ታላቅና ታናሽ፣ እናትና ልጅ እንበላቸውና ሁለቱም በጥበብ ቤት ሠርጉን ከምላሹ ፈጽመዋል:: ከፊት በቅዳሜ፣ ከኋላም በእሁድ ተከታትለዋል:: ጠላትን በጦር ድባቅ በመታንበት የአድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ ውስጥ አድዋ ለጥበብ ብለው ቄጤማውን ነስንሰው፣ ከላይ ጥቁሩ ጀበና ከማቶቱ፣ ከስር ነጫጭ ሲኒዎች ከረከቦቱ፣ በጎን የሉባንጃ ጢሱን ሽቅብ እያንቦለቦሉ የጥበብ ቤተሰብን ሁሉ በጥበብ የካደሙት ይመስላል::
በሀበሻ ጥበብ ቀሚስ ሽር ጉድ ሲሉ ከሁለት በአንዱ ተገኝቶ ያልተመለከተ ያለ አይመስለኝም:: ቅዳሜን በክብር ለጥበብ፣ እሁድን በአስቴር ትንሳኤ “መጀን በጥበብ” ያለ በቅምሻ ብቻ መጥገቡን አይዘነጋም:: “ዓመት ዓመት ያድርሰን…የከርሞ ሰው ይበለን” የሚባባሉበት የክብር ለጥበብ ዓመታዊ የእውቅናና የምስጋና ዝግጅት፤ የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ባሳለፍነው ቅዳሜ ስለቱ በዓመቱ ደግሶ ሽር አድርጎታል::
ከቤተሰቡ እንደ አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ደግሞ ቀጣይዋን ሰንበት ተረክቦ በተራው ሰንበቴውን ሲያበላና ሲያጠጣ አምሽቷል:: እንግዲህ ሳምንቱን እንደ ስንዱ እመቤት ሆነው በሠርግና ምላሹ ጠቢቡን ከጥበብ አፍቃሪው ሲያጠግቡት ሰንብተዋልና ከሁለቱም ትንሽ እንፈትፍት::
“ክብር ለጥበብ!” ላለ አሜንታን አይንፈገው! በታች ካቻምና አስቀድሶ፣ በካቻምና ደብሎ፣ አምናን ሰልሶ፣ በዘንድሮ ላይ ለአራተኛ ጊዜ ጉብ ብሏል:: ሕዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም ደማቁን የጥበብ ችቦ አብርታ አልፋለች:: በባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚዘጋጀው ዓመታዊው ክብር ለጥበብ የእውቅናና የምስጋና ሥነ ሥርዓት 2017ን ብሶ ተባብሷል:: እስከዛሬ የነበሩትን ዝግጅቶች ሁሉ የሚያስንቅ ነበር::
ለመታሰቢያነት በተዘጋጀላት አዳራሽ ውስጥ የሆነውን “ትናገር አድዋ!” ማለት ይቀላል:: በሀገራዊ ቃና ጥፍጥ ያለው የማርሽ ባንድ ሕብር ሙዚቃ ገና ከመክፈቻው ልብን ፍንቅል የሚያደርግ ነበር:: የሚሆነው ከአንድ አዳራሽ ውስጥ የማይመስለው ምትሀት የተሞላበቱ የሰርከስ ትርኢት እጅን በአፍ ከመጫን ሌላ ቃላት የማይገኝለት ነበር:: ከክልልና ፌደራል የተሰባሰቡት የዕለቱ ታላላቅ እንግዶችና ተሸላሚዎች፣ እንዲሁም ጥሪው ደርሷቸው የመጡ ሁሉ በሀገር ባህል ልብስ ሽቅርቅር ብለው ሲታዩ በራሱ ቀልብን የሚሰውር ነበር::
