የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ
እየተመዘገበ ያለው ስኬት አበረታች ነው!

 ዓለማችንን በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ከፍተኛ ስጋት ላይ እየጣሉ ከሚገኙ ቴክኖሎጂ አመጣሽ ችግሮች መካከል የሳይበር ጥቃት በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው። ጥቃቱ ሆን ተብሎ ባልተፈቀዱ የኮምፒውተር ስርዓቶች፣ መሰረተ-ልማቶች እና ኔትዎርኮች ላይ አጥፊ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም በህገወጥ መንገድ ዳታዎችን መበዝበዝ እና አገልግሎት የማስተጓጎል ተግባር ነው፡፡

የሳይበር ጥቃቶች በአብዛኛው ሲስተሞች፣ የኮምፒውተር ስርዓቶች እና መጠቀሚያ መሳሪያዎችን ክፍተት በመጠቀም፤ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚሰነዘርና በግለሰብ፣ በተቋም፤ ከዛም ባለፈ በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ችግሮችን በመፍጠር ከፍ ያለ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ነው።

ሀገራችንም ዘመኑን የሚዋጅ ቴክኖሎጂዎች ባለቤት መሆኗን፤ በተለይም ታላላቅ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሯን ተከትሎ ችግሩ እንደሀገር በስፋት መታየት ከጀመረ ውሎ አድሯል። ሊያስከትል የሚችለውንም ሁለንተናዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ችግሩን መከላከል የሚያስችል ፌደራል መሥሪያ ቤት/የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር/ አቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባ አድርጓል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የሀገራችንን የኢንፎርሜሽንና የኢንፎርሜሽን መሰረተልማቶች ከጥቃት በመከላከል ብሔራዊ ጥቅሞችን እንዲያስጠብቅ በ1999 ዓ.ም በህግ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ፤ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል ሰፋፊ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል።

ለሳይበር ጥቃት አጋላጭ ሀገር አቀፍ ክፍተቶችን በማጥናትና በመድፈን፤ ከዚያም ባለፈ በተለያዩ የፌደራልና የክልል ተቋማት ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን በመከላከል ውጤታማ አፈጻጸም እያስመዘገበ ነው። ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ወቅቶች ያወጣቸው የአፈጻጸም ሪፖርቶች እና ከዚያም በላይ በችግሩ ዙሪያ እንደሀገር የሚታዩ ተጨባጭ የመከላከል አቅሞች ጥሩ ማሳያ ናቸው።

ለዚህም አስተዳደሩ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የ2015 ዓ/ም የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፤ እንደ ሀገር 6 ሺህ 959 የሳይበር ጥቃቶች ተሰንዝረዋል። ከነዚህ ውስጥ 6 ሺህ 768 ያህሉን መመከት ተችሏል፤ የተቀሩት 191 የተሳኩ የሳይበር ጥቃቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ ምላሽ የሚፈልጉትን በመለየት 96 ነጥብ 02 በመቶ ምላሽ ሰጥቷል። 3 ነጥብ 98 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው።

የሳይበር ጥቃቶቹ ዒላማ ያደረጓቸው የፋይናንስ፣ የፀጥታና ደህንነት፣ የሚዲያ እና ቁልፍ የመንግሥት ተቋማትን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የክልል ቢሮዎች፤ የሕክምና እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደነበሩ ተገልጿል። ጥቃቶችን መከላከል በመቻሉ ከሀገሪቱ ካዝና ሊወጣ ይችል የነበር 23 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር መታደግ ተችሏል።

በጀት ዓመቱ በስፋት የተሞከሩት የሳይበር ጥቃት ዓይነቶች መካከልም የድረገጽ ጥቃት 2554፤ ማልዌር 1295፣ የመሠረተ ልማት ቅኝት 603፣ የመሠረተ ልማት ማቋረጥ 1493፤ ሰርጎ መግባት ሙከራ 695፣ በዋነኛነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የጥቃት ሙከራዎቹን መከላከል ባይቻል ሊያስከትሉ ይችሉ የነበረው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ስነልቦናዊ ቀውስ የከፋ ይሆን ነበር።

ሪፖርቱ ከአሀዝ ባለፈ ተቋሙ ምን ያህል የተሰጠውን የሀገርና የሕዝብ ኃላፊነት በአግባቡ ተረድቶ፤ በስኬት ለመወጣት፤ በሁለንተናዊ መልኩ ራሱን ብቁ እያደረገ ስለመሆኑ፤ ለዚህም ከፍ ባለ ቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ በተጨባጭ ማመላከት ያስቻለ ነው።

በብዛት እና በዓይነት፤ ከዚያም ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውስብስብ እየሆነ የመጣውን የሳይበር ጥቃት በተሳካ መንገድ በመከላከል፤ የሀገሪቱን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ አስተዳደሩ እየተንቀሳቀሰበት ያለው መንገድ እና ተቋማዊ ቁርጠኝነት ከፍ ያለ ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባውና ሀገርን ከጥፋት የመታደግ ተልዕኮ ስኬት አካል ነው።

ጥቃቶች ከመታሰባቸው ጀምሮ ክትትል በማድረግና ለይቶም በመተንተን ምላሽ ከመስጠት ባሻገር፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን በማቀናጀት እና በመምራት በየተቋማቱ የኢንፎርሜሽን ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ ባህል እንዲዳብር፣ መሰረተ ልማቶች እንዲገነቡ እና አደረጃጀቶች እንዲፈጠሩ እያከናወነ ያለውም ሥራም ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ሀገራዊ አቅሞችን ለመገንባት ትልቅ ዕድል መሆን የቻለ ነው!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *