የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደጉ ተግባር ቀጣይም፤ የወል ኃላፊነትም ይሁን!

ታዳጊዎች እና ወጣቶች ዕውቀትን ፈልገው ዘወትር ማልደው ወደ ደጆቻቸው የሚያቀኑባቸው ትምህርት ቤቶች፤ የተማሪዎቹን ፍላጎት አማክለው፣ መሻታቸውን ተገንዝበው እና ራሳቸውን በዛ ልክ አዘጋጅተው ሊጠብቁ፤ ተማሪዎቻቸውን ዕውቀት መግበውም ከምኞትና ሕልሞቻቸው ጋር ሊያገናኙ የተገባ ነው፡፡

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ወደ 239 ሺህ የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች በየእለቱ ተማሪዎቻቸውን ተቀብለው ያስተናግዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የእነዚህ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ ሂደት አውለው ከመላክ ተግባር የዘለለ ተደርጎ አይወሰድም የሚሉ አካላት አሉ፡፡

በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ጉባዔ ወቅትም የትምህርት ዘርፍን በሚመለከት በምክር ቤት አባላት ከተጠየቁ ጥያቄዎች መካከል፤ “ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ሲተገበር የተሟላ የመማሪያ መጽሐፍ አለመኖር፣ የትምህርት ግብዓት አለመሟላት፣ የቤተ ሙከራ የኬሚካል እጥረት፣ የቤተ ሙከራ መምህራን አለመኖር ችግሮች ናቸው። በ2016 ትምህርት ዘመን ችግሩ እንዳይቀጥል ምን ታስቧል?” ሲሉ መጠየቃቸውም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ትምህርት ሚኒስቴርም ቢሆን ይሄንን ሃቅ አልካደም፡፡ ይልቁንም በማስረጃ አስደግፎ የችግሩን ግዝፈት ዜጎች እንዲረዱት አደረገ እንጂ፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርቡ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ ካሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አብዛኞቹ ምቹ ያልሆኑ፤ ይልቁንም 99 በመቶዎቹ ለመማር ማስተማር ሂደት አመቺ አይደሉም፡፡

ሚኒስቴሩ በዚህ መረጃው እንዳመለከተው፣ ኢትዮጵያ ካሏት 239 ሺህ ገደማ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አራት ትምህርት ቤቶች ብቻ ከፍተኛውን ደረጃ አሟልተው የተገኙ ሲሆን፤ 99 በመቶዎቹ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን (የትምህርት ቤቶችን ደረጃን) ያሟሉ አይደሉም፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ 86 በመቶ የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ እንዲሁም 71 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፍፁም ከደረጃ በታች ናቸው። አንዳንዶቹም የዳስ ትምህርት ቤቶች፤ ሌሎችም የዛፍ ጥላ ስር መማሪያዎች ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ታዳጊዎችና ወጣቶች ትምህርትን ፈልገው የሚሄዱባቸው፤ ነገር ግን ውለው ከመግባት የዘለለ ትምህርት ሊማሩባቸው የማይችሉባቸው ስለመሆናቸው ዐቢይ ማረጋገጫ ነው፡፡

በመሆኑም ይሄንን ታሪክ መቀየር እና ትምህርት ቤቶች እንደ ስማቸው የመማር ማስተማር ሁነት የሚከወንባቸው አውዶች እንዲሆኑ ማስቻል ደግሞ ለነገ የሚተው ሳይሆን ዛሬ ያውም የመጀመሪያ ሥራ ተደርጎ ሊከወን የሚገባው ነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግስት ሥራውን ለመሥራት ብቻዬን ከሆንኩ ካለኝ አቅም አኳያ 30 ዓመታትን ይፈጅብኛል፤ ብሏል፡፡

እናም ይሄንን ሥራ በጋራ ተባብረን ልንሰራ፤ በነገው የልጆቻችን ሕልም እውን መሆን ላይ የየራሳችንን አሻራ ልናኖር ይገባል፤ በማለት “ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገራዊ የትምህርት ቤቶችን የማሳደግ ሥራን በንቅናቄ መልክ አስጀምሯል፡፡

ይሄ ንቅናቄ ደግሞ ለተወሰኑ አካላት ወይም ቡድኖችና ተቋማት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም የወል ተግባርና ተሳትፎ የሚሻ ነው፡፡ የአንድ ሰሞን ዘመቻም ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ሊከወን የሚገባው ነው፡፡

ምክንያቱም፣ ትውልድም እየበዛ፤ ፍላጎት እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ ይሄንን ቁጥርና ፍላጎት ማሟላት የሚችል የእውቀት አውድ ሆኖ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ደግሞ ከትምህርት ቤቶች የሚጠበቅ ነው፡፡ እነዚህን ትምህርት ቤቶች በግብዓት ማሟላት እና ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲገኙና ለትውልድ እውቀት መጋቢ እንዲሆኑ ማስቻልም የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ ይሻል፡፡

ምክንያቱም፣ ትምህርት ቤቶች መማሪያ መጻህፍት ይሻሉ፤ ቤተ መጻሕፍት ይፈልጋሉ፤ ተማሪዎቻቸውን በቤተ ሙከራዎቻቸው ማለማመድን ይናፍቃሉ፡፡ ተማሪዎቹም እነዚህን መሰረተ ልማቶች ከትምህርት ቤቶቻቸው ማግኘት፤ በተመቻቸ ክፍል ውስ ጥ ተቀምጠው መማርን ይመኛሉ፡፡

ከዳስ መውጣትን፣ ከዛፍ ጥላ መነሳትን፣ በድንጋይ ላይ ተቀምጦ ከመማር መላቀቅን፣ ጣራና ግድግዳቸው ከተሸነቋቆሩ ክፍሎች መውጣትን አብዝተው ይናፍቃሉ፡፡ የእነዚህን ታዳጊዎች ሕልም፤ የእነዚህን ወጣቶች ምኞች እውን እንዲሆን ማስቻል የሁሉም ዜጋ ተግባር ሊሆን፤ ያልተቆራረጠም ሂደት ኖሮት ሊከወን የሚገባው ነው፡፡

ልጆች እውቀትን ሽተው ትምህርት ቤት ሲገኙ የሻቱትን እውቀን እንዲቀስሙ ማስቻል፤ ትምህርት ቤቶችም ታዳጊዎችን በእውቀት፣ በክህሎትና በሥነምግባር አንጸው የሀገር ተስፋና ተረካቢ የሚሆን ሰብዕናን የሚያጎናጽፉበትን አቅም ማስታጠቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡

ምክንያቱም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሳደግ ሂደት ውስጥ የምናደርገው ተሳትፎ በልጆቻችን ነገ ላይ መሥራት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናና ልዕልና ላይ ዐሻራን ማሳረፍም ነው፡፡ ከዛሬ በተሻገረ ሕልም ነገን ብሩህ የማድረግ ምግባር ነው፡፡ በመሆኑም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደጉ ተግባር በዚሁ አግባብ ተጠናክሮ ሊቀጥልም፤ የወል ኃላፊነት ሊሆንም ይገባል!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *