የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ

ዝክረ ታሪክ፤

የመንግሥታት ግንኙነት ታሪክ የተመሠረተበትን ዘመን ለመወሰንም ሆነ ይህን ያህል ዕድሜ አለው ብሎ በግልጽነት ለመበየን በእጅጉ ያዳግታል። ስለምን ቢባል የመንግሥት ምሥረታና መስተጋብር የዘመናት ታሪክ ጉዞ የሚጀምረው ከሰው ልጆች አብሮ መኖርና ዕድገት ጋር ተያይዞ ስለሆነ የሚበጀው “ጥንት” የሚለውን ጥቅልና የሩቅ ዘመን አመላካች ቅጽል በመጠቀም ብቻ ይሆናል። ያለበለዚያ የብሉይውም ሆነ የዘመናዊቷ ዓለማችን የመንግሥታት የግንኙነት ታሪክ የተጀመረው እዚያ ሀገርና በዚያ ዘመን ነበር ብሎ መከራከሩ ጉንጭ አልፋነት ሊሆን ይችላል።

ረጂም የሚሰኘው የመንግሥታት ግንኙት መገለጫም እንዲሁ አንድ ሁለት እየተባሉ የሚዘረዘሩ ተግባሮችን ለመፈጸም ብቻ ሳይሆን እጅግ የረቀቁ መተሳሰሮችና ፍላጎቶች ያሉበት ስለሆነ ዳርቻና አድማሱ የሰፋ ነው። ለኢኮኖሚ የጋራ ተጠቃሚነት መንግሥታት ይፈላለጋሉ። “ኢኮኖሚ” ብለን በአንድ ቃል የምንወስነው ሥርዓት ደግሞ ጥልፍልፍ መረቡ የተወሳሰበ ስለሆነ ውሉን ተርትሮ ለመጨረስ ያዳግታል።

መንግሥታት ለጋራ ደህንነት መረጋገጥ ሲሉ ይሳሳባሉ። “ደህንነት” ሲባልም እንዲሁ “የሚያጠቃልለው ምንና ምንን ነው?” ብሎ ለመጠየቅ ቢሞከርም ቁርጥ ያለ መልስ ለመስጠት ብንሞክር ጭብጡ ርቆብንና ተራቅቆብን መሃል መንገድ ላይ ደርሰን ሃሳባችንን ለመሰብሰብ ዘዴው ሳይጠፋብን አይቀርም። የባህልና የቱሪዝም ዘርፎችም እንዲሁ ለመንግሥታት ግንኙነት ዋና ጉዳዮች ናቸው። በአጭሩ ሃሳቡን ለመጠቅለል መንግሥታት “እከክልኝ ልከክልህ” ይሉት ብጤ ማግኔት የሚያሳስባቸው በዓይነትም ሆነ በባህርይ እጅግ ውስብስብና ሰፊ የሆኑ የጋራ ጉዳዮች ስላሏቸው ነው።

አንዱ መንግሥት ለአንደኛው መንግሥት “ወገቡን እንዲያክልት” እናም ሌላውም እንዲሁ “የሚታከክለትን ጀርባውን የሚሰጥባቸው” ዘርፎች እጅግ የተወሳሰቡ፣ የተመሳጠሩና የእኔ እበልጥነት ስሜት የሚንጸባረቅባቸው ብጤዎች ስለሆኑ ዘርፎቹን ለመዘርዘር ብንሞክር እውነታው እየተሙለጨለጨ መቸገራችን አይቀሬ ይሆናል።

ጥቅል እውነታው ይህን ይምሰል እንጂ የመንግሥታት ግንኙነትና ስምምነት በዋነኛነት የሚመሠረተው “ከአንተ ዘንድ ምን አለ? ከእኔ ዘንድ ይህ አለ” በሚል “የእንካ በእንካ” መርህ ላይ ተመስርቶ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ወይንም ዲፕሎማሲው የሚጠቀምበትን መርህ እንዳለ እንጠቀም ከተባለም “win-win strategy” ብለን ልንገልጸው እንችላለን።

ቀደም ባሉት ረዥም ዘመናት የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነቱ ይፈጸም የነበረው አንድም የመንግሥትን ሹማምንት በልዑካን ቡድን ውስጥ በማካተት የመተዋወቂያ ወይንም የእጅ መንሻ ስጦታ አብሮ በመላክ ጭምር ነበር። ጉዳዩ እየጠነከረ ሲሄድም የመንግሥታቱ የእርስ በእርስ መጠቃቀም “ተስፋው ብርሃናማ” መሆኑ ሲታመንበት በየሀገራቱ የኤምባሲ ጽ/ቤቶችን በመክፈትና የሚሲዮኑን አባላት በመሾምና በመመደብ መቀራረቡን ይበልጥ ለማስተሳሰር ሲሞከር ኖሯል። ስለዚህም ነው “የኤምባሲ ጽ/ቤቶች የሉዓላዊ መንግሥታቱ ምሰለ ሀገራት ናቸው” የሚባለው።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመንግሥታት የእርስ በእርስ ግንኙነት ከነባሩና ከተለመደው የዲፕሎማሲ አካሄድ በመልኩም ይሁን በባህርይው በበርካታ ተጠቃሽ ምክንያቶች የተነሳ ግዙፍ ለውጥ ወደማምጣት ተደርሷል። በተለይም ዘመነ ሉላዊነቱ (Globalization) ዓለምን በመዳፋችን ላይ ማቀራረብ ከጀመረበት ጊዜያት ወዲህ የመንግስታቱ ውሎ አምሽቶ “ንፋስ እንደገባው እብቅ” በየሰኮንዱ ስለሚበተን በፕሮቶኮል በሚጀቦነው የመንግሥታት ግንኙነት ላይ ጥላ ማጥላቱ አልቀረም። ስለዚህም ነባሩና ጥንታዊው የመደበኛ ዲፕሎማሲ (Traditional Diplomacy) አካሄዱ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መጠናከር ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑ በመንግሥታት ዘንድ እየታመነበት በመሄዱ “Public Diplomacy” ዋናና ተመራጭ ብልሃት ሊሆን በቅቷል።

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ፤

ታሪኩ ረጅም፣ ጅምሩ የቅርብ የሆነው የሀገሬ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ትኩረት ያገኘው የሀገራዊው ደህንነት ፖሊሲ ስትራቴጂ ጸድቆ በሥራ ላይ እንዲውል ከተደረገበት ከሃያ ዓመት ወዲህ ነው። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት በሚታተም ቡሌቲን ከዚህ ጸሐፊ ጋር በተደረገ ኢንተርቪው ላይ የተጠቀሰውን አንድ ሃሳብ እንደሚከተለው ይነበባል።

“የሀገራችን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት (public diplomacy) ታሪካዊ ዳራ (historical background) ለረጅም ዘመናት የቆየ ቢሆንም መደበኛ በሆነ መልኩ በውጭ ጉዳይ አስተባባሪነት የተጀመረው ግን በቅርቡ ነው። ለጅማሮው መሰረት የሆነውም በተለይም የሀገር ውስጥን የተለያዩ አካላትን በማሣተፍ…ለዲፕሎማሲያችን ሥራ ዋነኛ ድጋፍ ሆኖ እንዲያገለግል ማድረግ ነው።

የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሠነድ እ.ኤ.አ በ2002 ዓ.ም ከመጽደቁ በፊት የሠነዱ ረቂቅ ለሕዝብና ለተለያዩ አካላት ውይይት ቀርቦ አስተያየቶችና ማሻሻያዎች ተደርጎበት የሀገራችን የውጭ ፖሊሲ…ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንዲከናወን ተደርጓል። በመሆኑም በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጽንሰ ሀሳብ መሠረት በሀገራችን የ“Domestic Dimension” ገና ፖሊሲውና ስትራቴጂው ሲረቀቅ የተጀመረ መሆኑን እንመለከታለን” ይላል።

ይሄው ፖሊሲ መነሻና ማነሳሻ ሆኖ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕለማሲ ቡድን የዛሬ አሥራ አምስት ዓመታት ግድም ሚሊኒዬሙን ታኮ ሊመሠረት ችሏል። የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዋነኛ መርህ ከመንግሥት መዋቅር ውጪ አድማስን በማስፋት በሀገራቸው በጎ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ዜጎችን ከተለያዩ ተቋማት በመምረጥ በውጭ ሀገራትና በሀገር ውስጥ ልዑካን አድርጎ ማሰማራት ነው። እነዚህ ዜጎች የሚመረጡት ከኪነ ጥበቡ ዘርፍ፣ ከሚዲያ፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከምሁራንና የሃሳብ ቋት ቡድኖች (Think-Tank-Groups)፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከልዩ ልዩ የሙያ ተቋማትና ሲቪል ማህበረሰብ ወዘተ. ተውጣጥቶ ነው።

በኢትየጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ውስጥ ተሰባስበው የነበሩት አባላትም የላይኞቹ መሥፈርቶች እንደተጠበቁ ሆነው በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በሰለጠኑበት ሙያና ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦና በተጽእኖ ፈጣሪነታቸው የተመረጡ ሲሆን አብዛኞቹን የማህበረሰብ ክፍሎችንና ሙያዎችን ይወክላሉ ተብሎም ታምኖባቸው ጭምር ነው።

ከልዑካን ቡድኑ የሚጠበቀው ዋነኛ ጉዳይ በሚደረጉት ስምሪቶች ሁሉ “ሕዝብን በመወከል፣ የሕዝብንና የሀገርን የጋራ ተጠቃሚነት መርህ” ማራመድ እንጂ የመደበኛ ዲፕሎማሲውን ሚና ለመጫወት አይደለም። የቡድኑ አባላት በሚንቀሳቀሱባቸው ተልዕኮዎች ሁሉ በንግግራቸው ውስጥ ሊያጎሉ የሚገባቸው “እኛ የሕዝብ ተወካዮች ነን!” የሚለው ድምጸት መሆን ይኖርበታል።

ያለበለዚያ የተወሰኑ ቡድኖችን የፖለቲካ አጀንዳ ወይንም ድብቅ ተልዕኮ ይዞ በመንቀሳቀስና በሕጋዊው የመንግሥት መዋቅር የሚሠራውን ተግባር ለመከወን መሞከር የተልዕኮን ገጽታ ማጥቆር ብቻ ሳይሆን በመንግሥታት የእርስ በእርስ ግንኙት ላይም ጥላ ማጥላቱ አይርም። ከሕዝብ ለሕዝብ ተልዕኮ በዋነኛነት የሚጠበቀው ውጤት በመንግሥታቱ መካከል መተማመን እንዲፈጠር መርዳት፣ የሀገርን በጎ ባህላዊ ዕሴቶች ማስተዋወቅ፣ የታሪክና የሥልጣኔ ገጽታውን አድምቆ ማሳየት እና በዘላቂነትም ከሀገራቱ ጋር መኖር ስለሚገባው ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ላይ መምከር ነው።

በዚህ ዓይነቱ መርህ ላይ ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን “በአዋላጅነትና በጥላነት” ድርሻ የነበረው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነበር። ሚኒስቴር መ/ቤቱ ቡድኑን ማደራጀት ብቻ ሳይሆን በሥሩ ያቋቋመው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ክፍልም ተልዕኮው ይህንኑ ዓላማ እንዲያስፈጽም ነበር። ከዚህም ላቅ ብሎ 12 ያህል ሚኒስትር ዴኤታዎችና ከፐብሊክ ዲፕሎማሲው የተወከሉ ሁለት ያህል ሰዎች የተካተቱበት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ምክር ቤት ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም የመከነው ግን አንድ ወይንም ሁለት ያህል ጊዜያት ብቻ ከተሰበሰበ በኋላ ነበር።

እርግጥ ነው የፐብሊክ ዲፕሎማሲው እንዲቋቋም ያስፈለገበት ዋነኛውና ተቀዳሚው ምክንያት በግንባታ ላይ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ለሀገራችን ከሚኖረው ትሩፋት ጎን ለጎን ለተቀሩት የናይል ተፋሰስ ሀገራትም ከፍ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረው እንጂ ለኢትዮጵያ ብቻ የታሰበ እንዳልሆነ ለተፋሰሱ ሀገራት ርዕሳነ መንግሥታትና ለሚመለከታቸው አካላት ማረጋገጫ ለመስጠት ታስቦ ነው።

በዚህ መሪ ዓላማ መሠረትም የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በግብጽ፣ በሱዳንና በዩጋንዳ ሀገራት በመገኘት የኢትዮጵያን ሕዝብ ወክሎ መልዕክቱን አድርሷል። ከእነዚህ ሀገራት በተጨማሪነትም በጅቡቲና በኤርትራ ሀገራት በመገኘት የወንድማማችነቱ ትስስር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የልዑካን ቡድኖችን ልኳል።

በዚህ ጸሐፊ እምነት እንደ ጀማሪ ሀገር የተገኙት ውጤቶች ከብዙ ጉድለቶቹ ጋርም ቢሆን ተልዕኮዎቹ የተሳኩ ነበሩ። በተለይም በግብጽ፣ በሱዳንና በዩጋንዳ የተደረጉት ሦስቱ ጉዞዎች በልዩነት የተሻለ የሚባል ውጤት ተመዝግቦባቸዋል። የጅቡቲው ተልዕኮ በዋነኛነት “ከወደብ አገልግሎት አሰጣጥና ከሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች” ጋር የተያያዘ ቢሆንም ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል። የልዑካን ቡድኑ አባላት ከዋናው ተልእኮ ጎን ለጎን ሀገሪቱ 41ኛውን የነፃነት በዓሏን ስታከብር በእንግድነት ተገኝተው ዝግጅቶቹን ታድመዋል። ኤርትራ የተጓዘው ቡድን በዋነኛነት የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች የተካተቱበት ስለነበር ተልዕኮውም ውስንና የተመጠነ ነበር።

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ ጎረቤት ሀገራት የፈሰሰ አልነበረም። የየሀገራቱ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኖችም ኢትዮጵያ መጥተዋል። በሚሊኒዬሙ ማግሥት በርካታ አባላትን ያቀፈ የግብጽ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አዲስ አበባ መጥቶ ነበር። የሱዳንም እንዲሁ ከሦስት ዓመታት በፊት ሀገራችን መጥተዋል። ከኤርትራም ቁጥራቸው በርከት ያለ የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች በሀገራችን ተገኝተው የተለያዩ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል። በቅርቡም የጅቡቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት በሀገራችን ተገኝተው ተልዕኳቸውን አሳክተው ተመልሰዋል።

ልምሻ ያልፈሰፈሰው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ፤ በርካታ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን እንደሚወጣ ታስቦ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ውስን ተልዕኮዎችን ካሳካ በኋላ ዛሬ ድምጹም ሆነ ተግባሩ ጠፍቶ ያሸለበ ይመስላል። “የት ናችሁ?” ባይ ከመጥፋቱም የተነሳ ቡድኑ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች” ተበታትነው በየሙያ ፊናቸውን ተሰማርተዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በቅርቡ ከመጣው የጅቡቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጋር በቅርበት ተገናኝቶ በጋራ ጉዳዮች ላይ ከመምከርና ከማቀድ ይልቅ እንደነገሩ ጉብኝት ከማድረግ ያልዘለለ ተልዕኮ ብቻ ፈጽመው እንዲመለሱ መደረጉ አግባብ አልነበረም። ሌላው ቢቀር ከዲያስፖራ ማኅበር ጋር “አብሮ ስለመሥራት” የጋራ ሰነድ ሲፈራሙ ዋናው ባለጉዳይ የሀገሪቱ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዜናውን በሚዲያ እንዲያደምጥ መደረጉ ብዙዎቻችንን ግራ አጋብቶናል።

ዘመኑ የሚፈቅደውን ተልዕኮ እንዲፈጽም የተዋቀረው የሀገሪቱ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ከትናንት ይልቅ ዛሬ በርካታ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ኃላፊነቶችን ሊወጣ ግድ በሚልበት በዚህ ወቅት ቡድኑ ከሥዕሉ ውስጥ እንዲጠፋ መደረጉ ነገም ሆነ ዛሬ የሚያስጠይቅ ይመስለናል። ውሎ ሲያድርም ታሪክ መሆኑ ስለማይቀር “እንዴትና ለምን ሊመክን ቻለ?” ተብሎ ቡድኑን ያደራጀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤታችን ቢጠየቅ አሳማኝ መልስ ይኖረዋል ለማለት ያዳግታል።

ቢያንስ ከአሥር ዓመታት በላይ ለሀገር አቀፍ ጉዳዮችና ለጎረቤት ሀገራት ተልእኮ ተሰጥቶት የአቅሙን ያህል ሲንቀሳቀስ የነበረው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ተበትኗል ቢባል አንኳን በአግባቡና በወጉ ተመሰጋግኖ መለያየት ቢቻል የተሻለ ይሆን ነበር። ይህ ጸሐፊ የቡድኑ አባልና ጊዜያዊ ሰብሳቢ ሆኖ ከባልደረቦቹ ጋር ሀገሩን ባገለገለባቸው ጊዜያት መልካም ውጤት መመዝገባቸውን በሚገባ ይመሰክራል። በቂና ከበቂ በላይ ማስረጃዎችንም መዘርዘር ይቻላል። በተጠናከረ መዋቅራዊ አደረጃጀትና ግልጽነት በተላበሰ ተልዕኮ እንዲመራ ቢደረግ ለሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ተልእኮ አንዳች ኃይል ሊሆን በበቃ ነበር ብሎም ይቆጫል።

ታላላቅ ተግባራትን በመፈጸምም ለኢትዮጵያ ክብርና ኩራት መሆን የማይችልበት ምክንያት አይኖርም። ቡድኑ ፈርሶም ከሆነ በይፋ ቢገለጽና የታሪኩ ምዕራፍ ቢዘጋ መልካም ይመስለናል። ግና መቼ ይሆን ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮችን ሆ ብለን ተሟሙቀን ጀምረን ከግብ ሳናደርስ ጅምሮቻችንን አምክነን “ነበርን ስንተርክ የምንኖረው”። ያገባኛል ባይ ተቋም መልስ ቢሰጥበት መልካም ይመስለናል። ሰላም ለሀገራችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 /2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *