማቀዷ ይፋ በሆነበት ጊዜ ብዙዎች ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል›› በሚል ጥያቄያዊ አስተያየት ሲሰነዝሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ዜጎቿ የማንንም ግፊት መጠበቅ ሳያስፈልጋቸው መሳተፍ ለራስ ብሎም የራስ ለሆኑ ሁሉ እንደሆነ በመረዳታቸው ታላቁን ገድል ከማሳካትም አልፎ የተያዘውን ቁጥር በብዙ የሚበልጥ ችግኝ መትከላቸው በወቅቱ ‹አጃኢብ›› አሰኝቶም ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ይህን ማድረጓ ለዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ታላቅ ውለታ እየዋለች ስለመሆኗ እና በተለይ ለዜጎቿ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እፎይታ ስትል እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ያለበለዚያ በከባድ የሙቀት መጠን እያጋየች ካለችው ዓለም ማምለጥ ይሉት ነገር እንደማይታሰብ ከወዲሁ መረዳቱ ብልህነት ነው፡፡

ከወንዛችን ውሃውን፣ ከማሳችን ሰብሉን፣ ከጎተራችን እህሉን፣ ከበረቱ ከብቱን፣ ከጋጣው እና ከጉሮኖው ደግሞ በግና ፍየሉን ማግኘት የምንችለው አካባቢያችንን በወጉ መጠበቅ ስንችል ነው፡፡ አካባቢያችን በአግባቡ ሊጠበቅ የሚችለው ትናንት ተክለን ዛሬ ላይ ደን የሆነውን አካባቢ በመጠበቅና ዛሬ ላይ የተከልነውን ችግኝ በተገቢው መንገድ መንከባከብ ስንችል ነው፡፡

ልክ የወለዱት ልጅ ሲድህ፣ በእግሩ ለመሄድ ደግሞ ሲውተረተር፣ ጉልበቱ ጠንክሮ ሮጥ ሮጥ ሲል ማየት ለወላጅ ከምንም በላይ ደስታ የሚያጭር እንደሆነ ሁሉ በእጃችን መዳፍ ይዘን በቆፈርነው ጉድጓድ ሻጥ ያደረግነው ችግኝም በዚያው በመዳፋችን መዳሰስን ፤ውሃ መጠጣትን ይሻልና የልጃችን ያህል ልንከባከበው የግድ ነው፡ ፡

ልክ እንቦቀቅላ ልጃችንን ሊጎዱት ከሚችሉ የትኞችም ነገሮች መከላከል ግዴታችን እንደሆነው ሁሉ ለልጅ የሚደረግለትን አይነት እንክብካቤና ጥንቃቄ የተሞላበት አያያዝ ለነገ አስበን ዛሬ ለተከልነው ችግኝም እንደሚገባ መዘንጋት የለብንም፡፡

ችግኝን ከመትከል ባለፈ መንከባከብ የውዴታ ግዴታ ከመሆን አልፎ ግዴታችን ወደመሆን መሸጋገር አለበት፡፡ ዓመታዊ የችግኝ ተከላ መርሃግብር እንደ ደራሽ ውሃ አልፎ እንደሚሄድ አይነት ተግባር አድርገው የሚያዩ አካላት ካሉም ከወዲሁ ከዚህ አይነት አመለካከታቸው እንዲታረሙ መደረግ ይኖር ባቸዋል፡፡

ይልቁኑ እስከ አምስተኛው ዓመት በተካሄደው በችግኝ ተከላ ወቅት የታየው አብሮነት ለችግኙ እንክብካቤም ሊደገም፤የተከልነውን ከፍ ሲል ደግሞ በሌሎች ወገኖቻችን የተተከለውን ችግኝ ከውሃ ማጠጣት እስከ ማረምና መኮትኮት ድረስ በመዝለቅ ልንከባከብ ይገባል፡፡

መንከባከብ ከመትከል ይልቅ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው በሦስት ዓመታት ውስጥ ከተተከሉት ችግኞችም በአማካኝ በአጠቃላይ 80 ነጥብ አምስት በመቶ የሚሆኑ ችግኞች መፅደቅ ችለዋል፣ ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ ተተክለው መፅደቅ ያልቻሉ ናቸው፡፡

የማይቻል የለም፤ የሁሉም ቀና ትብብር ከታከለበት የተተከሉ ችግኞች ሁሉ የማይበቅሉበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ሁሉም ከጸደቀ የነገ ደን ይሆናሉ፤ ለነገዎቻችን የምግብ ዋስትናችንን ያረጋግጣሉ፡፡ ለምናደልባቸውም ሆነ ለምናረባቸው እንስሳት በመኖነት ያገለግላሉ። አካባቢያችንን ምቹ የሆነ የአየር ጸባይ እንዲኖረው ያስችላሉ፡፡

ዛሬ ሁላችንም እንደምንረዳው በዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት አሉ የሚባሉ የበረዶ ግግሮች መቅለጥ ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡ የባህር ከፍታ መጨመር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከዚህም የተነሳ ዓለም በማይገመቱ የአየር መዛባት እየተሰቃየች፤ እኛም ቢሆን የዚህ አደጋ ሰለባ ልንሆን እንደምንችል ለመገመት አይከብድም፡፡

ነገ ልጆቻችን የሚኖሩባትን ምድር ገነት ማድረግ ባንችል እንኳ ጤናማ የሆነ የአየር ጸባይ እንዲኖራት ለማድረግ እድሉ በእጃችን ነው፡፡ በመሆኑም ሰሞኑን በብዙ መነሳሳት የተከልናቸው ችግኞችን የጨቅላ ልጃችን ያህል አስበን በቀጣይ ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ እንከባከባቸው።

የኛም ሆነ የመጭዎቹ ትውልዶች እጣ ፈንታን የሚወስኑ የነገ አቅሞቻችን መሆናቸውን ተገንዝበን በቂ እንክብካቤ ለማድረግ ከራሳችን ጋር ቃል እንግባ። ካልተንከባከብናቸው እንደሚጠወልጉ ብሎም እንደሚደርቁ እንረዳ፤ እንክብካቢያችንን ሳያገኙ ቀርተው እስከወዲያኛው የሚያሸልቡ ከሆነ ግን የእኛም የመኖር እጣ ፈንታ ወደዚያው እንደሆነ ለአፍታም አንዘንጋ እላለሁ፡፡ ሰላም !

 ወጋሶ

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *