ምዘና የገለጠው – የእውቀት እና ውጤት ተቃርኖ

እንደ መግቢያ

ሀገር ከችግር የሚያወጣ ትውልድ ትሻለች፤ ሀገር ከድህነት እና ኋላ ቀርነት የሚያላቅቅ እውቀትና ክህሎት ያለው ወጣት ትናፍቃለች፤ ሀገር ከዛሬ ባሻገር ያለውን ብሩህ ነገ የሚያሳያት ተመራማሪና ፈጣሪ ዜጋን ትፈልጋለች:: ይሄ በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ ሀገራት እውነት ነው::

እንደ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የሚጥር፤ ከኋላ ቀርነት ለመላቀቅ የሚውተረተር፤ ከጦርነትና ሰላም እጦት በሽታው ለመፈወስ የሚዳክር፤ ልማትና ዴሞክራሲን አብዝቶ ለሚፈልግ ሀገር ደግሞ በእውቀት የተገነባ፣ በክህሎት የበለጸገ፣ በስነምግባር የታነጸ ትውልድን በእጅጉ ይፈልጋል::

ይሄ ህልምና ምኞት ደግሞ እውን የሚሆነው በትምህርት እና ትምህርት ብቻ ነው:: ምክንያቱም የተማረ ያውቃል፤ የተማረ ይመራመራል፤ የተማረ ይፈጥራል፤ የተማረ በስነምግባር አድጎ ነገ ለአገርና ለወገን የሚበጅ ሃሳብ ያፈልቃል፤ ሃሳቡንም ወደ ተግባር ቀይሮ አገርና ሕዝብን ያሻግራል:: እናም አገራት እንደየራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ትምህርትን የሚያስተዳድሩበት አሰራር አላቸው::

ኢትዮጵያም የትምህርት ሥርዓቱን በበላይነት እንዲመራ የትምህርት ሚኒስቴር አቋቁማለች:: ይሄ ተቋም ታዲያ፣ “ጥራት እና ውጤታማነት” ከተቋማዊ እሴቶቼ ቀዳሚዎቹ ናቸው፤ “ብቁ ዜጋ የሚያፈራ፣ ጥራትና ፍትሃዊነት ያረጋገጠ የትምህርትና ስልጠና ስርአት በቀጣይነት መገንባት”ም ተቋማዊ ራዕዬ ነው፤ እና ሌሎችም በየተቋማት ደጃፍ ተሰድረው የሚታዩ ተለምዷዊ ገለጻዎችን በጽሑፍ ቢያሰፍርም፤ ሃቁ ግን ከዚህ በተቃራኒው እንደሆነ እየተገለጠ ታይቷል::

ምክንያቱም በኢትዮጵያ የትምህርት ክህሎት አጎናጻፊነት፤ የትምህርት የእውቀት ማዕድነት፤ የትምህርት የምርምርና የፈጠራ መድረክነት፤ የትምህርት በእውቀትም በክህሎትም በሥነምግባርም ትውልድን አንጾ የአገር አሻጋሪ ራዕይ ያላቸው ተተኪዎችን የመፍጠሪያ ኃይልነት ከእለት እለት እየኮሰመነ መጥቷል::

ትምህርት ቤቶች ከቁጥር ያለፈ መገለጫ የሌላቸው መሆናቸው፤ የመምህራን አቅም ከዘመን ዘመን እየተሸረሸረ መታየቱ፤ የተማሪዎች በራስ የመተማመን ልዕልና ላሽቆ በኩረጃ ላይ የተመሰረተ ከክፍል ክፍል ሽግግር ተለምዷዊ መሆኑ እና ሌሎችም የዘርፉ መገለጫዎች ከሆኑ ውለው አድረዋል::

ሌላው ቀርቶ ለትምህርት ጥራትና እድገት አጋዥ ይሆናሉ የሚል ተስፋ የተጣለባቸው የግሉ ሴክተር ትምህርት ቤቶች የእውቀት ሳይሆን የገንዘብ መፍጠሪያ ከሆኑ ውለው አድረዋል:: የእነዚህ ድምር ውጤት ደግሞ የትምህርት ጥራት እንዲወርድ ብቻ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ያለው የትምህርት ሁኔታ እጅጉን አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ስለመሆኑ በግልጽ ታይቷል::

ችግሩን ተረድቶ የመፍታት ጅማሬ

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣው የትምህርት ጥራት ችግር ተጽዕኖው በትምህርት ቤቶች ብቻ የሚገለጽ አይደለም:: ይልቁንም እንደ ተቋም፣ በአጠቃላይም እንደ ሀገር እና እንደ ትውልድ የሚገለጽ እንጂ:: ምክንያቱም ሀገር በተማረ የሰው ሃይል፣ በተመራማሪና ፈጣሪ ትውልድ የምትገነባ ቢሆንም፤ ትውልዱ መፍጠርና መመራመሩ ቀርቶ በወጉ የተማረውን ተረድቶ የክፍል ፈተና ማለፍ እንኳን የዳገት ያህል የከበደው ሆኗል::

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ ስሙን በወኩ የማይከትብ፤ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ሆኖ የሰለጠነበትን መስክ በቅጡ ያልተገነዘበ፤ በሥራ ዓለም ተሰማርቶ የተማረውንና ያወቀውን መተግበር ያልቻለ እየሆነ መጥቷል:: ሁሉንም በአንድ ቋት ማስቀመጥ ቢከብድም፤ አሁን ላይ ሕንጻ ቢሰራ በጅምር የሚናድ፤ መንገድ ቢገነባ ሳይጠናቀቅ ለጥገና ወጪ የሚጠይቅ፤ ዳኝነት ቢቀመጥ ፍርድ የሚያዛባ፤… ትውልድ እየተፈጠረ ነው::

ይሄ ደግሞ የትውልዱ ጥፋት ነው ብሎ መደምደም አይቻልም:: ምክንያቱም ትውልዱ የሥርዓቱ ውጤት ነው፤ ትውልዱ የማህበረሰቡ ብሎም የትምህርት ተቋማት ፍሬ ነው:: ይሄን ትውልድ ማጥፋትም፤ የአገር ዋልታ ማድረግም ከእነዚሁ አካላት የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው:: እናም ችግሩን አለ ከማለት ባሻገር፤ ችግሩ እንዴት ተፈጠረ? የሚለውን በወጉ መፈተሽ እና አስፈላጊውን እርምት ማድረግ የተገባ ነው::

ለምሳሌ፣ “የኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ጉዞ ከየት ወደየት እና የፖሊሲ ትግበራ ችግሮች” በሚል ርዕስ በ2010 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት የቀረበ ሰነድ እንደሚያመለክተው፤ አንድ አገር ሁለንተናዊ እድገቷን የምታረጋግጠው በዜጎቿ አቅም እንደሆነ የበለጸጉት አገራት አብይ ማሳያ ናቸው::

በኢትዮጵያም ይሄንን በመገንዘብ የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲን በማዘጋጀት ጭምር ተሰርቷል፤ በተለይ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን በማስፋፋት በኩል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል:: ይሁን እንጂ በተቀመጠ ፖሊሲ መሰረት ባለመፈጸምና ከዚህ ጋር በተያያዘ ባሉ የግንዛቤ ክፍተቶች ምክንያት ከትምህርት ተደራሽነት ጀምሮ በፍትሃዊነት፣ በጥራትና አግባብነት ላይ ከፍ ያሉ ችግሮች ታይተዋል::

ለአብነት፣ የትምህርት ሥርዓቱ ተግባር ላይ ከማተኮር ይልቅ በንድፈ ሃሳብ ላይ የታጨቀ መሆን፤ ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪነትን መሰረት ያላደረገ፤ የአገር በቀል የእውቀት ክምችትን በአግባቡ ያላካተተ፤ ስለ ቴክኖሎጂ እና ስለ ስራ ፈጠራ በቂ ትውውቅ ብሎም እውቀትና ክህሎት መፍጠር ላይ ያላተኮረ፤ ከዚህም በላይ በየጊዜው እየተፈተሸ የማይከለስ ሆኖ ዘልቋል::

ከትምህርት ሥርዓቱ በተጓዳኝ የትምህርት ሥርዓቱን ወደ ውጤት እንዲቀይሩ የሚጠበቁት መምህራን ላይም ሰፊ የአቅም ክፍተት የታየበት ነበር:: ምክንያቱም ሂደቱ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ያልቻለ የመምህራን ምልመላና ዝግጅት አካሄድ የሰፈነበት ሆኖ ቆይቷል::

ለምሳሌ፣ ከ2006 እስከ 2009 ዓ.ም በተካሄዱ የሙያ ፍቃድና ምዘናዎች ምዘናውን ከወሰዱ 140 ሺህ 435 የመጀመሪያ እና 24 ሺህ 63 የሁለተኛ ደረጃ መምህራን መካከል መቁረጫ ነጥብ በማሟላት ያለፉት 22 በመቶው መምህራን ብቻ ናቸው::

የትምህርት ቤቶች ደረጃም ሌላው አሳሳቢ ለትምህርጥ ጥራት ችግር ፈጣሪ ጉዳይ ተብሎ የተለየ ሲሆን፤ ይሄም ለመማር ማስተማር ብቁ ያልሆኑ እና በተገቢው መሰረተ ልማት ያልተደራጁ ይልቁንም በዳስ እና በዛፍ ጥላ ስር ጭምር ተማሪዎች የሚማሩባቸው አካባቢዎች እጅጉን መብዛታቸው ነው::

እነዚህ እና መሰል ጉዳዮች ደግሞ ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ብቁ እና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድረዋል:: በመሆኑም ከ2010 ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ይሄንኑ ስብራት መጠገን የሚያስችል ሪፎርም ማድረግ አንዱ የቤት ሥራ ተደርጎ ነው የተወሰደው::

በዚህም ዘርፉን የሚመራውን ተቋም አደረጃጀት ከማሻሻል ጀምሮ የትምህርት ሥርዓቱን ፖሊሲና ሌሎች አሰራሮችን ፈትሾ የትምህርት ጥራትን ማምጣት እና የተሻለ (በእውቀትም፣ በክህሎትም፣ በስነምግባርም የታነጸ) ትውልድ መፍጠር በሚያስችል መልኩ እንዲቀረጹ ተደርጓል:: በጥናት ላይ የተመሰረተ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅ ተደርጓል::

ጥናትን በተግባር የመፈተሽ እርምጃ

በዚህ መልኩ ችግሮች በጥናት ተደግፈው ከተለዩ እና በጥናት ላይ ተመስርቶም የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ በተዘጋጀ ማግስት፤ ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን እና ሪፎርሞችን በመስራት ፖሊሲው ወደተግባር እንዲገባ ተደርጓል:: ከዚህ ጎን ለጎን ግን ቀደም ሲል የታዩ የጥራት ችግሮችን በተግባር ለመፈተሽ እና አገራዊ የትምህርት ሥርዓቱን ዝንፈት ለማረቅ እንዲቻል የሚያግዙ ዘርፈ ብዙ የተግባር ፍተሻዎች ተከናውነዋል::

በዚህም የትምህርት ቤቶች ደረጃን የመፈተሽ፤ የመምህራንን አቅም ማሳደግ የሚያስችሉ አሰራሮች የመዘርጋት፤ የመማሪያ መጽሓፍትን የማዘጋጀት፤ የተማሪዎችን የምዘና ስርዓት የመለወጥ፤ የተመራቂ ተማሪዎችን አቅም የመፈተሽ እና ሌሎችም የመማር ማስተማር ሂደቱን ስብራት በወጉ ለመለየትና ተገቢውን እርምት ለመውሰድ የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል::

ለአብነት፣ በሥራ ላይ ያሉ መምህራንን አቅም የማሻሻል ስራ ከማከናወን ጎን ለጎን፤ ወደ መምህርነት ሙያ የሚገቡ ተመራቂዎች እየተመዘኑ እንዲገቡ፤ አዳዲስ ወደሙያው መግባት የሚሹትም ከፍ ያለ አቅምና ውጤት ያላቸው፣ ለሙያውም ፍቅርና ሥነምግባር ያላቸው እንዲሆኑ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራበት ይገኛል:: ይሄ ተግባር ደግሞ ቀደም ሲል አቅም ሳይገነቡ አቅም ያለው ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገውን አንካሳ አሰራር የሚያርም ስለመሆኑ እሙን ነው::

ከዚህ በተጓዳኝ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር አውድ እንጂ ተማሪዎች ውለው የሚገቡባቸው እንዳይሆኑ የሚያስችሉ ተግባራት ወደማከናወን ነው የተገባው:: በዚህም ለመማር ማስተማር ምቹ ያልሆኑ ትምህርት ቤቶች ተለይተዋል:: በዳስ እና በዛፍ ጥላ ስር ትምህርት ሲሰጥባቸው የነበሩ ቦታዎችም “ከዳስ ወደ ክላስ” በሚል ቅኝት ባለሃብቶችን በማሳተፍ ተሰርቷል::

ሌሎች ምቹ ያልሁኑ ክፍሎችን ደረጃ የማሳደግ እንዲሁም በተገቢው መሰረተ ልማት እንዲደራጁ የማድረግ ተግባር በጅምር ደረጃ ታይተዋል:: ይሁን እንጂ አሁንም ለመማር ማስተማር ብቁ ሆነው የተኙ ትምህርት ቤቶች ቁጥር እዚህ ግባ የማይባል መሆኑ በመታወቁ፤ ይሄንን የትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሳደግ ሀገርአቀፍ ንቅናቄ ተነድፎ እየተሰራበት ይገኛል:: ይሄንን ንቅናቄ በልኩ ተገንዝቦ የራስን አበርክቶ ማድረግ ደግሞ የአገርና ወገን ወዳዶች ኃላፊነት መሆኑን በእግረ መንገድ ለማስገንዘብ እወዳለሁ::

ወደ ጉዳዬ ስመለስ፣ ብቁ መምህራንን ከማዘጋጀት እና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሳደግ ጎን ለጎን ደግሞ፤ ባለው አውድ ውስጥም ቢሆን ተማሪዎች ምን አውቀዋል? የሚለውን ለመለየት የሚያስችለውን የምዘና ስርዓት መፈተሽ ሌላው ስራ ነበር:: ምክንያቱም ቀደም ሲል የፈተና ሂደቱ በትምህርት ቤቶች፣ በወረዳዎች፣ በዞኖች ብሎም በክልሎች መካከል እውቀትን ሳይሆን ውጤትን መሰረት ያደረገ ጤናማ ያልሆነ ፉክክር በመፈጠሩ ምክንያት ክልላዊና አገራዊ ፈተናዎች ሳይቀር እየወጡ መምህራት እንዲሰሩ ማድረግ የተለመደ ሆኖ ነበር::

በመሆኑም እነዚህን መስበር እና ተማሪዎች ከኩረጃና ከፈተና ስርቆት ተላቅቀው በራስ መስራትን እንዲለማመዱ፤ በዚያውም በራስ የመተማመን አቅም እንዲገነቡ እና የአገርም፣ የትውልድም ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚያስችላቸውን ስብዕና ከወዲሁ እንዲገነቡ ማስቻል ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፤ አዲስ የምዘናና ፈተና አሰራር ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል::

በዚህ ረገድ የአስራ ሁለተኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና አሰጣጥ ላይ የተወሰደው ርምጃ የመጀመሪያው ሲሆን፤ ተፈታኞች እንደ ቀድሞው በየትምህርት ቤቶቻቸው ሳይሆን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ገብተው ፈተናውን እንዲወስዱ የተደረገበት ነው:: ይሄ ርምጃ ደግሞ ቀደም ሲል በትናንት ከታየው በላቀ መልኩ የትምህርት ሥርዓቱ መታየት ችሏል::

ምክንያቱም፣ ሂደቱ ኩረጃንም፣ የፈተና ስርቆትንም ያስቀረ፤ ተማሪዎች ባወቁት ልክ ሰርተው እንዲገለጡ ያደረገ በመሆኑ፤ ፈተናውን ከወሰዱት 896 ሺህ 520 ተማሪዎች ውስጥ 29 ሺህ 909 የሚሆኑት ተማሪዎች ብቻ ናቸው 50 በመቶ እና በላይ ማስመዝገብ የቻሉት::

በሃገር አቀፍ ደረጃ ፈተናውን ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሰባት ትምህርት ቤቶች ብቻ ያስፈተኑትን ተማሪዎች 100 በመቶ ማሳለፍ በቻሉበት በዚህ ፈተና፤ በሺህ የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ምንም ተማሪ ማሳለፍ ያልቻሉበትም ነበር:: እናም ውጤቱ ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ በርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፋፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ስርዓታችን ያለበትን ደረጃ ያመላከተ ሆነ::

እንደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያው ሁሉ በዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን ቆይታ አጠናቅቀው ለምርቃት የሚበቁ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችም፤ ከመመረቃቸው በፊት በቆይታቸው ምን ያህል እውቀትና ክህሎት ጨብጠዋል የሚለውን በመውጫ ፈተና የመፈተሽ ተግባር በዚህ ዓመት ተከናውኗል:: በዚህም ከመንግስት 77ሺ 981 እና ከግል 72ሺ 203፣ በድምሩ 150ሺ 184 ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን ወስደዋል::

ምዘና የገለጣቸው ገመናዎች

ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ታዳጊዎችና ወጣቶች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ:: እነዚህ ታዳጊዎችና ወጣቶች ደግሞ በትምህርት ቤት ቆይታቸው በሚያገኙት የእውቀት፣ የክህሎትና የመልካም ስነምግባር አቅም ተጠቅመው ለአገር እና ሕዝብ አሻጋሪ የምርምርና ፈጠራ ውጤቶችን የማፍለቅ፤ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን የማበርከት ከፍ ያለ ኃላፊነትን መወጣት ይጠበቅባቸዋል::

በዚህ ረገድ የመንግስት የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት አቅም በመንግስት አቅም ልክ የተሰፋ እንደመሆኑ፤ ይሄንን ሴክተር በተሻለ አቅምና ቴክኖሎጂ ከመደገፍ አኳያ የግሉ ዘርፍ ሚና እጅጉን አስፈላጊ ነው:: ይሄንን አስፈላጊነት በመገንዘብም በኢትዮጵያ የግል የትምህርትና ስልጠና ተቋማት በእጅጉ እንዲስፋፉ ተደርጓል::

እነዚህ የግል የትምህርት ተቋማት ታዲያ እንደ አገር በእውቀትና ክህሎት ብሎም በስነምግባር የተገነባ ትውልድን ከመፍጠር ከቁጥራቸው ብዛት አንጻር በተለይ የተማረ የሰው ኃይልን በማፍረት ረገድ መልካም የሚባል ስራን እየሰሩ ይገኛል::

እነዚህ የግሉ ዘርፍ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ታዲያ ወደስራ ሲገቡ ሊያሟላቸው የሚገቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ:: በተለይ ከሰው ሃይላቸው፣ ከተገቢ የመማር ማስተማር ከባቢ እንዲሁም በተገቢው የመማር ማስተማር ሂደት ማሳለጫ ግብዓቶች የተደራጁ መሆንን ከግምት አስገብተው የሚደራጁና ወደስራ የመግባት ፈቃድ የሚያገኙ ናቸው::

ምክንያቱም እነዚህ ተቋማት ከመንግስት የተሻለ አቅምና ቴክኖሎጂን ታጥቀው በዘርፉ አንድ ርምጃ የሚያራምድ ተግባር ሊወጡ ስለሚገባ ነው:: በማህበረሰባችን ውስጥ ያለው ምልከታም ሆነ በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ የሚታየው የውጤት ሁኔታ ሲነግረን የኖረውም ይሄንኑ ከፍ ያለ ኃላፊነታቸውን በተገቢው መልኩ እየተወጡ ስለመሆናቸው ነው::

ውጤት ደግሞ በተማሪዎች ብቻ ሳይሆን፣ በወላጆችም ሆነ በጥቅሉ በማህበረሰባችን ውስጥ የተማሪዎች የእውቀት እና ክህሎት መለኪያና መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል:: በዚህ ረገድ በመንግስት እና በግል የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት መካከል ያለው የተማሪዎች የውጤት ልዩነት ለዓመታት የመንግስት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን በወጉ እውቀት እንደማያስጨብጡ፤ በአንጻሩ የግል የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ተማሪዎቻቸውን በአግባቡ አስተምረውና እውቀት አስጨብጠው እንደሚያበቁ እንድናስብ አድርጎን ቆይቷል::

ለዚህ ማሳያ ከሚሆኑ በርካታ ጉዳዮች መካከል አንድ ሁለቱን ለመጥቀስ ልሞክር:: የመጀመሪያው ጉዳይ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ከክፍል ክፍል ለመሸጋገር ከ90 በመቶ በላይ ውጤት ማስመዝገብ ከዳገት ጉዞ የከበደ ነው:: ከ80 በመቶ በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎችም በአብዛኛው የደረጃ ተማሪ የሚባሉ ናቸው::

በአንጻሩ በግል ትምህርት ቤቶች ከክፍል ክፍል ለመሸጋገር 80 በመቶ ቀርቶ 90 በመቶ ማስመዝገብ የተማሪዎች ጭራ የሚያደርግ ውጤት ነው:: የደረጃ ተማሪ ለመሆን ደግሞ ከ99 በመቶ በላይ ማስመዝገብ የግድ ይሆናል:: 98 በመቶ ማስመዝገብ በራሱ የመካከለኛ ደረጃ ተማሪዎች ጎራ የሚያስመድብ ውጤት ነው::

በተመሳሳይ መልኩ፣ የስምንተኛ፣ የአስረኛ እና የአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና ውጤቶች ላይ የሚታየውም ይሄው ነው:: ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን 100 በመቶ ስለማሳለፋቸው ብቻ ሳይሆን፤ አብዛኛዎቹንም እጅግ በከፍተኛ ውጤት ስለማሳለፋቸው ብዙ ነጋሪ ሳያሻ በየደጃፎቻቸው ከሚለጥፏቸው ባነሮች መረዳት ይቻላል::

በአንጻሩ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ይሄ እምብዛም አይታይም:: ጥቂት የሚባሉ በከፍተኛ ውጤት ስለማለፋቸው የሚያሳዩ ባነሮች በየበሮቻቸው ከመለጠፍ ያለፈ፤ ሙሉ በሙሉ አሳለፍን የሚል ሐተታን አብረው አያኖሩም::

ወደ ከፍተኛ ተቋማት (ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች) ዘልቀን ስንመለከትም ተመሳሳይ ሃቅ እናያለን:: በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከሦስት ነጥብ በታች ማስመዝገብ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ አብዛኛው የሚያስመርቋቸው ተማሪዎቻቸው የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂዎች ናቸው::

በአንጻሩ ግን ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ተማሪዎች ከሦስት ነጥብ በላይ እንዳያስመዘግቡ የተባለ እስኪመስል ድረስ አብዛኛው ተማሪ ከሦስት ነጥብ በታች ይዞ የሚመረቅባቸው ናቸው::

ከዚህም በላይ ብዙ የልዩነት ማንጸሪያና ማሳያ የሚቀርብላቸው የግል እና የመንግስት ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ታዲያ፤ በዚህ ምክንያት በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው ገጽታ እንደ ውጤታቸው ሁሉ እጅጉን የተራራቀ ነው:: አንዳንዴም ወላጆች ልጆቻቸውን የተሻለ እውቀት ለማስጨበጥ፤ አለፍ ሲልም በከፍተኛ ውጤት ተመርቀው ስራን እንዲይዙላቸው (በአብዛኛው የስራ ውድድሮች ላይ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁት ውጤታቸው ከፍ ያለ በመሆኑ ቀድመው እንደሚቀጠሩ ልብ ይሏል) ሲሉ ከሌላቸው ላይ ቀንሰው ወደ ግል ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ሲያስገቡም ማየት የተለመደ ሆኗል::

ይሁን እንጂ ነገሩ “እውነት እና ንጋት፣ እያደር ይጠራል” ይሉትን ሆኖ፤ እንደ ሀገር የታየውን የትምህርት ስብራት በማከም ሂደት ውስጥ የተገለጠው ሃቅ ሌላ ገጽ ኖሮት ነው የተገኘው:: ይሄ ፍጹም የተሳሳተ አካሄድም፣ የተለበጠ ገጽም መሆኑን አሁን ላይ መረዳት ተችሏል::

ምክንያቱም በሀገራዊ የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት ሂደት ውስጥ ይሄን መሰል አካሄድ የራሱ ችግር የነበረው፤ በተለይ በትምህርት ጥራት ላይ ለታየው ቀውስ ትልቅ ብልሽት አምጪ አካሄድ መሆኑን በ2014ቱ ብሔራዊ ፈተና እና በዘንድሮው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ሂደት መገንዘብ የተቻለበት እድል ፈጥሯል::

እንዴት ቢሉ፣ የትምህርት ጥራት ችግርን ለማስተካከል በተደረገው ጥናትን በተግባር የመፈተሽ እርምጃ እነዚህ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት (ሁሉም ማለት ባይቻልም) ከስምና ዝና የዘለለ የሚጠበቅባቸውን አበርክቶ እያደረጉ አለመሆኑን መመልከት ተችሏል::

በዚህ በኩል የውጤት እና እውቀት ተቃርኖን ገመና ገላጭ የሆነው የ2014ቱ የብሔራዊ ፈተና ነው:: ይሄ ፈተና እንደ አገር የታየውን ችግር፣ በተለይም ከ2008 ዓ.ም ወዲህ እየተባባሰ የመጣውን ፈተናን አውጥቶ ለተማሪዎች የመስራት በሽታ አክሞ ፈውስ የሰጠ ነበር::

ምክንያቱም ተማሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ በየተማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ፈተና ወጥቶ እየተሰራላቸው የሚያልፉበትን ሳይሆን፤ ከተማሩበት ትምህርት ቤት ውጪ ተጉዘው በየዩኒቨርሲቲዎች ፈተና ወጥቶ ሳይሰራላቸውና ሳይኮራረጁ በተማሩትና ባወቁት ልክ ሰርተው እንዲያልፉ የግድ ያለበትን አጋጣሚ የፈጠረ ነበር::

እናም ይሄ ወቅት የትምህርት ቤቶች የቀደመ መኮፈስና የ100 በመቶ በከፍተኛ ውጤት አሳልፌያለው ዲስኩር ትቢያ የለበሰበት ሆነ:: 100 በመቶ በከፍተኛ ውጤት ያሳልፉ የነበሩ የግል ትምህርት ቤቶች፤ ፈተናውን 50 በመቶ ውጤት አምጥቶ ማሳለፍ ያልቻሉበት እና የ100 በመቶ ያላማሳለፍ የውድቀት ታሪክ የጻፉበት (አንድ ወይም ሁለት ትምህርት ቤቶች በቀደመ ዝናቸው መቆየታቸውን ሳንዘነጋ) ሆነ::

ፈተናውን ከወሰዱት 896 ሺህ 520 ተማሪዎች ውስጥ 29 ሺህ 909 ተማሪዎች ብቻ 50 በመቶ እና በላይ ባስመዘገቡበት ከስርቆትና ከኩረጃ በጸዳው የ2014ቱ ሀገራዊ ፈተና፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ፈተናውን ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሰባት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች 100 በመቶ ማሳለፍ የቻሉት:: እዚህ ጋ ታዲያ እነዚያ 100 በመቶ ያውም በከፍተኛ ውጤት በማሳለፋቸው ምክንያት ለተማሪዎቻቸው ከፍ ያለ እውቀትን እያስጨበጡ ስለመሆኑ የሚናገሩትና የሚነገርላቸው የግል ትምህርት ቤቶች ወዴት ገብተው ነው? ብሎ መጠየቁ ተገቢነት ያለው ይመስለኛል::

እንደ ብሔራዊ ፈተና ሁሉ ሌላው የውጤትና እውቀት ተቃርኖን አደባባይ ያወጣው ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተገበረው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ነው:: ይሄ ፈተና የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና በተማሩት የትምህርት መስክ ከፍተኛ ግንዛቤ ያላቸውን ተመራቂዎች ለማፍራት እንዲቻል እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት መካከል አንዱ ነው::

በዚህም መሰረት ከ2015 ጀምሮ በየትኛውም የትምህርት መስክና ከየትኛውም በኢትዮጵያ ካሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና በሁሉንም የቅድመ ምረቃ መርሃ-ግብሮች ትምህርታቸውን ተከታትለው የሚወጡ ተማሪዎች በኦንላይን የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ አድርጓል:: ፈተናው ከመሰጠቱ በፊትም የትምህርት ተቋማቱ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉና ተማሪዎችንም እንዲያለማምዱ ከማድረግ ባሻገር፤ ስለ ፈተናው አጠቃላይ ሁኔታ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ “ብሉ ፕሪንት” ጭምር ስለመላኩ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት::

በዚህም 150ሺ 184 እጩ ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ከመንግስት 77ሺ 981፣ ከግል ደግሞ 72ሺ 203 መሆናቸውን ነው የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ የሚያሳየው:: በዚህ መልኩ የመውጫ ፈተናውን ከወሰዱ እጩ ተመራቂዎች ውስጥ ደግሞ በድምሩ 61ሺ 54 ተማሪዎች (40 ነጥብ 65 በመቶ) ብቻ ናቸው የማለፊያውን 50 ነጥብ እና ከዚያ በላይ ማስመዝገብ የቻሉት::

ይሄ ውጤት በተናጠል ሲታይ ደግሞ፤ ከመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለፈተና ከተቀመጡት 77ሺ 981 ተፈታኞች ውስጥ 62ነጥብ 37 በመቶ ያህሉ ፈተናውን ማለፍ (50 ነጥብና ከዚያ በላይ ማምጣት) የቻሉ ሲሆን፤ በአንጻሩ ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለፈተና ከተቀመጡት 72ሺ 203 ተፈታኞች ውስጥ 17ነጥብ 2 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ፈተናውን ማለፍ (50 ነጥብና ከዚያ በላይ ማምጣት) የቻሉት::

ይሄ ደግሞ ቀደም ሲል የመውጫ ፈተና ይሰጥ ባልነበረበት ወቅት በዩኒቨርሲቲዎቹ ያለውን የውጤት ሁኔታ በእጅጉ ጥያቄ ውስጥ የሚከትት ሲሆን፤ በተለይ የግል ዩኒቨርሲቲዎች ከሦስት ነጥብ በላይ የመመረቂያ ውጤት አሸክመው የሚያስመርቁበት፣ በአንጻሩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ከሦስት ነጥብ በታች አስይዘው የሚያስመርቁበትን አግባብ ለተመለከተ ውጤት እና እውቀት በእጅጉ የተራራቁ ስለመሆናቸው ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ነው::

ምክንያቱም ውጤት የእውቀት መለኪያ ቢሆን ኖሮ ከመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይልቅ የግሎቹ የተሻለ የመውጫ ፈተናውን ማሳለፍ የሚችሉበት እድል ይኖራቸው ነበር:: ነገር ግን እውነታው የተገላቢጦሽ ሆኖ፤ በዝቅተኛ ውጤት የማስመረቅ ልምድ ያላቸው የመንግስት ተቋማት ብዙ አሳልፈው፤ በከፍተኛ ውጤት በማስመረቅ የሚታወቁት የግሎቹ አነስተኛ ቁጥር ያለው ተመራቂን ነው የመውጫ ፈተናውን ማሳለፍ የቻሉት::

ይሄንን ሃሳቤን ለማጠናከር አንድ መረጃ ልጨምር ወደድኩ:: የእነዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ ኃላፊነት ተማሪዎችን በእውቀትም በክህሎትም መቅረጽ እና የፈጠራ አቅም ኖሯቸው እንዲወጡ ማስቻል ነው:: በዚህ በኩል የተሻለ ውጤት የሚመዘገብበት የትምህርት ተቋም የተሻለ የፈጠራ አቅም ያላቸውን ተማሪዎች የማውጣት እድል ይኖረዋል:: እንደ ኢትዮጵያ ያለው ሃቅ ግን ይሄ አይደለም::

ለምሳሌ፣ ከግንቦት 16 እስከ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም በቻይና ሼንዘን ከተማ በተካሄደው በ7ኛው የሁዋዌ ዓለም አቀፍ የአይሲቲ ፍጻሜ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉት እና እስከ ፍጻሜ ተጉዘው የሦስተኝነት ደረጃን አግኝተው የተመለሱት ተማሪዎች ከመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት(ከጎንደር፣ ዋቸሞ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች) ናቸው::

እነዚህ ተማሪዎች አገራቸውን ወክለው በዚህ ውድድር ለመሳተፍ የአገር ውስጥ ማጣሪያ ውድድሮችን በማለፍ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው ሶስት አባላት ያላቸው ሶስት ቡድን በመሆን የራሳቸውን የፈጠራ ሃሳብ ይዘው ተሳትፈዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ውድድሩ ከ36 አገሮች የተውጣጡ 146 ቡድኖች የተሳተፉበት ነው።

እነዚህ እና መሰል በምዘና ሂደት የተለዩ የእውቀትና ውጤት ተቃርኖዎችን የሚያሳዩት፤ እንደ ሀገር የገባንበት የትምህርት ሥርዓት ችግር ብዙ ዋጋ ያስከፈለን ስለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ በዚህ ሂደት ውስጥ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ድርሻቸው እስከምን እንደሆነም ያስገነዘበ ስለመሆኑ ነው:: እናም በተለይ የውጤት እና እውቀት ተቃርኖን ሊገራ የሚችል ስርዓት መዘርጋት በተለይም በግል ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ያለውን የመማር ማስተማር ሂደት በወጉ መፈተሽም፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግም እንደሚገባ ነው::

ማሙሻ ከአቡርሻ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *