ኢትዮጵያና የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተፅዕኖዋ

እአአ በ1983 ሄልሲንኪ ላይ የመጀመሪያው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሲካሄድ 123 ሜዳሊያዎችን የተለያዩ አትሌቶች አስመዝግበዋል። ከእነዚህ ሜዳሊያዎች መካከል በአፍሪካዊያን አትሌቶች የተመዘገቡት ሦስት ብቻ ነበሩ። በአንጻሩ ባለፈው በኦሪገን የዓለም ቻምፒዮና አፍሪካውያን አትሌቶች 28ቱን ማጥለቅ ችለዋል። ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያስመዘገቡት የሜዳሊያ ቁጥር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በመጀመሪያው የሄልሲንኪ ቻምፒዮና በአንድ ሜዳሊያ የተጀመረው የኢትዮጵያ የስኬት ጉዞ 18ኛው የኦሪገን ቻምፒዮና ላይ ወደ 10 ተመንድጋል።

ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው ውጤታማ ሀገር እየሆነች መምጣቷን መገንዘብ ይቻላል። ይህም ኢትዮጵያን በቻምፒዮናው የአርባ ዓመታ ጉዞ ከአፍሪካ ሀገራት ትልቅ አሻራ ያሳረፈች ያደርጋታል። 19ኛው የሃንጋሪ ቡዳፔስት የዓለም ቻምፒዮና 24 ቀናት ብቻ የቀሩት መሆኑን ተከትሎም የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ ካካተታቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ አፍሪካውያን በቻምፒዮናው ከምን ተነስተው የት ደረሱ የሚለው ነው። በዚህም ርዕስ ስር በስፖርቱ መልካም ስምን የገነባችው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላት ተመልክቷል።

በመጀመሪያው ቻምፒዮና የሜዳሊያ ባለቤት የነበሩት አፍሪካውያን አትሌቶች ከናይጄሪያ፣ ሞሮኮ እና ኢትዮጵያ የተገኙ ናቸው። በወቅቱ በኦሊምፒክ መድረክ የገነነ ስም የነበራት ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያ በከበደ ባልቻ በማራቶን የብር ሜዳሊያ በማጥለቅ ነበር ውድድሩን የፈጸመው። በእርግጥ ይህ ውጤት ከአትሌቶቹ ሀገር አንጻር የውቅያኖስን ጠብታ እንደማለት ቢሆንም በዓመታት ተሳትፎ 95 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ 6ኛ ደረጃ ላይ ልትቀመጥ ችላለች። በዚህም ከጎረቤት ሀገር ኬንያ በቀር በአህጉሪቱ የሚቀድማት የለም። የኦሪጎኑ ቻምፒዮና ላይ በ4የወርቅ፣ 4የብር እና 2 የነሃስ በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎች ከዓለም ሀገራት በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ልትቀመጥ ችላለች። ይህ ታሪካዊ ድልም ለሌሎች በብዙ ተምሳሌት ሆኖ ተነሳሽነትን የፈጠረ ነው።

ሌሎች አፍሪካውያን ሀገራትም እየበረቱ በስፖርቱም እንደየቀጣናቸው በተለያዩ ርቀቶች ተጽእኖ እስከመፍጠርም ደርሰዋል። ለአብነት ያህል የሰሜን አፍሪካ አትሌቶች በመካከለኛ ርቀት ቀዳሚ ተጠቃሽና ውጤታማ የመሆናቸውን ያህል ምስራቅ አፍሪካንም በረጅም ርቀት ሩጫዎች በመላው ዓለም የሚስተካከላቸው አልተገኘም። በዚህም ስማቸው በተለየ የሚነሱት ኢትዮጵያና ኬንያ ሲሆኑ፤ እንደ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ እና ሶማሊያ ያሉትም ልዩነት ፈጣሪ አትሌቶችን ማፍራት ችለዋል። ይሁንና በዚህ ዘርፍ ከእነ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በላይ የደመቀ ታሪክ ያለው አትሌት ፈልጎ ማግኘት ያዳግታል።

እአአ በ1993 ስቱትጋርት ቻምፒዮናን የተቀላቀለው ኃይሌ በ10ሺ ሜትር የወርቅ እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያን በማጥለቅ በርቀቱ ያለውን የበላይነት አስመስክሯል። እአአ በ1995፣ 1997፣ 1999፣ 2001 እና 2003 የቻምፒዮናው ተሳትፎም በእነዚሁ ርቀቶች 4 የወርቅ፣ 2የብር እና 1 የነሐስ በድምሩ 7 ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ ችሏል። የረጅም ርቀት ጀግናው ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ 5 የወርቅ እና 1 የነሐስ በጥቅሉ 6 ሜዳሊያዎች በቻምፒዮናው አሳክቷል። በሴቶችም አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ 5 የወርቅ እና 1 የብር በጠቅላላው 6 ሜዳሊያዎችን አስመዝግባለች። በአህጉሪቷ ከኬንያዊው እዝቂየል ኬምቦይ በቀር አንድም ይህንን ታሪክ የሚጋራ አትሌት የለም፤ ይኸውም ሦስቱ አትሌቶች ብቻቸውን ምስራቅ አፍሪካን በረጅም ርቀት ውድድር ስኬታማ ሊያስብል ይችላል።

በሴቶች በኩልም ኢትዮጵያ ታሪካዊ ሀገር ስትሆን፤ ለበርካቶች ተምሳሌት የሚሆኑ ድሎችም ተመዝግበዋል። ለአብነት ያህል እአአ በ2001 ኤድመንተን ላይ በ10ሺ ሜትር በአትሌት ደራቱ ቱሉ፣ ብርሃኔ አደሬ እና ጌጤ ዋሚ ከወርቅ እስከ ነሐስ ያለውን ሜዳሊያ በማጥለቅ አስደናቂ ድል ማስመዝገብ ችለዋል። ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች ያስቆጠረቻቸው ሜዳሊያዎች ሊደገሙ ያልቻሉና በተመሳሳይ አቋም የመገኘትን ምስጢር ሊያስተምር የሚችል ነው።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 /2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *