የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አቅም የፈተሸበት የመውጫ ፈተና

የዘንድሮው ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና በብዙ መልኩ ከበፊቱ ይለያል:: ከዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው በሁሉም የትምህርት መስክ ለሚመረቁ ተማሪዎች ፈተናው መሰጠቱ ነው:: ከዚህ በፊት ፈተናው ለጤናና ለሕግ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ይሰጥ ነበር:: ውጤቱም በሥራ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል:: ተማሪዎችን ተወዳዳሪ አድርጓል:: እንደሀገር ብቁ ዜጎችን ለማፍራትም አስችሏል:: መውጫ ፈተናው በሌሎች ትምህርቶች ላይ ያለውን ችግር እንዲፈታ መተግበር አለበት በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ለሚወጡ የሁሉም ትምህርት ክፍሎች ተማሪዎች ተሰጥቷል::

መውጫ ፈተናው የተለያዩ መሪ ሀሳቦች ተገኝተውበት ለቀጣይ ተጨማሪ ሥራዎች አምጥቷል:: ከዚህ ውስጥ አንዱ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉበትን ደረጃ እንዲያዩ ማድረግ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ የትምህርት ክፍሎች ምን ያህል ተማሪዎቻቸውን እንዳገዙና እንዳበቁ የሚለኩበት ነው:: በተመሳሳይ የግልና የመንግሥት ተቋማት በምን ዓይነት ደረጃ ላይ እንደሚቀመጡ ለመለየት አግዟል::

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደሚናገሩት፣ መውጫ ፈተናው ከሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ቀናት ሲሰጥ ቆይቷል:: በዚህም እንደመንግሥት ተቋም ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል:: በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የሚታዩ ችግሮችም ተለይተዋል:: በተመሳሳይ በየትኛው የትምህርት መስክ ትልቅ ችግር እንዳለና ማሳለፍ ያልቻሉበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለመመልከትም ዕድል ሰጥቷል::

መውጫ ፈተናውን ይፈተናሉ ተብለው የተገመቱት 240 ሺህ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ ለፈተናው ብቁ ሆነው መመዝገብ የቻሉት ግን ከ48 ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ 84 ሺህ 627ቹ ናቸው:: 171 ከሚሆኑት የግል ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ደግሞ መመዝገብ የቻሉት 109 ሺ 612 ናቸው:: ከግልና ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የመውጫ ፈተናውን ለመውሰድ በድምሩ 194 ሺህ 239 ተማሪዎች ተመዝግበዋል::

ይሁንና የመውጫ ፈተናውን ለመውሰድ ከተመዘገቡት ውስጥ ፈተናውን የወሰዱ ተማሪዎች ቁጥር ቀንሷል:: ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች 77 ሺህ 981 ወይም 92 ነጥብ 15 ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን፤ ከግል ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ 72 ሺህ 203 ወይም 65 ነጥብ 87 በመቶ ያህሉ የመውጫ ፈተናውን ወስደዋል:: በድምሩ 150 ሺህ 184 ተማሪዎች ብቻ ፈተናውን ወስደዋል::

ሚኒስትር ዴኤታው እንደሚያብራሩት፣ ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለፈተና ከተቀመጡ ተማሪዎች ውስጥ 62 ነጥብ 37 በመቶ ከ 50 በላይ ወይም የማለፊያ ነጥብ አመጥተዋል:: ከግል ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ደግሞ 17 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ብቻ የማለፊያውን ነጥብ ማምጣት ችለዋል:: ይህም በግል ዩኒቨርሲቲዎች በኩል ላይ ብዙ ሥራ መሠራት እንዳለበት ያመላክታል:: ዩኒቨርሲቲዎቹ ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ለማፍራት ብዙ መሥራት እንዳለባቸውም ያስጠነቅቃል:: እንደ ትምህርት ሚኒስቴርም ከፍተኛ ክትትልና የድጋፍ ሥራ እንደሚጠይቅ ይጠቁማል::

የፈተና ውጤቱ ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችም ቢሆን ብዙ ነገሮችን ያመለክታቸዋል:: ከዚህ ውስጥ አንዱ የትምህርት ክፍሎች ያስመዘገቡት ውጤታማነት መለያየቱ ነው:: ሌላው ደግሞ ፈተናው ሀገር አቀፍ ቢሆንም በተማሪዎቻቸው ውጤት ምክንያት ዩኒቨርሲቲዎች ያስመዘገቡት ውጤት ልዩነት ማሳየቱ ነው:: ከ80 በመቶ በላይ ተማሪዎቹን ያሳለፈ ዩኒቨርሲቲ ቢኖርም ከ50 በታች ያሳለፈም ተገኝቷል:: በተመሳሳይ በትምህርት ክፍል ሲታይ ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎቹን ያሳለፈ ተገኝቷል:: ከ20 በመቶ በታች ያሳለፈም አለ:: ከዚህ አንፃር ውጤቱ በየአቅጣጫው ሁሉም መገምገም እንዳለበት ያሳየና ለቀጣይ ሥራ የሚያዘጋጅ ነው::

ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎች ያመጡትን ውጤት ልኮ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉበትን ደረጃ ለክተውና መርምረው እንዲሠሩበት እያደረገ ነው:: በዚህ ሳምንት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን ውጤት ልኮ ይጨርሳል::

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፣ ተማሪዎች ውጤታቸውን ለፈተናው የተሰጣቸውን User Name በመጠቀም https://result .ethernet.edu.et ሊንክ ውስጥ በመግባት ማወቅ ይችላሉ:: በተመሳሳይ ተማሪዎች በመውጫ ፈተናው ዛሬ የሚፈለገውን የማለፊያ ውጤት ያላስመዘገቡም ቀጣይ ዕድሎች አሏቸውና መዘጋጀት ይችላሉ:: ይህም ቅድመ ምሩቃን ተማሪዎች ፈተናውን በየስድስት ወሩ ደጋግመው እንዲወስዱ የተመቻቸው ዕድል ነው:: ዕድሉ ተማሪዎች ስህተታቸውን አውቀው አቅማቸውን ለማሳየት የሚጠቀሙበት መሆን ይገባዋል::

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ በተደረገውና በሁሉም ትምህርት መስኮች የሚሰጠው የዩኒቨርሲቲዎች መውጫ ፈተና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባሉት ስምንት ኮሌጆች፣ ሁለት ኢንስቲትዩቶችና አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ 73 የትምህርት ክፍሎችን ይሰጣል:: በነዚህ የትምህርት ክፍሎች የመውጫ ፈተናውን የወሰዱት በአጠቃላይ 3 ሺህ 089 ተማሪዎች ናቸው:: ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 2 ሺህ 760 89.35 ከመቶዎቹ ተፈታኞች በብቃት ፈተናውን ማለፍ ችለዋል። ፈተናውን ከወሰዱ 73 ትምህርት ክፍሎች መካከል ደግሞ 34 ትምህርት ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸውን አሳልፈዋል::

ከአጠቃላይ ተፈታኞች መካከል በመደበኛ መርሐግብር ዩኒቨርሲቲው ካስፈተናቸው 2 ሺህ 919 ተማሪዎች 2 ሺህ 703 ወይም 92.6 በመቶ ያለፉ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 170 ተማሪዎች በተከታታይ መርሐግብር ተፈትነው 57 ወይም 33.53 በመቶዎቹ ፈተናውን ያለፉ ናቸው:: ይሁንና በተገኘው ስኬት መኩራራት ሳይሆን የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል:: ውጤቱ አበረታች ቢሆንም ለቀጣይ ትልቅ ኃላፊነትን የሚሰጥም እንደሆነ ተገልጿል::

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን እንደሚሉት፣ ውጤቱ የመጣው በብዙ ሥራና ልፋት ነው:: ለአብነት ሰላም ላይ መሠራቱ የውጤቱ አንዱ ማሳያ ነው:: በተለይ ተማሪዎች ሰላም ተሰምቷቸው፤ ተረጋግተው እንዲያነቡና እንዲዘጋጁ ከማድረግ አኳያ ዩኒቨርሲቲው የፈጠረው ‹‹የጎንደር የቃልኪዳን ቤተሰብ›› የተሰኘው ቤተሰብ ለውጤቱ ማማር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል:: ቤተሰቡ የጎንደር ማኅበረሰብ ተማሪዎች ነፃነት እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል:: ተማሪዎችም ለተሰጡት ቤተሰብ የፈለጋቸውን ጥያቄ መጠየቅ ይችላሉ:: ተማሪዎች እናትና አባታቸው ጋር ሆነው የመማር ያህል ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል:: ይህ ደግሞ ተማሪዎች የሚሰጣቸውን ትምህርት በአግባቡ እንዲከታተሉ አግዟቸዋል:: በፈተናው ውጤታማ ለመሆንም አስችሏቸዋል::

ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ከገቡበት ቀን ጀምሮ ትምህርት በአግባቡ እንዲሰጣቸውና ጠንከር ያሉ ፈተናዎችን እንዲወስዱ ማድረጉም ለመጣው ውጤት የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል:: የተማሪዎች ዝግጅት ከመነሻው የተመቻቸ መሆኑና ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረው የመውጫ ፈተና አካሂዱን ተረድቶ ለመጓዝ ግንዛቤ በመወሰዱ እንደዩኒቨርሲቲ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል::

ፕሬዚዳንቱ እንደሚገልፁት፣ በትምህርታቸው ደከም ላሉና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች ተደጋጋሚ ቲቶሪያል መሰጠቱ፤ የትምህርት ሚኒስቴር ብሉ ፕሪንት ከላከበት ጀምሮ ፈተና በማውጣትና ትምህርቱ በዚያ መስፈርት መስጠት መቻሉ፤ ተማሪዎች የሥነልቦና ችግር እንዳያጋጥማቸው ዝግጁ የሚሆኑበትን ሥልጠና በባለሙያዎች ጭምር እንዲሰጣቸው መድረጉና ፈተናው የሚሰጠው ቴክኖሎጂን በመጠቀም በመሆኑ ተማሪዎች ችግር እንዳያጋጥማቸው ሥልጠና የሚወስዱበትን ሁኔታ በማመቻቸቱም ውጤት ለማስመዝገብ አስችሏል::

ዩኒቨርሲቲው እንደሀገርና እንደመንግሥት ተቋም ጥሩ ውጤት ቢያስመዘግብም አሁንም በርካታ ክፍተቶችን መሙላት ይጠበቅበታል:: ሁሉም የትምህርት ክፍሎችና ኮሌጆች ተመሳሳይ ውጤት ማምጣት ስላልቻሉ ክፍተታቸውን እያዩ መሙላት ይኖርባቸዋል:: በሌላ በኩል ውጤቱ በትንተና ችግሮቹ ሊለዩለት ይገባል:: ይህ ደግሞ ለዩኒቨርሲቲው ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ተሞክሮ ይሆናል:: በቀጣይም ይህ ተግባር እንደሚከናወን ይሆናል:: የማሻሻያ ሥራዎች ልዩ ትኩረት እንዲያገኙም ይደረጋል::

እንደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበበት ትምህርት ክፍል አካውንቲንግ ነው:: ምክንያቱ ደግሞ ፈተናው ከብሉፕሪንቱ ውጪ በመውጣቱ የተፈጠረ ችግር ነው:: በዚሁ መነሻነት ለትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርበናል:: ከዚህ አኳያ የሚለይ ውጤት ይመጣል ተብሎ ይገመታል:: የትምህርት ጥራት በአንድ ጀንበር የሚመጣ አይደለምና በየጊዜው የተሻለ ተማሪ ማፍራት ላይ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ጠንክረው ሊሠሩ ይገባል:: የተጀመረውን የለውጥ ሥራ አምነውበት ለውጤታማነቱ የተቻላቸውን ማድረግ ይኖርባቸዋል::

የትምህርት ሚኒስቴር በፌስቡክ ገፁ የተማሪዎችን የማሳለፍ ምጣኔ በመቶኛ ይፋ ባደረገበት ዝርዝር ውስጥ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ይገኛል:: ይህ ዩኒቨርሲቲ እንደ ጎንደር ከፍተኛ ውጤት አላስመዘገበም:: ተማሪዎችን የማሳለፍ ምጣኔው ከ50 በመቶ በታች ነው:: ይህም ማለት ያለፉት ተማሪዎች 41 በመቶ ብቻ ናቸው:: ዩኒቨርሲቲውም ይህንን ውጤት አምኖ ተቀብሏል:: አሁን የታየው ውጤት ሞዴል ላይ ከነበረው የፈተና ውጤት ጋር ተቀራራቢ እንደሆነም አምኗል::

በዩኒቨርሲቲው የሦስት አካዳሚክ ፕሮግራም ተፈታኞች ሙሉ በሙሉ ፈተናውን ማለፍ አልቻሉም:: የመውጫ ፈተናውን ውጤት ከወዲሁ ገምቶታል:: በዚህም በቀጣይ ጠንካራ ሥራዎችን ሠርቶ ውጤቱን የማሻሻል ፍላጎት አለው:: የዚህ ችግር ክስተት መንስኤም በዋናነት ፈተናው ከየትኛውም ስርቆት እና ኩረጃ ነፃ በሆነ መንገድ ስለተሰጠ መሆኑን አረጋግጧል::

በዚሁ መነሻነት ዩኒቨርሲቲው ለተሻለ ውጤት እንደሚሠራ ገልጿል:: ለዚህ ደግሞ የተቋሙ ማኔጅመት የተመዘገበውን ከግማሽ በታች ውጤት ተቀብሎ፤ እውነተኛ ችግር መሆኑን አምኖ ውጤቱ ዝቅተኛ የሆነበትን ምክንያት ለይቶ ለመሥራት ኮሚቴ እንዲዋቀር ወስኗል። ኮሚቴው የችግሩ መነሻዎችና ችግሩ ያደረሰውን ጉዳት በማጥናት ምክረ ሃሳቦችን ያቀርባል:: ከዚያ ዩኒቨርሲቲው ይህንን ምክረሀሳብ በመያዝ ውጤቱን ለማሻሻል ይተጋል::

 ጽጌረዳ ጫንያለው

ዘመን ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *