የኢትዮ ቴሌኮም ስኬታማ አፈፃፀም

የተቋማት ስኬት የሀገር እድገትን ከሚያረጋግጡ ዋና ምሰሶዎች ውስጥ ይመደባል። በመንግሥትም ይሁን በግል ኩባንያዎች የሚመሩ ተቋማት የሚያስመዘግቡት እድገት እንዲሁም የሚሰጡት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በጥቅል የሀገርን ብልፅግና ያሳካል።

ተቋማቱ ከሁሉም በላይ ለዜጎች የኑሮ ውጣ ውረድን በማቅለል ፍላጎትን ከማርካታቸው ባሻገር የኩራት ምንጭና የስኬታማነት ምሳሌ ይሆናሉ። በኢትዮጵያም ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ ጥቂት ተቋማትን ማንሳት እንችላለን። በመንግሥት ከሚተዳደሩት ውስጥ ረዘም ላሉ ዘመናት የኢትዮጵያ ምልክት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮምና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በልማት ድርጅትነት ከሚያስተዳድራቸውና ስኬትን እያስመዘገቡ ከሚገኙ ተቋማት መካከል አንዱ ኢትዮ ቴሌኮም ነው። ይህ ተቋም በፍጥነት እያደገ የሚገኝና በቴሌኮምና በፋይናንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማሟላት ስኬታማ ጉዞ እያደረገ ያለ ግዙፍ ኩባንያ ነው። ለዚህ እንደ ማሳያ የሚሆነው በየዓመቱ በገቢና በሁለንተናዊ ተቋማዊ እድገት እያስመዘገበ የሚገኘው ስኬት ነው። ይህንን ጉዳይ በዝርዝር ለመረዳት እንዲያስችለን የዝግጅት ክፍላችን በኢትዮ ቴሌኮም የ2015 ዓ.ም አመታዊ አፈፃፀም ላይ ትኩረቱን አድርጎ የስኬት ጉዞውን ለመቃኘት ወድዷል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ እንደሚሉት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የቴሌኮም ኢንዱስትሪው ለሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት ለማስቻል እንዲሁም በቴሌኮም ውድድር ገበያው የመሪነት ሚናውን እያጠናከረ ለማስቀጠል የሚያስችለውን የሦስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂ ነድፏል።

የትኩረት አቅጣጫና የስትራቴጂ መስኮችን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ዝርዝር ስትራቴጂያዊ ግቦችን ቀርፆ ግቦቹን ሊያሳኩ የሚችሉ እርምጃዎችና ተግባራትን በማቀድ ከ2015 በጀት ዓመት አንስቶ ትግበራውን እንደ ጀመረ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ይናገራሉ።

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ እንዳሉት፤ ኩባንያው እያደገ ያለውን የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎትን ማዕከል በማድረግ ደንበኞቹን በማርካት ፈጣንና ተለዋዋጭ በሆነው የቴሌኮም ገበያ ብቁና ተመራጭ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለመሆን በትጋት እየሠራ ይገኛል። በዚህም የተለያዩ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

2015 የገቢ አፈፃፀም ስኬቶች

«በበጀት ዓመቱ ኩባንያችን የገቢ ምንጮችን በማስፋት በዋናነት ከመሠረታዊ ቴሌኮም አገልግሎቶች ጋር ያሉ በርካታ ተቋማትና አጠቃላይ ደንበኞችን ማዕከል ያደረጉ የዲጂታል መፍትሔዎች፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ እንዲሁም የኔትወርክና የሲስተም አቅምን በማሳደግ 75 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 101 በመቶ አሳክቷል» ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ይህ ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ23 ነጥብ5 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ይናገራሉ።

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ፤ የተገኘው ገቢ በአገልግሎት ዓይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 43 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ ሲኖረው ዳታና ኢንተርኔት 26 ነጥብ ስድስት በመቶ ዓለም አቀፍ ገቢ 9 በመቶ፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች 6 ነጥብ9፣ የቴሌኮም መጠቀሚያ መሣሪያዎች (ቀፎ፣ ዶንግል፣ ሞደም) 4 ነጥብ 7 በመቶ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 7 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ አላቸው። የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች (ዓለም አቀፍ ኢንተርኮኔክት፣ ሮሚንግ፣ ከመሠረተ ልማት ኪራይ እና ከሀዋላ አገልግሎት) በአጠቃላይ 164 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት የተቻለ ሲሆን፣ አፈጻጸሙም 107 ነጥብ 8 በመቶ መሆኑን ወይዘሪት ፍሬህይወት ገልፀዋል።

«የገቢ እድገቱ የተመዘገበው በሁሉም አገልግሎቶች ላይ የተስተናገደ የትራፊክ መጠን በመጨመሩ ነው» የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በድምጽ ትራፊክ የ34 ነጥብ 5 በመቶ እና በዳታ ትራፊክ 94 ነጥብ 5 እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል። የተጣራ ትርፍን 22 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ክንውኑ 25 በመቶ ሲሆን፣ የትርፍ መጠን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ109 በመቶ እድት ማሳየቱን ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ይፋ አድርገዋል።

ስኬት- ተጠቃሚ ደንበኞች

ወይዘሪት ፍሬ ህይወት ተጠቃሚ ደንበኞችን በሚመለከት ኩባንያቸው ያስመዘገበውን ስኬት አስመልክተው ሲናገሩ፤ በበጀት ዓመቱ የአገልግሎቶች ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 72 ሚሊዮን መድረሱን ይፋ አድርገዋል። ይህም ካለፈው በጀት አመት ጋር ሲነጻጸር የ8 በመቶ እድገት፤ እንዲሁም ከእቅድ አንጻር የ98 በመቶ ስኬታማ አፈፃፀም መመዝገቡን ነው ያነሱት። በአገልግሎት ዓይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 69 ነጥብ 5 ሚሊዮን፤ የመደበኛ ብሮድባንድ (Fixed Broadband) 618 ነጥብ 3 ሺህ፤ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 53 ነጥብ 6 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 33 ነጥብ 9 ሚሊዮን ናቸው ብለዋል። የቴሌኮም ስርጸት (teledensity) መጠን 66 ነጥብ 8 መሆኑንም ነው ያመለከቱት። ዓለም ላይ ካሉ 774 ኦፕሬተሮች መካከል በሞባይል ደንበኛ ቁጥር ኩባንያው በአፍሪካ 2ኛ ደረጃ እንዲሁም በዓለም 21ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

«የተመዘገበው የገቢና የተጠቃሚ ደንበኛ አፈጻጸም እጅግ የላቀ ነው» የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ውጤቱ የተመዘገበው የደንበኞችን ቁጥርና አጠቃቀምን ለማሳደግ፣ ተሞክሯቸውን ለማሻሻል እንዲሁም ደንበኞችን ለማቆየት የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያ፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም የደንበኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ወቅታዊነትን የተላበሱ 203 (116 አዳዲስ እና 87 ነባር የሆነ ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን በማሻሻል ለደንበኞች ማቅረብ በመቻሉ እንደሆነ ዘርዝረዋል።

የዲጂታል ፋይናንስ ስኬቶች

«የሀገራችንን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ፍላጎትን ለማርካትና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ታስቦ የቴሌ ብር አገልግሎት ተጀምሯል» የሚሉት ወይዘሪት ፍሬህይወት፤ በዚህም ከ34 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ማፍራትና አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ የግብይት መጠኑም 679 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማንቀሳቀስ እንደተቻለ ገልፀዋል። የቴሌብር የዲጂታል ሥርዓት የፋይናንስ አካታችነትን እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቴሌብር ሳንዱቅ፣ ቴሌብር እንደኪሴ፣ ቴሌብር መላ የተሰኙ የቴሌብር የፋይናንስ አገልግሎቶችን ከአጋሮቹ ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም የላቀ ስኬት መመዝገቡን ነው ይፋ ያደረጉት።

የሰው ኃይል ካፒታል ሥራዎች

«ኩባንያችን የነደፈውን ስትራቴጂና ዓመታዊ እቅድ በብቃት ለመፈጸም እና ግቡን ለማሳካት በአመለካከት፣ በክህሎትና በብቃት የተገነባ አሠራርና ሠራተኛ መኖር ቅድሚያ የሚሰጠውና ቀጣይነት ባለው መልኩ በትኩረት እየሠራበት ያለ ቁልፍ ጉዳይ ነው» የሚሉት ወይዘሪት ፍሬህይወት፤ የኩባንያው የማስፈፀምና የመፈጸም አቅምን በማጎልበት ቀጣይነት ያለው እድገትን ለማረጋገጥ የሰው ኃይሉን በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም የሥራ ባህል ከማነጽ አኳያ ተከታታይነት ያለው ስልጠና በአካል ከ17 ነጥብ 8 ሺህ በላይ እና በዲጂታል አማራጭ ከ22 ነጥብ 8 ሺህ በላይ ሠራተኞች ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን ገልፀዋል።

ማህበራዊ ኃላፊነት

ኩባንያው ከተቋቋመለት የቢዝነስ ዓላማ በተጨማሪ ማህበራዊ ፋይዳ ባላቸው ዘርፈ ብዙ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ የበኩሉን መልካም ዐሻራ እያሳረፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም የረጅም ጊዜ ልማት ተጠቃሚነትን ማጠናከር በሚችሉ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት እና ማስዋብ በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ለትምህርት፣ ለጤና፤ ለሰብአዊ ድጋፍ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአረንጓዴ ልማትና ማስዋብ እና ለመንግሥት ፕሮጀክቶች በበጀት አመቱ በድምሩ ከ439 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ የተደረገ ሲሆን፣ በዓይነትና በአገልግሎት (200 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር) እና በገንዘብ (229 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር) ድጋፍ ተደርጓል።

ኩባንያው ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሠራተኞቹ በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፤ ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል።

ተግዳሮቶችና የመፍትሔ እርምጃዎች

እንደ ወይዘሪት ፍሬ ህይወት ገለፃ፤ ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥ፤ በወቅቱ የጥገናና የማስፋፊያ ወይም የማሻሻያ ሥራዎች ማከናወን አለመቻል፤ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት፣ በኔትዎርክ ሀብትና በተቋም ንብረት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች እንዲሁም የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፤ የመሬት አቅርቦት መዘግየት፤ የቴሌኮም ማጭበርበር፣ የነዳጅ እጥረት፣ የግንባታ ሥራ ግብአቶች እጥረት፣ የገበያ አለመረጋጋት እንዲሁም የኮንትራክተሮች በውላቸው መሠረት የመፈጸም አቅም ውስንነት በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው። ችግሮቹን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ እንዲሁም የተለያዩ የቢዝነስና የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመውሰድ የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ መቀነስ መቻሉን ነው የተናገሩት።

ለተመዘገበው ስኬት ቁልፍ ሚና የነበራቸው ጉዳዮች

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገለጻ፤ ኢትዮ ቴሌኮም ላስመዘገበው ስኬት በተለይም በውድድር ገበያና ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ በማለፍ በዋና ዋና የአፈጻጸም መለኪያዎች የተመዘገበው ውጤት ለበለጠ ስኬት የሚያነሳሳና የኩባንያውን የመፈጸም አቅምና የገበያው እምቅ አቅም ሰፊ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ይህ የላቀ ውጤት የተመዘገበው የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ከኩባንያው አመራር ጋር በመናበብና በመደጋገፍ፣ የኩባንያው አመራርና ሠራተኞች ለኩባንያቸው ያላቸው የባለቤትነት ስሜትና በውድድር ገበያው በሁሉም መስክ የመሪነት ሚናውን ለማስቀጠል ካላቸው ህልም፣ ለውጤታማነቱ ባሳዩት ቁርጠኝነት እንዲሁም በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናትና በአግባቡ በመወጣት ላቀዷቸው ግቦች መሳካት ባደረጉት ያልተቆጠበ ጥረትና ሰፊ ርብርብ ነው።

በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም ለውድድርና ለእድገት የሚያበቃውን ግልጽ የሆነ ራዕይና ተልዕኮ በመቅረጽና ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ በመንደፍ የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላትን የዓላማው ተጋሪ ማድረጉ፣ የወጭ ቁጠባ አሠራርና ባህል በማዳበሩ፤ ፈጣንና ውጤትን ያማከለ በጥናት የተደገፈ ውሳኔ የመውሰድ ባህል ማዳበሩ፣ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋሉ፣ ከቢዝነስ አጋሮችና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ተናቦ በትብብር መሥራቱ፣ ኩባንያው ያሉትን የተለያዩ እምቅ አቅሞች (ሰፊ የኔትወርክና የሲስተም መሠረተ ልማት፣ የአገልግሎት ተደራሽነት፣ ሰፊ የቢዝነስ ኢጋሮችና የአገልግሎት ማዕከላት፤ የአሠራር ሥርዓት፤ ሥራ ልምድና ክህሎት፣ ያለውን ሠራተኛ እንዲሁም ታማኝ ደንበኞቻችን/ መጠቀም መቻሉ ለተመዘበው ውጤት ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ወይዘሪት ፍሬ ህይወት ለሁሉም የመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *