ሄዝቦላህ ከ100 በላይ ሮኬቶችን ወደ ደቡባዊ እስራኤል መተኮሱን ገለጸ።
የሊባኖሱ ቡድን ለባለፈው ሳምንት የመገናኛ መሣሪያ እና ለቤሩቱ ጥቃት አጻፋውን በወሰደበት ርምጃ በሃይፋ ከተማ አቅራቢያ የመኖሪያ ህንጻ ሲመታ የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
ሄዝቦላህ ሌሊቱን በፈጸመው ጥቃት የወታደራዊ ጣቢያዎች እና የጦር መሣሪያ ማምረቻዎችን ኢላማ ማድረጉን ነው ያስታወቀው። የእስራኤል ጦር በበኩሉ አብዛኞቹ የሄዝቦላህ ሮኬቶች (105) ተመተው መውደቃቸውንና የተወሰኑት ቤቶችን መምታታቸውን ገልጿል። ይሁን እንጂ በጥቃቱ ስለደረሰው ጉዳት በዝርዝር አልጠቀሰም።
ሄዝቦላህ በቤሩት አቅራቢያ 37 ሰዎች ለተገደሉበትና ባለፈው ሳምንት በመገናኛ መሣሪያዎች ፍንዳታ ለደረሰው የ39 ሰዎች ሞትና ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች መቁሰል አጻፋውን እንደሚወስድ መዛቱ ይታወሳል።
የቡድኑ መሪ ሀሰን ናስራላህም “እስራኤል ሁሉንም ቀይ መስመሮች አልፋለች፤ ፍትሃዊ ቅጣት ይጠብቃታል” ሲሉ መዛታቸውን ተከትሎም ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ማዝነቡን ቢቢሲ ዘግቧል።
ሄዝቦላህ የሮኬት ጥቃቱን ከመፈጸሙ በፊት የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመው የአየር ጥቃት ከ180 በላይ የሮኬት ማስወንጨፊያ ጣቢያዎችን ማውደሙን የጦሩ ቃልአቀባይ ዳኔል ሃጋሪ ተናግረዋል።
ከትናንትና ሌሊቱ የሄዝቦላህ የሮኬት ጥቃት በኋላ የእስራኤል ጦር በደቡባዊ እስራኤል እና በደቡባዊ የጎላን ኮረብቶች በሚኖሩ ዜጎች እንቅስቃሴን የሚገድብ ክልከላ አውጥቷል። ሃይፋ ከተማን የሚያካትተው ክልከላ በግልጽ ቦታ ከ10 በላይ ሆኖ መሰብሰብን የሚከለክል ነው ተብሏል።
ሄዝቦላህ እና እስራኤል ከ18 ዓመት በኋላ ጦርነት ሊጀምሩ ይችላሉ የሚለው ስጋት ማየሉን ተከትሎ አሜሪካ ዜጎቿ ከሊባኖስ እንዲወጡ የሚያሳስብ መግለጫ አውጥታለች። ጎረቤት ዮርዳኖስም በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎቿ በተቻለ ፍጥነት ከሀገሪቱ እንዲወጡ አሳስባለች።
ሄዝቦላህ የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን ለማሳየት በእስራኤል ላይ የሚሳኤልና ሮኬት ጥቃት በማድረስ ላይ ይገኛል። ቴል አቪቭም በቴህራን ይደገፋል የምትለውን ቡድን ይዞታዎች በጄቶች ስትደበድብ የቆየች ሲሆን፥ በርካታ አመራሮቹንም ገድላለች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት ባለፈው ሃሙስ “አዲሱ የጦርነት ምዕራፍ ትኩረቱን ወደ ሰሜን ያደርጋል” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፥ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው ማስመለስም የጦርነቱ ግብ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢራን በበኩሏ የእስራኤል ሊባኖስን ያለማቋረጥ መደብደብ ጦርነቱን ቀጣናዊ መልክ እንዲይዝ ከመፈለግ የመነጨ ነው በሚል ለሃማሱ ኢስማኤል ሃኒየህ ግድያ አጻፋ ለመውሰድ የያዘችውን እቅድ ማራዘሟን መግለጿ አይዘነጋም።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም