በሞያዋ አርክቴክቸር ናት። በዋናነት ሰስተነብል አርክቴክቸርና ኢንቴሪየር ዲዛይን ላይ በተለይ ደግሞ በእንጨት ሥራ ላይ አተኩራ ትሰራለች። በኢጋድ በኩል በተዘጋጀ ውድድር በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩና አስተዋፅኦ እያደረጉ ያሉ ወጣቶች በሚል በምስራቅ አፍሪካ ሽልማትና ‹‹ግሎባል ኧርዝ ቻምፒዮና›› የሚል ስያሜ ካገኙ ሶስት ወጣቶች ውስጥ አንዷ ሆናለች። በይበልጥ ደግሞ ‹‹ሲድ ቦል ኢትዮጵያ›› በተሰኘው የራሷ የስራ ፈጠራ ትታወቃለች። ከአየር ንበረት ለውጥ ጋር በተያያዘም ለኢትዮጵያ ሁለት ተጨማሪ ሽልማቶችን አስገኝታለች። አሁን ደግሞ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ሪኤጀንት ቢዝነስ ትምህርት ቤት በኢንተርፕሪነርሺፕ የኦን ላይን ትምህርት እየተከታተለች ትገኛለች፡- የዛሬዋ ሴቶች አምድ እንግዳችን ህሊና ተክሉ።
ህሊና በአርክቴክቸር የትምህርት ዘርፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች። በዚህ የትምህርት ዘርፍ ሰስተነብል አርክቴክቸርና ላንድስኬፕ የተሰኙ ኮርሶችን ተከታትላለች። ይህም ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ ለመስራት ፍላጎት እንዲኖራት አድርጓታል። በዚህም እ.ኤ.አ በ2016 ‹‹ክላይሜት ቼንጅ አፍሪካ›› የተሰኘ ድርጅት አቋቁማ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ያሏቸው ወጣቶች የሚሳተፉበት መድረክ በማመቻቸት ከተለያዩ ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላት ጋር ተገናኝተው ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ አድርጋለች። ከኢትዮጵያ ባለፈ ኬንያ ድረስ ሁነቶችን በማዘጋጀት ሰርታለች።
በዚህ ሂደት ህሊና በይበልጥ ወደ መድረክ እያወጣች የነበረቸው በአብዛኛው የወጣቶችን ፕሮጀክት በመሆኑ የእርሷን ስራ ችላ ብላ ነበር። በጋጣሚ እ.ኤ.አ በ2018 አንድ በውጪ ሀገር የሚኖር ጓደኛዋ ስለ ‹‹ሲድ ቦል›› ፅንሰ ሃሳብ አስተዋወቃት። እርሱ ያስተዋወቃት ‹‹ሲድ ቦል›› /የዘር ኳስ/ ድጋሚ ጥቅም ላይ በሚውል የተድቦለቦለ ወረቀት ውስጥ ተዘጋጀ የእህል ዘር ነበር። እዚህ ጋር የተማረችው የላንድ ስኬፕ አርክቴክቸር ኮርስ ትዝ አላት። ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ ተክሎች እንዴት እንደሚተከሉም አስታወሰች። ስለዚህ ይህ ነገር እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ተለውጦ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል አሰበች። ምርምር ጀመረች።
ምርምር ማድረግ እንደጀመረች በምእራቡ ዓለም ‹‹ሲድ ቦል›› በበረዶም ጭምር ተድቦልብሎ እንደሚሳራ አረጋገጠች። እንደውም ህፃናትም ጭምር በክረምት በጭቃ የሚሰሩት እንደሆነም ለማወቅ ቻለች። ሲድ ቦልን ወደ ሀገሯ ነበራዊ ሁኔታ ለማምጣት ስትሰራ ታዲያ ኢትዮጵያ የተለያዩ የተፈጠሮ ሀብት እንዳሏት በመረዳት በተለየ መልኩ በአፈር ለመስራት ሙከራ ጀመረች።
በአዲስ አበባ ከተማ ለግብርና ለደን ልማት አመቺና በቂ ቦታ ባለመኖሩ ይህን የምርምር ስራዋን ለመስራት ወደ ጉራጌ ዞን አገና ከተማ እዣ ወረዳ አቀናች። እዛ በነበራት የአራት አመታት ቆይታ ሲድ ቦል /የዘር ኳስ/ ለመስራት የተለያዩ ምርምሮችን ስታደርግ ቆይታለች። የተማረችበትን የአርክቴክቸርነት ሙያዋንም በመተው ሙሉ ትኩረቷን በዚሁ የምርምር ራ ላይ አሳልፋለች። በተለያዩ አፈሮችና የአፈር ማዳበሪያዎች ላይ ሙከራዋን ስታደርግ ቆይታ በመጨረሻ የሚሰራላትን የአፈር አይነት አገኘች።
ህሊና ባገኘችው ተስማሚ አፈር በውስጡ ለዘር አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ያሉበት በተድቦለቦለ ጭቃ የተዘጋጀ ዘር መፍጠር ችላለች። ይህ ነው እንግዲህ ሲድ ቦል/ የዘር ኳስ/ የሚባለው። ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን የጠበቀ የፈጠራ ውጤቷ በድቡልቡል ጭቃ ዘርን ከአስፈላጊ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች ጋር አካቶ በመያዝ ለረጅም ግዜ ማቆየት የሚችል ነው።
ዘሮች በድቡልቡል ጭቃ ውስጥ ስለሚሆኑ በትል ከመበላት ይጠበቃሉ። በአዝርት ወቅት የሚደርሰውን የዘር ብክነትም ይቀንሳል። የዘር ኳሶቹ በውስጣቸው ለዘር አስፈላጊ የሆኑ ንጠረ ነገሮችን ማለትም ናይትሮጂን፣ ፖታሺየምና ካልሺየም የተፈጠሮ ማዳበሪያ የያዙ በመሆናቸው ለዘርና ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ የሚወጣውን ወጪም ይቀንሳል። ከዚህ ባለፈ በተለይ ሴቶች በግብርና ስራ ላይ ዘር ሲተክሉ ያለባቸውን ድካም ያቃልላል። ለመትከል ጉድጓድ መቆፈር አስፈላጊ ባለመሆኑ የችግኝ ተከላና የማፍላት ስራን ጭምር አቅልሏል።
ስለዚህ የዘር ኳሱ መሬት ላይ ሲተከል በውስጡ ያለውን ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በቅፅበት መመገብ ስለሚጀምር ወዲያው ያድጋል። በዝናብ ወቅትም ቢሆን መሬት ላይ የወደቀው የዘር ኳስ ራሱን እየሸረሸረ ወደ እድገት ደረጃ ይሸጋገራል። እድገቱም ፈጣን ነው። አንድ ዘር ለመብቀል የሚፈጅበትን የአራት ወር ጊዜም ወደ ሁለት ወር ያሳጥራል።
ማንኛውም ዘር የአገልግሎት ጊዜው ያልፋል። ከዚህ አንፃር ህሊና የዘር ኳሱ ቆይታ ጊዜው እንዲጨምር ተጨማሪ ምርምር በማድረግና በውስጡ ያሉትን ንጥረ ነገሮች በማሻሻል ለአንድ አመት እንዲቆይ ማድረግ ችላለች።
በድቡልቡል ጭቃ ውስጥ ያሉ የዘር ብዛቶች እንደየዘሮቹ አይነቶች የሚለያዩ ሲሆን ለምግብነት የሚውሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘሮች በአንድ ኳስ ውስጥ አራት ዘሮችን ይይዛሉ። ንቦችን የሚስቡ የአበባ ዘሮች ደግሞ በአንድ የጭቃ ኳስ ውስጥ ከአምስት እስከ ስደስት ይኖራሉ። ዛፍ ከሆነ አንድ ዘር፤ ፍራፍሬዎች ደግሞ ሁለት ዘር በውስጣቸው እንዲኖር ይደረጋል።
በአሁኑ ጊዜ ህሊና ሽሮ ሜዳ አሜሪካ ኤምባሲ አካባቢ የሲድ ቦል/የዘር ኳስ/ ማምረቻ ፋብሪካ ከፍታለች። በዚሁ ሲድ ቦል የማምረት ሥራ ለሶስት ሴቶችና ለአንድ ወንድ የሥራ እድል ፈጥራለች። በዚህ ስራም በዋናነት ለሴቶች ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። በፋብሪካው አስራ አራት አይነት የአትክልት ዘሮች የሚመረቱ ሲሆን፤ ፋብሪካው በቀን 1 ሺ የሲድ ቦል ዘሮችን የማምረት አቅም አለው። 50 ሺ የተቀመጡ የአትክልት ሲድ ቦል ዘሮችንም ይዟል። ስድስት አይነት የአበባ ዘሮችም በፋብሪካው ይመረታሉ። አስራ አንድ አይነት ሀገር በቀል የዛፍ ዘሮችንም እንዲሁ ፋብሪካው ያመርታል። በአጠቃላይ 100 ሺ የሚጠጉ ሲድ ቦሎች/የዘር ኳሶች/ ፋብሪካው አለው።
ለዘር አስፈላጊ የሆነው አፈርና ማዳበሪያ ተመጣጥኖና አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች በውስጡ ተካተውበት ውሃ ሳይበዛ ይቦካል። ከዛ እንደየዘሩ አይነት ብዛት በተቦካው አፈር ላይ በመጠቅለል እንዲድቦሎቦል ይደረጋል። የፀሃይ ሙቀት ኳሱን ሊሰነጥቀውና በውስጡ ዘሩ የያዘውን ንጥረ ነገር ሊጎዳው ስለሚችል በቤት ውስጥ በከሰል ጭስ ወይም በንፋስ እንዲደርቅ ይደረጋል። በዚህ መልኩ ዘሩ ተመርቶ ለገበያ ይቀርባል። የናሙና ቦታዎችም ተዘጋጅተውለታል።
የዚህ ሥራ ዋነኛ ዓላማ አርሶ አደሩ ጋር ለመድረስ እንደመሆኑ ዘሮቹ ለአርሶ አደሮች የሚደርሱበት መንገዶች እየተመቻቹ ነው። ለአብነትም በአማራ ክልል ያሉ አርሶ አደሮች የአትክልት ዘሮችን በሙከራ ደረጃ እንዲጠቀሙ ተሰጥቷቸዋል፤ ውጤቱም ተስፋ ሰጪ መሆኑ ታይቷል። በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልልም የዛፍ ዘሮች ለአርሶ አደሩ ቀርበው ተቀባይነትን አግኝተዋል። በአዲስ አበባም ተመሳሳይ የሙከራ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። የመንግሥት ተቋማትም ዘሮቹን ወስደው እንዲሞክሯቸው እየተደረገ ነው። ከዚህ ባለፈ ስራው ለወጣቶችና በተለይ ለሴቶች በራሳቸው የሥራ እድል እንዲፈጠሩ እያስቻለ ነው።
ተዘጋጅቶ ለገበያ የሚቀርበው የዘር ኳስ ተፈጥሯዊ ነው። በአሲድና በኬሚካል በተበላሹ መሬቶች የዘር ኳሱ በተደጋጋሚ ሲተከል የተጎዳውን መሬት በሂደት ወደነበረበት የመመለስ አቅም አለው። በጠባብ መሬት ላይ በመትከል ለመጠቀም ያስችላል። በገጠርም በግብርና ወቅት የሚውለውን የኬሚካል ማዳበሪያ ያስቀራል። በሌላ በኩል ደግሞ በአይር ንብረት ለውጥ ኢትዮጵያ እያጣቻቸው ያለችውን ብርቅዬ እፅዋትን በዚህ መንገድ ለመመለስ ያስችላል። የተሻለ ግብርና ምርት እንዲኖርም ያግዛል። የምርት ንጥረ ነገር ይዘትን በመጨመር ረገድም ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።
ህሊና በምርምር ያወጣቸው የዘር ኳስ በሚመለከተው የመንግሥት አካል በኩል አስፈላጊውን የፍተሻ ሂደት አልፏል፤ ተሞክሮም ጥሩ ግብረ መልስ ተገኝቶበታል። በአሁኑ ጊዜም የማረጋገጫ ኮድ ለማግኘት ሂደቶችን እየተከተለ ይገኛል። ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየተደረጉ ያሉ ንግግሮችም አሉ።
ህሊና የስራው ጀማሪ እንደመሆኗ በቀጣይ ከመንግሥትና ከሌሎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የዘር ኳስ ማምረት ስራውን ይበልጥ በማስፋት በተለይ ሴቶች በዚህ ሥራ ገብተው ተጠቃሚ እንዲሆኑና ራሳቸውንም እንዲለውጡበት የማድረግ ህልም አላት። በእናቷ ብቻ ማደጓ ሳይሆን አይቀርም ህሊና በተለይ ያለ ባል ልጆቻቸውን ለሚያሳድጉ እናቶች ላይ ትኩረት አድርጋ የመስራት ፍላጎትም አላት።
በሌላ በኩል ደግሞ የዘር ኳሱን በተለይ ለገበሬው በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ትፈልጋለች። የሲድ ቦል ኢትዮጵያ ዋነኛው ዓላማም ረሃብን በተቻለ አቅም መግታት ነው። በተለይ ደግሞ በግብርናው ዘርፍ ትልቅ አስተዋፅኦ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ምርታማነትን መጨመር ነው። በብዝሃ ህይወት በኩልም በዋናነት አረንጓዴ አሻራን ከመደገፍ አንፃር ሲድ ቦል ኢትዮጵያ በተለይ ችግኝ ለመትከል አስቸጋሪ በሆኑ ተራራማ ቦታዎች ላይ ተደራሽ በመሆን የሀገሪቱን የደን ሽፋን የማሳደግ ውጥን ይዟል። ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎችን በብዛት በማምረት ህዝቡ ጠግቦ እንዲያድር የማድረግም ህልም አለው።
በሌላ በኩል ደግሞ የሙከራ ሂደቱን ያጠናቀቀው ሲድ ቦል ከሚመለከተው የመንግሥት አካል የማረጋገጫ ኮድ በዚህ ክረምት መጨረሻ እንዲያገኝ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እንደምታደርግ ህሊና ትናገራለች። ከዚሁ ጎን ለጎን ግን የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል ትገልፃለች። ከዚህ በተጓዳኝ በወጣቶች ሥራ ፈጠራ፣ የኢንቨስትመንት ዝግጅትና የራስ ክህሎት ማዳበር ዙሪያ የጀመረችውን የማስተማር ሥራ አሁንም ማስቀጠል እንደምትፈልግ ትናገራለች።
ወጣቶች ከባለሙያዎችና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተገናኝተው የሚወያዩበት መድረክ በማመቻቸት ተፈጥሮ ተኮር መፍትሄ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ እንዲያመጡ የማስቻል ስራዎችን አጠናክሮ ያማስቀጥል እቅድም እንዳላት ትጠቁማለች። ይህም ወጣቶቹ ከተለያዩ ባለሙያዎችና የመንግሥት አካላት ጋር የመነጋገርና ፕሮጀክቶቻቸውን ተናግረው ወደ ራሳቸው ቢዝነስ እንዲገቡ የሚያስችል ስለመሆኑም ትጠቅሳለች።
ሴት በውስጧ ያለውን እምቅ ችሎታ አውጥታ ራሷንም ሆነ ቤተሰቧን መቀየር የምትችለው ደፍራ አደባባይ ስትወጣ ነው የምትለው ህሊና፤ አይደለም ሴት ወንዶችም ሃሳባቸውን እንደልብ መግለፅ የማይችሉበት ባህል ባለበት በኢትዮጵያ ሴቶች ባህሉን ሰብረው ወደፊት መውጣት እንዳለባቸው ትጠቁማለች። በውስጣቸው ያለባቸውን ችግር ከማውራት ይልቅ ያላቸውን የመስራት አቅም ማውጣትና ወደ ውጤት መቀየር እንዳለባቸውም ታሳስባለች።
ሴቶች ‹‹ይህን ነገር አደርገዋለሁ! እችለዋለሁ!›› ማለትን መልመድ እንዳለባቸውም ነው ህሊና የምትገልፀው። ከዚህ በተረፈ ግን ሴቶች ራሳቸውን ማወቅ እንዳለባቸውና ከራሳቸው ጋር መነጋገር እንደሚኖርባቸውም ትመክራለች። ሴት ልጅ ስትማር ሙሉ ቤተሰቧ፣ ከዚህም አልፎ አካባቢ፣ ማህበረሰብና ሀገር ይማራል ትላለች። ስለዚህ ሴት ልጅ ለራሷ ቅድሚያ ሰጥታ መስራት እንደሚኖርባት፤ የእርሷ መለወጥ ለሌላውም እንደሚተርፍ መልእክቷን ታስተላልፋለች።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2015