በስንዴ የተገኘውን ውጤት በሩዝ ምርት ለመድገም
የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥሉ ḷ

 ኢትዮጵያ በግጭቶች፣ መከራዎችና ረሃብ ስትፈተን የቆየች ሀገር ብትሆንም አሁን ላይ ግን ካለፈው ትምህርት ወስዳ ሁኔታዎቹን ወደ ዕድል እየቀየረች ያለች ሀገር ነች፡፡ ቀደም ሲል በጦርነት፣በርሃብና ድርቅ የሚታወቀውን ስሟን የሚለውጡ ሥራዎችንም በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡

በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በግብርና፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በኃይል አቅርቦት እና በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት የሀገሪቱ መጻኢ ዕድል ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረጉ ጥረቶች በምግብ ሰብል ራሷን ከመቻል አልፎ ስንዴን እና አቮካዶን የመሳሰሉ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ አዲስ ታሪክ በመጻፍ ላይ ትገኛለች፡፡

በቅርቡ ደግሞ እንደ ስንዴው ሁሉ ለሩዝ ምርት ትኩረት በመስጠት ከሀገራዊ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለመላክ በትኩረት በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ በተለይም ሀገሪቱ ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሆነ የአየር ጸባይና ምቹ መሬት ያላት መሆኑ ያቀደችውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደማያዳግታት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

ሩዝ በርካታ የዓለም ህዝብ በስፋት ከሚመገባቸው የምግብ አይነቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በተለይም ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላቸው እንደ ህንድና ቻይና በመሳሰሉ ሀገራት ሩዝ ዋነኛ የምግብ አይነት ሲሆን፤ ሀገራት በምግብ ራሳቸውን ለመቻል በሚያደርጉት ጥረትም ሩዝ የጎላውን ስፍራ ይይዛል፡፡ ስለዚህም እያደገ ያለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ሩዝ መተኪያ የሌለው ምርት ነው፡፡

በምግብ ንጥረ ነገር በኩልም ሩዝ በዋነኝነት ከኃይል ሰጪ የምግብ አይነቶች ውስጥ ቢካተትም ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ቫይታሚኖችና ንጥረ ነገሮች የበለጸገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ካልሲየም፤ ኮፐር (መዳብ)፤ ብረት፤ ፎስፈረስ፤ ዚንክና የመሳሰሉትን የማዕድን አይነቶችንም በማካተቱ ለጤና ተመራጭ ምግብ ነው፡፡ ሩዝ በዋነኝነት ውሃን የመምጠጥና ጨውን ከሰውነት የማስወገድ ብቃት ስላለው ለጤና ተስማሚ ከሚባሉ ምግቦች ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያ ምቹ የአየር ጸባይ፤ ለም አፈርና አምራች የሰው ኃይል ቢኖራትም ለዘመናት ከዚህ ሰብል ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለከትውም በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በሩዝ መልማት የሚችል መሬት ቢኖርም በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ ሩዝ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ታደርጋለች፡፡

ሆኖም በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሥርዓት መተግበር ከጀመረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግሥት ፊቱን ወደ ሩዝ ምርት በማዞር በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል፡ ፡ በስንዴ ምርት የተገኘውን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ተሞክሮ በሩዝ ምርት ላይም ለመድገም እየተደረገ ባለው ጥረት ከወዲሁ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ነው፡፡

አሁን ላይ ሩዝ በስፋት የሚመረተው በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ትግራይ ክልሎች ሲሆን፤ በዘንድሮው 2015/2016 የምርት ዘመን በአማራ 150 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ በመሸፈን 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው። በተመሳሳይም በኦሮሚያ ከ 1ሚሊዮን ሄክታር በላይ በሩዝ ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን 700ሺ ሄክታሩን ማሳካት ተችሏል፡፡ የሁለቱ ክልሎች እንቅስቃሴ ብቻ በሀገር ውስጥ ለምግብ ፍጆታነት የሚጠበቀውን ከ6 ሚሊዮን ያልበለጠ ፍላጎት በመሸፈን ቀሪውን ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ነው፡፡

የማምረቻ ማሽኖች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መደረጋቸው፤ በአማራ ክልል በፎገራ ወረዳ ከ200 ሚሊዮን በላይ በሆነ ወጪ ዘመናዊ የሩዝ ምርምር ማዕከል መከፈቱና መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱ ኢትዮጵያ በሩዝ ምርት ከራሷ አልፎ ወደ ውጪ ለ መላክ የምታደርገውን ጥረት የሚያግዙ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ላይ ያገኘችውን ውጤት በሩዝ ምርትም ለመድገም የምታደርገው ጥረት በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት ከመደገፉም በሻገር ወደ ውጪ ከሚላከው ምርትም ከፍተኛ ዶላር የማስገኘት አቅም ያለው ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በድህነት፣ በርሃብ፣ ድርቅ፣ ስደትና መፈናቀል የምትታወቀውን ሀገር አዲስ ገጽታ እንድትላበስ ያስችላል፡፡ በዲፕሎማሲው ረገድም ከርዳታና ከውጭ ጥገኝነትም እንድትላቀቅ የሚያግዝ በመሆኑ የተጀመረው የሩዝ ልማት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *