ሁላችንም የየትምህርት ቤቶቻችንና ያሳደገን ማህበረሰብ ዕዳ አለብን፤

 እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን ከተማርንበት ትምህርት ቤትም ሆነ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ድርሽ ትሉና ተብለን የተባረርን፤ ከትምህርት ቤታችን ጋር ተጣልተንና ተቆራርጠን አይንህን ለአፈር ተባብለን ዳግም ላለመመለስ ድንጋይ ወርውረን የወጣን ይመስላል። ባደኩባት የፍኖተ ሰላም ከተማ የ1ኛና የመለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት ወይም ከ1 እስከ 8 የተማርኩት ከቤታችን ፊት ለፊት መንገድ ተሻግሮ በሚገኘው የፍ/ሰላም 1ኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ነው። በጣፋጩ የልጅነት ህይወቴ ልዩ ቦታ ያለው፤ በትዝታ ዛሬም እየመነዘርኩ የምኖረው የማንነቴ መሠረት ነው። በፈረቃ ቢሆንም የተማርነው ለቤታችን ቅርብ ስለሆነ የጧት ፈረቃ ከሆንኩ ከጓደኞቼ ጋር ለጨዋታ ከሰዓት፣ የከሰዓት ከሆንኩ ጧት ት/ቤት መሔዴ አይቀርም።

አንዳንድ ጊዜ የጧት ፈረቃ ሆነን 6:15 እንደተለቀቅን ወደቤት ከመሄድ ይልቅ እስከ ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በ”ፍሪሾት”ወይም በቅርጫት ኳስ ሜዳው ከልጅነትና የክፍል ጓደኞቼ ከእነ መብራት አጥናፍ፣ ስማቸው አለሙ፣ ሲሳይ ጌታነህ፣ ቸርነት ስራው፣ አበበ ይልማና ተስፋዬ ቄሴ ጋር ሳንቲም እያስያዝን ኳስ እንጫወት ነበር። አይርበንም። አይጠማንም። ጨዋታ የምናቆመው ወላጆቻችን ስንዘገይ ስለሚጨነቁ መጥተው አንድ በአንድ ስለሚወስዱን ቡድኑ ተመናምኖ ስለሚፈርስ ነው።

የአንዳችን ወላጅ ስትመጣ ቡድኑ ሊፈርስ እንደሆነ ስለምናውቅ እንዴት እንደምንከፋና እርስ በእርስ እንደምንተያይ ዛሬ ድረስ አልዘነጋውም። ሜዳው ለእነ ቸርነት ስራው ቤት ቅርብ ስለነበር በብዛት ቀድመው የሚመጡት እናቱ እማ ደብሬ ነበሩ። ብዙ ሳንቆይ የሲሳይ ጌታነህ አያት እማ እብስቴ፣ የእኔ እናት እታለምዬ ይመጡና ይወስዱናል። የዕለቱ ቡድን ይፈርስና እንለያያለን። በበነጋው እንደምንገናኝ ግን ሳንነጋገር በአይን እንቃጠር ነበር። የትምህርት ዓመቱን እንዲህ እንዲህ እያልን እናሳልፋለን።

ሰኔ 30 ካርድ ተቀብለን ትምህርት ቤታችን ሲዘጋ እንኳ ዘበኞች እነ አባ ቦራና አባ አንዳርጌ ሳያዩን ከሰፈር ልጆች ጋር በአጥር ሾልከን ገብተን እንጫወት ነበር። ሳሩና ጓሳው ስለሚያድግ በት/ ቤቱ የእግር ኳስ ሜዳ እንደ እንቦሳ እንዘልና እንፈነጥዝ ነበር። የአድዮውን ማደግና የአደዩን ማበብ ተከትሎ ደግሞ ለሁለት ወራት ተዘግቶ የነበረው ትምህርት ቤት ስለሚከፈትና ከናፈቁን የክፍል ጓደኞቻችን ጋር ስለምንገናኝ አበክረን እንደሰትና ተስፋ እናደርግ ነበር።

የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ተፈትነን ወደ ዘጠነኛ ክፍል ስንዛወር ግን ሁኔታዎች መቀየር ይጀምራሉ። ጨዋታው ይቀንሳል። እኛም እንረጋጋለን። በቅጡ ነፍስ ማወቅ እንጀምራለን። ትኩረታችን ወደ ትምህርታችንና ወደ አዲሱ የዳሞት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይሆናል። ከአራት ዓመት በኋላ ማትሪክ ተፈትነን ዩኒቨርሲቲ ስንገባ እንዲሁ ትኩረታችን የደረስንበት ላይ ይሆንና ዳሞት 2ኛ ደረጃን እንተውና ዩኒቨርሲቲው ላይ ይሆናል። ተመርቀን ስንወጣ ደግሞ እሱን እርግፍ አድርገን ትተን ትኩረታችን ወደ ስራው ዓለም ይሆናል። ከዛ ወደ ቤተሰብ ወደ ልጆቻችን።

የእናንተን አላውቅም። ምን አልባትም ከእኔ የተለየ ላይሆን ይችላል። እውነቱን ለመናገር እኔ ግን የተማርኩባቸውን የ1ኛ፣ የ2ኛ ትምህርት ቤቶችንም

 ሆነ ስድስት ኪሎን በምን ሁኔታ ይሆን የሚገኙት ብዬ ተመልሼ አላየኋቸውም። አልፎ አልፎ ስድስት ኪሎ እሄድ የነበረው መጀመሪያ ከቡክ ሴንተር አዲስ መጽሐፍ ለመሸመት፤ በኋላ ደግሞ 2ኛ ዲግሪዬን ለመማር ለምዝገባ ከዛ ለፈተና በመጨረሻም ለመማር ነው። 1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቼን ካየሁ አንድ ትውልድ አልፎ ሁለተኛው እየገሰገሰ ነው። ያው ያንድ ትውልድ እድሜ እስከ 30 ዓመት እማይደል። የሚገርመው በዓመት ሁለት ጊዜ ለአዲስ ዓመትና ለትንሳኤ ፍኖተ ሰላም ቤተሰብ ጥየቃ እየተመላለስኩ አንድ ቀን እንኳ የተማርኩባቸውን ትምህርት ቤቶች የሚገኙበትን ሁኔታ አይቼ አላውቅም።

እድሜዬ እየገፋ ሲመጣ ለተማርኩበት ትምህርት ቤት እና ላሳደገኝ ማህበረሰብ ምን ትርጉም ያለው ነገር አደረግሁ ብዬ ሳስብ ምንም አለማድረጌ፤ በዛ ላይ ባጋጠመኝ የጤና እክል የተነሳ አካል ጉዳተኛ ስለሆንኩ ዛሬ ሄጀ ልጎብኛቸው ብል እንኳ ከባድ ነው የሚሆነው። ይህን ማድረግ አለመቻሌ እንደ እናቴ ሞት የግር እሳት ሆኖ ያንገበግበኛል። እኔ ላይ የደረሰው የራስ ሙግትና ቁጭት በእድሜ አመሻሽ ላይ ብቅ ማለቱ አይቀርምና በጉብዝናችሁ ወራት ትምህርት ቤቶቻችሁን ጎብኙ፤ ያሳደጋችሁን ማህበረሰብ፣ ያስተማሯችሁን መምህራን ጠይቁ። ጐብኙ። ዳብሱ።

ላለፉት 50ና 73 ዓመታት እልፍ አእላፍን አስተምረው ለወግ ለማዕረግ እንዳላበቁ ዛሬ ሁለቱም ት/ቤቶች በመፈራረስ ላይ መሆናቸውን ስመለከት በራሴ አፈርኩ። መሸሸጊያ መደበቂያ አጣሁ። ባለፈው ሚያዚያ የዳሞት 2ኛ ደረጃ ት/ቤት 50ኛ ዓመት ሲያከብር ያ የሚያምር ባለ ግርማ ሞገስ ትምህርት ቤት እንዳልሆነ ሆኖ እንደ ማንኛውም ባለዕዳ ተመልካች በአማራ ቴሌቪዥን የራሴን ገመና ተመለከትኩ። ሕንጻው ፈራርሶ፣ መስታወቶቹ ተሰባብረው፤ እነዛ የምንጓጓላቸው የፊዚክስና የኬሚስትሪ ቤተ ሙከራዎች ተራቁተው። የግቢው ልምላሜው ጠፍቶ እንደ ችግረኛ ሰው ተጎሳቁሎ አየሁት። ያን ሁሉ መምህር፣ ምሁር፣ ነጋዴ፣ ነርስ፣ የልማት ጣቢያ ሰራተኛ፣ ባለሙያ፣ ቢሊየነር፣ ፕሮፌሰር፣ ዶክተር፣ መሐንዲስ፣ ጋዜጠኛ፣ ወዘተረፈ ያፈራ ት/ቤት ለልጆቹ የድረሱልኝ ጥሪ ሲያስተላልፍ ስሰማ እንደ እግር እሳት ውስጤን አንገበገበኝ።

አስበን ልንደርስለት ሲገባ አፍ አውጥቶ ድረሱልኝ አለን። ከ9 እስከ 12 በሚያማምሩ በባለመደገፊያ ወንበሮች በማይካ በተለበጠ የሚያምር ጠረጴዛ፣ በሚያምሩ የመስታውት መስኮቶች፤ የሚያምር ኮርኒስ በተሰራለት፤ ጻፉብኝ ጻፉብኝ በሚል በተንጣለለ ጥቁር ሰሌዳ ቁጭ ብለን እንዳልተማርን፤ የዛሬ ተማሪዎች ግን የሚማሩት ግድግዳው በመፈራረስ ላይ ባለ፤ መስኮቱ በተሰባበረ፣ ኮርኒሱ በተገነጣጠለ፣ ወለሉ በአፈርና በአቧራ በተሞላ፣ ለመቀመጥ በማይመች አግዳሚ ወንበርና ጠረጴዛ ለዛውም በክፍል እስከ 60ና 70 ተማሪ ተጠቅጥቆባቸው አይደለም ለመማር ለደቂቃዎች ለመቆየት እንኳ በማይመች ሁኔታ ነው።

እኔ ቢረፍድም አልዘገየም ብዬ እነዛ የልጅነቴና የወጣትነቴ ማህደር የሆኑ ትምህርት ቤቶቼ እየፈራረሱ ስለሆነ እንዲጠገኑ፤ በተማሪ ብዛት ስለተጨናነቁ ተጨማሪ የመማሪያ ብሎኮች እንዲገነቡላቸው በሙያዬ የቻልኩትን እየጣርኩ ሲሆን፤ በዚች ባተሌ እድሜዬ ያሰባሰብኳቸውንና ወደ 50ሺህ ብር የሚያወጡ ከ200 በላይ መጽሐፍትን ለተማርኩበትና ለምወደው ዳሞት አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ለመስጠት ወስኛለሁ። ለአብርኆት የሕዝብ ቤተ መጽሐፍትም እንደ አቅሚቴ በኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ በኩል አበርክቻለሁ።

እኔ የተማርኩባቸውን ትምህርት ቤቶች አነሳሁ እንጂ በመላ ሀገሪቱ ያሉ ትምህርት ቤቶች ይዞታ ተመሳሳይ መሆኑን በዚያ ሰሞን ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው አስደንጋጭ መረጃ አርድቶናል። ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ የትምህርት ቤቶችን ጉዳይ አስመልክቶ በተዘጋጀው አንድ ሥነ ሥርዓት ከ49 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ86 በመቶ በላይ የአንደኛና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ያልተሟሉላቸውና ከደረጃ በታች መሆናቸውን፤ ከ71 በመቶ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ መሠረተ ልማቶች ስላልተሟሉላቸው ተማሪዎች በተጓደለ የትምህርት ከባቢ ውስጥ እንዲማሩ መገደዳቸውን፤ በአገሪቱ የትምህርት ጥራት ችግር መንስዔዎች ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም የትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ አለመሆን፣ ከመሠረታዊ ችግሮች አንዱና ዋነኛው መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) እሑድ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ሚኒስቴሩ ‹‹ትምህርት ለትውልድ›› በሚል መሪ ቃል የትምህርት ቤቶች ደረጃና ጥራት ማሻሻያ አገራዊ ንቅናቄ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ባስጀመረበት መድረክ ላይ፣ የጥናት ውጤት አጣቅሰው ማብራሪያ ሰጥተዋል ይለናል የአማርኛው ሪፖርተር ጋዜጣ፡፡

በአገራችን ካሉ 49 ሺሕ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት አመቺነት በአራት ደረጃ መድቦ ማለትም አራተኛ ደረጃ የተሟላ፣ ሦስተኛ ደረጃ የተሟላም ባይሆን ብቁ፣ ሁለተኛና አንደኛ ደረጃ ፍፁም ለትምህርት ቤትነት የማይመጥኑ ወይም ከደረጃ በታች ብሎ በመደባቸው ጥናት በጣት የሚቆጠሩ ወይም 0.01 በመቶ ብቻ አራተኛ ደረጃ የደረሱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲኖሩ፣ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግን የሉንም፤ ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

ከ86 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአንደኛና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ከ71 በመቶ በላይ የሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ለትምህርት ቤትነት የማይመጥኑ ወይም ፍፁም ከደረጃ በታች ናቸው ሲሉም አክለዋል፡፡ ይህ ቁጥር አስደንጋጭ እውነታ ነው፤ ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ የትምህርት ሥርዓቱ ውድቀት ከታች የሚጀምር መሆን እንደሚጠቁም በመግለጽ፤ ችግሩ ለነገ ሳይባል ሊፈታ እንደሚገባና ለዚህም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተማረባቸውን ትምህርት ቤቶች ማገዝ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህንንም በተቀናጀ መንገድ ለማከናወን የተጀመረውን ንቅናቄ ይፋ አድርገዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ባስጠናው ጥናት 33.2 በመቶ የአንደኛና መካከለኛ ደረጃና 55.6 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ የንፁህ መጠጥ ውኃ አገልግሎት እንደሚያገኙ፤ ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች 21.3 በመቶ አንደኛና መካከለኛ፣ እንዲሁም 49.1 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቧንቧ ተጠቃሚ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ትምህርት ቤቶች ምንም ዓይነት የውኃ አቅርቦት እንደሌላቸው ተገልጿል፡፡ በትምህርት ቤቶች የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ሲታይ 37 በመቶ አንደኛና መካከለኛ፣ እንዲሁም 43 በመቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመፀዳጃ ቤቶች ቢኖራቸውም የተቀሩት አገልግሎቱ እንዳልተዳረሰላቸው የተደረገው ጥናት ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም 29.4 በመቶ አንደኛ ደረጃ፣ እንዲሁም 74.5 በመቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዳገኙ ተጠቅሷል፡፡

በሆነ ጊዜ ትውልድ ኢንቨስት አድርጎባችሁ በነፃ የተማራችሁ ሰዎች አሁን ተባብረን በመንግሥት፣ በሕዝብና በጎ ልብና አዕምሮ ባላቸው ሰዎች ትምህርት ማስፋፋት ካልቻልን በስተቀር በሚቀጥለው ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ አገር መሆን አንችለም፤ ያሉት በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ናቸው ፡፡ ዛሬ የተገናኘነው ትናንት ያስተማረን ማኅብረሰብ ዕዳ ስላለብን ነው፤ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ የተማራችሁ ሁሉ የተማራችሁባቸው ትምህርት ቤቶች ዛሬ የእናንተን ድጋፍ ይሻሉ፤ ብለዋል፡፡

ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶች የሚለው ችግር በመንግሥት አቅም ብቻ ለመፍታት ቢታሰብ ከሦስት አስርት ዓመታት ያላነሰ ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል፤ ችግሩን ለመፍታት በየደረጃው ያሉ አመራሮች የአካባቢ ማኅበረሰብ፤ የቀድሞ ተማሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም ባለሀብቶች በትውልድ ቦታቸው፣ በተማሩበት ቦታ፣ በሚሠሩባቸውና በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማቶች ማሻሻል ሲቻል በመሆኑ፣ እነዚህን ትምህርት ቤቶች በሕዝብ ንቅናቄ ለማሻሻል ዕቅድ መዘጋጀቱን በአገራዊ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ማሻሻል ለመንግሥት ብቻ የተተወ ኃላፊነት ባለመሆኑ፣ በየደረጃው ያለው ማኅበረሰብና ልዩ ልዩ አካላት የገንዘብ፣ የሐሳብና የጉልበት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጥሪ አድርገዋል፡፡ በንቅናቄ መድረኩ ላይ ንግግር ካደረጉ ተሳታፊዎች አንዱ የሆነው ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ እስካሁን በርካታ ትምህርት ቤቶችን መገንባቱንና በትምህርት ሥራ ላይ ኢንቨስት ማድረጉን ገልጾ፤ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ትምህርት ላይ ከሠሩ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት በአጭር ጊዜ ማሻሻል ብሎም አገርን መለወጥ ይቻላል ብሏል፡፡ ባለሀብቶችና አቅሙ ያላችሁ ሁሉ በሕይወታችሁ ደስታን ከፈለጋችሁ ትምህርት ቤትና ትውልድ ላይ ሥሩ፤ ሲል ሻለቃ ኃይሌ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት በማሻሻል ከግል ትምህርት ቤቶች እኩል ለማድረግ፤ 50 ሺሕ ትምህርት ቤቶችን በሕዝባዊ ተሳትፎ እንደሚያሳድስ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ ሰኔ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ አለመሆናቸው ለትምህርት ጥራት መጓደል መንስዔ ከሆኑ ችግሮች ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት፣ ትምህርት ቤቶችን በሕዝባዊ ንቅናቄ መገንባት ያስፈለገው፤ በመንግሥት ቢተገበር ከ30 እስከ 40 ዓመታት ስለሚወስድ ነው፡፡ ድሮ በእኛ ጊዜ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በሁሉም ነገሮች ከግል ትምህርት ቤቶች እኩል ነበሩ፤ ያሉት ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን ከዓመታት በኋላ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ደረጃ፣ ጥራትና መሰል እንቅስቃሴ ሲፈተሽ እየወረደና ደረጃቸው ዝቅ እያለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ሻሎም !

አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን )

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *