እገታ-ወፍ ዘራሹ የሀገራችን በሽታ!

ከዓመታት በፊት ወደ አረብ ሀገራት የሚሰደዱ ሰዎችን መንገድ ላይ እያገቱ ገንዘብ የሚጠይቁ አጋቾችን ጉዳይ ከርቀት እየሰማ አጃ ኢብ ! ያላለ ኢትዮጵያዊ አልነበረም። ምክንያቱም እንዲህ አይነቱ ጸያፍ ተግባር ከኢትዮጵያውን ስነልቦና ጋር አብሮ የማይሄድ እና ከእሴታችን ያፈነገጠ በመሆኑ፤ እንዲሁም ድርጊቱን ሰው በሰው ላይ ይፈጽመዋል ብለን የማንገምተው እንግዳ ነገር ስለሆነብን ነው። ታዲያ እዚያ አረብ ሀገር የተፈጸመው ግፍ ስሜቱና ንዝረቱ እዚህ ድረስ ማስተጋባቱና በራችንን ማንኳኳቱ አልቀረም።

ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውን የእገታው ሰለባ የነበሩ ዘመዶቻቸውን ነፍስ ለመታደግ ሲሉ ያላቸውን ጥሪት አሟጠው ልከዋል። ከስንት አንድ ተሳክቶላቸው በሕይወት ያተረፏቸው ሰዎች እንዳሉ ቢታመንም አንዳንዶቹ ከገንዘባቸውም ከታገቱ ዘመዶቻቸውም ሳይሆኑ ቀርተዋል።

‹‹ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው›› እንዲሉ ይህ በሊቢያና በየመን ሀገራት ሲፈጸም እንሰማው የነበረ የአጋችና የታጋች ድራማ ብዙም ሳይቆይ በሀገራችን ተከስቷል። በኢትዮጵያ ሰዎችን አግቶ በገንዘብ መደራደር አንድ ብሎ የጀመረው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በዋናነትም በሰሜን ጎንደር አካባቢ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። የአጋቾቹ ወጥመድ በተለይም ሕጻናት፣ ወጣቶችና ጎልማሶች ላይ ያነጣጠረ እንደነበር አንረሳም።

ሰሜን ጎንደር ውስጥ በጅምላ ታግተው የተጠየቁትን ገንዘብ የሚከፍልላቸው ሰው ባለማግኘታቸው ምክንያት ያለ ሃጥያታቸው የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሕጻናት ጉዳይ ከማይረሱ አሳዛኝ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ሰው በዚህ ጉዳይ ሕይወቱን አጣ? ሰዎችን ለማስለቀቅ ምን ያህል ገንዘብ ተከፈለ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለጊዜው ለሚመለከታቸው አካላት እንተውላቸው።

አግቶ ገንዘብ የመጠየቁ ርካሽ ባሕል ወደ ሀገራችን ከገባ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም አሁን አሁን በሀገሪቱ የተፈጠረውን አለመረጋጋት እና በግለሰቦች እጅ የገባውን ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ እንደምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ መንሰራፋት የዳዳው ይመስላል። እገታ ዛሬ ከዳረኛው የሀገራችን ክፍል ወደ መሃል ዘልቆ በማህበረሰቡ የዘወትር እንቅስቃሴ ላይ ፈተና ሆኗል። በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደውም ወጥቶ የመግባትን ነገር አሳሳቢ አድርጎታል።

በሥራ ወይም በጉዞ ላይ ያለ ሰውን ድንገት አግቶ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ካላመጣህ እገድልሃለሁ ማለት ኢትዮጵያዊ መገለጫ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ፍጹም ከሰውነት ጎራ መውጣትም ነው። ይህ ድርጊት ከማህበረሰባችን ሃማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶች በእጅጉ ያፈነገጠና ከኢትዮጵያዊ ስብዕናችን ጋር የሚጋጭ ፀያፍ ተግባር ነው።

እንዲህ አይነቱ ነውር ሥራ በሀገራችን ስር የሚሰድ ከሆነ ቱባውን የመከባበር፣ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባህላችንን እየሸረሸረ አደጋ ላይ የሚጥልና ማህበራዊ መዋቅራችንን የሚያበላሽ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ይህን ፀያፍ መጤ ባሕል ከወዲሁ መታገልና በእንጭጩ መቅጨት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

‹‹በሬ ካራጁ … ›› እንዲሉ ባለንበት ዘመን አጋቾችና ታጋቾች አሳዳጅና ተሳዳጅ ሆነን በአንድ ቤት ፣ በአንድ ከተማ ፣ ከፍ ሲልም በአንድ ሀገር አብረን እየኖርን ነው። እገታው ተለዋዋጭ መልክ ያለው ቢሆንም የመጨረሻ ግቡ ግን ገንዘብ ነው። በግለሰብ ቤት ተቀጥረው ከሚሠሩ የቤት ሠራተኞች ጀምሮ ሕገ-ወጥ መሳሪያ ታጥቀው እስከሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ድረስ በዚህ ፀያፍ ተግባር እንዲሰማሩ ያስገደዳቸው የገንዘብ ፍቅራቸው እንደሆነ ለመታዘብ አይከብድም፡

ባሳለፍናቸው ዓመታት ሕጻናትን ከእናቶቻቸው ጉያ ነጥቀው በመሰወር በገንዘብ ሲደራደሩባቸው የነበሩ የቤት ሠራተኞችን ጉድ ተመልክተናል። አንዳንዶቹ አጋቾች ደግሞ እገታውን የፖለቲካ መልክ ለማስያዝ ሲሞክሩ ተስተውሏል፤ የብሔረሰብን ጥላ ተጠልለው ቆሜለታለሁ በሚሉት ማህበረሰብ ውስጥ ተሸጉጠው መልሰው እገሌ ከገሌ ሳይሉ አግተው ዋጋ እየተመኑ ሲደራደሩም አይተናል።

መንገደኞችን ከተሳፈሩበት መኪና ላይ ፣ አርሶ አደሮችን ከማሳቸው ላይ ፣ ባለስልጣናትን ከሥራ ቦታቸው ሌሎችንም ከመኖሪያ ቤታቸው አግተው እየወሰዱ ለሽያጭ እንደቀረበ እቃ ዋጋ እየተመኑ ገንዘብ የሚቀበሉ ግለሰቦች ፀረ-ሕዝብነታቸውን በገሀድ እያየነው ፖለቲከኞች ነን ሊሉን ይፈልጋሉ። ፖለቲከኛ ለህዝብ ይቆረቆራል እንጂ ሕዝብን አያቆረቁዝም፤ በግፍ አይገድልምም።

በኢትዮጵያ ምድር እንዲህ አይነቱ ጭካኔ ይፈጸማል ተብሎ ባይታመንም ተፈጽሞ አይተናል። ሀገራችን ወዴት እየሄደች ነው የሚለው ነገር ያላሳሰበው፣ በሁኔታው ያልተረበሸ ፣ ያልደነገጠ፣ ያላዘነና ያልተናደደ ሰው አለ ከተባለ አጋቾች ብቻ ናቸው።

ለህሊናቸው፣ ለሕገ-እግዚአብሄርና ለሕገ-መንግሥት ያልተገዛ ጨካኝ ልብ ያላቸው እና በወገናቸው ላይ ስቃይና መከራ የሚያደርሱ፤ ያሻቸውን ለማድረግ የተሰናዱ አጋቾችን በጉያችን አቅፈን የያዝናቸው እኛው ነን። የሚያውኩን በጣት የሚቆጠሩ የምንታወክ ደግሞ ብዙዎች ነን። ብዙኋኑ ከተባበረ ሰላሙን፣ ወጥቶ የመግባት ነጻነቱን ማስከበር አያዳግተውም። ጥቂቶችን እንደፈለጋችሁ ብሎ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ ከሆነ መቼም ቢሆን ከስጋት ውጪ ሊኖር አይችልም።

አጋቾች አድብተው የሚቀመጡበት ቦታ፣ የሚገቡበትና የሚወጡበት ከብዙኋኑ የተሰወረ ሊሆን አይችልም። ከሕዝብ መሃል እየወጡ ሕዝብን እንዲያጠቁ፣ እንዲያማርሩና እንዲያስለቅሱ ብዙኋኑ እድል ሊሰጣቸው አይገባም።

ሰዎች በታገቱ ቁጥር ጣታችንን ወደ ሌላ አካል ከመጠቆማችን በፊት ማህበራዊ ኃላፊነታችንን ከመወጣት አንጻር እኛስ ምን ሠራን ብለን እራሳችንን መጠየቅ ይገባናል። እርግጥ ነው መንግሥት የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ይታመናል። ነገር ግን በየመንደሩ የሚፈጸምን የወሮ በላ ሥራ ሁሉ አዳርሶ መልስ መስጠት ሊያዳግተው ይችላል።

አጋቾች በአንድ ጊዜ የሚያግቷቸውን ሃያ እና ሰላሳ ሰዎች የሚሸሽጓቸው የት ነው? ከተባለ እኛው መሃል ነው። መረጃውን ለሚመለከተው የፀጥታ አካል ከማሳወቅ ይልቅ መረጃ በመደበቅ የምንተባበራቸውም እኛው ነን። ለዚህ ደግሞ ምክንያታችን ጥቃት እንዳያደርሱብን ከመፍራት ወይም የእኩይ ተግባራቸው ተባባሪ ከመሆን አያልፍም።

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ታጋቾችን መታደግ የሚችሉት ማህበረሰቡ ሲተባበራቸው እንጂ አጋቾችን በጉያው ይዞ ጣቱን ወደ መንግሥት አካላት በመጠቆም ሊሆን አይገባም። በእገታ ጉዳይ ተጠያቂ መሆን የሚገባን በተለይም እገታው በሚፈጸምባቸው አካባቢ የምንኖር ሰዎች ነን።

‹‹ነግ በእኔ..›› እንደሚባለው ዛሬ በሌሎች ላይ የሆነው ነገር ነገ በእኛ ላይ የማይፈፀምበት ምክንያት የለም። ቢያንስ በየአካባቢያችን እንዲህ አይነቱን ወንጀል የሚፈጽሙ አካላትን ለመንግሥት የጸጥታ አካላት በመጠቆም እንተባበር። እገታን መቆጣጠር የሚቻለው በመተባበር ነው። ይህን ሥጋት የፈጠረብንን ወፍ ዘራሽ በሽታ ከሀገራችን ነቅለን ለመጣል ያለን አማራጭ ተባብረን መንቀሳቀስ ነው። ለዚህ ደግሞ ወትዋች መጠበቅ የለብንም፤ ነጋችንን የሚያጨልም ማህበራዊ ነቀርሳ ስለሆነ ቀን አንስጠው ! ።

ሜላት ኢያሱ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *