ተገቢውን መንገድ አልፎ መመረቅ ያኮራል!

 ወቅቱ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለዓመታት ሲማሩ የቆዩ ተማሪዎች የሚመረቁበት ነው።ይህ ወቅት እንደ ተመራቂ፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም፣ እንደ ቤተሰብና ማኅበረሰብ ይህ ወቅት ትልቅ ትርጉም ይሰጠዋል።

ተማሪዎቹ በተቋማቱ ሲከታተሉ የቆዩትን ትምህርት አጠናቀው ወደ ሥራው ዓለም ለመሰማራት ወይም ወደ ሌላ የትምህርት ምዕራፍ ለመሸጋገር አንድ ማረጋገጫ ያገኙበት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎቻቸውን፣ ቤተሰብም የልጆቹን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስኬት በዚህ ወቅት ያጣጥማሉ።ለእዚህም ተመራቂዎች ብቻም ሳይሆኑ ሁሉንም ባለድርሻዎች እንኳን ደስ አላችሁ! እንላለን።

የዘንድሮ ምሩቃን እንኳን ደስ አላችሁ የሚባሉበት መንገድ ግን ከመቼውም ጊዜ ይለያል።ለዓመታት ስትከታተሉት የቆያችሁትን የዩኒቨርሲቲ ትምህርታችሁን መንግስት ዘንድሮ አዲስ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የመውጫ ፈተና ወስዳችሁ፣ አልፋችሁ የተመረቃችሁ በመሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ስትባሉ በልዩ ሁኔታ ሊሆን ይገባል።

የሀገራችን የትምህርት ተቋማት ያሉበት ደረጃ በእጅጉ አሳሳቢ ሊባል የሚችል ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የተማሪዎች ውጤቶች፣ ጥናቶች ወዘተ ሲያመለክቱ ቆይተዋል።ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል አንደሚባለውም የትምህርት ቤቶች ውጫዊ እና ውስጣዊ ሁኔታዎችም ይህንኑ ያመለከቱ ናቸው።በቅርቡ በይፋ የተጀመረውን የትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሳደግ ንቅናቄ አስመልክቶ የወጡ መረጃዎች ደግሞ ይህን እውነታ የበለጠ ፍንትው አድርገው አስገንዝበዋል፡፡

ትምህርት ቤት ወይም ዩኒቨርሲቲ ዕውቀት የሚቀሰምበትና በዕውቀት ላይ ዕውቀት የሚደረብበት እንጂ እድሜ የሚቆጠርበት አይደለም።በሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታየው ሁኔታ ግን ይህን እያመለከተ አልነበረም።ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መመረቅ ከመመረቅ ባሻገር ሊሆን አልቻለም፤ ምሩቃን በተመረቁበት ልክ ለራሳቸውም ለሀገራቸውም እየሠሩ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍርም አልሆነም።

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባትም እንዲሁ በፈተና ላይ በሚፈጸም ስርቆት ሳቢያ ውጤት ሲጋሽብ በተደጋጋሚ ታይቷል፤ ይህም የፈተና ሚዛኑን ከሚዛንነት አውጥቶት ቆይቷል።ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተማሪዎች ላይም ብዙ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል።በቅርቡ በከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና ውጤትም ይሄ እውነታ ፍንትው ብሎ ታይቷል።

መንግስት ይህን ችግር ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎችን ወደ መውሰድ ገብቷል፤ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥበትን መንገድ ቀይሯል፤ በዚህም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎችን በአግባቡ መለየት መቻል ተጀምሯል፤ አሁን ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎችን ተቋሞቻቸው የሚመዝኑባቸው መንገዶች እንዳሉ ሆነው ትምሀርት ሚኒስቴር እንደ ሀገር የመውጫ ፈተና በማዘጋጀት ብቁ ተማሪዎች እንዲለዩ አድርጓል።እነዚህ ተማሪዎች ናቸው በአሁኑ ወቅት እየተመረቁ ያሉት።

ፈተና እየተሰረቀ ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች የማይገባቸውን ነጥብ እየያዙ ከፍተኛ ትምህርት ሲገቡ የነበረበት ሁኔታ፣ ሌሎች ብርቱዎች ደግሞ በንጽህና ሰርተው ውጤታቸው መውረዱን ተከትሎ የመማር ህልማቸው የከሸፈበት ሁኔታ የሀገሪቱን የትምህርት ስርአት ጥያቄ ውስጥ ከቶት ቆይቷል።

ለዚህ ቀውስ ነው መንግስት መፍትሄ አስቀምጦ እየሰራ ያለውና ውጤትም እያስመዘገበ የሚገኘው።የመንግስት ጥረትና እየተመዘገበ ያለው ውጤትም በአበረታችነት የሚጠቀስ እንደመሆኑም ትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡

በትምህርቱ የሌሉ፣ በውጤቱ ፊት ለፊት ለመሰለፍ የበረቱ በርካቶችን አይተናል፤ በብርቱዎች መያዝ ያለባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቦታዎች በተሰረቀ ፈተና ባለውጤት ተብዬዎች እንዲያዙ ተደርገዋል። በትምህርቱ ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉት ግን ተጥለዋል።መንግስት ይህን አስከፊና እና ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት ተንቀሳቅሷል፤ በዚህም ብርቱዎች የሚገቧቸውን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ነው።

የመውጫ ፈተናው እና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እየተሰጠ ያለበት መንገድ የሀገሪቱ የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ ያላቸው ፋይዳ በእጅጉ ከፍተኛ ነው።የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እየተሰጠ ያለበት መንገድ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች በሚመጥናቸው ተቋም ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያስችላል፤ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁትም እንዲሁ በዕውቀታቸው መሰረት ተወዳድረው የሥራውን ዓለም የሚቀላቀሉበትን፣ በዚህም ራሳቸውንም ሀገራቸውንም የሚጠቅሙበትን እንዲሁም ወደ ቀጣዩ የትምህርት ምዕራፍ የሚሸጋገሩበትን ሁኔታ ይፈጥራል።

በትምህርት ሂደቱ ላይ የታየው ቀውስ በአንድ ጀምበር የመጣ አይደለም።የቆየና ስር የሰደደ ችግር ነው።ይህን ችግር ለመፍታት ይህ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችል ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

አሁን የጥረቱን እሸት ነው እየታየ ያለው።ዋናው አዝመራ ወደፊት ነው የሚታየው።በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና ላይ የተጀመሩት ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸው እንዳለ ሆኖ በየደረጃው በመማር ማስተማር ስራ ላይ የሚታዩ መፍትሄ የሚፈልጉ ችግሮችን ለመፍታቱ ስራ ከልብ መስራት ያስፈልጋል።

የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ብሄራዊ ፈተና ውጤት እየተበላሸ የመጣው፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚመረቁ ተማሪዎች በኩልም ቀውስ እየተከሰተ ያለው ተማሪዎች በመኮረጃቸውና በመሳሰሉት ምክንያቶች ብቻ አይደለም፤ በእዚህ ውስጥ የበርካታ አካላት እጆችም አሉበት።እነዚህ እጆች ሁሉ እንዲሰበሰቡ ማድረግ ላይም መስራት ይገባል።ከዚህ አኳያ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲዎች አስገብቶ ፈተና እየተሰጠ ያለበት ሁኔታ ይህን ችግር ለመፍታት አንድ ትልቅ ርምጃ ነው፡፡

ለተማሪዎች ድጋፍ ማድረግ የሚፈልግ አካል መንግስት በመላ ሀገሪቱ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በጀመረው ንቅናቄ በንቃት በመሳተፍ የትምህርት ዘርፉን ከገባበት ማጥ ማውጣት ይችላል።ለተማሪዎችም ለሀገርም የሚጠቅመው ይሄ ነው።አሁንም የዘንድሮ ተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ!

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *