ኢትዮጵያዊው የአጥቂዎች አውራ ያልተጠበቀ ስንብት

‹‹በጨዋነት ምሳሌ ሆነህ የተገኘህ የሀገራችንም ባለውለታ አጥቂ ነበርክ። ‘መረብ ወጣሪ’ ብለን የጨፈርንልህ በወሳኝ ቀናት በሰራሀቸው አስደናቂ ታሪኮች ምክንያት ነው›› ረጅም ዓመት ያገለገለው ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድ ተጫዋቹን ስንብት ተከትሎ በማህበራዊ ገጹ ያሰፈረው ሃሳብ ነው። ፍጥነትን ከጉልበት እንዲሁም ከድፍረት አጣምሮ የያዘው የፊት መስመር አይምሬ የጎል ጨራሽ እነ ሆ ጫማ መስቀሉን አስታውቋል፡፡

በሜዳ ላይ ድንቅ ችሎታውን በማሳየት የደጋፊዎችን ልብ በአስደናቂ አጨዋወቱና አጨራረሱ የማረከው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ሳልሃዲን ሰዒድ በመጨረሻም ከሚወደው እግር ኳስ መለየቱን ከትናንት በስቲያ በይፋ አስታውቋል።በሁለት አስርት ዓመታት የእግርኳስ ህይወቱ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስከ አፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ በፊት አውራሪነት ማገልገል ችሏል። በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም የማይረሱ እና ብዙዎችን ያስፈነደቁ ታሪካዊ ግቦችን አስቆጥሯል።

አስፈሪው አጥቂ ግን ደግሞ ቁጥቡ ተጫዋች ሳልሃዲን ሰዒድ የእግር ኳስ ህይወቱን ከቤተሰቡ የወረሰ ሲሆን፤ ኮከብ የመሆን ጉዞውን በ13 ዓመቱ ፕሮጀክትን በመቀላቀል ነበር የጀመረው። ተስፋውን የተመለከተው ሙገር ሲሚንቶ ክለብ ‹‹ቢ›› ቡድኑ ውስጥ መቀላቀሉን ተከትሎም ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ተዋውቋል።ከጅምሩ ልዩ ችሎታው ግቦችን በማስቆጠር ቢያስመሰክርም ለኮከብ ተጫዋችነት የሚደረገው ጉዞ ግን በፈተና የታጀበ ነበር።እንደ ወጣት ተጫዋች ፍጥነቱን፣ ቅልጥፍናውን እና ጥሩ የኳስ ቁጥጥሩ ተመልካቾች በአድናቆት እንዲመለከቱት አድርጓል።

የቀድሞ አስደናቂ ወጣት የአሁኑ አንጋፋ የእግር ኳስ ኮከብ በአገር ውስጥ ለሶስት ክለቦች መጫወት ችሏል። ለትልቅ ደረጃ ያንደረደሩትን ስኬቶች የተቀዳጀበት ታሪካዊው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲሆን፤ ከ1998-2004 ዓ.ም ቆይታው 112 ጨዋታዎችን አድርጎ 41 ግቦችን አስቆጥሯል። ከክለቡ ተለያይቶ በድጋሚ ከ2008-2013 ዓ.ም ድረስ በመጫወትም 15 ግቦችን አስቆጥሯል። በፈረሰኞቹ ቤት በነበረው የማይዘነጉ የ12 ዓመታት ቆይታም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በ2001፣ 2002፣ 2008 እና 2009 ዓ.ም አንስቷል። በ2000 ደግሞ በ21 ግቦች የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብርንም ተቀዳጅቷል። በ2009 ቡድኑ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ረጅም ጉዞ ሲያደርግ ወሳኝ ግልጋሎት ማበርከት ችሏል። በዚህም በአፍሪካ የሚጫወቱ ምርጥ ተጫዋቾች ሽልማት 30 እጩዎች ውስጥ በመግባቱ ታሪኩን በደማቅ ብዕር ከትቧል። በዚህም ‹‹መረብ ወጣሪ›› የሚል ቅጽል አግኝቷል።

ለጅማ አባ ጅፋር እና ለሲዳማ ቡና ክለቦችም የተጫወተው ሳላሀዲን ከሀገር ውስጥ ስኬቶቹ ባለፈ በፕሮፌሽናል ደረጃ ለመጫወት ወደ ውጭ ክለቦች አምርቷል። በስድስት ዓመታትም ለግብጹ አል-አህሊ እና ዋዲ ዳግላ፣ ለአልጄሪያው ኤምሲ አልጀርስ እንዲሁም ወደ አውሮፓ በማቅናት ለቤልጂየሙ ሊርስ ተጫውቷል።

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋሊያዎቹም የጎላ ተሳትፎ የነበረው ተጫዋቹ ቡድኑን ወክሎ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ተከላካዮችን በመረበሽ እና የሚያገኛቸውን ኳሶች ሳያባክን ወደ ጎል በመቀየር ለብዙ ድሎች አስተዋጽኦ ያደረገ ቁልፍ ተጫዋች ነው። በ2005 ዓ.ም ብሄራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ በመመለስ ዋነኛው ተዋናይ ነበር። በመጨረሻው የሱዳን ጨዋታም ወርቃማ የሆነች ጎል በማስቆጠር በአዲስ አበባ ስታዲየም በጭንቀት ጨዋታውን ሲከታተል የነበረውን ደጋፊ ጮቤ አስረግጧል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለብራዚሉ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎችን አድርጎ ማለፍ ባይችልም ሳለሃዲን ቡድኑን በወኔ እየመራ ግቦችን በማስቆጠር ከምርጥ አስር የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ተርታ እንድትሰለፍ አስተዋጽኦ ማበርከት ችሏል። ለብሄራዊ ቡድኑ በ28 ጨዋታዎች ተሰልፎ 14 ግቦችንም ማስቆጠር ችሏል።

በተለያዩ ክለቦች እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግልጋሎት የሰጠው አጥቂው በተደጋጋሚ የሚያስተናግደው ጉዳት የእግር ኳስ ህይወቱን ፈታኝ ሲያደርግበት ቆይቷል። ሆኖም ሳልሃዲን በሜዳ ላይ የሚያሳየው ብቃት እና ሁለገብነቱ ከሌሎች ተጫዋቾች ልዩ አድርጎታል።እንደ አጥቂ ወይም የአጥቂ አማካይ ሆኖ ከተለያዩ ቦታዎች በመነሳት መጫወቱ ለአሰልጣኞች ተገማች የማይሆን የአጨዋወት ስልቶችን እንዲተገብሩ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርም ችሏል። ሜዳ ውስጥ መሮጥ የማይደክመው፣ ፈጣኑ፣ ጉልበተኛው እና ደፋሩ ተጫዋች የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችን በበላይነት በማሸነፍ ተወዳዳሪ የለውም። በግብ ሳጥን ውስጥ ቀድሞ በመገኘትና ከርቀት ኳሶችን በፍጥነት ገፍቶ በመሄድ ድንቅ ግቦችን ያስቆጥራል። የተቃራኒ ቡድን ተከላካዮች እሱን ለማቆም ቢሞክሩም ወኔ አንሷቸዉ ሲፍረከረኩም ተስተውሏል።

ሳላሀዲን ሰኢድ በእግር ኳስ ስኬቶቹ በተለይ በኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ የእግር ኳስ ተጫዋቾች መነሳሳት ምክንያት ነው። ረጅሙ የእግር ኳስ ህይወቱ ልዩ ችሎታ እና አስደናቂ የስኬት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ለእግር ኳስ እራስን የመስጠት እና በተግባር እግር ኳስን የመኖር ማሳያም ነው። በሜዳ ላይ ያሳየው ድንቅ ብቃት ለእግር ኳስ ካለው ወሰን የለሽ ፍቅር ጋር ተዳምሮ በእግር ኳስ አፍቃሪዎች ላይ የማይረሳ አሻራን ጥሏል። ታታሪነቱ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ለሚሹ አዳዲስ ተጨዋቾች ብርታት እንደሚሆንም ጥር ጥር የለውም። በተለያዩ ክለቦች እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግልጋሎት የሰጠው አንጋፋው አጥቂ ራሱን ከእግር ኳስ ማግለሉን ማሳወቁ በስፖርት ቤተሰቡ ድንጋጤን ጭሯል። ከ2000 ዓ.ም ወዲህ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከታዩ ምርጥ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው ሳለሃዲን ከሁለት አስርት ዓመታት የእግር ኳስ ቆይታ በኋላ ጫማውን መስቀሉን ይፋ እስካደረገበት ጊዜ ድረስ የሲዳማ ቡና ተጫዋች ነበር።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *