የተማረ ኃይል ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ መተኪያ የሌለው ነው። ከዚህ የተነሳም ሀገራት ዘመኑን የሚዋጅ የተማረ ኃይል ለመፍጠር ከፍተኛ ሀብት ያፈሳሉ። የትምህርት መሠረተ ልማቶችን ጨምሮ ውጤታማ የሰው ኃይል በማሠልጠን ይተጋሉ። የትምህርት ሥርዓታቸውም ፍሬያማ መሆኑን ትኩረት ሰጥተው በየጊዜው ይመረምራሉ።
ወላጆችም እንደ ሀገር ለትምህርት ከተሰጠው ትኩረት ባለፈ፤ ልጆቻቸው የተሻለ ትምህርት አግኝተው ነገዎቻቸው ብሩህ እንዲሆኑ፤ ከራሳቸውም አልፈው፣ ለቤተሰባቸው፣ ለማኅበረሰባቸው እና ለሀገራቸው ተስፋ ብቁ ዜጎች ሆነው እንዲገኙ ባላቸው አቅም ሁሉ፤ ማድረግ አለብኝ የሚሉትን ሲያደርጉ ማየት የተለመደ፤ ትልቅ የቤተሰብ ኃላፊነት ተደርጎ የሚወሰድ ጉዳይ ነው።
ይህ በወላጆች ላይ የሚታየው ኃላፊነት የልጆችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ፤ ልጆች በትምህርቱ ዓለም ሊኖራቸው ለሚችለው ስኬታማነት ትልቅ አቅም ነው። ከዚህም የተነሳ የወላጆች አበርክቶ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ፤ ሊያስከፍላቸው የሚችለውም ዋጋ ከፍ ያለ እንደሚሆን ይታመናል።
መምህራንም ቢሆኑ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ካላቸው ማዕከላዊ ቦታ አንጻር፤ ተማሪዎቻቸውን ለውጤት ለማብቃት፤ በሚገኘውም ውጤት ለመርካት ፤ ብቁ ትውልድ በመፍጠር ሀገራዊ ነገዎችን ባለተስፋ ለማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። የዕውቀት አባት ከመሆናቸው አንጻርም ያለባቸው ኃላፊነት ከባድ፤ ብዙ ዋጋ መክፈልንም የሚጠይቅ ነው።
ተማሪውም ከራሱ ሆነ የመገኘት መሻት ባለፈ፤ ለቤተሰቡ ፣ ለማኅበረሰቡ እና የሀገሩ ሆኖ እንዲገኝ የሚጠበቅበትን ሆኖ ለመገኘት፤ ትምህርቱን ጀምሮ እስኪጨርስ የሚሄድበት በውጣ ውረድ የተሞላ መንገድ ፤ የዓላማ ጽናትን እና ከዚህ የሚመነጭ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ነው። ነገዎችን በተስፋ እያዩ ዛሬ የሚጠይቀውን ሁሉ ዋጋ መክፈልንም የሚፈልግ ነው።
በአንድ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሚያልፍ ዜጋ ውጤታማነት ፤ በአጋጣሚ ወይም በቀላሉ የሚገኝ ሳይሆን ፤ የብዙ አካላትን የጋራ ድካም፤ የባለቤቱን ምጥ የሚጠይቅ ትልቅ ማኅበራዊ ስኬት ነው። ለዚህም ነው አንድ ተማሪ ሲመረቅ ደስታውን ብዙዎች የሚጋሩት፤ በደስታውም ደስተኞች የሚሆኑት።
አስተማሪዎቹ፤ ያስተማረው ተቋም፤ የጉረቤት፣ የሰፈር ሰው ሁሉም የደስታው ተካፋይ በመሆን «እንኳን አደረሰህ ለዚህች ቀን» የሚሉት፤ ቀኗ ምን ያህል በውድ ዋጋ እንደተገዛች ስለሚረዱ፤ ከዚያም በላይ ተስፋ ያደረጋቸው ቀናቶች ለእሱ እና ለቤተሰቡ ፤ ለሀገሩ እና ለወገኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቅርብ ሆነው መገኘታቸውን ለማብሰር ነው።
አሁን አሁን ይህ እውነታ መልኩን እየቀየረ፤ ለትምህርት፣ ለተማሪ እና ለምረቃ የሚሰጠው ግምት አሳንሶታል ፤ የትምህርት ስኬቱ እንደጉሊት ሸቀጥ በየገበያው መቸርቸር መጀመሩ እና ለረጅም ጊዜ ሀይ ባይ አጥቶ መቆየቱ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ድካምና ልፋት ከንቱ አድርጎታል።
ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣው ሕገወጥ የትምህርት ማስረጃ ጉዳይም ሆነ ያለ በቂ ዕውቀት የሚታደለው የትምህርት ማስረጃ፤ ትምህርት ለአንድ ሀገር ነገዎች ብሩህነት የነበረውን ሁለንተናዊ አቅም አዳክሞታል። ይህ ሀገራዊ ችግር ከሁሉም ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሠራ የሚገባው ዋናው የቤት ሥራችን ነው ።
ይህ በማይሆንበት ሁኔታ ዛሬ ላይ ብዙ ዋጋ ተከፍሎባቸው እና ከፍለው እየተመረቁ ያሉ ዜጎቻችን ምረቃ የተሟላ ትርጉም የሚኖረው፤ ይዘውት የመጡት፤ ቤተሰቦቻቸው እና ሀገር በእነርሱ ተስፋ ያደረጓቸው ነገዎች ተጨባጭ የሚሆኑት ሕገወጥነትን ከትምህርት ሥርዓቱ ማጥራት ሲቻል ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ለነገ የማይባል የዛሬ ትልቁ ሥራችን ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም