ሲምቦ ዓለማየሁ – የዓመቱ ኮከብ ወጣት አትሌት እጩ

የዓለም አትሌቲክስ በተለያዩ ዘርፎች የዓመቱን ምርጥ አትሌቶች የመጨረሻ ሁለት እጩዎች ይፋ ሲያደርግ የኦሊምፒክ ማራቶን ቻምፒዮኑ ታምራት ቶላ ከቤት ውጪ ውድድሮች ዘርፍ ላይ መካተቱ ይታወቃል። የዓለም አትሌቲክስ ከቀናት በፊት የዓመቱን ወጣት ኮከብ አትሌቶች (ከ20 ዓመት በታች) የመጨረሻ ሦስት እጩዎች ይፋ ሲያደርግም ኢትዮጵያዊቷ ሲምቦ ዓለማየሁ አንዷ ሆናለች።

በ2024 የውድድር ዓመት በፓሪስ ኦሊምፒክ፣ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና፣ በዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና፣ በዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮናና በሌሎች የግል ውድድሮች አስደናቂ ብቃት ማሳየት የቻሉ እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ አትሌቶች እጩ ሆነው መቅረባቸውን የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።

በሴቶች ከመጨረሻዎቹ ሦስት እጩዎች አንዷ መሆን የቻለችው ወጣቷ አትሌት ሲምቦ ዓለማየሁ፣ በዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና በ3ሺ ሜትር መሰናክል አሸናፊ መሆኗ የሚታወስ ሲሆን፣ በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክም በተመሳሳይ ርቀት ድንቅ ተፎካካሪ በመሆን አምስተኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው። ይህም የውድድር ዓመቱ ስኬቷ ከእድሜ አንፃር የዓመቱን ኮከብ ወጣት አትሌቶች ሽልማት ለማሸነፍ እንድትታጭ አድርጓታል።

ሲምቦ እንደ በርካታ ከዋክብት አትሌቶች ሁሉ የአትሌቲክስ ሕይወትን የጀመረችው የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለች ነው። ለዚህም በፕሮፌሽናል ደረጃ የሩጫ ልምምዶችን ትሰራ የነበረች ታላቅ እህቷ እንዲሁም የአካል ማጎልመሻ መምህሯ ያበረታቷት እንደነበር ለዓለም አትሌቲክስ በአንድ ወቅት በሰጠችው ቃለምልልስ ተናግራለች።

ሲምቦ አትሌቲክስን ስትጀምር ቤተሰቦቿ ከስፖርቱ ይልቅ ትምህርቷ ላይ ብቻ እንድታተኩር ነበር ፍላጎታቸው። አባቷ ግን በተለየ ሁኔታ በአትሌቲክስ ሕይወቷ እንድትገፋበት ያግዟት ነበራቸው። “አባቴ አትሌት እንድሆን የተለየ ፍላጎት ነበረው፣ ይህ ፍላጎቱ ምናልባት ልጅ እያለሁ ፈጣን ስለነበርኩ የመነጨ ይሆናል፣ የትም ቦታ ሲልከኝ ፈጥኜ ስራዬን ጨርሳለሁ፣ በዚህ ላይ አትሌት የመሆን ፍላጎቴንም የተረዳ ይመስለኛል” ትላለች።

ተወልዳ ያደገችው ሳሙዔል ተፈራ፣ ኮረኒ ጀሊላ፣ ሹራ ቂጣታና ሌሎችም አትሌቶች በተገኙበት ምዕራብ ሸዋ ነው፡፡ ወደ አትሌቲክስ ሕይወት እንድትገባ ምክንያት የሆነቻት ግን ከልጅነት አንስቶ ስትሮጥ እየተመለከተቻት ያደገችው ጀግናዋን አትሌት ደራርቱ ቱሉ ናት፡፡ ‹‹አባቴ በአትሌቲክስ እንድገፋ ሊያበረታታኝ የቻለው በደራርቱ ምክንያት ነው፣ ምክንያቱም እሷ እንደ ሀገር ኩራት ከመሆኗ ባሻገር ለበርካቶች ተነሳሽነት ምክንያት ነች፣ ከልጅነቴ ጀምሮ እወዳታለሁ፣ የ5ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ የእሷ ፎቶ ግራፍ በደብተሮቼ ውስጥ አይጠፋም ነበር›› በማለት ሲምቦ ትናገራለች፡፡

ሲምቦ ከሌሎች የመም ውድድሮች ይልቅ ፈታኙን የ3ሺ ሜትር መሰናክል መምረጧ ራሷን በአስቸጋሪ ነገሮች ለመፈተን ካላት ፍላጎት የመነጨ መሆኑን ታስረዳለች፡፡ ‹‹ፈታኝ ነገሮችን መሞከር እወዳለሁ፣ ለዚህም ከወንዶች ጋር ሳይቀር እየተወዳደርኩ አሸንፍ ነበር፣ ፈረስም እጋልብ ነበር፣ ለዚህም ይመስለኛል ከልጅነቴ አንስቶ ጠንካራ የነበርኩት›› ትላለች፡፡ የሲምቦ አሰልጣኝ ብርሃኑ መኮንን ሲናገርም ‹‹እሷ በተፈጥሮ ጠንካራ ተፎካካሪና አሸናፊ ነች፣ ከመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ውድድሯ ጀምሮ የመጣችበት መንገድም ይህን ያረጋግጣል፣ ገና ወደፊትም ብዙ ስኬቶች ይኖሯታል›› በማለት ከዓመት በፊት ለዓለም አትሌቲክስ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

እጩ ሆና የቀረበችው ሌላኛዋ አትሌት ሰርቢያዊቷ የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪ አንጀሊና ቶፒክ ናት። ይህች ወጣት አትሌት በዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና የከፍታ ዝላይ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ስትሆን፣ በፓሪስ ኦሊምፒክ የፍፃሜ ተፋላሚና በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ሦስተኛዋ እጩ ቻይናዊቷ የጦር ውርወራ ተወዳዳሪ ያን ዢዪ ስትሆን፣ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ከማሸነፏ በተጨማሪ የዓለም ከ20 ዓመት በታች የጦር ውርወራ ክብረወሰንን መስበር ችላለች። ይህም ክብረወሰኗ ከሁለቱ ተፎካካሪዎቿ አንፃር በውድድር ዓመቱ የተሻለች ስኬታማ ወጣት አትሌት ሆና ሽልማቱን ለማሸነፍ እንድትታጭ አድርጓታል።

የእነዚህ እጩ ኮከብ አትሌቶች የሽልማት ስነስርዓት በመጪው የፈረንጆች ወር የመጀመሪያ ቀን በሞናኮ ሲካሄድ በአዋቂዎቹም አሸናፊ የሚሆነው አትሌት በተመሳሳይ ቀን ይከናወናል፡፡

ቦጋለ አበበ

 አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You