ለአንድ ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ እድገት ትምህርት ትልቁ እና ዋነኛው አቅም እንደሆነ ይታመናል። ይህንንም ታሳቢ በማድረግ እያንዳንዱ ኅብረተሰብ ባለው አቅም፤ በደረሰበት የንቃተ ህሊና ደረጃ ለትምህርት ከፍያለ ትኩረት ሰጥቶ ይንቀሳቀሳል። በዚህም ዛሬዎቹን ብቻ ሳይሆን ነገዎቹንም ብሩህ በማድረግ ትውልድ በተቻለ ሁሉ ከስጋት ነጻ ሕይወት እንዲኖር ይተጋሉ።
እያንዳንዱ ትውልድም ለዚሁ አትራፊ አስተሳሰብ ተገዥ በመሆን፤ በደረሰበት የዕውቀት ልክ፣ የየራሱን ታሪክ /አሻራ በማስቀመጥ፤ ማኅበረሰቡ የተንሰላሰለ የሰላም ዘመናት እንዲኖረው፤ ሰላም የሚወልደውን ልማትና ብልጽግና እንዲያጣጥም አቅሙ በፈቀደው ሁሉ ሲንቀሳቀስ ይስተዋላል። በዚህ መንገድ የተሳካላቸው ሀገራትም ከራሳቸው ተርፈው ለሌሎች መሆን መቻላቸውም የአደባባይ ሚስጥር ነው።
በእኛም ሀገር የትምህርት ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጣቸው ማኅበራዊ አጀንዳዎች መካከል አንዱና ዋንኛው ነው። ከቀደሙት ዘመናት ጀምሮ እስከ ዛሬ ያለው ትውልድ ለትምህርት የነበረው እሳቤ ከፍያለ፤ የትምህርት ጉዳይ ታላቅ ሀገር እና ማኅበረሰብ ለመመስረት ትልቁ አቅም እንደሆነ በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
በሀገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት መጀመሩን ተከትሎ በመንግስትም ሆነ በማኅበረሰቡ ውስጥ የታየው መነቃቃት፤ መነቃቃቱ ይዞት የተነሳው ሀገራዊና ሕዝባዊ ዓላማ የቱን ያህል ትልቅ እንደነበር ለማስታወስ የሚከብድ፤ ስለ ሕዝብ አብዝቶ ማሰብ የቻለ፤ ለዚህም ሕይወቱን ለመሰዋት ከራሱ ጋር ለመምከር ወደኋላ ያላለ ትውልድ በማፍራትም ጥሎት የሄደው አሻራ ፈጥኖ የሚጠፋ አይደለም።
አሁን ላለው ትውልድ ሳይቀር የሕዝባዊነትና የሀገር ወዳድነት መንፈስ የማጋራት አቅሙ ትልቅ የሆነው፣ በቀደሙት ትውልዶች በትምህርት እና ትምህርት በሚወልደው መነቃቃት የተፈጠሩ ስብዕናዎች፤ ለዛሬ /ለራሳችን /ሆነ ለመጪዎቹ ትውልዶች እጣ ፈንታ /ብሩህ ነገዎች ወሳኝ አቅም ስለመሆናቸው ብዙም የሚያጠያይቅ አይደለም።
በተለይ መማር /ፊደል መቁጠር/ ከራስ ወዳድነት/ፍጥረታዊ ማንነት/ ነጻ በማውጣት ለሌሎች ማሰብ፤ ለዚህ የሚሆን አዲስ የተገራ ስብእና መገንባት የሚያስችል ስለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው። ይህ ደግሞ ማኅበረሰባችንም ሆነ ሀገራችን ካሉበት የዛሬ ፈተና ለዘለቄታው በማውጣት ዛሬን በአግባቡ የሚኖር፣ ነገንም በተሻለ ተስፋ የሚቀበል ትውልድ ለመፍጠር ይረዳናል።
በርግጥ ላለፉት አራት አስርት ዓመታት የመጣንባቸው የትምህርት ስርአቶች፤ በትምህርት ሕዝባችን እንደ ሕዝብ የሚፈልገውን ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል አቅም መሆን ችለዋል የሚያስብሉ አይደሉም፤ ሕዝቡ በሌለው አቅሙ ተስፋ አድርጎ ለትምህርት የከፈለውን ዋጋ ያህል ፍሬ አፍርቷል ለማለት የሚያስደፍሩም አይደሉም ። ከዚህ ይልቅ እውነታው” ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” አይነት ሆኖ ኖሯል።
በቀደመው ዘመን የነበረው ትውልድ ለሀገሩና ለሕዝቡ ለመሞት የመጀመሪያ ረድፈኛ እንዳልሆነ፤ በዚህም በደሙ መቼም ቢሆን ሊረሳ የማይችል ታሪክ ሰርቶ ማለፍ እንደቻለ፤ በዚህ ዘመን ያለው ቀለም ቀመስ ትውልድ፣ በሕዝቡ፣ መከራ እና ስቃይ፤ ከዚህ በሚመነጭ ተስፋ መቁረጥ ለመቆመር ራሱን የሚያዘጋጅ ከሆነ ውሎ አድሯል።
ፌስ ቡክን ጨምሮ የዲጂታል ቴክኖሎጂው በፈጠራቸው አስቻይ የመረጃ ማሰራጫ አማራጮች በመጠቀም ጥላቻና ሁከትን፤ ፅንፍ የወጡ የዘርና ሀይማኖት እሳቤዎችን በስፋት በመርጨት የሕዝቡን ዘመን የተሻገሩ ማኅበራዊና መንፈሳዊ እሴቶችን ለማክሰም ያልተገቡ ርቀቶችን ሲጓዙ፤ በዚህም ሀገርና ህዝብን ላልተገባ ጥፋት ሲዳርጉ ይስተዋላል።
በተገለፀው የፖለቲካ መድረክም ቢሆን፤ ሀገርና ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አስተሳሰቦችን በጭፍን ከመቃወም ጀምሮ፤ ሕዝቡ በራሱ ጉዳይ የመወሰን መብቱን በመጋፋት ስንኩል በሆኑ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ለመጫን ረጅም ርቀት ሲሄዱም ማየት እና መስማት የተለመደ ነው።
ዛሬ ላይ ብዙ ውጣ ውረዶች አልፈው ረጅሙን የትምህርት ዘመን አጠናቀው በተለያዩ ደረጃዎች የሚመረቁ ምሩቃን ከሁሉም በላይ፤ መማራቸው፣ ለትልቅ ደረጃ መድረሳቸው፤ ሀገርና ሕዝብን ታሳቢ ያደረገ እና ለዚሁ የተገዛ ዓላማና ተልዕኮ መሆኑን በአግባቡ ሊያጤኑት ይገባል።
የእነሱም ሆነ ቀጣዩ ትውልድ ተጠቃሚነት መሰረት የሚያደርገው፣ ራሳቸውን ታሳቢ ባደረገ የሕይወት ተልዕኮ ሳይሆን እንደሀገር በጀመርነው ለውጥ ስኬት ላይ የተመሰረተ መሆኑን መገንዘብ፤ በትምህርት ዘመናቸው ባካበቷቸው ዕውቀቶችም ለሀገራዊ ዕድገት አቅም መሆን ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም