ፊስቱላ- ዛሬም ትኩረት የሚሻ የእናቶች የጤና ጉዳይ

እ.ኤ.አ በ2020 በተጠና ጥናት በኢትዮጵያ 100 ሺ ሕፃናትን ከሚወልዱ እናቶች ውስጥ 267 የሚሞቱ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በዓመት 10 ሺ፣ በቀን 27 እንዲሁም በሰዓት ከአንድ በላይ እናቶች እንደሚሞቱ እነዚሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከእያንዳንዱ የእናቶች ሞት በተጨማሪ ከ20 እስከ 30 የሚሆኑ እናቶች ከባድ የጤና ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ከሚከሰቱት ከባድ የጤና ችግሮች መካከል ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላ አንዱ ነው።

ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላ በእናቶች ላይ ከሚያስከትለው ከባድ የጤና ችግር በዘለለ በሚደርስባቸው መገለል ምክንያት ራሳቸውን ደብቀው ለስቃይ ስለሚዳረጉ ችግሩን አስከፊ ያደርገዋል። በፍርሃትና በመሸማቀቅ ምክንያት ወደ ጤና ተቋማት የሚሄዱ እናቶች ቁጥርም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በግንዛቤ እጥረት ከህመማቸው ጋር ተደብቀው በየቤቱ የሚኖሩ እናቶች ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም። ከዚህ አንፃር በብዙ ምክንያቶች በሽታው ትኩረት ከሚሹ የጤና ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች ጤና ባለሞያ ወይዘሮ እቴነሽ ገብረዮሐንስ እንደሚናገሩት፣ ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላ በሴት ብልትና በፊኛ ወይም በሴት ብልትና በፊንጢጣ መካከል የሚከሰት ክፍተት ሲሆን፤ ያለማቋረጥ የሽንት ወይም የሰገራ አለመቆጣጠር ችግርን ያስከትላል። ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላ በተራዘመና በተደናቀፈ ምጥ ምክንያት በሰዓቱ ህክምና ባለማግኘት ይከሰታል። መከላከል የሚቻል ቢሆንም ከተከሰተ በኋላ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያስከትላል።

ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላ ዋና ዋና ምልክቶች ሽንት ወይም ሰገራ ያለማቋረጥ መፍሰስ፣ መጥፎ ጠረን/ሽታ፣ በሴት ብልትና በፊኛ ወይም በፊንጢጣ መካከል ቀዳዳ መኖር፣ ኢንፌክሽን፣ የነርቭ ጉዳት… ወዘተ ናቸው። የዓለም ጤና ድርጅት በእስያና ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሴቶች ከወሊድ ጋር ተያይዞ ከሚከሰት ፊስቱላ ጋር እንደሚኖሩ ገልጿል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ50 እስከ 100 ሺ የሚሆኑ ሴቶች ከወሊድ ጋር ተያይዞ በሚከሰት ፊስቱላ እንደሚጠቁም ድርጅቱ አስቀምጧል። ይሁንና ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላ ስርጭት ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ በቂ መረጃ የለም።

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2016 በተሠራ ጥናት በወሊድ ዕድሜ ክልል ካሉ ሴቶች ውስጥ ከ31 ሺ 961 በላይ ያልታከሙ ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላ ተጠቂዎች ይኖራሉ ተብሎ ተገምቷል። ጥናቶችም እንደሚያመለክቱት ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላ ከፍተኛ መገለል የሚያስከትልና ትኩረት ከሚሹ በሽታዎች መካከል አንዱ ነው።

ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ፊስቱላ ከጊዜ ወደ ጊዜ መስፋፋቱን መገመት አያዳግትም። ምክንያቱም ሀገራዊ መደበኛ ቅኝት/ክትትል ባለመኖርና በርካታ እናቶች ከችግሩ አስከፊነት የተነሳ ራሳቸውን ከማኅበረሰቡ አግለውና በቤት ተደብቀው ስለሚኖሩ ነው።

ባለሞያዋ እንደሚሉት፣ ከወሊድ ጋር ተያይዞ ለሚከሰት ፊስቱላ በርካታ አጋላጭ ሁኔታዎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተለይ ደግሞ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚከሰት እርግዝናና የሴት ልጅ ግርዛት …ወዘተ ናቸው። የሕፃናትና ሴቶች የአመጋገብ ችግር፣ የሴቶች የመወሰን አቅም አናሳ መሆን፣ በቅድመ እርግዝናና በእርግዝና ጊዜ በቂ የሆነ ክትትል እንዲሁም የጤና ባለሞያ ምክር አለማግኘትም ከወሊድ ጋር ተያይዞ ለሚከሰት ፊስቱላ አጋላጭ መንስኤ ናቸው።

በቤት ውስጥ መውለድም ሌላኛው ከወሊድ ጋር ተያይዞ ለሚከሰት ፊስቱላ አጋላጭ ምክንያት ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያ 50 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች በቤት ውስጥ የሚወልዱ እንደመሆናቸው ከወሊድ ጋር ተያይዞ ፊስቱላ እንዲከሰት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።

ከነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች በመነሳት ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላን ለመከላከል የሚሠሩ በርካታ ሥራዎች አሉ። ከነዚህ ውስጥም ፊስቱላን ለመከላከል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በተለይም ያለዕድሜ ጋብቻ፣ በአሥራዎች የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ እርግዝናና የሴት ልጅ ግርዛትን ማስወገድ ይገኝበታል። የሕፃናትና እናቶችን አመጋገብ ማሻሻል፣ የሴቶችን የመወሰን አቅም ማጎልበት በፊስቱላ ዙሪያ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ዘርፈ ብዙ ትብብርን ማጠናከር በተለይ ደግሞ ከትምህርት ሴክተር፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሴቶች ማህበር፣ የሕግ አስከባሪ አካል፣ የወጣቶች ማህበራትና ከኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤቶች ጋር አብሮ መሥራት ያስፈልጋል።

በሌላ በኩል የቅድመ ወሊድ ክትትልና በጤና ተቋማት ወሊድ አገልግሎት ተጠቃሚነት ፍላጎት መፍጠርን ማጠናከር፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት፣ ጥራት ያለው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ማስፋት፣ የእናቶች መቆያ ቤት አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ይገባል። ከዚህ ውጪ ጤና ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ ድንገተኛ የወሊድና የጨቅላ ሕፃናት ጤና እንክብካቤ አገልግሎት እንዲሰጡ ማጠናከርና የአምቡላንስ አገልግሎትን ጨምሮ የቅብብሎሽ ሥርዓትን ማጎልበት የግድ ይላል።

ባለሞያዋ እንደሚያብራሩት፤ ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላ መከላከልና መታከም የሚችል ሲሆን ህክምናው በቅድሚያ ችግሩን መለየት፣ ከዚያ ምርመራ ማድረግ፣ ቀጥሎ ህክምና ወደሚሰጥበት ተቋም መላክ፣ ህክምና መስጠት፣ ማገገምና ማኅበረሰቡን እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሂደቶችን ያጠቃልላል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘጠኝ የፊስቱላ ህክምና ማዕከላት ማለትም ስድስት የሃምሊን ፊስቱላና ሦስት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች አሉ። ይሁንና ካለው መጠነ ሰፊ ችግር አኳያ እነዚህ ማዕከላት ብቻ በቂ ባለመሆናቸው ሌሎች ህክምና ማዕከላትን በተለይ ደግሞ በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ማስፋት ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ አሁንም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ፊስቱላ ተጠቂዎች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። ይህም በዋናነት ፊስቱላ የመለየትና የሪፈራል ሥርዓትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ያመላክታል።

በዚሁ በጀት አመት ከኩፍኝ ክትባት ዘመቻ ጋር በማቀናጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ሺ 377 በፊስቱላ ተጠቂ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ተለይተው 720ዎቹ ምርመራ እንዲያገኙ በማድረግ 299 በምርመራ ፊስቱላ እንዳለባቸው በማረጋገጥ 244ቱ በህክምና ላይ ይገኛሉ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላን ለማጥፋት በርካታ ዓለም አቀፍ ጥረቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። አሁን አሁን ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላ ባደጉት ሀገራት ታሪክ ሆኗል። በአሜሪካና በአውሮፓ በ1935 እና 1950 መካከል ባሉት ዘመናት ተወግዷል። ፊስቱላን ለማስወገድ/ለማጥፋት ከተቀመጡት ስልቶች ውስጥ የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድ፣ ድንገተኛ ወሊድና የጨቅላ ሕፃናት ጤና እንክብካቤ /EMONC/ አገልግሎት በተሟላ ሁኔታና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ መሆን አንዱ ነው።

ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚከሰት እርግዝናና የሴት ልጅ ግርዛት ከወሊድ ጋር ተያይዞ ለሚከሰት ፊስቱላ አጋላጭ ሁኔታዎች ቢሆኑም ባደጉት ሀገራት ግን በቂ ግንዛቤ በመኖሩና እነዚህ ጎጂ ልማዶች ዋነኛ ችግሮች አይደሉም። UNFPA እና አጋሮቹ ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላን ለማስወገድ እ.ኤ.አ በ2003 ዓለም አቀፍ ዘመቻ አውጀዋል። በወቅቱ ዘመቻው የታወጀው እ.ኤ.አ በ2012 ፊስቱላን ለማስወገድ ነበር።

እ.ኤ.አ በ2013 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግንቦት 23 ዓለም አቀፍ ፊስቱላ ቀን እንዲሆን ተወስኖ ሀገራት ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላን ለማጥፋት የሚሠሩ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። በዚህ ዓመትም ‹‹20 years on –progress but not enough! Act now to to end fistula by 2030›› በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአሥራ አንደኛ ጊዜ ተከብሯል። ቀኑ በሀገር አቀፍ ደረጃም በተመሳሳይ ተከብሯል።

ባለሞያዋ እንደሚገልፁት፣ በኢትዮጵያ ፊስቱላን ለመከላከልና ለማጥፋት የሚያግዙ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለዚህ አጋዥ የሚሆኑ በጤና ፖሊሲው ውስጥ የተካተቱ ሰነዶች አሉ። ለምሳሌ ፊስቱላን የማጥፋት ስትራቴጂ፣ የተፋጠነ የአዋላጆች ሥልጠና፣ የተለያዩ መመሪያዎች፣ ፕሮቶኮሎች፣ የልጅነት ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ የተዘጋጀ ፍኖተ ካርታ ይጠቀሳሉ።

ድንገተኛ የወሊድና የጨቅላ ሕፃናት ጤና እንክብካቤ አገልግሎት /EMONC facilities/ የሚሰጡ ጤና ተቋማትን የማስፋት፣ ከክፍያ ነፃ የእናቶች ጤና አገልግሎትን የማጠናከርና የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን የማጎልበት ሥራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ። የሪፈራል አገልግሎትን ለማሻሻልና ለማፋጠን በተለይ እናቶች የድንገተኛ የወሊድ አገልግሎት በወቅቱ እንዲያገኙ ለማድረግ 3 ሺ 52 አምቡላንሶች ተገዝተው ተከፋፍለዋል። ይህ ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉ አምቡላንሶችን ቁጥር ወደ 4 ሺ ከፍ አድርጎታል። በሃምሊን ፊስቱላ ማዕከላት የፊስቱላ ቀዶ ህክምናና የማገገሚያ አገልግሎቶች እንዲሁም በሦስቱ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የህክምና አገልግሎቱ በነፃ እየተሰጠ ነው።

ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የፊስቱላ ህመም ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ እነዚህንና መሰል ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም አሁንም ድረስ በርካታ ተግዳሮቶች አሉ። ማኅበረሰቡ ስለፊስቱላ ህመም ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ የፊስቱላ ታማሚዎችን የመለየትና ወደ ህክምና ማዕከላት መላክ ደካማነት፣ የበጀት እጥረት፣ የፊስቱላ ህመምተኞች ከታከሙ በኋላ የሚያገግሙበትና ተመለሰው ወደማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራ ላይ የሚሠሩ አጋር ድርጅቶች ውስንነት፣ የመሠረተ ልማት በተለይ ደግሞ የመንገድ ችግር፣ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ዝቅተኛነትና ሌሎችም ከተግዳሮቶቹ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።

ከነዚህ ተግዳሮቶች በመነሳት ታዲያ በቀጣይ በፊስቱላ ዙሪያ የማኅበረሰቡን ግንዛቤና ተሳትፎ ማጠናከር ያስፈልጋል። የሀገር ውስጥ ፋይናንስን ማጠናከርም ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም። መንግሥትም ለሌሎች የጤና ጉዳዮች የሚመድበውን ያህል ለፊስቱላም የፋይናንስ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅበታል። የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው በጋራ ሊሠሩ ይገባል።

በብዙ ሀገሮች የታየና ፊስቱላን መቶ በመቶ መከላከል የሚቻል በመሆኑ በቅድመ እርግዝና፣ እርግዝናና ወሊድ አገልግሎት በሚደረገው ጥረት ሁሉ ፊስቱላን መከላከል ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል። የቤተሰብ እቅድ፣ ቅድመ ወሊድ፣ ወሊድና ድህረ ወሊድ አገልግሎቶችን ማጠናከር ብሎም ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላን መከላከልና ማከም እንደሚቻል፣ ይህንን ለማስወገድ የመንግሥትና ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ርብርብ ያስፈልጋል።

አስናቀ ፀጋዬ

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *