ለፖለቲካ ህመሙ በእጃችን ያለ መፍትሄ

 ችግሮችን ተቀራርቦ በመነጋገርና በመወያየት ስለመፍታት አስፈላጊነት የምንጠቀምባቸው ለዘመናት የቆዩ የሀገራችን ብሂሎች አሉ። ለምሳሌ ያህል “ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል” የሚለው አንደኛው አባባል፣ እያንዳንዳችን ፍላጎታችንን፣ ችግራችንን እና በሆነ ጉዳይ ላይ ያለንን የግል አስተሳሰብ ሌላው ያውቅ ዘንድ፣ እኛም የእነርሱን ፍላጎትና አቋም መረዳት እንድንችል ነጻና ግልጽ ውይይት ማድረግና ለችግሮች መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ያመላክታል።

“ህመሙን የደበቀ መድኃኒት .አይገኝለትም” የሚለው አባባል ሌላው በኢትዮጵያ ስነ ቃል ውስጥ ስንሰማውና ስንናገረው የኖርነው ብሂል ነው። ይህም በተመሳሳይ ህመሙን፣ ችግሩን፣ ፍላጎቱን፣ በደሉን … ለሌላ ያላወያየ፣ ያላማከረና ያልመከረ ያለበትን ችግር ለማስወገድ እንደሚቸገር ለማመላከት ስንጠቀምበት የቆየ አነጋገር ነው።

እነዚህ ምሳሌዎች በማህበራዊም ሆነ በፖለቲካው ዓለም ውስጥ ያሉ ችግሮችንና አለመግባባቶችን በውይይትና በምክክር መፍትሄ መስጠት ካልቻልን የሚያስከትለውን ውጤት ቆም ብለን እንድናጤን የሚያግዙ መሰረተ ሀሳቦች ናቸው ብዬ አምናለሁ።

የሀሳብ ልዩነት በሰው ልጆች ምድራዊ አኗኗር ውስጥ ያለና ወደፈትም የሚኖር ነገር ነው። የሰው ልጆች ግንኙነትና መስተጋብር ባለበት ቦታ ልዩነት አይጠፋም። ሰዎች ተመሳሳይ ሀሳብና እይታ ቢኖራቸው ኖሮ ዓለም አሁን ያላት ቅርጽና ይዘት ባልኖራት ነበር። ዓለም በማያቋርጥ የለውጥ/ የእድገት ሂደት ውስጥ የማለፏ አንዱ ሚስጥር በሰዎች መካከል የተለያየ አስተሳሰብና አመለካከት መኖሩ ነው።

ይህን አስመልክቶ ታዋቂው አሜሪካዊ የጦር ጄነራል ጆርጅ ፓተን (George S. Patton) ሲናገር “If everyone thinking alike, then somebody is not thinking” ይላሉ። ትርጉሙም “ሰው ሁሉ ተመሳሳይ ሀሳብ ቢኖረው ኖሮ፥ ሌላው ሰው ማሰብ አያስፈልገውም ነበር ” እንደማለት ነው ። ይህ በማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎችም ተቀባይነትን ያገኘ መሰረተ ሀሳብ ነው።

የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ሰዎች በሚኖራቸው የእርስ በርስ ግንኙነት የሚያካሂዷቸው ውይይቶችና የሚሰጧቸው አስተያየቶች በከፊል በሚቃረኑ ሀሳቦች (Negative communications) ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ይህም የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሮአዊ (Real) መሆኑን ያሳያል።

ባሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የምናያቸው የአስደናቂ ፈጠራዎችና ሳይንሳዊ ግኝቶች መሰረት የሰው ልጅ የአእምሮ አቅሙን ተጠቅሞ በተለየና ባልተለመደ አቅጣጫ (Thinking out of the box) ማሰብ የመቻሉ ውጤት ነው። ስለሆነም በዓለም ላይ ካሉ ጥበቦች አንዱና ዋነኛው በጋራ ጉዳይ ላይ መወያየት፣ መነጋገርና የሀሳብ ፍጭት ማድረግ ነው ማለት ይቻላል።

በዚሀ መሰረት ሰዎች በማያግባቧቸው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እየተደራደሩና እየተነጋገሩ ተስማምቶና ተቻችሎ ከመኖር ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸው ማመን ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ ”እንደ እኔ አስብ፣ እኔን ምሰል፣ የምልህን ብቻ ተግብር….” ማለት የጫጨ አስተሳሰብ ማሳያ ነው። የብዙ ውዝግቦች፣ የብዙ ግጭቶች፣ የብዙ ጦርነቶች መነሻ እነዚህና መሰል አስተሳሰቦችና እይታዎች ናቸው።

ዶ/ር ሳሙኤል ወልዴ የተባሉ ደራሲ “ከመደነጋገር መነጋገር” በሚል መጽሀፋቸው በመነጋገር የጋራ

 አላማን ማስጠበቅ፣ በመነጋገር የጋራ ግንዛቤ መፍጠር፣ በመነጋገር ጥርጣሬንና ሐሜትን ማስወገድ እንደሚቻል ያስረዳሉ። እንደ ጸሀፊው አባባል፤ በግልፅ የተመከረበት ሀሳብ፣ በጋራ የዳበረ ጉዳይ ሩቅ ለመራመድ ጉልበት አለው። በተቃራኒው ያልተመከረበትና ውይይት ያልተደረገበት ሀሳብ መደነጋገርን ብቻ ሳይሆን ጥርጣሬንም ይፈጥራል።

የበርካታ ሀገራት የመበታተን፣ የመፈራረስ፣ የህዝብ ዕልቂትና ስደት መነሻና ምክንያቱ አለመነጋገርና የጋራ ምክክር ማድረግ አለመቻል መሆኑን በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ። በመሆኑም መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ውይይትና ምክክር አድርጎ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ የውዴታ ግዴታ ነው።

የውስጥ ችግራቸውን በጨዋ ደንብ ተወያይተው መፍታት ያልቻሉ ሀገራት የገጠማቸውን ፈተናና መከራ መግለጽም መናገርም ከሚቻለው በላይ ነው። ለምሳሌ ትናንት በብዝሀ ማንነቷ ትታወቅ የነበረችው ዩጎዝላቪያ ዛሬ ላይ በዓለም ካርታ ላይ ስሟ ተፍቋል። ይህ የሆነው ዜጎቿ ባካሄዱት ብሄር ተኮር ጦርነት በመፈራረሷ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በስሯ የነበሩት ስድስት ሪፐብሊኮች የራሳቸውን ሉኣላዊ አገር ለመፍጠር ችለዋል።

ጎረቤታቸን ሶማሌም ቁልቁል ወርዳ አዘቅት ውስጥ ከገባች ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ምዕራብ ኤሺያዊቷ ሶሪያም የገጠማት ዕጣ ፈንታም ከዚህ ብዙም የተለየ አይደለም። ሀገሪቱ በልጆቿ አለመግባባት የጦር አውድማ ሆና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ በሁሉም የዓለም ማዕዘናት በስደት ተበትነዋል። ከተሞቿ በአሰቃቂ ሁኔታ ፈራርሰዋል። በድምሩ ሀገሪቱ በቀላል የማይሽር ጠባሳ አርፎባታል። የመንም የዚሁ እውነታ ተጋሪ ናት። የብዙ ሀገራት የመበታተን፣ የመፈራረስ፣ የህዝብ እልቂትና ስደት መነሻው ይሄው የአለመነጋገርና የአለመደማመጥ አባዜ ነው።

አስገራሚው ነገር ግን በርካታ መንግስታት አስከፊ የመከራ ዝናብ ከወረደበቸው ከእነዚህ ሀገራት ትምህርት መቅሰም ተስኗቸው በፍጥነት ወደዚያው መንገድ እየተንደረደሩ መሆኑ ነው። ለዚህም ባሁኑ ወቅት ከባድ ግጭት እያስተናገደች የምትገኘውን ጎረቤታችን ሱዳንን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። ይህ ሁሉ የሆነው መሪዎቹና የሀገሪቱ ሊሂቃን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ ሆነው መገኘት ባለመቻላቸው ነው። ሰሚም (አድማጭ) ሆነ ምላሽ ሰጪ በመታጣቱ…. ነው።

በሌላ መልኩም አንዳንድ ሀገራት ካለፈው የተሳሳተ አካሄዳቸው ተጸጽተው፣ ትምህርት ቀስመው እና ከደረሰባቸው አሰቃቂ መዓት ወጥተው በሁሉም መስክ ዓለምን ያስደመመ ለውጥ አስመዝግበዋል። እያስመዘገቡም ይገኛሉ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው የመካከለኛ አፍሪካዊቷ ሀገር ሩዋንዳ ናት። ሩዋንዳ እ.አ.አ በ 1994 አጋጥሟት ከነበረው የዘር ማጥፋት ወንጀልና ደም አፋሳሽ የርስ በርስ ጦርነት በመውጣት ትክክለኛ አቅጣጫ ይዛ ወደፊት መስፈንጠር የቻለችው በደሎችን በመናዘዝ፣ ይቅር በመባባል እንዲሁም የህዝቡን አብሮነት የሚሸረሽሩ፣ እርስ በርስ የሚያቃቅሩና የሚከፋፍሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸው ነው።

ከዚህ አኳያ በ 1994 ዓ.ም ከተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል በሁዋላ ሩዋንዳ ውስጥ ማንም ሰው ሌላውን ጎሳህ ምንድን ነው ብሎ እንዳይጠይቀው በህግ መከልከልን ጀምሮ ወሳኝ ፖለቲካዊ እርምጃዎችን በመውሰዳቸው ዛሬ ላይ

 አገሪቱ ብሄርን መሰረት ካደረገ ጥላቻና ግጭት ነፃ ሆናለች፤ ብሄራዊ አንድነትን (Social fabric) በመፍጠር ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ጽኑ መሰረት ጥላለች። ለዚህ ምንም የተለየ ምስጢር የለውም። ከደረሰው የዘር ፍጅት ጭፍጨፋ በመነሳት የጋራ ጉዳያቸውን ሰከን ብለው በጠረጴዛ ዙሪያ የመነጋገራቸውና የመወያየታቸው ውጤት ነው።

ጀርመኖችና ጃፓኖችም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከደረሰባቸው ውድመትና ጥፋት ተምረው ዛሬ የሚገኙበት ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱት ውይይትና ንግግርን መሰረት ያደረገ አዲስ የፖለቲካ መስመር በመምረጣቸው ነው። በቁጭትና በዕልህ ወደ ሰለጠነና ዘመኑን ወደዋጀ የፖለቲካ ምዕራፍ በመሸጋገራቸው ነው።

ዛሬ ላይ በዲሞክራሲ ስኬታቸው በተምሳሌትነት የሚጠቀሱት አሜሪካን ጨምሮ አብዛኞቹ ምእራባውያን ሀገራት አሁን ያሉበት ከፍታ ላይ የደረሱት ባጋጣሚ ሳይሆን አንድም የውይይት፣ ተነጋግሮ የመግባባት፣ ምክንያት የመሞገትና ሀገርን ሊያበለጽጉ የሚችሉ አማራጭ ሀሳቦችን የማመንጨት አቅማቸው የዳበረ በመሆኑ፣ አንድም እነዚህን ሁኔታዎች እንደ ምቹ መደላደል ተጠቅመው የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አቅማቸውን በማሳደጋቸው ነው። በዚህም ምክንያት የዲሞክራሲ ባህል እንዳልዳበረባቸው ሀገራት ለተለያየ ቀውሶችና አለመግባባቶች ሲጋለጡ ማየት አልተለመደም።

የመነጋገር፣ የመመካከር፣ የመቻቻልና የመተባበር ባህል ለእኛ (ለኢትዮጵያውያን) አዲስ ነገር እንዳልሆነ ይታወቃል። ማህበረሰቡ ችግሮች ሲያጋጥሙት የሚፈታባቸው ለዘመናት የቆዩ ባህላዊ ስርአቶች አሉት። ችግሮችን በባህላዊ እርቅና ሽምግልና ሥርዓት በመነጋገር ማብረድና መቋጨት ለዘመናት የቆየ የአባቶቻችን እሴት ነው።

እንደ አውጫጭኝ፣ አፈርሳታ፣ ሌባሻይና ሼንጎ የመሳሰሉ የግልግል እና የእርቅ ሥርዓቶችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ እሴቶች በተለይ ዘመንኛው (Contemporary) የፍትህ ስርአት በቀላሉ ተደራሽ ባልነበረባቸው ገጠራማው የሀገራችን ክፍል ሰላማዊና ጤናማ ማህበራዊ ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ነበራቸው።

በሌላም በኩል ህዝቦቿ በተደጋጋሚ የተቃጣባቸውን የውጭ ወረራ እምቢኝ አሻፈረኝ ብለው በጋራ በመመከት የአይበገሬነትና የነፃነት ተምሳሌት መሆን ችለዋል። የፍቅር፣ የመቻቻል፣ እንዲሁም የአብሮነት ዕሴት ባለቤቶች ስለመሆናቸውም አብሮ ሲመሰከርላቸው ቆይቷል።

“በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” ሆኖብን አሁን አሁን ይህን ባህልና ትውፊታችንን አክብረን ከመያዝ ይልቅ ያቀለልነው ይመስላል፣ ዋጋው አንሶብናል። ስጋቶችንም ሆነ ችግሮችን በሰከነ ውይይትና መደማመጥ እንዲፈቱ የማድረግ ባህላችን ተመናምኗል። ይህም በመሆኑ “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” እንዲሉ በእጃችን ላይ ያሉ አኩሪ እሴቶቻችንን ተጠቅመን የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻችንን በቀላ መፍታት እንዳንችል አድርጎናል።

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት እንደመሆኗ ብዙ መልካምም መጥፎም ታሪክ ያሳለፈች ሀገር ናት። በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ አንዳንዴ ያጋጠሟትን ችግሮች መፍታት በመቻሏ (ለዚህ አስረጂነት የአድዋን ድል መጥቀስ ይቻላል) የአሸናፊነትና የጥንካሬነት ምሳሌ ሆና እንድትታይ ያደረጋት ሲሆን፤ በሌላ ወቅት ደግሞ ዜጎቿ ያላቸውን ልዩነት አጥብበውና አቻችለው ለተሻለች ኢትዮጵያ መፈጠር በደንብ ስላልሰሩ ሀገሪቱ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶባታል። ወደተሻለ የእድገት ደረጃ ለመሸጋገር እንችልባቸው የነበሩ ብዙ ወርቃማ እድሎችም ዳር ሳይደርሱ መክነው ቀርተዋል።

በተለይ ከ1960ዎቹ ወዲህ ባሉ የተለያዩ ጊዚያቶች ተስፋ ሰጪ እድሎች አጋጥመውን የነበረ ቢሆንም እነዚህን እድሎች ባግባቡ መጠቀም ባለመቻላችን እድገታችን ከመሻሻል ይልቅ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ እየተጓዘ እዚህ ደርሰናል። ያጋጠሙንን እድሎች እንዲጨናገፉ ያደረጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከእነኚህም መካከል የተለያየ ጥያቄ (ፍላጎት) ባላቸው የፖለቲካ ሀይሎች ለዘመናት ሲነሱ በነበሩ ጥያቄዎች ዙሪያ ጥልቅ ውይይት አድርጎ የጋራ መግባባትና መተማመን መፍጠር የሚያስችል (ምቹ መደላድል) መፍጠር አለመቻል አንደኛው ነው።

የሌላውን ሀሳብ ከማድመጥ ይልቅ “እኔ ያልኩት ይሁን”፣ “የእኔ ፍላጎት ይፈጸምልኝ”፣ “እውነትም መንገድም እኛ ነን፣ አዳኝና መፍትሄ ሰጪዎቹ እኛ ብቻ ነን ፣….የሚለው ሰንካላ አስተሳሰብ ስር መስደዱም ሌላው ምክንያት ነው። በዚህ ላይ ሰጥቶ የመቀበል የዳበረ ተሞክሮ (trend) የለንም። የራስን ሀሳብ ሌላው ላይ መጫን እንጂ በምክንያት መከራከርና ሌሎችን ሀሳብ የማስተናገድ ባህል አልዳበረም። ይህንን እውቁ ባለቅኔ ጸጋዬ ገ/መድህን “እናት ዓለም ጠኑ” በሚለው ቲያትሩ “የኛ ሰው አመሉ፣ ቀልተናል ቅሉ፣ ጠልተናል ጥሉ፣ በልተናል ብሉ ።” ብሎ በግጥም ስንኙ ለማስተላለፍ በሞከረው ቁምነገር በደንብ ተገልጿል።

ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም። እድል ገጥሟቸው ወደ ስልጣን መንበሩ በመጡ ገዢ ፓርቲዎችና በተቃውሞው ጎራ በተሰለፉ ሀይሎች መካከል ያለውም ግንኙነት ጤናማ የሚባል እንዳልሆነ በተለያየ አጋጣሚ ታይቷል። ግንኙነታቸው ባብዛኛው በሴራ፣ በመጠላለፍ፣ በመካሰስ፣ አንዱ ላንዱ የመቀበሪያ ጉድጓድ በመማስ…ላይ ያተኮረና ያመዘነ ነው።

ስልጣን የጨበጡት የፖለቲካ ተዋንያን የሚያራምዱትን ፖሊሲና አቋም የሚተች/የሚገዳደር አካል በዋዛ አይታለፍም። ትችቶችንና ምክንያታዊ አስተሳሰቦችን በመመርመር ገዢውን ሀሳብ አንጥሮ በማውጣት ያለውን ችግርና ክፍተት ከመሙላት ይልቅ ‘ከእኔ (እኛ) በላይ ዕውቀት ለአሳር ነው’ በሚል መታበይ የሀሳቡን ባለቤቶች ስልታዊ በሆነ ዘዴ ጥግ ማስያዝ፣ ማናናቅ፣ ባስ ካለም በሀይል ማሸማቀቅና ዝም ማሰኘት የአብዛኛው የፖለቲካው ልኢቃን ዋና መለያ (trend) ነው።

”በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖ የትግላቸው ዓላማ ዲሞክራሲያ እንዲሰፍን ማድረግ እንደሆነ በሚናገሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰፈርም ያለው የውይይትና የንግግር ባህል ያን ያህል የዳበረ የሚባል አይደለም። የሃሳብ ልዩነቶችን ተፈጥሮአዊ አድርጎ መገንዘብ ካለመቻል አንስቶ እስከ ውስጣዊ ሽኩቻና ክፍፍል፣ ከመካሰስ ቂም እስከመያያዝ… የጠብና የቅራኔ ምንጮች ሲሆኑ በተደጋጋሚ አስተውለናል። ይህ ነው- የንግግርና የምክክር ጸር ሆኖ እዚህ የዘለቀው።

የሚገርመው ሁሉም ፖርቲዎች (ስልጣንና መንበሩን የያዙትን ጨምሮ) ያለመታከት ስለዲሞከራሲ ያነበንባሉ፤ ዲሞክራሲን ይሰብካሉ፤ ዘወትር ስለዲሞክራሲ ትሩፋት ይቃኛሉ። ሆኖም “ከበሮ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር” እንዲል ተረቱ አማላይ ንግግራቸው መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሀቅ ጋር አልጣጣም እያለ ሀገራችንን ብዙ ዋጋ እንድትከፍል አድርጓታል፣ እያደረጋትም ይገኛል። ለምሳሌ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት… ዛሬም እንደ ሀገር ብሎም እንደ ትውልድ የሚያሳስቡን እና የሚያጨቃጭቁን ጉዳዮች ናቸው።

ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲያጨቃጭቁና ሲያወዛግቡ የነበሩ፣ ህዝቡ ጠይቋቸው ሳይመለሱ የቀሩ ችግሮች እንዲሁም ከትናንት ተንከባለው ዛሬም የዘለቁ ሀገራዊ ጉዳዮች አሁንም ዋነኛ የመነታረኪያ፣ የግጭትና የክፍፍል አጀንዳዎች እንደሆኑ ቀጥለዋል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የሰላም፣ የፍቅር የመልካምነት፣ አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን.. ትተን አትምጣብኝ አልመጣብህም እየተባባልን እንገኛለን። ልጆቻችንን የጥላቻ፣ የጎሰኝነትና የዘረኝነት ትርክት እየቀለብናቸው ለጥላቻና ለጸብ እየገፋናቸውና እያዘጋጀናቸው ነው።

ይህ አልበቃ ብሎ ምክንያት እየተፈለገ በየቦታው እጅግ በሚያሳዝን መልኩ የሰው ሕይወትና ንብረት በመጥፋት ላይ ይገኛል፤ በርካታ ዜጎች ያለማቋረጥ እየተፈናቀሉና እየተሰደዱ ይገኛሉ። የዜጎች መታፈን የዜጎች መታገት እየጨመረ መጥቷል። በየአካባቢው ግጭቶችና ውጊያዎች ተበራክተዋል። በሰላም ወጥቶ መግባቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። በዚህ ላይ በማንስማማባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተነጋግረን እንዳንግባባና ሰላም እንዳናገኝ ላይና ታች እያሉ የሚገኙ የግጭት ነጋዴዎች እኩይ ሴራም በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ላይ ሌላ ተጨማሪ ስጋት ደቅኗል።

ለዚህ ሁሉ የዳረገን በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርአት አስተማማኝ በሆነ መልኩ አለመዘርጋቱና ከአሮጌው የቆየ አስተሳሰብ አንጎበር መላቀቅ አለመቻላችን ነው። ህዝብን እያሸበሩና አገርን እየናጡ ያሉት ችግሮች በዝምታ ያለፍናቸውና በመነጋገርና በመመካከር መፍትሄ ያልሰጠናቸው እንከኖች ናቸው:: ሀገራችን ከገጠማት ችግር ለመውጣት ቁልፉ ነገር ካለንበት ጥልቅ ዝምታና የአለመተማመን ስሜት ወጥተን በአገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስለነጋችን የሰከነ ውይይትና ምክክር ማድረግ ነው።

በታሪክ ዙሪያ ያሉን የተዛቡ አመለካከቶችንና በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ቅራኔዎችን መፍታት የሚቻለውና ጥላቻዎች የሚሻሩት በጠረጴዛ ዙሪያ ተመካክሮና ተማምኖ አገራዊ መግባባት ላይ መድረስ ሲቻል ብቻ ነው። ባሁኑ ጊዜ በእጃችን ያለው ብቸኛ መፍትሄ ይሄ በመሆኑ ዕድሉን በብልሃት፤ በጥበብና በአርቆ አሳቢነት ልንጠቀምበት ይገባል። ከዚህ ውጪ የሆነ ሌላ መንገድና መፍትሄ አለ የሚል እምነት የለኝም። ከዚህ አንጻር ተስፋ ከተጣለበት የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን በርካታ የምንጠብቀው ነገር አለ።

ስለሆነም በጉጉት የምንጠብቀው ሀገራዊ ምክክር የተሳካ እንዲሆን ግጭትንና አለመግባባቶችን ከሚፈጥሩ ትርክቶችና አሉባልታዎች መራቅ፣ የጋራ ችግሮቻችንን ለመፍታት ለዘመናት ስንጠቀምባቸው የኖርነውንና አሁን ላይ እየተዘነጉ የመጡትን ነባር ባህላዊ እሴቶቻችንን ፈጠራ በታከለበት መንገድ ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት እንደ አስፈላጊነቱና እንደ ተጨባጭ ሁኔታው ስራ ላይ ማዋል እንዲሁም ለስልጡን የፖለቲካ ሂደት ራሳችንን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

ከሁሉም በላይ ግን መንግስት በየቦታው የሚፈጠሩ ግጭቶችንና ብጥብጦችን ከአሁኑ በበለጠ እንዲረግቡ በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት፣ እንዲሁም ኮሚሽኑ ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን በአካታች ሀገራዊ ምክክር ለመፍታት ለሚያከናውነው መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ አስፈላጊ ግብአቶችን በማሟላት ምቹ መደላድልና ምህዳር መፍጠር የበለጠ ይጠበቅበታል።

ቸር እንሰንብት!

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

ዳግም መርሻ /ኢዜአ/

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *