በካታር ዶሃ ጅማሬውን ያደረገው የ2023 ዳይመንድሊግ ውድድር አስረኛ መደረሻው ከተማ የሆነችው ለንደን ደርሷል:: በ14 የተለያዩ የዓለም ከተሞች ተካሂዶ ፍፃሜ የሚያስገኘው የዳይመንድሊግ ፉክክር በእስካሁኑ ጉዞው በተለያዩ ውድድሮች ያልተጠበቁ አስገራሚና ክብረወሰኖች እየተሻሻሉበት ይገኛል::
አስረኛ የውድድሩ መዳረሻ ከተማ የሆነችው ለንደን ከትናንት በስቲያ በንግስት ኤልሳቤት ስቴድየም የዓለም ከዋክብት አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች ተፋልመውባታል:: ከነዚህ ፉክክሮች ተጠባቂ በነበረው የሴቶች 5 ሺ ሜትር ውድድርም አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በርቀቱ የቦታውንና የራሷን ክብረወስን አስመዝግባ አሸንፋለች::
ጉዳፍ የ5ሺ ሜትሩን ርቀት ለመጨረስ 14 ደቂቃ ከ12 ሴኮንድ የፈጀባት ሲሆን፣ ጠንካራ ተፎካካሪዎች የነበሩትን ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፋን ሀሰንን እና ኬንያዊት ቢትሪስ ቺቤትን አስከትላ በመግባት በበላይነት ማጠናቀቅ ችላለች:: ጉዳፍ በ2023 የውድድር ዓመት ከቤት ውጪ የሚደረጉ ውድድሮችን ስታሸንፍ ይህ የመጀመሪያዋ ሲሆን፤ ከተፎካካሪዎቿ ጠንካራ ፉክክር ገጥሟት ነበር:: ያምሆኖ የአጫራረስ ብቃቷን በልዩ ሁኔታ በመጠቀም በበላይነት ማጠናቀቅ ችላለች:: በለንደኑ ትንቅንቅ የዓለም ቻምፒዮን እና የ1 ሺ 500 ሜትር የክብረወሰን ባለቤቷ ጉዳፍ ፀጋይ የኦሊምፒክ ቻምፒዮናዋን ሲፋን ሀሰንን እና የዳይመንድ ሊግ ቻምፒዮኗን ቢትሪስ ቺቤትን ማሸነፏ ከሳምንታ በኋላ በቤልግሬድ በሚካሄደው የዓለም ቻምፒዮና እንድትጠበቅ አድርጓታል::
ጉዳፍ ባለፈው የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቋ የሚታወስ ሲሆን፤ ለለንደኑ ዳይመንድሊግ በተመሳሳይ እለት ከዓመት በኋላ ማሸነፏ ግጥምጥሞሹን አስገራሚ አድርጎታል::
ጉዳፍን በመከተል ኬንያዊቷ ቢትሪስ ቺቤት 14፡12፡ 92 በሆነ ሰዓት 2ኛ ሆና ስታጠናቅቅ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሰን 14፡13 በሆነ ሰዓት 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች:: የኦሪገኑን ድርብ ድል በቡዳፔስት ለመድገም እየተዘጋጀች የምትገኘው አትሌት ጉዳፍ፤ በዳይመንድሊጉ ድል በዓለም ቻምፒዮናውም በጉጉት እንድትጠበቅ አድርጓታል::
በለንደኑ ዳይመንድ ሊግ ላይ የዓለም የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ክብረወሰንን ደግሞ አትሌት መዲና ኢሳ በማሻል አሸንፋለች፡፡ አትሌት መዲና ኢሳ እአአ 11 ነሐሴ 2004 በኖርዌይ በርገን በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የነበረውን 14 ደቂቃ 30 ሰከንድ ከ 88 ማይክሮ ሰከንድ የነበረውን የዓለም የክብረወሰን ከ14 ሰከንድ በላይ በማሻሻል 14:16’54 በመሮጥ አዲስ የዓለም ክብረወሰንን ማሻሻል ችላለች:: አትሌቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየች በመጣችው መሻሻሎች የሚደነቁና ለወደፊትም በርቀቱ ተስፋ መሆኗን የሚያሳይ ሆናል::
ጉዳፍ በዳይመንድሊጉ በርቀቱ አንድ ውድድር ብቻ በማድረግ 8 ነጥቦችን ሰብስባ ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ ተቀምጣለች:: ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ለምለም ኃይሉ ሶስት ውድድሮችን አከናውና 15 ነጥቦችን መሰበሰብ ችላለች:: አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ 12፣ መዲና ኢሳ 11 ለተሰንበት ግደይ 7 እና እጅግአየሁ ታዬ 6 ነጥብ መሰብሰብ የቻሉ አትሌቶች ናቸው::
ከለንደን አስቀድሞ ዓርብ እለት በፈረንሳይ ሞናኮ በተካሄደው የወንዶች 5 ሺ ሜትር የዳይመንድሊግ ውድድርም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት ማሸነፍ ችለዋል:: አትሌት ሀጎስ ገብረህይወት በ12 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ ከ18 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት በቀዳሚነት አጠናቋል:: ሌላኛው አትሌት በሪሁ አረጋዊ 12 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ 58 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ እንዲሁ ጥላሁን ሃይሌ በተመሳሳይ 12 ደቂቃ ከ 42 ሰከንድ ከ70 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል::
ርቀቱን በድምር ውጤት ወጣቱ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ሶስት ውድድሮችን በማድረግ 21 ነጥቦችን ሰብስቦ ሲመራ፤ ጥላሁን ኃይሌ አራት ውድድሮችን አካሂዶ በተመሳሳይ 21 ነጥቦችን በመሰብሰብ ሁለተኛ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ ሁለት ውድድሮችን አድርጎ 15 ነጥቦችን በመሰብስብ ሶስተኛ አትሌት ሀጎስ ገብረህይወት ሁለት ውድድሮችን ከውኖ በአስራ አራት ነጥቦች አራተኛ ደረጃን በመያዝ ተቀምጧል::
በሞናኮ በሶስት 3ሺ ሜትር መሰናክል የወንዶች ውድድር ደግሞ አትሌት አብረሃም ስሜ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ አትሌት ሳሙኤል ፍሬው አራተኛ ሆኖ አጠናቋል:: በአንድ ማይል የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች:: በቀጣይ አራት የዳይመንድሊግ መርሃግብር ውድድሮች ዙሪክ፣ ሼንዘን፣ ብራሰልስ እና ኦሪገን በመካሄድ የሚጠናቀቅ ይሆናል::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2015