በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፉ ከመጡ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል አንዱ የሆርቲካልቸር ዘርፍ ነው። የሆርቲካልቸር ዘርፍ ከሌሎች የውጭ ንግድ ዘርፎች በተለየ መልኩ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ሀገሪቱን በብዙ ይጠቅማሉ ተብለው ከተለዩ ዘርፎች መካከል ተጠቃሽ ነው። ከሆርቲካልቸር ዘርፍ አንዱ የአበባ ልማት ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ለአበባ ልማት ምቹ የአየር ጸባይ፣ መልከአምድራዊ አቀማመጥና ሰፊ የሰው ኃይል ያላት ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላት ዕምቅ ሀብት፣ ተደማምሮ በአበባ ልማት ዘርፍ ተመራጭ አድርጓታል።
ኢትዮጵያ የአበባ ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ መላክ ከጀመረች ጥቂት ጊዜያት ቢሆንም ከአፍሪካ ከኬንያ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ። አሁን ላይ በሀገሪቱ በአበባ ልማት ኢንቨስትመንት ብቻ ከ60 በላይ የሆኑ ባለሀብቶች ተሰማርተዋል። ይህም አገሪቷ ወደ ውጭ ገበያ የምትልከው የአበባ ምርት መጠንና የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ እያደገ የመጣ መሆኑን ያሳያል። በየጊዜው ወደ ውጭ በምትልከው የአበባ ምርቶች የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ እየጨመረ ስለመምጣቱ መረጃዎች ያሳያሉ። ለአብነትም በ2014 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ የአበባ ምርቶች የውጭ ንግድ 421 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ በ2015 በጀት ዓመት 567 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል።
በግብርና ሚኒስቴር የአበባ ልማት ዲስክ ኃላፊ አቶ እሸቱ አብረሃም እንዳሉት፤ በአበባ ልማት ዘርፍ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም አበረታች ውጤት የተመዘገበበት ነው። 2014 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ገበያ የተላከውን የአበባ ምርት መነሻ በማድረግ በ2015 በጀት ዓመት 122 ሺ 045 ቶን የአበባ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ታቅዶ፤ 112 ሺ 985 ነጥብ ሰባት ቶን የአበባ ምርቶች ወደ ውጭ መላክ ተችሏል። አፈጻጸሙም 92 ነጥብ ስድስት በመቶ ሲሆን፤ በ2014 በጀት ዓመት ላይ 110 ሺ 290 ቶን የአበባ ምርቶች ወደ ውጭ ገበያ ተልከዋል።
‹‹አሁን ላይ የአበባ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የመላኩ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል›› የሚሉት አቶ እሸቱ፤ ነገር ግን ወደ ውጭ ገበያ የሚላከው የአበባ ምርት መጠን ከዚህም በላይ እንዲጨምር እየተሠራ ነው። ይሁንና የምርት መጠኑን ለመጨመር በሚደረገው ጥረት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ስለመኖራቸው ጠቅሰው በዚህ ምክንያት ብዙ የአበባ ምርት ወደ ውጭ ገበያ መላክ አለመቻሉን ነው የገለጹት።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በአበባ ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የማስፋፊያ ቦታ እንደልባቸው ማግኘት አልቻሉም። ክልሎችም በሚፈለገው መጠን የመሬት አቅርቦት እየሰጡ ስላልሆነ የአበባ ምርትን ለማስፋፋትና አዳዲስ ባለሀብቶችን ወደ ዘርፉ መሳብ ሳይቻል በመቅረቱ አሁን ላይ የአበባ ልማቱ እየተስፋፋ እንዳይደለ ጠቅሰው፤ አዳዲስ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአሁን ወቅት የአበባ ምርት ልማት በማስፋፋት ላይ እምብዛም ለውጥ አለመታየቱን የጠቆሙት አቶ እሸቱ፤ ወደ ውጭ በመላክ ከሚገኘው ገቢ አንጻር ወይም በዶላር ላይ እየታየ ያለው ለውጥ ካለው ገበያ አንጻር ዋጋው በመጨመሩ ምክንያት ተፈጠረ ነው ይላሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ የአበባ ምርት እንዳይጨምርና እንዳይስፋፋ ካደረጉ ተግዳሮቶች መካካል ለማስፋፊያ በቂ መሬት አለመገኘቱ አንዱ ሲሆን፤ የሩሲያና የዩኩሬን ጦርነትም ሌላኛው ምክንያት ነው። በጦርነቱ ምክንያት የነዳጅ አቅርቦት በመቀነሱ ግብዓቶች፣ ኮንቴነሮች፣ መጓጓዣዎች እና ሌሎች ግብዓቶች ላይ ዋጋ እንዲጨምርና ምርቱ በሚፈለገው መጠን እንዳይገኝ አድርጓል። ይህም ምርቱ ላይ ተፅእኖ ይፈጥራል። በተመሳሳይ በጦርነቱ የተነሳ ወደ ሩሲያ ይላክ የነበረው የአበባ ምርት የመላክ ሥራ ተቋርጧል። በዚህም ከሩሲያ የሚገኘው የአበባ ገበያ ቀንሷል። የአየር ንብረት ለውጥም ሌላኛው ተግዳሮት እንደሆነ ጠቅሰው፤ እንደሀገር በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፤ እነዚህ በአበባ ምርት ላይ የሚታዩ ዋና ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸውን ነው አቶ እሸቱ የሚገልጹት።
አበባ ሲመረት በዋናነት የሚያስፈልገው ነገር ግብዓት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ እሸቱ፤ በበጀት ዓመቱ ከተሰሩ ሥራዎች ውስጥ የአበባ ልማት ላይ ከሚገጥሙ ችግሮች አንዱ የሆነው ግብዓት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን አመላክተዋል። ‹‹ ቀደም ሲል በአበባ ልማት የተሰማሩ ባለሃብቶች የግብዓት አቅርቦት ለማግኘት እኛ ጋር ይመጡ ነበር፤ ከዚያም ወደ ግብርና ሚኒስቴር የሚላኩበት የተጓተተ አሠራር ነበር›› የሚሉት አቶ እሸቱ፤ አሁን ግን በአበባ ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚፈልጉትን ግብዓት ለማግኘት ሲፈልጉ በኦንላይን አመልክተው ለአበባ ምርት የሚያስፈልገው ግብዓት በትክክል እንዲቀርብላቸው በግብርና ባለስልጣን መስሪያ ቤት በኩል የሚጨርሱበት አሠራር ተዘርግቷል ይላሉ።
ለአበባ ምርት የሚያስፈልጉት እነዚህ ግብዓቶች የምንላቸው ኬሚካል፣ ማዳበሪያ እና አሲዶች እና የመሳሳሉትን የሚያካትት መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ የኦንላይን አሠራር (ሲስተም) ባለሀብቶቹ የሚፈልጉትን ግብዓት በፍጥነት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
በቀጣይ የአበባ ልማት ዘርፉን አስፋፍቶ ለማስቀጠል በዋናነት በተግዳሮትነት ሲነሳ የነበረው የመሬት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚቻልበት ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባ የገለጹት አቶ እሸቱ፤ የመሬት አቅርቦቱን በማበራከት የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስፋት ያስፈልጋል ይላሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚነሱ ችግሮችም እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሁኔታ ሲረጋጋ የሚስተካከሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የገበያ መዳረሻዎች የሚሰፉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ነገር ግን ተጨማሪ የገበያ አማራጮችን ማስፋት አስፈላጊ በመሆኑ እንደ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና የመሳሳሉ ሀገራት ላይ ለማስፋት ታስቦ ሥራዎች እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል። የሩሲያ ጦርነት የሚያቆም ከሆነ ገበያውን በድጋሚ መጠቀም የሚያስችል ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አስረድተዋል። ይህም ከገበያ አንጻር የሚሠራ ሥራ በመሆኑ ከምርት አንጻር ባለሀብቱ ግብዓት ፍለጋ የሚያደርጋቸውን ምልልሶች በመቀነስ ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።
የአበባ ምርት መዳረሻ ገበያዎች ከሆኑት ዋነኛው ኔዘርላንድ ስትሆን ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነውን የአበባ ገበያ የያዘች ሀገር ናት። ሳውዲ አረቢያ፣ ዩናይትድስ ኪንግደም፣ ዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ አረብ ኢምሬት፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያና ካናዳ እንደየቅደመተከተላቸው የተወሰነ የገበያ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።
አሁን ላይ በአበባ ኢንቪስትመንት ላይ የተሰማሩ ከ60 በላይ ባለሀብቶች መኖራቸው የሚናገሩት አቶ እሸቱ፤ ዝዋይ፣ ቆቃ፣ ቢሾፍቱ፣ ሆለታ፣ ሰበታ አካባቢ የአበባ እርሻዎች በስፋት የሚገኙባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ባህርዳር እና ወልቂጤም እንዲሁ የአበባ እርሻ የሚገኝ እንደሆነ ገልጸዋል። ‹‹በአበባ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ቴክኖሎጂን ከአገር ውስጥ አይፈልጉም፤ በአገር ውስጥ እንዲመቻችላቸው የሚፈልጉት ግብዓቶችን ነው›› ይላሉ።
በኢትዮጵያ የሚመረተው የአበባ ምርት በሦስት አይነት የሚከፈል ሲሆን፤ በከፍተኛ ደረጃ የሚመረተው ሮዝ ወይም ጽጌረዳ አበባ ነው። ሰመር ፍላወር እና ከቲንግ ፍላወር (በቁርጥራጭ) የሚሸጡ አበባዎች እንዲሁ ይመረታሉ። አሁን ላይ ባለው ሁኔታ የሀገር ውስጥ የአበባ ምርት ገበያ ስታንዳርዱን ያልተከተለ (መስፈርቱን ያላሟላ) ምርት ወደ ውጭ ገበያ መላክ የማይችል ሲሆን፤ አበባ ገዢ የሆኑ ሀገራትን መስፈርት ማሟላት ያልቻሉ የአበባ ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ ይውላሉ። በተለይም ከእድገት መጠን በላይ የሆነ እድገት (Over grew) ቢያጋጥም፣ አበቦቹ ቢፈነዱ እና መሰል ጉዳቶች ሲገጥማቸው ወደ ውጭ ኤክስፖርት ቢደረጉም ተቀባይነት ስለማያገኙ ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲውሉ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።
አበቦች ወደ ውጭ በሚላኩበት ጊዜ ጥራታቸው ጠብቀው የሚጠበቅባቸውን መስፈርት አሟልተው እስካልተላኩ ድረስ ተቀባይ ሀገራትም የአበባ ምርቶቹን አይቀበሉትም የሚሉት አቶ እሸቱ፤ ‹‹የአበባ ምርቶች ወደ ውጭ ሲላኩ ዓለም አቀፍ ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች እንዲያሟሉ ተደርገው ስለሚላኩ እስካሁን በጥራት ሆነ በመስፈርት ባለማሟላት ረገድ የሚታዩ ችግሮች የሉም፤ ወደ ውጭ ተልኮ መስፈርቱን ሳያሟሉ ቀርተው ተመለሱ የሚባሉ የአበባ ምርቶች አልገጠመንም ›› ነው ያሉት።
እስካሁን ባለው ሂደት ምናልባት ኳርንቲን ቴስት እንኳን ቢከስት ወዲያውኑ አስተካክለው እንዲላክ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩ ጠቁመው፤ የአበባ ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ መላክ (ኤክስፖርት) በማድረግ የጎላ ችግር ገጥሞ አያውቅም ይላሉ። የአበባ ምርቶች ወደ ውጪ ሲላኩም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ መስፈርቶችን በመጠቀም እንደየደንበኞቻቸው ፍላጎት አይነት ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች አሟልተው ስለሚዘጋጁ በዚህ ረገድ ብዙ ችግሮች አይስተዋሉም ነው የሚሉት።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በአበባ ኢንቪስትመንት ላይ የሚነሱ የፍሳሽ አወጋገድ ላይ ቅሪቶችን አጣርቶ የሚለቅ ዌስት ላንድ ማኔጅመንት የአሠራር ሥርዓት (ሲስተም) እንዲዘረጉ ተደርጓል። ከ40 ያላነሱ በአበባ ልማት ኢንቪስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ይህንን የአሠራር ሥርዓት ዘርግተው የአበባ ቅሪት አጣርተው የሚለቁበት ግንባታ አካሂደው ኬሚካል አጣርቶ እንዲለቅ ለማድረግ እየተጠቀሙበት ይገኛል። ይህ የአሠራር ሥርዓት (ሲስተም) ኬሚካል አጣርቶ እንዲለቅ የሚያደርግ የአሠራር ሥርዓት ያለው በመሆኑ ወደዚያ ፍሳሽ እንዲገባ ሲደረግ የነበረው የኬሚካል መጠን እንዲቀንስ እና ኬሚካሉን ወደ ንጽህ ውሃ እንዲቀየር በማድረግ እንዲወገድ የሚያደርግ የአሠራር ሥርዓት ያለው መሆኑን ጠቁመዋል። የተቀሩት የአበባ ኢንቪስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወደ አሠራር ሥርዓቱ (ሲስተሙ) ለመግባት የሚያስችላቸውን ግንባታ በመገንባት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የሆርቲካልቸር ምርት አምራቾችና ላኪዎች ማህበር አማካይነት አጠቃላይ ከአየር ንብረት አንጻር የሚሰራ የመልካም እርሻ አተገባበር ሥራ ለመስራት የሚያስችል የአሠራር ስርዓት ተዘርግቶ እንዲሰሩ ለማድረግ ማህበሩ ክትትልና ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
‹‹ በቀጣይም ከአየር ንብረት ለውጥ አንጻር በስፋት መስራት እንፈልጋለን ›› የሚሉት አቶ እሸቱ፤ ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር፣ የመሬት አቅርቦቱን በማሻሻል ባለሀብቶቹ የሚገጥሟቸውን ችግሮች በቅርበት ሆኖ ለመፍታት፣ እና በአበባ ልማት ላይ የሚሰማሩ ተጨማሪ ባለሀብቶች እንዲገቡ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ለማከናወን ታቅዶ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ነው የሚናገሩት።
ኢትዮጵያ ይህንን ማድረግ የምትችልበት እድሉም አቅሙም አላት የሚሉት አቶ እሸቱ፤ ‹‹በአበባ ልማት ላይ በደንብ ከተሰራበት በሦስት ዓመት ውስጥ ከአበባ ልማት ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ይቻላል›› ይላሉ። በ2015 በጀት ዓመት 567 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ መሆኑን አስታውሰው፤ ለሚቀጥለው በጀት ዓመት ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ይገኛል ተብሎ የታቀደ እንደሆነና ይህንንም ከግብ ለማድረስ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል። ለዚህም 158 ሺ ቶን የአበባ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ ታቅዶ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፤ ከ621 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 /2015