መድረኩ በኢቢኤስ ጋዜጠኞች እየተመራ ማክተሚያው ድረስ እየተቀዳ ሲቀርብ የነበረው የጥበብ ወይን የሚያሰክር፣ ሰክረውም የሚንገዳገዱበት ነበር ቢሉ ማዳነቅ አይሁን፤ የጠጣው ያውቃልና::
በአራተኛው የ2017 ዓ.ም ክብር ለጥበብ ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የተመረጡ 28 የጥበብ ባለሙያዎች ቅዳሜ ከሰዓትን በአዳራሹ ተሞሽረዋል:: ከተለያዩ 12 የሙያ ማኅበራት ተፈልቅቆ 36 ባለሙያዎችን በማውጣት የዘንድሮውን የጥበብ ክብር እንዲጎናጸፉ ሆኗል:: በድምሩም 64 የጥበብ መድፈኞች የዘንድሮውን ኒሻን አጥልቀዋል:: በመሃከል መስማት ለተሳናቸው የጥበብ ኮማሪያንም ከዕድሉ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ተደርጓል::
ክብር ለጥበብ ከዓመት ዓመት ከፍ ብድግ እያለ በመጀመሪያው የ2013 ዓ.ም ዝግጅት ላይ 48 የነበሩት ባለክብሮች፤ በ16 አድገው ዘንድሮ 64 ደርሰዋል:: ቀጣዩ 2018 ዓ.ም ደግሞ በመግነጢሳዊ የቁጥር መወንጨፍ እንደሚመጣ ተስፋ እናድርግ:: የዘንድሮውን ግን ለመረጃ ቅምሻ ያህል በዚሁ እናክትመው::
ከቅዳሜው የእሁድ ሰው ብሎን ለሌላ አጀብ አሁንም ከአድዋ መታሰቢያ አዳራሽ አስቴርን ፍለጋ መግባታችን ነው:: በዘመን ርቀት፣ በዓመታት ብዛት ያረጀና ያፈጀው “አስቴር” የተሰኘው ፊልማችን ራሱን እንደ ንስር አድሶ ከአሁኖቹ የቴክኖሎጂ ዘመን ፊልሞቻችን ጋር ሊወዳደር መጥቷል ሲሉ ሰምተን፣ እኛም ደረስንና አፋችንን በእውነት አብሰን ወጣን:: ዳግም ተወልዶ መምጣቱ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ የፊልም ኢንዱስትሪያችን ለመብረር ለሚያደርገው ጥረት የከፍታው መሰላል ለመሆንም ችሏል::
በ1980ዎቹ የፊልም ኢንዱስትሪያችን የነበረበትን ቦታ ሁላችንም የምናውቀው ነው:: ፊልም ለመሥራት ቀርቶ የተሠራውን ለመመልከት እንኳን የነበረው ውጣውረድ ለአሁኑ ዘመን አስቂኝ ሊሆን ይችላል:: ዕድል ቀንቶ የማየቱን አጋጣሚ ቢያገኙ እንኳን ከነበረው የድምጽና የምስል ጥራት የተነሳ በሕልም ብዥታ ውስጥ ያሉ ያህል ነበር:: ታዲያ “አስቴር” የተሰኘው ፊልምም የተሠራው በዚያው ሰሞን ቢሆንም አዲስ የቴክኖሎጂ ግብአት ተጨምሮና በድንቅ ሀገር በቀል የፊልም ጠቢባን የተሠራ ስለነበረ ያኔም ግሩም የሚባል ዓይነት ነበር::
በፊልም ኢንዱስትሪያችን ታሪክ በጥቁርና ነጭ የተሠራው የመጀመሪያው ፊልም “ሕይወት” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ይሄው “አስቴር” ነው:: በጊዜው የነበረው የመጨረሻ አቅምም በጥቁርና ነጭ ቀለም መሥራት ነበር:: ታዲያ ለዚያ ዘመን እንጂ ጥቁርና ነጭ ለአሁኑ ዘመን ቁልቁል የሚያሽሟጥጡበት ነው:: ያም ሆነ ይህ ግን አስቴር ፊልም የኛ የመቻልና በራስ አቅም የመቆም ቀንዲል ነው:: ምክንያቱም በርከት ያሉት የሀገራችን ፊልሞች በውጭ ባለሙያ እርዳታ ሲሠሩ በነበረበት ጊዜ በሀገር የፊልም ጠቢባን በድንቅ ሁኔታ የተሠራ በመሆኑ::
ዛሬም ከፊልም ኢንዱስትሪው ስሙ ያልጠፋው ብርሃኑ ሽብሩን በ”አስቴር” ፊልም እንድናደንቀው ከሚያስገድደን ነገር አንዱ በተዋናይ መረጣ (ካስቲንግ) ጥንቅቅ ያለና የተዋጣለት መሆኑ ነው:: ተፈሪ ዓለሙ፣ ጥላሁን ጉግሳ፣ ትዕግስት ደጉ፣ ኤልሳቤጥ መላኩ፣ ጀማነሽ ሰለሞን፣ አብራር አብዶ፣ ፍቃዱ ተ/ክለማርያም፣ ጌታነህ ምህረቱ፣ ኃይለማርያም ሰይፉ፣ ተስፋዬ ስንቄ እና ሌሎችም የተሳተፉበት ፊልም ነበር::
በጊዜው ለአስቴር ፊልም ከመረጣቸው ተዋንያን መካከል 80 ከመቶ የሚሆኑት ዛሬ ላይ አንጋፋ ብለን የምንዘምርላቸው ለመሆን በቅተዋል:: የብርሃኑ ሽብሩ ዓይኖች የተለዩ ነበሩ:: በዚህ ፊልም ውስጥ እርሱን የምናደንቅበት ሌላኛው ነገር የቦታ መረጣ (ሎኬሽን) ላይም የተሳካለት መሆኑ ነው:: የዘመኑ ትልቁ ችግር በነበረው ሲኒማቶግራፊ የተሳተፈበት አበበ ቀፀላ የአቅሙን ጥግ ድረስ ስለመጠበቡ ፊልሙን የተመለከተ ዛሬም ይመሰክርለታል:: አድማሱ ዓለሙ በአርት ዳይሬክተርነት፣ ሙሉ አረጋይ ደግሞ በኤዲተርነት ሁሉንም ተጋፍጠው አሸንፈውበታል::
በድርሰትና ዝግጅት ሰለሞን በቀለ ወያ ከፊታውራሪነቱ ጋር እያሳመረ በውብ ጎዳና ላይ መርቶታል:: በዓድዋ መታሰቢያ አዳራሽ በነበረው ዝግጅት ላይም በሕይወት ያሉት አንጋፋዎቹ ከታዳሚው ፊት ተቀምጠው ፊልሙን ሲሠሩ የገጠማቸውንና የነበረውን ሁኔታ ሁሉ በትዝታ አጫውተውታል::
የአስቴር ዳግም ውልደት ምንድነው? ፊልሙ ተሠርቶ ለእይታ ከበቃ 34 ዓመታት ሞልተውታል:: ሰው ቢሆን ኖሮ በወጣት አሊያም በጎልማሳ ዱካ ላይ እናስቀምጠው ነበር:: እንደፊልም ግን አርጅቶ ሸብቷል ለማለት ይቻላል:: አሁን ላይ የተሠራና ለወደፊቱ የዛሬ 34 ዓመት ቢሆን ኖሮ መላ አናጣለትም ነበር፤ ግን ከወደኋላ የዛሬ 34 ዓመታት በመሆኑ እንደነበረው ሆኖ ዛሬ ላይ የመታየት ዕድል አልነበረውም::
በዚያን ዘመን ፊልሞች ሲታዩበት የነበረው ቴክኖሎጂ በደረስንበት ዘመን ከተጣለበት እንኳን ለቅርስነት አይገኝምና እንደመላው ካልዘየዱላቸው ፊልሞቹም አብረው መጥፋታቸው አይቀርም:: አሁን ዘመኑ የዲጂታል ዘመን ነው:: ያኔ ደግሞ አይታወቅም ነበር:: እናም ሽግግሩ አዲስ ለሚሠሩት ፊልሞቻችን ተድላ ቢሆንም ቀደም ሲል ለተሠሩት ግን መቃብር ቆፍሮ አፈር እንደማልበስ ነው:: መቃብራቸው ላይም ሳር በቅሎባቸዋል:: ይህን የተመለከተው የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ነበር እኚህን የሞት መንገድ ተጓዥ የሆኑትን ፊልሞቻችንን ለማዳን ሲል በየፊናው ሕይወት አድን አሰማርቶ ከሞት መንጋጋ መንጠቅ መጀመሩ::
ከዘመኑ ጋር ተኳርፈው ዘመን ሊበላቸው የነበሩትን እያስመለጠ ከዘመኑ ጋር ያስማማቸው ገባ:: አማራጩም ከወደቁበት እያነሱ በቴክኖሎጂው ማዘመን ነበር:: ከዚህ ቀደም “ሂሩት አባቷ ማነው?” የተሰኘውን ፊልም በማዘመን ለእይታ እንዲበቃ ለሲኒማ ቤቶች አስረክቧል:: አሁን ደግሞ “አስቴር” ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ተጣጥሞ በጥራት እንዲታይ፣ ከነበረበት 35 ሚሜ ተንቀሳቃሽ ምስል ወደ ዲጂታል መልክ በመቀየር ስኬታማ ሆኗል::
ሂደቱ ቀላል አልነበረም:: ከፍተኛ በጀት በመመደብ ወደ ግሪክ ሀገር ድረስ ተልኮ ነበር ዳግም ውልደቱን ያገኘው:: ታሪክ ሳይነካ፣ ባሕል ሳይቆራረስ፣ ማንነት ሳይሸራረፍ ከዘመኑ ጋር መዘመን ማለት እንዴት እንደሆን የዚህ ፊልም የለውጥ መንገድ ትልቅ ማስተማሪያ ነው::
ፊልሙ ትናንትናንና ከትናንት በስቲያ የነበረውን ዘመን በማኅበረሰባዊ መስታየቱ ያሳናል:: ከ34 ዓመታት በፊት ደራሲው ሲጽፈው በዘመን የተለያዩ ሁለት ለየቅል የሆኑ ማኅበረሰባዊ ጣሪያና ወለል እየተመለከተ ነበር:: እኛ ደግሞ አሁን ያለንበትን ሌላ አንድ በመጨመር በሦስት የዘመን መስታየቶች ፊት ቆመን እንመለከተዋለን::
ዓመታትን ተሻግሮ ዛሬ ላይ ስንመለከተው ያኔ ያነበረውን ሌላ አዲስ ገጽታ እንድንመለከት ስለሚያደርገን የፊልሙ ጊዜና ታሪክ ነጋሪነቱ ወደር አይገኝለትም:: ለእይታ የበቃው በ1984 ዓ.ም ቢሆንም የተጻፈው ግን በ1970 ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ነው:: ታዲያ ያ ጊዜ ማለት አስቀድሞ የነበረው የፊውዳል ሥርዓት ከበርቴና ጪሰኛነት እየሟሟ፣ ኅብረተሰባዊነት እየተቀጣጠለ፣ ከፊት ደግሞ ፌደራላዊ ፈረስ እየገሰገሰ ሲመጣ የሚታይበት ጊዜ ነበርና የፊልሙ መስታየት ምስሉ እጅግ ወሳኝ ነው:: በደራሲው እይታ ግን ከፊት ያለው በተዘዋዋሪ ቢሆንም በቀጥታ ዓይን ውስጥ አልገባም::
ለፊልሙ ታሪክ መሰላል አድርጎ ለመጠቀም የፈለገው ከኋላ በርዝራዥ እያለፈው ያለውንና ያለበትን ዘመን ነው:: የፊልሙ አስኳል የሆኑትን ባልና ሚስትን አንዱን ከከበርቴው ቤተሰብ፣ ሌላውንም ከታችኛው የጪሰኛ መደብ ላይ ቀድቶታል::
ተፈሪ ዓለሙ የሚጫወተው ዶክተር ከበደ ከከበርቴው ቤተሰብ የተገኘ አፈንጋጭ ነው:: ምስኪኗ አስቴር ደግሞ በድህነት ብቻም ሳይሆን ከማይፈቀፈቅ የሕይወት አሳር ጋር የኖረችና የምትኖር አሳዛኝ ሴት ናት:: እኚህ ሁለት ለየቅል የሆኑ የሁለት ዓለም ሰዎች ግን በትዳር ተጣመሩ:: ፊልም ገና ሲጀምር የ5ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸው ለማክበር እንግዶቻቸውን ሲጠባበቁ ነው::
የተጠራው ሁሉ በሰበብ አስባቡ ቀርቶ ጠሪ አክባሪ ለመሆን የቻሉት ጥላሁን ጉግሳ የሚጫወተው ገጸ ሰብና ባለቤቱ ናቸው:: በዓሉን ሁለቱ ጥንዶች ለአራት ሆነው በማክበር ላይ ናቸው:: ድንገት ግን በአባት የቅርብ ክትትልና እንክብካቤ የተነፈጋቸው ሁለቱ ማቲ ልጆቻቸው መረን ለቀው በመሃል የዝግጅቱን ድባብ ቀየሩት:: እሳት ለብሶ፣ እሳት ጎርሶ የተነሳው አባታቸው ዶክተር ከበደ አሳዶ ከገቡበት ክፍል ውስጥ በአይቀጡ ቅጣት ቡጢውን ጨብጦ ሲነርታቸው ዳፋው ለማስጣል መሃል ለገባችው እናታቸው አስቴርም ሆኖ ይደቁሳታል::
ቤቱ ውጥንቅጡ ወጥቶ ሳለ የቤቱ ስልክ ያቃጭልና ከበደ ሆዬ አንስቶ ካነጋገረ በኋላ ስልኩን እንደዘጋ ወደ ሀኪም ቤት መሄድ አለብኝ ሲል እንግዶቹን ተጫወቱ ብሎ ፈትለክ ይላል:: ከበደ አስቴርን ከቤት ጎልቶ ከውጭ የለመደው አመል ስለነበረ ወደ እቁባቶቹ እንጂ የእውነትም ወደ ሀኪም ቤት አልነበረም:: ከዚህ በኋላ ያለው የታሪክ ፍሰቱ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በምልሰት ወደኋላ ትውስታ ነገራ ነው::
ስክሪፕት አዘጋጁም ለምልሰቱ ድልድይ አድርጎ የተጠቀመው የታሪኩ ባለቤት የሆነችውን አስቴርንና ከባለቤቱ ጋር የተገኘውን እንግዳውን ወዳጃቸውን ነው:: ሁሉንም ነገር ከስር መሠረቱ ለማወቅ የጓጓው ወዳጃቸው ሲጠይቃትና ስትነግረው ምሽቱ ነጉዶ ሌት ይቀራረባል::
ከእናቷ ሞት የሚጀምረው አሳሯ በእንጀራ እናት እየተገፋች፣ እናስተምራታለን ብለው በወሰዷት ከበርቴዎች በደልን እየተጋተች፣ የረገጠችበት ሁሉ የመከራ ድግስ ሆነ:: ልጄ እየተማረች ልትደርስልኝ በሚል የተስፋ ብርሃን የከረመው አባቷ ይህን ያወቀ ዕለት ከአሳዳጊዎቿ ወስዶ ከራሱ ጋር ቢያደርጋትም የእንጀራ እናት ግን በመርዝ እስከመመረዝ ደረሰች:: በዚሁ ምክንያት ሆስፒታል በተኛችበት ነበር በዶክተር ከበደ ልብ ውስጥ የገባችው::
የሚያደርግላት እንክብካቤ ገዝቷታል:: መቀራረባቸው ጠንክሮም ከሀኪም ቤት ከወጣች በኋላም ይገናኙ ጀመር:: በመሃል አርግዛለች በማለት የእንጀራ እናቷ ታሳብቅባትና ከአባቷ ቤትም ትባረራለች:: ከበደ ግን ማርገዟን ቢያውቅም ወዷት ነበርና ከበርቴዎቹ ወላጆቹ ያጩለትን አቻውን ትቶ አስቴርን አገባት:: እስከተወሰኑ ጊዜያት ከበደ የምርም ወዷት ነበር:: አስቴርም የሰላምና ጥሩ የትዳር ሕይወት ጀምራ የእስከዛሬው በደሏ የተካሰች ሲመስላት ድንገት መሃል ላይ መክሰም ጀመረ::
በሰው ምክርና በወላጆቹ ንዝነዛ አመሉ መለዋወጥ የጀመረው ዶክተር ከበደ ፈገግታዋን እያጨለመው የመከራዋ ምንጭ መሆን ጀመረ:: እሷን ከቤቱ አኑሮ ደጅ ደጁን ወጣ:: ልጆቹን ከነመፈጠራቸው ረስቶ ቸል አላቸው:: ማታ እንግዶቹን ጥሎ ከእቁባቱ ጭን ያደረው ከበደ በጠዋቱ ከቤት ሲደርስ ባለቤቱ አስቴር በገዛ አልጋዋ ላይ ከሌላ ወንድ እቅፍ ውስጥ መስላው ለሞት ሲሰናዳ እንግዶቹ ጥንዶች ሆነው አገኛቸው::
አስቴር ማታ የት እንደነበረ ከምታምነው ሰው ተደውሎ ተነግሯታል:: ወዳለችበት ክፍል ዘልቆ መነታረክ ጀመሩ:: ከደቂቃዎች በኋላ ግን ሁሉም ነገር እንዳልነበረ ሆነ:: ትዕግስትና ተስፋዋ ተሟጦ በመጥፎ የዝምታ ምሬት ውስጥ የነበረችው አስቴር አፈሙዙን አነጣጥራ የደገነችውን ሽጉጥ ቃታውን ሳበችው:: ከበደ ከወለሉ ላይ ተዘረረ:: ከፊልሙ መቋጫ በኋላ ያለው የልጆቹ ሕይወት ምናልባትም የአስቴርን መጀመሪያ የሚደግሙት ይመስላል:: ካበቃው የፊልም መጨረሻ ከታሰበበት ለሌላ ሁለተኛ ፊልም መጀመሪያ ሊሆን የሚችል ነው::
ምስኪኗ አስቴር ግን ገና በለጋነቷ በስቃይ የጀመረችው ሕይወት ሳያዝን አሳልፎ ለመጨረሻው ሰቆቃ ሰጣት:: የቆሰለው ልቧ የማያመረቅዝ፣ እንባዋ የማይደርቅ አሳዛኝ ነብስ ናት:: ምናልባትም ልክ እንደፊልሙ ሁሉ ከዘመናት ሞት በኋላ ዳግም ትስቅ ይሆናል:: ከልጆቿ እጣፈንታ ጋር ሁሉም ነገር በእንዲህ እንዳለም ፊልሙ ለሲኒማ ቤቶች ተበርክቷል:: የአንዱ መጨረሻ የሌላው መጀመሪያ ነውና ሌላም እናይ ይሆናል::
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም